Saturday, 12 December 2015 11:55

“ትኩረቴ ትርፍ ላይ ሳይሆን ሥራ ሰርቶ ማሳየት ነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(7 votes)

    ዘንድሮ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ለገናና ለፋሲካ በዓላት የሚዘጋጀውን የንግድ ኤክስፖ ጨረታ በ22.5 ሚሊዮን ብር ያሸነፈው ኢዮሃ አዲስ ኢንተርቴይንመንት ነው፡፡ ድርጅቱ የቀይ መስቀልንም የ5 ቀናት ኤግዚቢሽን ጨረታ አሸንፏል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከኢዮሃ አዲስ ኢንተርቴይንመንትና ኤቨንት ሥራ አስኪያጅና ባለቤት ጋር አጭር ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

    ኢዮሃ መቼ ነው የተመሰረተው?
ድርጅታችን የተመሰረተው በ2000 ዓ.ም ነው። የተለያዩ ስራዎችን ይሰራል፡፡ ጎን ለጎንም ወደ ፊልም ኢንዱስትሪው በመቀላቀል ኢዮሀ ሲኒማን ከፍቶ፣ ፊልሞችንም ያሳያል፡፡ በኢዮሃ አዲስ ኢንተርቴይንመንትም የተለያዩ ስራዎችን ሰርተናል፤ እየሰራንም እንገኛለን፡፡ ከዚህ ቀደም 50ኛ አመት የፊልም ፊስቲቫልን፣ የቡሄ በዓልን፣ የመስቀል በዓላትንና ሌሎችም በርካታ ሁነቶችን አዘጋጅቷል፡፡
የተማሩት ትምህርት ከመዝናኛ ኢንዱስትሪው ጋር ይገናኛል?
የተማርኩት እንኳን ከቢዝነስ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በማኔጅመንት ዲግሪ አለኝ፡፡ በኮምፒዩተር ሳይንስና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂም እንዲሁ ምሩቅ ነኝ፡፡ ነገር ግን ወደ መዝናኛው ያተኮርኩት ፍላጎት ስላለኝ ነው፤ ሆኖም ዘርፉ ሰፋ ያለ በመሆኑ ከበድ ይላል። ከውጭ ሆነን እንደምንመለከተው ቀላል ስራ አይደለም፡፡ በርካታ ፈተናዎችም አሉት፡፡ ሆኖም በጥንካሬ እየሰራን ነው፡፡
የገናና የፋሲካ ኤክስፖ ጨረታን አሸንፈፋችኋል። ውጤቱን ጠብቃችሁት ነበር?
በዋናነት የ2008 እቅዳችን እነዚህን ትልልቅ ኤክስፖዎች አሸንፈን በስራው ላይ መሰማራት ነበር፤ እሱም ተሳክቶልናል፡፡ እርግጥ ሁለቱም አለም አቀፍ ኤክስፖዎች እንደመሆናቸውና በርካታ ተሳታፊዎችን እንደመያዛቸው በርካታ አገራዊ ሥራዎችን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ ስራ የአገርን መልካም ገፅታ ከመገንባትም አኳያ በርካታ ከባድ ስራዎችን ይጠይቃል፡፡ እሱንም በስፋት ተዘጋጅተንበት እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡
ኢዮሀ ከዚህ ቀደም በዚህ ደረጃ ኤክስፖ አዘጋጅቶ ያውቃል?
በርካታ ስራዎችን ቢሰራም በዚህ ደረጃ ኤክስፖ ስናዘጋጅ የመጀመሪያችን ነው፡፡ ባልሳሳት የገናና የፋሲካን አንድ ላይ በማሸነፍም የመጀመሪያ ነን ብዬ አምናለሁ፡፡
ሁለቱንም ማሸነፋችሁ ስራውን አያከብድባችሁም?
ስራው ሊከብድ ይችላል ግን የስራውን ክብደት ግምት ውስጥ በማስገባት በሰው ኃይልም በፋይናንስም በአጠቃላይ ለስራው በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ በቂ ዝግጅት አድርገናል፡፡ ስለዚህ እንወጣዋለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ሁለቱንም  ማሸነፋችን እንደውም ስራውን ከማክበድ ይልቅ ያቀለዋል፡፡
እንዴት ማለት?
አሁን የገናን ተሳታፊ ድርጅቶች ስንመዘግብ የፋሲካውንም ምዝገባ ጎን ለጎን እያስኬድነው ነው። እንደውም ምዝገባውን ልንጨርስ ተቃርበናል፤ የፋሲካውን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የገናውን እንደዘጋን በዚያው ስሜት የፋሲካውንም እንቀጥላለን፡፡
