Saturday, 02 January 2016 11:31

የኢትዮጵያ እሴቶች በአራት የአውሮፓ አገሮች ሊተዋወቁ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

     አይ ጂ ኢንተርቴይመንትና ውብሸት አስመጪና ላኪ “ሉሲ ዓለም አቀፍ ጉዞ ለኢትዮጵያ ንግድና ባህል ኤግዚቢሽን” በማለት የመሰረቱት ጥምረት፤ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች በሚካሄዱ ኤግዚቢሽኖች በመሳተፍ የኢትዮጵያን ባህል፣ ምርቶች፣ ቅርሶችና አገሪቷ የ“እኔ” የምትላቸውን እሴቶች እንደሚያስተዋውቅ አስታወቀ፡፡
የአይ ጂ ኢንተርቴይመንት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይስሐቅ ጌቱ፣ የውብሸት አስመጪና ላኪ ድርጅት ባለቤት አቶ ውብሸት ጉታና በአርት (መዝሙር፣ ሙዚቃና ውዝዋዜ) ዝግጅት የሚታወቁት አቶ ሙሉ ገበየሁ ከትናንት በስቲያ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በሰጡት መግለጫ፤ በየዓመቱ በቤዳፔስት - ሃንጋሪ በሚካሄድ 5ኛው ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን በመሳተፍ የአገሪቷን እሴቶች እንደሚያስተዋውቁ ገልጸዋል፡፡
አቶ ውብሸት፣ አምና ከ20 የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ድርጅቶች ባህላቸውን፣ ምርቶቻቸውንና እሴቶቻቸውን ባቀረቡበት 4ኛው የአፍሪካ ኤክስፓ፤ በግላቸው እንደተሳተፉ ጠቅሰው ያኔ ብቸኛ ስለሆኑ የኢትዮጵያን ባህል፣ ምርቶች፣ ቅርሶች፣ እሴቶች፣ …. በሚገባ ስላላስተዋወቁ፣ የተለያዩ ድርጅቶችንና አካላትን ይዘው በመሄድ የኢትዮጵያ ምርት፣ ባህል፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህቦች … በማስተዋወቅ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሩ ለማስገኘት እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡
ከማርች 3-6,2016 በቡዳፔስት - ሃንጋሪ በሚካሄደው ኤክስፖ ለመሳተፍ ውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ የባህልና ቱሪዝም ሚ/ር እንዲሁም የንግድ ሚ/ር ጠይቀን ሀሳባችንን በደስታ ተቀብለው ለሚመለከተው ሁሉ የድጋፍ ደብዳቤ ጽፈውልናል ያሉት አቶ ውብሸት፣ በምርት ጥራታቸውና በአገልግሎታቸው የተመረጡ ሆቴሎችና ሪዞርቶች፣ የቢራና የወይን ጠጅ ፋብሪካዎች ቱርና ትራቭል ኤጀንሲዎች፣ የቆዳ ፋብሪካዎች፣ ቡና ላኪዎች፣ … በኤግዚቢሽኑ ላይ ተገኝተው ምርትና አገልግሎታቸውን ያስተዋውቃሉ ብለዋል፡፡
አውሮፓውያን ኢትዮጵያን በድርቅ እንጂ የከበረ ባህልና ወግ ያላት መሆኗን አያውቁም ያሉት አቶ ይስሐቅ፣ አገራችን የሰው ዘርና የቡና መገኛ፣ የቀደምት የሥልጣኔ ባለቤት፣ የተለያየ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ፣ በርካታ የሚዳሰሱ የማይዳሰሱ፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህቦች፣ ተዝቆ የማያልቅ የተፈጥሮ ሀብት፣ … ባለቤት መሆኗን ከማስተዋወቅ በተጨማሪ፣ የተለያየ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ … ያላቸው በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ተስማምተው የሚኖሩባት አገር መሆኗን፣ በኅብረተሰቡ ባህላዊ ጭፈራና ባህላዊ አለባበስ የተደራጀ የኪነት ቡድን ይዘን ሄደን ትርዒትና ሞዴል ሾው በማቅረብ ኢትዮጵያን እናስተዋውቃለን ብለዋል፡፡
ቡድኑ በመጀመሪያው ምዕራፍ በአራት የአውሮፓ አገሮች የሚዘዋወር ሲሆን፣ በቅድሚያ ከማርች 3-6 ለ4 ቀን በሃንጋሪ፣ ከማርች 12-13 በኦስትሪያ፣ ከማርች 19-20 በስውዘርላንድ በመጨረሻም ከማርች 26-27 በጀርመን ኤግዚቢሽኑን አቅርቦ ማርች 30, 2016 ወደ አዲስ አበባ እንደሚመለስ ታውቋል፡፡

Read 1336 times