Saturday, 02 January 2016 11:57

አትክልት ቤቶች፣ ስጋ ቤቶችና እህል ቤቶች በዲጂታል ሚዛን እንዲጠቀሙ ሊደረግ ነው

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(2 votes)

ባለፉት 5 ወራት 525 ሚዛኖች ተወግደዋል ተባለ

  አትክልት ቤቶች፣ ስጋ ቤቶችና የሰብል ግብይት ቦታዎች ዲጂታል ሚዛን እንዲጠቀሙ ለማድረግ ማቀዱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡ የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ገመቺስ መላኩ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ የስነ ልክ መሳሪያዎች ትክክለኛነት አለመረጋገጡ ሰው በከፈለው ልክ የሚገባውን ጥቅም እንዳያገኝ እያደረገው ነው፡፡
ችግሩን ለመፍታትም ቢሮው በእያንዳንዱ ሚዛን ላይ አመታዊ ልኬት ከማድረጉም በተጨማሪ በየጊዜው ድንገተኛ ክትትልና ፍተሻዎችን የሚያካሄድ ሲሆን አብዛኛው ጉድለትም በነዳጅ ማደያ፣ እንዲሁም በአትክልትና ስጋ ቤቶች እንደተገኘ ተገልጿል፡፡
አንዳንድ ነጋዴዎች ሚዛኑን ከኋላ በመጠምዘዝ፣ ብረት በመለጠፍና መሰል ህገ ወጥ ተግባሮችን በመፈፀም ሚዛን እንዲሳሳት ያደርጋሉ ያት አቶ ገመቺስ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም በነጋዴዎች የማይጠመዘዝና በሰው እጅ የማይስተካከሉ ዲጂታል ሚዛኖች እንዲጠቀሙ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የዲጂታል ሚዛን የአቅርቦት ችግር መኖሩን በመጠቆም ችግሩ ከተፈታ ዕቅዱን ዘንድሮ ለመተግበር ታስቧል ብለዋል፡፡
ባለፉት 5 ወራት 3897 ሚዛኖች ላይ ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጎ 525 ሚዛኖችና 1 ሺህ 682 ማነፃፀሪያዎች ጉድለት ተገኝቶባቸው መወገዳቸውን ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከኢትፍሩት በስተቀር ዲጂታል ሚዛንን የሚጠቀም የንግድ ድርጅት አለመኖሩም ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ወጥነት ያለው ፍትሃዊ የንግድ ክትትልና ቁጥጥር ስርአትን ለመዘርጋት የሚያስችል መመሪያ በስራ ላይ እንዲውል መደረጉ የተጠቆመ ሲሆን መመሪያው በዋናነት ከህብረተሰቡ የሚነሱትን “ፍትሃዊ ስርአት የለም፣ ኪራይ ሰብሳቢነት በድርጅቱ ሰራተኞች ላይ ይስተዋላል፣ ተመሳሳይ ስህተት የሰሩ ንግድ ቤቶች የአንዱ ሲታሸግ የሌላው ይተዋል” የሚሉና መሰል ቅሬታዎችን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡ መመሪያው ግልፅነትን በመፍጠር መሰል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ያለመ ነው ብለዋል አቶ ገመቺስ መላኩ፡፡

Read 1738 times