Saturday, 12 December 2015 13:12

አቅም የሌላቸውን ብርቱ ያደረገ የፍትህ አሠራር

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(11 votes)

       የስድስት ልጆቻቸውን እናት ድንገት ሞት ሲነጥቃቸው ዙሪያው ገደል ሆነባቸው፡፡ ኑሮ በጣም ከበዳቸው፡፡ ለሥራ ያልደረሱ ለእህል ያላነሱ ህፃናት ልጆቻቸውን የማሳደጉ ኃላፊነት ችግርና በሽታ በደቋቆሰው ትከሻቸው ላይ ወደቀ፡፡ 3 ጥማድ በሚያውለው የእርሻ ማሳቸው እያረሱ ልጆቻቸውን የማሳደግ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቢጣጣሩም ኑሮ ከዕለት ወደዕለት እየከበዳቸው ሄደ፡፡ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ማሰብ ተስኖአቸው ግራ በተጋቡበት ወቅት በአካባቢያቸው የሚገኝ አንድ የቀበሌ ባለስልጣን የእርሻ ማሳቸውን በመያዣነት ይዞ 1700 ብር ብድር ሊሰጣቸው ተስማማና ለ1 ዓመት መሬቱን በዋስትና ይዞ ብሩን አበደራቸው። የተባለው ጊዜ ቢደርስም የብድር ገንዘቡን ለመክፈል ባለመቻላቸው አበዳሪው መሬቱን ለ3 ዓመት እንዲጠቀምበትና የብድሩ ገንዘብም በዚሁ ቀሪ እንዲሆን ተስማምተው አበዳሪው በመሬቱ ይጠቀምበት ጀመር፡፡
የ3 ዓመት የውል ጊዜ ሲጠናቀቅም መሬታቸውን ለመረከብ አበዳሪውን ጠየቁት፡፡ የምን መሬት አለ አበዳሪ፡፡ ለ3 ዓመት እንድትጠቀምበት ነው የተስማማነው የያዝከውን አሉት፤ የ60 ዓመቱ አዛውንት አቶ ዑመር አብሮ፡፡ “እሱንማ እኮ ሸጠህልኝ ገዝቼህ ነው፡፡” ሲል አስረግጦ ነገራቸው። በዚህ ብቻም አላበቃ እንደውም አንተ ወንጀለኛ ነህ ይልና ወስዶ ያስራቸዋል፡፡
ከቀናት እስር በኋላም ሁለተኛ መሬት አለኝ ብለህ ብትጠይቅ ሌላ ነገር ነው የሚደርስብህ ብሎ አስፈራርቶ ይለቃቸዋል። ከመሞት መሰንበት ያሉት አዛውንት ያለአግባብ የተነጠቁትን መሬት ግለሰቡ አይናቸው ስር እያረሰ ሲጠቀምበት እያዩ 6 ልጆቻቸውን ይዘው እጅግ አስቸጋሪ ህይወት መግፋታቸውን ቀጠሉ፡፡
አሁን ልጆቻቸው በዕድሜም በአካልም እያደጉ ነው፡፡ ከእነዚህ ልጆች ትልቁ የወላጆቹ መሬት ያለአግባብ በጉልበተኛ መነጠቁ እጅግ ያንገበግበው ነበር፡፡ ሁኔታውን በዝምታ አይቶ ለአመታት ቢዘልቅም የአባቱና የእህት ወንድሞቹ ችግርና ስቃይ ጉዳዩን በዝምታ ማለፍ እንዳይችል አደረገው፡፡ ሰውየው ከስልጣኑ ላይ በመነሳቱም ወደ ሰውየው በመሄድ መሬቱ የወላጆቹ በመሆኑ እሱ ሊጠቀምበት እንደማይገባና ለባለቤቶቹ ማስረከብ እንዳለበት ነገረው፡፡
ከዚህም አልፎ መብታቸውን መጠየቅ በሚገባቸው መንገድ ሁሉ ከመጠየቅ ወደ ኋላ እንደማይሉ አሳሰበው፡ ግለሰቡም በመሬቴ ላይ ሁከት አነሱብኝ ሲል በወረዳው ፍ/ቤት ክስ አቀረበ። አዛውንቱ ፍ/ቤት ተጠሩ፡፡ መሬቱ የእሳቸው እንደሆነ፣ ያለአግባብ መነጠቃቸውን ቢናገሩም ክርክሩን በሥርዓትና በአግባቡ ለመቀጠል የሚያስችል የገንዘብ አቅም ስለሌላቸውና መብታቸውን በአግባቡ ለፍርድ ቤቱ ለማስረዳት ባለመቻላቸው፣ መሬቱ ለሰውየው የሚገባ መሆኑንና ያለአግባብ ስለአጉላሉትም 14ሺህ ብር ካሳ እንዲከፍሉት ተወሰነባቸው፡፡ የተጣለባቸው ፍርድ በእጅጉ አሳዘናቸው፡፡ እንኳንስ 14ሺ ብር ቀርቶ 14 ብር በእጃቸው ለሌለ አቅመደካማና ህመምተኛ አዛውንት ውሳኔው የቀልድ ያህል ነበር። በውሳኔው እጅግ የተበሳጨው ልጃቸው ግን የኦሮሚያ ዩኒቨርሲቲ በኦሮሚያ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞንና በሐረር ክልል እየሰጠ ባለው ነፃ የህግ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆኖ ጉዳዩ በይግባኝ ወደ ሐረር ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲሄድ አደረገው። አዛውንቱ ዩኒቨርሲቲው በሚሰጠው ነፃ የህግ አገልግሎት በሚደረግላቸው የህግ ድጋፍ ታግዘውም ከ10 ዓመት ቆይታ በኋላ ያለአግባብ የተነጠቁት የእርሻ መሬት እንዲመለስላቸው ተወሰነላቸው፡፡
“ዛሬ በአገሬ ላይ ድሃም ፍትህን እንደሚያገኝ አረጋገጥኩ፡፡ ለ10 ዓመት እነዚህን ህፃናት ይዤ ያለእናት ሳሳድግ የደረሰብኝን መከራና ስቃይ አውቀዋለሁ፡፡ እንዲህ በሽተኛ የሆንኩት በሃዘንና በብስጭት ነው፡፡
ይህ የነፃ የህግ አገልግሎት እንደኔ ላሉ አቅመ ደካማና ድሃ ሰዎች የሚኖረው ጠቀሜታ ብዙ ነው። ሁሉም የቸገረው እንደኔ ይጠቀምበት” በሐረሪ ክልል ሐረማያ ወረዳ ፍ/ቤት ውስጥ አግኝቼ ያነጋገርኳቸውና ዩኒቨርሲቲው በኦሮሚያ ክልል በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌና በሐረሪ ክልል ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ እየሰጠ ባለው ነፃ የህግ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑት አዛውንት ነበሩ እንዲህ ያሉኝ፡፡
