Tuesday, 29 December 2015 07:16

“በለውጥ ጎዳና ላይ ያለ ተቋም

Written by 
Rate this item
(4 votes)

     ታህሳስ 2 ቀን 2008 ዓ.ም ባወጣው አዲስ አድማስ፤ “የመንግስት ብክነት በቢሊዮንና በሚሊዮን…” በሚል ርዕስ ስር ስለ ሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ማዕከል የቀረበው ዘገባ የተሳሳተና ወቅታዊነቱን ያልጠበቀ በመሆኑ ተከታዩ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
ይህ አንጋፋ የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ማዕከል፤ በ1961 ዓ.ም ሲቋቋም በሁለት የሙያ ዘርፎችና በ21 ሰልጣኞች የተጀመረው ስልጠና፤ በአሁኑ ወቅት በ13 የተለያዩ የሙያ ዘርፎች ማለትም በ7 የተለያዩ የሆቴል የሙያ ዘርፎችና በ6 የቱሪዝም የተለያዩ ሙያዎች ከደረጃ 3 እስከ ደረጃ 5 እንዲሁም በዲግሪ መርሃ ግብር በሆቴልና በቱሪዝም ማኔጅመንት ስልጠና በመስጠት ላይ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡ በተገባደደው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ 17 ሺ 884 አስራ ሰባት ሺ ስምንት መቶ ሰማንያ አራት/ ባለሙያዎች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በመደበኛ፣ በማታ ተከታታይ መርሃ ግብርና በአጫጭር ስልጠና በማሰልጠን ለዘርፉ ኢንዱስትሪ ዕድገትና የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፤ በማድረግ ላይም ይገኛል፡፡ ተቋሙ በእስከአሁን የስራ ዘመኑ፣ በገነት ሆቴል የማስፋፊያ ፕሮጀክት በማጠናቀቅ ተጨማሪ 36 የመማሪያ ክፍሎች፣ 13 የቤተ ሙከራ ክፍሎችና 5 የገላ መታጠቢያ፣ 16 የተለያዩ ቢሮዎችና 35 የወንድና የሴት መፀዳጃ ቤቶች በማስገንባት፣ የኮምፒውተር ቤተ ሙከራ ከተሟላ ከኢንተርኔት ጋር የተገናኘ ስልጠና እየተሰጠበት ይገኛል፡፡ እንዲሁም በተሟላ የመስተንግዶ ቤተ ሙከራ፤ በኮምፒውተርና በኢንተርኔት የተደገፈ የቱሪዝምና ሆቴል ቤተ ሙከራና የተሟላ የቤት አያያዝና ላውንደሪ ቤተ ሙከራ ውስጥ የተለያዩ የሆቴልና የቱሪዝም ሙያ ዘርፎች በማሰልጠን ላይ እንገኛለን፡፡
በተጨማሪም በ5 ሺ 474 የተለያዩ ወቅታዊ የማጣቀሻ መጻሕፍቶች፣ በ47 የኦዲዮ ቪዥዋል የትምህርትና ስልጠና መሣሪያዎች፣ የሙያ ብቃት ምዘና በመውሰድ ብቃታቸውን ባረጋገጡ ብቁ አሰልጣኞች /75% የሁለተኛ ዲግሪ/ ያላቸውና የሙያ ብቃት ምዘና በመውሰድ ብቃታቸውን ባረጋገጡ አሰልጣኞች ስልጠና የሚሰጥ ተቋም መሆኑን ጋዜጣው ልብ ሊለው ይገባል፡፡
ማሰልጠኛ ማዕከሉ የዘርፉ የሙያ ብቃት ምዘና ማዕከል ሆኖ ተመርጦ የምዘና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ይህም የሆነው ማሰልጠኛ ማዕከሉ ለዘርፉ ስልጠና የሚውል የተሟላ የስልጠና ግብአት፣ ቀልጣፋና ውጤታማ የሆነ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋቱ መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡
