Saturday, 19 December 2015 10:14

የቅማንት ጥያቄ ምላሽ ቢያገኝም ግጭቱ ተባብሶ ሰንብቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(36 votes)

መንግሥት ሁከት በሚፈጥሩት ላይ የማያዳግም እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል

   በጎንደር ጭልጋ አካባቢ ቅማንትና አማራ በሚል በተደራጁ ቡድኖች መካከል በተፈጠረ ግጭት በርካቶች ለሞት መዳረጋቸው የተገለፀ ሲሆን ነዋሪዎች በስጋት ከቤታቸው ሳይወጡ እንደሰነበቱ ምንጮች ገለፁ፡፡
ግጭቱ ስር የሰደደ እንደነበር የጠቆሙት የአካባቢው ምንጮቻችን፤ ከመስከረም ጀምሮ ተማሪዎች ትምህርታቸውን መከታተል እንዳልቻሉ፣ ከሳምንት በላይ ባስቆጠረው አደገኛ ግጭትም ኢትዮጵያን ከሱዳን የሚያገናኘው መንገድ ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡
ቅማንት በሚል የተደራጀው ቡድን፣ “የቅማንት ጥያቄ እስኪመለስ ትምህርት የለም፤ እናንተም አትማሩም” በሚል ት/ቤቶች ላይ ጥቃት ሲፈፅሙ እንደነበር የጠቀሱት ምንጮች፤ በዚህም የተነሳ የአካባቢው ልጆች ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለዋል ይላሉ፡፡ የቅማንቶች የማንነት ጥያቄ ምላሽ ካገኘ በኋላ ከሰሞኑ ለተፈጠረው ግጭት መነሻ የሆነው “ዞን ይዋቀርልን፣ ድንበር ይከለልልን” በሚል በተነሳ ጥያቄ ነው ተብሏል፡፡
ቅማንቶች የማንነት ጥያቄ ማቅረብ ከጀመሩበት ከ3 ዓመት በፊት አካባቢው ውጥረትና ግጭት ተለይቶት እንደማያውቅ የሚጠቅሱት ነዋሪዎች፤ ከሁለት አመት በፊት ሚያዚያ ወር ላይ በአይከል ከተማ ከፍተኛ ረብሻ ተነስቶ ሰዎች መጎዳታቸውንና በርካታ ሱቆችና መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ያስታውሳሉ፡፡
ባሳለፍነው ሐሙስ ህዳር 30 ቀን 2008 ዓ.ም ግጭቱ በከፍተኛ ደረጃ መቀስቀሱን የጠቀሱት ምንጮቻችን፤ በእለቱ አንድ የቅማንት ወጣት መገደሉን ተከትሎ ቅማንት በሚል የተደራጁ ቡድኖች፤ ዳቦ ቤት ማቃጠላቸውንና ሱቅ ማውደማቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ይህን ተከትሎ የአማራ ብሔር ተወላጆች በሚል የተደራጁ ወገኖች በቋራ፣ ሺንፋ፣ ነጋዴ በሃርና ገንዳ ውሃ በተባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ቅማንቶችን እያባረሩ ቤት ንብረት ማቃጠል እንደጀመሩ ይገልፃሉ፡፡
ከእነዚህ አካባቢ የተባረሩ ሰዎች በአሁኑ ወቅት ጭልጋ ውስጥ በየድንኳኑ ተጠልለው የአካባቢው ህብረተሰብ የእለት ጉርስ እያቀረበላቸው እንደሚገኝና ሰሞኑን ምክትል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ የክልሉ ባለስልጣናት ህዝቡን ሰብስበው እንዳወያዩ ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም የተነሳ በአካባቢው ውጥረት መንገሱን የሚጠቅሱት ምንጮች፤ ሰዎች ከቤት መውጣት እንደተሳናቸውና በየመንገዱ ጦር፣ ገጀራ፣ ቢለዋ፣ መጥረቢያና የጦር መሳሪያዎች የያዙ ሰዎች እንደሚዟዟሩ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ትናንት በአንፃሩ ሠላማዊ እንቅስቃሴ እንደነበር ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
በገጠር አካባቢዎች ተደራጅተው ለጠብ የተዘጋጁ የቅማንት ተወላጆችን መበተን እንዳልተቻለ የሚጠቅሱት የሚናገሩት ምንጮች፤ የመንግስት ባለስልጣናት ከህዝቡ ጋር ባደረጉት ውይይት ግን ከዚህ በኋላ በግጭቱ ተሳታፊ የሚሆኑና ፀብ የሚጭሩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ መናገራቸን ጠቅሰዋል፡፡ ህብረተሰቡም የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ላለመግባት ተስማምቷል ተብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፤ ከቅማንት ብሄረሰብ የማንነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ግጭቶች በመንግስት ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመው የአካባቢውን ሰላም በሚያውኩት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

Read 13813 times