Saturday, 12 December 2015 11:51

ኢትዮ-ቻይና የንግድና ቢዝነስ ፎረም ተመሰረተ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

    መንግሥታዊው የቻይና ዓለም አቀፍ ኮሜርስ ም/ቤትና የኢትዮጵያ ንግድ ም/ቤትና የዘርፍ ማኅበራት በጋራ ያዘጋጁት ኢትዮ ቻይና የንግድና ቢዝነስ ፎረም ተቋቋመ፡፡
በደቡብ አፍሪካ-ደርባን ከተካሄደው የአፍሪካ ቻይና ፎረም መልስ በሳምንቱ መጀመሪያ በራዲሰን ብሎ በተካሄደው ጉባኤ፣ የኢትዮ - ቻይና የንግድና ቢዝነስ ፎረም የተመሰረተ ሲሆን፣ ዓላማውም ኢትዮጵያውያን የቢዝነስ ሰዎች ኤክስፖርትን እንዲያስፋፉ የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪን እንዲያስፋፉና የአገር የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪን እንዲሳድጉ፣ የቻይና ኩባንያዎች ቴክኖሎጂና የማኑፋክቸሪንግ ክህሎት እንዲቀስሙና የእርስ በርስ ትስስር እንዲፈጥሩ መሆኑን የቻይና ዓለም አቀፍ ፕሮሞሽን አማካሪ ሚ/ር ዘሆ ጂንያግ አስታውቋል፡፡
ከማኑፋክቸሪንግ ከእርሻ፣ ከአቶሞቲቭ፣ ከኮንስትራክሽን፣ ከሴራሚክ፣ ከቴሌኮሙኒኬሽን፣ … ለተውጣጡ 30 የቻይና ልዑካን አባላት በተለያዩ ዘርፎች በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት አመቺነት አራት ጽሑፎች ቀርበው ውይይት የተደረገ ሲሆን ቻይናውያኑን ባለኢንዱስትሪዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ቢያደርጉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡
አገሪቷ በምታካሂዳቸው የልማት ዘርፎች ሁሉ ቻይናውያን ይሳተፋሉ ያሉት የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትና ዘርፍ ማኅበራት ምክትል ጸሐፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜ፤ ቻይናውያም፣ ከኮንስትራክሽን እስከ ጨርቃጨርቅና ቆዳ፣ ከእርሻ እስከ ሆቴልና ሬስቶራንቶች፤ ከአግሮ ፕሮሰሲንግ እስከ ማዕድን፣ ከሪል እስቴት እስከ ትምህርት፣ … እየተሳተፉ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያና በቻይና መካከል በሚደረገው ንግድ ሚዛኑ ወደ ቻይና ያጋደለ መሆኑን የጠቀሱት አቶ እንዳልካቸው፤ በ2013 ኢትዮጵያ ከውጭ ካስገባችው ዕቃ 27 በመቶው ከቻይና ነበር ብለዋል፡፡
በኢንቨስትመንት ረገድ ከ1984-2006 ባለው ጊዜ 32.6 ቢሊዮን ብር (1.6 ቢሊዮን ዶላር) ያስመዘገቡ የቻይና ኩባንያዎች ሥራ ጀምረዋል፣ በግንባታ ላይ ወይም በቅድመ - ግንባታ ላይ መሆናቸውን የጠቀሱት ምክትል ጸሐፊው፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በእርሻ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ኢትዮጵያ ወደ ቻይና የምትልከው ሰሊጥ፣ ቆዳና ሌጦ፣ የቅባት እህሎችና በከፊል የተዘጋጀ የቆዳ ውጤቶች ነው፡፡  
ከቻይና የምታስገባው ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ሁሉንም የኢንዱስትሪ ምርቶች ነው፡፡ ስለዚህ የንግድ ሚዛኑ ወደ ቻይና ያደላ ነው፡፡ ይህን የንግድ ሚዛን መዛባት ቻይና ታጠበዋለች የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡

Read 1901 times