ማዕከሉ ባሳለፍነው የ2007 የትምህርትና ስልጠና ዘመን የአሰልጣኞችን የማሰልጠን አቅም ለማሳደግ ከሞርሸስ፣ ከኬንያ፣ ከቻይና እንዲሁም ከዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በአገር ውስጥ የተለያዩ የሙያ ማሻሻያ ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ የወቅቱ ሰልጣኞች ከነበሩት ውስጥ 98.26% ሰልጣኞች የሙያ ብቃት ምዘና በመውሰድና ብቃታቸውን በማረጋገጥ ወደ ኢንዱስትሪው እንዲቀላቀሉ ተደርገዋል፡፡
በተጨማሪ ማዕከሉ በሆቴልና ቱሪዝም ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 15 ያህል ችግር ፈቺ ጥናታዊ ጽሑፎች በማዘጋጀትና በየዓመቱ 4 ጊዜ 1 ጥናታዊ ኮንፍረንስ በማካሄድ፣ ለዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት እንዲዳረስ አድርጓል፡፡ የማማከር አገልግሎትን በተመለከተ ለተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ማለትም በሁሉም ክልላዊ መንግስትና ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ በሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለተሰማሩና ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ሙያዊ የማማከር አገልግሎት ሰጥቷል፤ በመስጠት ላይም ይገኛል፡፡
በአሁኑ ጊዜም አንጋፋነቱን ጠብቆ እየታደሰ ያለ ተቋም መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡ በያዝነው የትምህርትና ስልጠና ዘመን በመደበኛ፣ በማታ ተከታታይ ትምህርት ከደረጃ 3 እስከ ደረጃ 5 እንዲሁም በዲግሪ መርሃ ግብር ከ2000 በላይ ሰልጣኞች በሜክሲኮ ካምፓስና በገነት ካምፓስ በማሰልጠን ላይ ይገኛል፡፡ እንዲሁም በአገር ደረጃ በዘርፉ የተሰማራውን የሰው ኃይል ያለበት ደረጃና ለቀጣይ አምስት ዓመታት ለኢንዱስትሪው የሚያስፈልገውን የሰለጠነ የበቃ የሰው ኃይል ፍላጐት የሚያመላክት ደረጃውን የጠበቀ የዳሰሳ ጥናታዊ ጽሑፍ ለባለድርሻ አካላት አቅርበዋል፡፡
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አገራዊ ተልዕኮና ኃላፊነትን እየተወጣ ያለውን ተቋም ጋዜጣው ባወጣው ዘገባ፤ በማሰልጠኛ ማዕከሉ፡-
የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ማዕከል የ5 ሚሊዮን ብር አስደናቂ ድራማ
በ8 የቆርቆሮ ክፍሎች ያለ መማሪያ መጽሐፍ
የማሰልጠኛ ክፍሎችን አድሳለሁ ብሎ በቦምብ የታረሱ እያስመሰለ
የኢንተርኔት መስመር መዘርጋት ያቃተው
መጽሐፍ ብርቅ የሆነበት ተቋም
ኮምፒውተር የለም
ማሰልጠኛ ተቋሙ ለስልጠና ጉዳዮች ሳይሆን ለአስተዳደራዊ ጉዳዮች ነው ትኩረት የሚሰጠው
የመኝታ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው ገነት ሆቴል፤ በ5 ሚሊዮን ብር ወጪ ተቦዳድሶ በዝናብ እየተበላሸ፣ ሙጃ እየወረረው የጥንት ዘመን ፍርስራሽ መስሎ አረፈው…
በሚል ያልተገባ፣ ሚዛናዊነቱንና ወቅታዊነቱን ያልጠበቀ ጽሑፍ ማውጣቱን እናሳውቃለን፡፡  
(የሆቴልና የቱሪዝም
ሥራ ማሰልጠኛ ማዕከል)

Read 1811 times