Monday, 11 January 2016 11:50

ቄራዎች ድርጅት በበግ እርድ ከ900 ሺ ብር በላይ መክሰሩን ገለፀ

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(8 votes)

ባለፉት 4 ወራት በበግ እርድ ከ900 ሺህ ብር በላይ መክሰሩን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ያስታወቀ ሲሆን ለገና በዓል በሬዎችና በጎችን ጨምሮ የ6ሺ ከብቶች እርድ ማከናወኑን ገልጿል፡፡
የድርጅቱ ተወካይ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሸዋለፍ ይትባረክ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ 4 ወራት ድርጅቱ ከ116 ሺህ ብር በላይ ያተረፈ ሲሆን ዘንድሮ ግን በበግ እርድ የተነሳ ከ900 ሺ ብር በላይ ኪሳራ ደርሶበታል።
“ለኪራሳው ዋነኛ ምክንያት በጎቹ ከታረዱና የተለያዩ ሂደቶችን ካለፉ በኋላ ንፁህ ሥጋ ተመዝኖ የሚገኘው የተጣራ ኪሎ ዝቅተኛ መሆኑ ነው” ያሉት አቶ ሸዋለፍ፤ ይሄ ደግሞ ከበጉ ጥራት ጋር በቀጥታ የተያያዘ በመሆኑ ኪሳራው እንዳይቀጥል የበግ አገዛዝ ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ነዋሪ የታረደ የበግ ስጋ ገዝቶ መጠቀምን ባህል አድርጎታል ያሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ በየቀኑ በአማካይ የ300 በጎች እርድ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ በየኮንዶሚኒየሙ የበግ ሥጋ መሸጫ ሱቆች እንደነበሩት ጠቁመው አብዛኞቹ ግን በተለያየ ምክንያት አገልግሎት በማቆማቸው በአሁኑ ወቅት ቄራው በር ላይ የሚገኘውን የመሸጫ ሱቅ ብቻ እየተጠቀምን ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት አራት ወራት ድርጅቱ ከበግ ስጋ ሽያጭ ጋር በተያያዘ ከ900 ሺ ብር በላይ ኪሳራ ደርሶበታል ያሉት አቶ ሸዋለፍ፤ በእነዚሁ ጊዜያት ወቅት ከእርድ አገልግሎትና ከተረፈ ምርት ሽያጭ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉንም ገልፀዋል፡፡

Read 2039 times