Saturday, 19 December 2015 10:10

“...አንዲት ነርስ ለስምንት እና አስር ልጅ...”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሳምንት እትም የጨቅላ ሕጻናት ጤንነትን ለመጠበቅ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ

በአገሪቱ ሪፈራል በመሆን የሚያገለግለውን የጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን አሰራር ለአድማጮች ማስነበባችን ይታወሳል፡፡ ይህንን ሕክምና ለመመልከት በባህርዳር ፈለገሕይወት ሆስፒታል ቆይታ ያደረግን በመሆኑ ለዚህ እትም ከጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል የጨቅላ ሕክምና ክፍል ካላጠናቀቅነው ማብራሪያ ጋር አክለነዋልና ታነቡ ዘንድ ጋብዘናችሁዋል፡፡
ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የሚወለዱ ሕጻናት ባደጉት አገራት ካሉት ይበልጥ 15 እጥፍ ይሞታሉ፡፡ የ2013 ዓ.ም ጥናት እንደሚያሳየውም 6.3 ሚሊዮን ያህል ህጻናት እድሜያቸው 5 አመት ሳይደርስ ሞተዋል፡፡ ከጠቅላላው ሞት ወደ 45 በመቶ የሚሆነው ሞት በቂ ምግብ ባለማግኘት መሆኑንም ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ በተለይም ገና እንደተወለዱ በጨቅላነት እድሜያቸው የሚያልፉት ሕጻናት ቁጥር በየአመቱ ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጋ ሲሆን ይህም በአንድ ወር እድሜያቸው ነው፡፡ በተመሳሳይም ሲወለዱም ሕይወት የሌላቸው ጨቅላዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ከሚሞቱት ግማሽ ያህሉ በ24 ሰአት እድሜያቸው ሲሆን ወደ 75 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በመጀመሪያ ሳምንታቸው ለህልፈት ይዳረጋሉ፡፡  
እናቶች በሰለጠነ የሰው ኃይልና በጤና ተቋማት በሚወልዱበት ጊዜ ግን ይህ የተገለጸው አደጋ በእጅጉ እንደሚቀንስ አያጠራጥርም፡፡ እናቶች በጤና ተቋማት ሲወልዱ ለጨቅላው ጤንነት የሚበጅ ብዙ ነገር አለ ባለሙያዎች እንደሚጠቅሱት፡፡
ልጁ እንደሚተነፍስ እና እንደማይተነፍስ ማረጋገጥ፣
ጡት መጥባት መቻል አለመቻሉን ማየት ፣
ልጁ ተገቢውን ሙቀት እንዲያገኝ እና ልጁን ከመንካት በፊት እጅን መታጠብ አስፈላጊ መሆኑ ጭምር ለእናትየውም ሆነ ለቤተሰቡ ትምህርት ይሰጣል፡፡
ቀደም ሲል የተጠቀሱትና ሌሎችም ለተወለደው ጨቅላ የሚጎዱና የሚጠቅሙ ነገሮች በደንብ ተለይተው እንዲታወቁና ልጁም በጤንነት እንዲቆይ እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ ይመከራል፡፡
ዶ/ር ባዘዘው ፈቃድ በባህርዳር በፈለገሕይወት ሆስፒታል የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ሲሆኑ በሆስፒታሉ የማዋለጃውንና የጨቅላ ሕጻናቱን ክፍል የሚመሩ ናቸው፡፡ እንደእሳቸው ማብራሪያ፡-
“...ሁሉም ሕጻናት መጀመሪያ እንደተወለዱ እንክብካቤ የሚደረግላቸው በጽንስና ማህጸን ሕክምና ክፍሉ ዘርፍ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ ያዋለዱት የህክምና ባለሙያዎች ለተወለደው ልጅ አስፈላጊውን ክትትል ካደረጉ በሁዋላ ምናልባትም ልጁ ተጨማሪ የህክምና እርዳታ የሚያስፈልገው ከሆነ ወይንም እናቱ ብትታመም አሊያም ከማደንዘዣም ያልነቃች ከሆነ ሕጻኑን ወደ ሕጻናት ማቆያ ክፍል እንዲሄድና አስፈላጊው ክትትል እንዲደረግለት ይደረጋል፡፡”
