Monday, 11 January 2016 12:16

ዳንጐቴ ሲሚንቶ ለሜቄዶንያ 200 ሺ ብር ለገሰ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር፤ለመሰረት በጐ አድራጐት 100ሺ ብር አበረከተ

   በናይጀሪያዊው ባለሀብት አሊኮ ዳንጐቴ፣ የተቋቋመው ዳንጐቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ለሜቄዶኒያ አረጋዊያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የ200ሺ ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ፡፡
የዳንጐቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የስራ አመራሮች ባለፈው ረቡዕ የገና ዋዜማ ዕለት ኮተቤ ብረታብረት አጠገብ የሚገኘውን የሜቄዶኒያ ማዕከል ከጎበኙ በኋላ፤ ለበዓሉ የሚሆን የ200ሺ ብር ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን የፋብሪካው የሽያጭና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ መስፍን አበራ ባደረጉት ንግግር፤በጉብኝቱ እጅግ አስደናቂ ነገር ማየታቸውን በመግለጽ ለመቄዶንያ የተደረገው ድጋፍ የመጀመሪያ መሆኑን ጠቁመው፣ ለአረጋዊያን ማረፊያ የታቀደው የማዕከሉን ግንባታ ሲጀምር ተከታታይ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
የገንዘብ ስጦታውን የተረከቡት የሜቄዶኒያ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ንጉሴ በበኩላቸው፤ከዳንጐቴ ሲሚንቶ ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልፀው፣ ሌሎችም አካላት የፋብሪካውን አርአያ በመከተል ለማዕከሉ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ማዕከሉ በአሁኑ ሰዓት ከ800 በላይ አረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማንን ከየወደቁበት አንስቶ እየደገፈ ሲሆን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተረከበው 30ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የአረጋዊያን ሁለገብ ማዕከል ለመገንባት ወደ 300 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልገውና የተለያዩ አካላት ለግንባታው ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ እያቀረበ መሆኑ ይታወቃል።    
በሌላ በኩል ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር፣ ለመሰረት በጐ አድራጐት ድርጅት 100 ሺ ብር የለገሰ ሲሆን ድርጅቱም ለሚደግፋቸው 680 ቤተሰቦች፣ ለእያንዳንዳቸው አንድ ዶሮና ስድስት እንቁላል በመስጠት፣የገና በዓልን በደስታ እንዲያሳልፉ ማድረጉን አስታውቋል፡፡  
በሚሊኒየም አዳራሽ የገና ገፀ በረከት ባዛርና ኤግዚቢሽን ላይ በነፃ ቦታ አግኝተው ለ12 ቀናት  በቆዩበት ወቅት 34ሺ ብር መሰብሰባቸውን የገለፁት የመሰረት በጐ አድራጐት ድርጅት መስራችና ዳይሬክተር ወ/ሮ መሰረት አዛገ፤አጋጣሚው ከገንዘቡ በላይ በርካታ ወደፊት ሊደግፏቸው የሚችሉ ግለሰቦችን፣ ድርጅቶችንና ዲያስፖራዎችን የማግኘት እድል እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ማስተር ፊልም ፕሮዳክሽንንና የፕሮዳክሽኑን ማናጀር አቶ ቢኒያም ከበደን እንዲሁም ድጋፍ ያደረጉላቸውን ሁሉ አመስግነዋል፡፡

Read 1616 times