በአንድ በኩል ድርጅትን መምራት፣ በሌላ በኩል እንደ እናት ልጆችን ማሳደግ፣ እንደገና እንደዚህ አይነት ትልልቅ ዝግጅቶችን ማስተናገድ አይከብድም?
ከባድ አይደለም አልልሽም፡፡ ነገር ግን ሴትነት ራሱ ጥንካሬ ነው፡፡ ሁሉንም አቻችሎ መምራት ጥንካሬ ይጠይቃል፡፡ ድርጅት፣ ቤተሰብ እንደገና የኤክስፖ ስራዎችን መምራት ሀገራዊ ኃላፊነትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ነገር ግን በአመራር ስራ ላይ ልምድ ስላካበትኩም እየተወጣሁት ነው፡፡ ያቅተኛል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሴትነት ትልቅ ስጦታ ነው፤ ሁሉንም እንድንችል አድርጎ ነው ፈጣሪ የፈጠረን ብዙ ጊዜ ሴትነትን እንደ ችግር የሚያዩት አሉ፡፡ እኔ ከዚህ በተቃራኒው ነው የማስበው፤ እንደውም ሴትነት ፀጋ ነው፡፡ ሴት የጥንካሬ ተምሳሌት ናት። እኔ በበኩሌ የውጭውም የቤቱንም ስሰራ የበለጠ እየጠነከርኩና እየበረታሁ ነው የምሄደው፡፡ እየተዝናናሁና ደስ እያለኝ ነው የምሰራው፡፡
የቀይ መስቀልን የአምስት ቀን ኤግዚቢሽንም አሸንፋችኋል፡፡ የቀይ መስቀሉ ኤግዚቢሽን ምንን የተመለከተ ነው?
ቀይ መስቀል የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት አስመልክቶ የሚካሄድ ኤግዚቢሽን ነው፡፡ ለአምስት ቀን የሚቆይ ነው፡፡ የፋሲካውን ኤክስፖ እንደጨረስን ወደዚያው እንዞራለን፡፡ በእርግጥ ከባድ ነው፡፡ ከባድ ቢሆንም ግን እኛ በፋይናንስም በተደራጀ የሰው ኃይልም ስራውን ይዘነዋል፡፡ ጥሩ ስራ ሰርተን ውጤታማ የምንሆን ይመስለኛል፡፡
ሁለቱን ኤክስፖዎች በምን ያህል ብር ነው ያሸነፋችሁት? የጨረታውስ ሂደት ምን ይመስል ነበር?
የጨረታው ሂደት ግልፅና የማያሻማ ነበር። በመክፈቻው ዕለት አንዳችን አንዱ ያስገባውን ዋጋ መጠንና ዶክሜንት የማየት እድል ነበረን፤ በጣም ግልፅነት የተሞላበት ነበር፡፡ የተለያዩ የሚመለከታቸው አካላትና የሚዲያ ሰዎችም ነበሩ። የጨረታው ሂደት ይህን ይመስላል፡፡ በምን ያህል ብር አሸነፍሽ ላልሽኝ፣ የገናና የፋሲካ የብሩ መጠን የተለያየ ነው፡፡ የገና 12 ሚሊዮን 599 ሺ ብር ሲሆን የፋሲካ 9 ሚሊዮን 599 ሺ በአጠቃላይ በ22.5 ሚሊዮን ብር ነው ያሸነፍነው፡፡
ኤክስፖውን ምን ያህል ሰው ይጎበኘዋል ተብሎ ይጠበቃል?
በቀን 30 ሺህ ሰው ይጎበኘዋል ብለን እንጠብቃለን፡፡ እንደነገርኩሽ ከጠዋት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 3፡00 በድምቀት እንሰራለን፡፡ የመግቢያ ዋጋም ከእስከ ዛሬው የተለየ አይደለም፡፡
በስራው ምን ያህል ትርፍ ለማግኘት አቅዳችኋል?
እኔ ትኩረቴ ትርፍ ማትረፍ አይደለም፤ ስራውን የመስራት አቅም እንዳለኝ ሰርቼ ማሳየቱ ላይ ነው። ከዚያ በኋላ ባተርፍ አልጠላም፤ ብከስርም የሚቆጨኝ አይደለም፡፡ ሁሉንም ትኩረቴን ያደረግሁት ስራውን መስራቱ ላይ ነው፡፡
በመጨረሻ የሚሉት ነገር ይኖራል?
ከፊት ለፊቴ እየቀደመ መሰናክሌን እያነሳ ሁሉን የሚያሳካልኝን እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡ በመቀጠል ባለቤቴን በጣም አመሰግነዋለሁ፤ ምንም እንኳ ከፊት እኔ ብታይም ከጀርባ ጥንካሬ የሚሰጠኝ እሱ ነውና ከልብ አመሰግነዋለሁ፡፡
የኢዮሃ አዲስ ኢንተርቴይመንትና ኢቨንት ከላይ እስከ ታች ያሉ ሰራተኞችንና ከጎኔ ያሉትን ላመሰግን እወዳለሁ፡፡  

Read 2920 times