በፈለገ ሕይወት ሆስፒታል ያለው የጨቅላ ሕጻናት መተኛ ክፍል ያለበትን ሁኔታ እንዴት ያዩታል በሚል ስለክፍሉ ሁኔታ ለቀረበላቸው ጥያቄ ዶ/ር ባዘዘው የሚከተለውን መልስ ሰጥተዋል፡፡
“...እንደሚታወቀው ሆስፒታሉ በማዋለጃው ክፍልም ሆነ በህጻናት ክፍሉ በሚሰጠው አገልግሎት በአካባቢው ብቸኛው ሆስፒታል ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህም የተነሳ የወላጆች ቁጥር መጨመር እንዲሁም ሪፈራል ሆስፒታል እንደመሆኑ ከየአካባቢው ችግር ያለባቸው እርጉዝ እናቶች ተመርጠው ወደ ሆስፒታሉ ሪፈር ስለሚባሉ ችግር ያላቸው ሕጻናት የመወለድ እድላቸውም ሰፊ     ነው፡፡ ስለዚህም ካለቀናቸው ወይንም ከክብደት በታች ሆነው የሚወለዱ እንዲሁም የተለያዩ የጤና ችግሮች ያሉባቸው ጨቅላዎች በሙሉ ለተወሰኑ ጊዜያት እንዲቆዩ ስለሚደረግ ክፍሉ     በጣም ይጠባል፡፡ ስለዚህም ወደፊት እንደመፍትሄ የተያዘው፡-
1ኛ/ የሕጻናት ሐኪሞችን ቁጥር ማበራከት፣
2ኛ/ የህክምና ክፍሉን ሰፋ ማድረግ፣
ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫ ሲሆን በተጨማሪም ሕጻናት ካለቀን መወለድ ወይንም የክብደት ማነስ እንዲሁም ሌሎች ችግሮች ቢገጥሙዋቸው በተገቢው መንገድ በተሟላ ሁኔታ ሕክምናውን ለመስጠት አስፈላጊ የህክምና መሳሪያዎች ግዢ በመፈጸም ላይ ነው፡፡
አሁን ባለንበት ሁኔታ ግን ክፍሉ ሰፋ ያለ ችግር የሚታይበት ነው፡፡ የክፍል ጥበት የሰው ኃል እጥረት እንዲሁም የማቴሪያል እጥረት ያለበት ነው፡፡”
በእርግጥ በባህርዳር ፈለገ ሕይወት ሆስፒታል የተመለከትነውና ዶ/ር ባዘዘውም የመሰከሩለት የክፍል ጥበትና የሕክምና አሰጣጥ አለመሟላት በዚያ የሚቀር ሳይሆን በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልም የሚስተዋሉ አንዳንድ ችግሮች አሉ፡፡
ዶ/ር አስራት ደምጸ በጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል የህጻናት ሐኪምና ኒዎናታሎጂስት ለሕጻናቱ በሚሰጠው እንክብካቤ ጉድለት ነው ያሉትን እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፡  
“...የጥቁር አንበሳ ሸክም ከባድ ነው፡፡ አልጋ የለምና ይዛችሁ ወደሌላጋ ሂዱ የማይባልበት ነው፡፡     መጀመሪያውኑም የሚመጡት የተሻለ ሕክምና ፈልገው ስለሆነ ወደሌላ ሂዱ አይባሉም፡፡     ምናልባት እንኩዋን ቀለል ያለ ነው ሂዱ ቢባልም ታካሚዎችም እሺ አይሉም፡፡ አልተለመደም፡፡ ስለዚህም ጨቅላዎቹ ምናልባት አልጋ እንኩዋን ቢያጡ በአንድ አልጋ ላይ እስከ ሁለት ልጅ የምናስተኛበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የነርስ አገልግሎቱን በሚመለከትም ያለው ነርስና ታካሚ     ጨቅላ ቁጥር ተመጣጣኝ አይደለም፡፡ አንዲት ነርስ ለስምንት እና አስር ልጅ ነው አገልግሎት የምትሰጥበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አንድ ነርስ ለአምስት ወይንም ለሶስት ቢሆን ጥሩ ነበር ነገር     ግን ያ ስላልሆነ ከባድ ነው፡፡”
