Saturday, 16 January 2016 09:55

“ናሁ ቲቪ” በየካቲት የ24 ሰዓት መደበኛ ስርጭት ይጀምራል

Written by 
Rate this item
(8 votes)

የሙከራ ስርጭቱን በናይል ሳት 11595 ጀምሯል
   መቀመጫውን በኬንያ ያደረገውና በኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች የተቋቋመው “ናሁ ቲቪ” የተሰኘ የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ በመጪው የካቲት ወር መደበኛ የ24 ሰዓት ስርጭቱን እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡
ከትላንት በስቲያ ቦሌ በሚገኘው ጎልደን ቱሊፕ ሆቴል በተከናወነው የጣቢያው ይፋ የምረቃ ስነስርዓትና ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የቴሌቪዥን ጣቢያው ባለቤትና ፕሬዚዳንት አቶ ወንድ ወሰን ካሴ እንደተናገሩት፤ በናይል ሳት 11595 ቨርቲካል (V) ላይ የሙከራ ስርጭቱን ቀደም ብሎ የጀመረው “ናሁ ቲቪ” በየካቲት ወር መደበኛ የ24 ሰዓት ስርጭቱን የሚጀምር ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም በኢቴል ሳት 70 ዲግሪ ዌስት 70w እና IP ቲቪ በኩል ስርጭቱን ለመላው አለም ለማዳረስ አቅዷል፡፡
የቴሌቪዥን ጣቢያው በመላው አለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተደራሽነቱን ለማስፋትና ጥሩ የመረጃ አማራጭ ለመሆን በማሰብ፣ በሰሜን አሜሪካና አውሮፓ የዜና ወኪል ለመክፈት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም የ “ናሁ ቲቪ” ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ቅዱስ ዳኛቸው ተናግረዋል፡፡
“ናሁ” የሚለው ቃል የግዕዝ ቃል መሆኑንና “አሁን” የሚል ትርጉም እንዳለው የተናገሩት አቶ ቅዱስ፤ “ጊዜው አሁን ነው” ወይም “Now is the time” የሚል መርህ ያነገበው ጣቢያው፤ ከሚያቀርባቸው ፕሮግራሞች 75 በመቶው በሪያሊቲ ሾው ፎርማት፣ 25 በመቶው ደግሞ በቶክ ሾው አቀራረብ እንደሚዘጋጁም ገልጸዋል፡፡
በጣቢያው የሚተላለፉት ፕሮግራሞች ሙያዊ የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ እንደሚሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የቴሌቪዥን ጣቢያው ሙያ ነክ ጋዜጠኝነት ላይ እንደሚያተኩርና በተለያዩ የሙያ መስኮች የሰለጠኑና የሚሰሩበትን ጉዳይ በጥልቀት የሚያውቁ ባለሙያዎች በአዘጋጅነት እንደሚሳተፉበትም ተገልጿል፡፡
እያዝናና መረጃ በመስጠት ላይ ትኩረቱን ባደረገው “ናሁ ቲቪ”፣ በርካታ ታዋቂ ግለሰቦችና ባለሙያዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ አዝናኝና አስተማሪ ፕሮግራሞችን ለማቅረብ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ አካባቢያዊ አቀፍ (Local frequency) የቴሌቪዥን ጣቢያ ለመክፈት ለሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን ባስተላለፈው ጥሪ መሰረት ተገቢውን መስፈርት አሟልቶ የተመሰረተው ቱባ ሚዲያ፣ መቀመጫውን በኬንያ ካደረገው ናሁ ጋር በመቀናጀት ጣቢያውን መክፈቱ ታውቋል፡፡



Read 10504 times