Saturday, 12 December 2015 11:52

ጁኪ በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት መክፈቱን አስታወቀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

     መሰረቱ ጃፓን በሆነው ጁኪ (Juki) ኮርፖሬሽን ስር የሚተዳደረው የሲንጋፑሩ ጁኪ የጨርቅ የቆዳ ልብሶች ስፌት መሳሪያ በማምረት በዓለም ቀዳሚ ሲሆን በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት መክፈቱን ገለጸ፡፡
ሰሞኑን በሂልተን ሆቴል በተካሄደው የማስተዋወቅ ፕሮግራም በክብር እንግድነት የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚ/ር ዴኤታ አቶ ታደሰ ኃይሌ፣ የረዥም ጊዜ ዕቅድ በቀላል ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እሴት መጨመር የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለቴክኖሎጂ ሽግግር መሰረታዊ በመሆኑ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው አመልክተዋል፡፡
የኢንዱስትሪውን ልማት በሁሉም ዘርፍ የምናስተዋውቅበትንና የሚመራበት ሲስተምና አሰራር መፈተሽ መሰረታዊ ነው ያሉት ሚ/ር ዴኤታው፣ የአልባሳትና የቆዳ ዘርፎች ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጣቸው ስለሆኑ አልባሳት ለማምረትና ወደ ውጭ ለመላክ፣ ጨርቅ ያልሆኑትንም በብዛት ብቻ ሳይሆን በጥራትም አምርተን ለመላክ አቅደን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
በዚህ መሰረት፣ መሳሪያውን በመሸጥ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ጥራት ማኔጅመንትና ካይዘን የዳበረውን ቴክኖሎጂያቸውን በማስተላለፍ ከፍተኛውን ሚና እንደሚጫወት እምነቴ ነው። በተለይ ደግሞ የጃፓኑ ጁኪ ኮርፖሬሽንና ጁኪ ሲንጋፖር የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪያችን ለመደገፍ በአገራችን ቅርንጫፉን በመክፈቱ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የጁኪ ማኔጅመንት እንቅስቃሴያቸውን በማስፋት ፋብሪካቸውን በአገራችን እንዲያቋቁሙ በማክበር አሳስባለሁ በማለት ገልፀዋል፡፡
በሦስት ቀናት አራት ሰሚናሮች አዘጋጅተን ስለምርታማነት ከውጭ ከመጣ ባለሙያ ከተለያዩ ፋብሪካዎች ለመጡ ሰራተኞች ትምህርት እየሰጡ መሆኑን የተናገሩት የጁኪ-ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሐጎስ መረሳ፤ ምርታማነትን እንዴት ማሳደግና ወጪ መቀነስ እንደሚቻል፣ ኃይል እንዴት እንደሚቆጠብ፣ የቦታ ቁጠባ፣ የጥራት አጠባበቅ፣ ሰውና መሳሪያ ስለሚኖራቸው ግንኙነትና ስለሥራ አካባቢ አጠባበቅ ትምህርት መስጠቱን ገልጸዋል፡፡
አቶ ሐጎስ፣ ሰልጣኞቹ አውቶማቲክ የሆኑትን የስፌት መሳሪያዎች እንዲያዩና እንዲለማመዱ 32 የስፌት መሳሪያዎች ማዘጋጀታቸውንና 30ዎቹ የጨርቅና ሁለቱ የቆዳ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች በአገር ውስጥ ባለሀብቶችና በውጭ ኢንቨስተሮች እየተስፋፉ ስለሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂና ቀዳሚ የሆነው ጁኪ እዚህ ቅርንጫፍ መክፈቱ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ፤ እዚህ ያለው ቢሮ ማሽኖቹን አስመጥቶ አይሸጥም፤ እኛ የምንሰጠው ሰርቪስ ነው ብለዋል፡፡
ኤል ሲ ከፍቶ ግዢውን ሲንጋፖር ወደብ ላይ የሚፈጽመው ደንበኛው ነው፤ እኛ ከግዢ በፊት ምክር ከግዢ በኋላ ሰርቪስ እንሰጣለን፡፡ ማሽኑን የገዙት ብቻውን ሳይሆን ከቴክኖሎጂው ጋር ስለሆነ በነፃ ሰርቪስ እንሰጣለን፡፡ ማሽኑ ባለበት ቦታ ሁሉ የእኛ የቴክኒክ ሰው መኖር አለበት፡፡ አሁን በአዲስ አበባና በመቀሌ የቴክኒክ ሰዎች አሉ፡፡ በሀዋሳም የኢንዱስትሪ ዞኑ በቅርብ ስለሚጠናቀቅ እዚያም ይኖሩናል በማለት አስረድተዋል፡፡
ጁኪ በ1938 በዲሴምበር ወር በ149.9 ሚሊዮን ዶላር መቋቋሙን የጠቀሱት የሲንጋፖሪ ጁኪ ምክትል ሥራ አስፈጻሚና ዳይሬክተር ሚ/ር ኖሪአኪ ሳኢቶ፤ የኩባንያው ምርት በስድስት አኅጉር ከ160 በላይ አገሮች እንደሚሸጡ፣ እንደሲንጋፖሩ ራሳቸውን የቻሉ 34 ቅርንጫፎች እንዳላቸው፣ አጠቃላይ ሰራተኞቻቸው 6,955 እንደሆኑና በ2014 አጠቃላይ የተጣራ ትርፋቸው 881 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Read 1484 times