አዛውንቱ በተሰጣቸው ነፃ የህግ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነው ለሐረር ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤት ባቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ፣ ያለአግባብ የተነጠቁት የእርሻ መሬታቸው እንዲመለስላቸው ተወስኖላቸዋል፡፡
በዕለቱ በሥፍራው ያገኘኋቸውም የአፈፃፀም ማመልከቻ ለማቅረብ ነፃ የህግ አገልግሎት ወደሚሰጥበት ቢሮ መጥተው ነው፡፡ እንደ እሳቸው ሁሉ ጉዳያቸውን ለፍርድ ቤት ለማቅረብ የሚያስችል የገንዘብም ሆነ የህግ እውቀት የሌላቸውና በዩኒቨርሲቲው ነፃ የህግ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ወደ ሥፍራው የመጡ ባለጉዳዮችን አነጋግሬአለሁ፡፡ አብዛኛዎቹ ጉዳያቸው ከመሬት ይዞታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አፏን በጨርቅ ታስራ በ15 ዓመቱ ታዳጊ የተደፈረችው የስምንት ዓመት ህፃንም በዩኒቨርሲቲው ነፃ የህግ አገልግሎት ፍትሕ ካገኙት መካከል ተጠቃሽ ናት፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከዩኤስአይዲ ጋር በትብብር በሚሰራውና በክልሎቹ ውስጥ በሚገኙ 43 ወረዳዎች ቢሮ አቋቁሞ ተግባራዊ በማድረግ ላይ በሚገኘው በዚሁ ነፃ የህግ አገልግሎት እስከአሁን ድረስ 336ሺ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸውንና ይህም በገንዘብ ሲተመን ወደ 80 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ እንደሆነ የዩኒቨርስቲው የህግ ዲፓርትመንት የማህበራዊ ፍትህ ማዕከል ኃላፊና የፍትህ ተደራሽነትና ንቃተ ህግ ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ሱልጣን ቃሲም ገልፀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት በመታመኑና ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ስልጠና እንዲያገኙ ለማድረግ ታስቦ፣ በ2001 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እገዛ ሥራ መጀመራቸውን የገለፁት አቶ ሱልጣን፤ በአረማያና በሐረር ከተሞች ላይ 2 የነፃ የህግ አገልግሎት መስጫ ቢሮዎችን ከፍተው ይንቀሳቀሱ እንደነበርና በሂደትም የቢሮዎቹን ቁጥር ወደ 11 ከፍ በማድረግ እስከ 2006 ዓ.ም ድረስ ሲሰሩ መቆየታቸውን አስተዋል፡፡ የነፃ የህግ አገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ምክንያት ዩኒቨርሲቲው ከዩኤስአይዲ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ቢሮዎቹን ወደ 43 በማድረስ፣ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞንና በሐረር ክልል ውስጥ ለሚገኙና በገንዘብ እጦት ምክንያት ፍትህ ያጡ የማህበረሰብ አባላትን እያገለገለ ይገኛል፡፡
በዚህ የነፃ የህግ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑት ሴቶች፣ ህፃናት፣ አዛውንቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የኤችአይቪ ሕሙማን፣ የህግ ታራሚዎችና የገንዘብ አቅም የሌላቸው መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከቀበሌ ማቅረብ የሚችሉ ሰዎች ናቸው፡፡
የዩኒቨርሲቲው የህግ ዲፓርትመንት ተማሪዎች፤ ማህበረሰቡን እያገለገሉ የተግባር ልምምድ የሚያደርጉበትን ሁኔታ ማመቻቸቱን አቶ ሱልጣን ቃሲም ገልፀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት 379 ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 79 ሴቶች መሆናቸውንና በ2020 ዩኒቨርሲቲው በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ እንዲሆን የማድረግ ዕቅድ ይዘው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ አቶ ሱልጣን ተናግረዋል፡፡

Read 5028 times