ሌላው ነገር የእናቶች መኝታ ጉዳይ ነው፡፡ በአዲስ አበባ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጨቅላ ሕክምና ክፍል እናቶችን በሚመለከት የታዘብነው ነገር ጨቅላው ሙቀት ፈልጎ ወይንም ክብደቱ እስኪሟላ አሊያም ለኦፕራሲዮን... ወዘተ እንዲተኛ ሲደረግ እናቶቹ ግን መተኛ አልጋ የላቸውም፡፡
“...ወርቄ እባላለሁ፡፡ ልጄን በወለድኩ በሁለተኛ ቀኔ ነው ከሆስፒታል የገባሁት፡፡ ከወንበሬ ላይ እያንቀላፋሁ... ልጄ ጡት ስትጠባ እያጠባሁ አሁን ሶስት ቀን ሆኖኛል፡፡ ልጅትዋ  ሙቀት ስለሚያስፈልጋት ይበቃታል እስክትባል ድረስ የምቆየው በዚሁ ሁኔታ መሆኑ ነው የተነገረኝ፡፡ በወንበር ላይ፡፡”
በባህርዳር ፈለገ ሕይወት ሆስፒታልም የተመለከትነው ነገር እናቶቹ አልጋ እንደሌላቸውና ነገር ግን ባለው ክፍት ቦታ ሁሉ ...ማለትም በየኮሪዶሩ የእስፖንጅ ፍራሽ ዘርግተው መተኛት እንደሚችሉ ነው፡፡ ይህ ድርጊት በተጨማሪነት በክፍሉ ላይ የመጣበብ ነገር ቢኖረውም ግን ከወለደች ገና በቀናት እድሜ ያለች ሴት ከወንበር ላይ ውላ ከምታድር ይሻላል ይላሉ ዶ/ር ባዛዘው፡፡
“...እናቶቹ ከዚህ እንዲቆዩ መደረጋቸው የሚመጡበት አካባቢ በአብዛኛው እራቅ ያለ በመሆኑም ጭምር ነው፡፡ ለሕጻናቱ ጡት ቢያስፈልግ ወይንም አንዳንድ የሚፈለግ ነገር ቢኖር እርቀው ከሄዱ ለማግኘት አስቸጋሪ ስለሚሆን እንደምንም ተጣበን ለእግር መተላለፊያ እስኪጠፋ ድረስ ኮሪደሩ ሁሉ በፍራሽ ተጣቦ ይታያል፡፡ ይህ እንግዲህ ትክክለኛው አሰራር ስላይደለ ወደፊት በሚሰሩ የማስፋፊያ ስራዎች ለእነዚህ እናቶችም ማረፊያ ይኖረናል ብለን እንገምታለን፡፡”
ሌላው በጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ያየነው ችግር የመጸዳጃ አገልግሎት ጉዳይ ነው፡፡ አንዲት እናት በወለደችበት ወቅት ለተወሰነ ጊዜ የተሟላ እና የተመቻቸ የመጸዳጃ አገልግሎት ማግኘት አለባት፡፡ ምናልባት እንደኑሮው ደረጃ ቢለያይም ነገር ግን ማንኛዋም እናት በቂ ውሀ ኖሮአት በብረት ምጣድ ላይም ይሁን በሻወር መልክ እየታጠበች ለልጅዋም ይሁን ለእራስዋ ጤና ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡ በጥቁር አንበሳ ያየነው ነገር ግን ከዚህ ይለያል፡፡ ዶ/ር አስራት ደምጸ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
“...ሆስፒታሉ ብዙ ተገልጋይ ያለውን ከተሰራም ረዥም ጊዜ የሆነው ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ይመስላል የመታጠቢያ ቤቱ ቶሎ የሚበላሽ ሲሆን አሰራሩንም ስንመለከት ለዚያ ሁሉ እናት አንድ መጸዳጃ ቤት ያለበት ሁኔታ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ንጽህናቸውን በአግባቡ እየጠበቁ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ወደጨቅላ ሕጻናቱ መግቢያ ላይ ግን የእጅ     መታጠቢያና ሳሙና ስላዘጋጀን ማንኛውም ሰው ሲገባ እንዲታጠብ ይደረጋል፡፡ እሱም ቢሆን ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ውሀ  የለውም፡፡ ስለሆነም በበርሜል ውሀ አዘጋጅተን     ተግባራዊ እንዲሆን እያደረግን ነው፡፡ እናቶችም እጆቻቸውን ሳይታጠቡ ልጃቸውን አይነኩም፡፡ አሁን ሆስፒታሉ በእድሳት ላይ ያለ ስለሆነ ይሄ ችግር ከግንዛቤ ገብቶ  ለእናቶች ምቹ የሆን  መጸዳጃዎች መታጠቢያ ቤቶች ቢሰሩልን በዚሁ ጥሩ ይሆናል፡፡

Read 1933 times