Saturday, 16 January 2016 10:01

“በአቶ ኤርሚያስ ላይ የተንቀሳቀሰው ቀድሞ የተቋረጠው ክስ ነው” - አቶ ኑረዲን አህመድ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ለቤት ፈላጊዎች በአክሰስ ሪል ስቴት ስር ያሉ መሬቶች ይከፋፈላሉ

   የአክሰስ ሪል ስቴት መስራችና ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፤ ከቤት ገዥዎች 1.4 ቢ. ብር ከሰበሰቡ በኋላ የገቡትን ውል ሳይፈጽሙ ባልታወቀ ምክንያት ከአገር መሰወራቸው ይታወሳል፡፡ መንግስት የቤት ፈላጊዎችን ተደጋጋሚ ክስና ቅሬታ መነሻ በማድረግም አቶ ኤርሚያስ ከአንድ ዓመት በፊት ያቀረቡት ዕቅድ ተቀባይነት አግኝቶ ወደ አገር ቤት መመለሳቸው ይታወቃል፡፡ ባቀረቡት እቅድና በተሰጣቸው ጊዜ አንድም ነገር አላከናወኑም በሚል ሰሞኑን በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየካሄደባቸው ተጠቁሟል፡፡ ከዚህ በኋላ የቤት ፈላጊው ዕጣፈንታ ምን ይሆናል? የገባበት ያልታወቀው የ1.4 ቢ. ብር ጉዳይስ? አቶ ኤርሚያስ የታሰሩት ያቀዱት ባለመሳካቱ ነው ወይስ በሌላ? በሚሉና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ችግሩን ለመፍታት በመንግስት የተቋቋመው ኮሚቴ ሰብሳቢ ከአቶ ኑረዲን አህመድ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡  
አቶ ኤርሚያስን በዋናነት ለእስር የዳረጋቸው ጉዳይ ምንድነው? የተሰጣቸው የጊዜ ገደብ አልቆ ነው ወይስ…?
የጊዜ ገደብ አልቆ አይደለም የታሰሩት፡፡ ሆኖም በንግግራቸው መሰረት አልፈፀሙም፡፡ ከውጭም ሆነው የላኩትና እዚህም መጥተው ያቀረቡት የስድስት ወር እቅድ ነበረ፡፡ ይህ እቅድ በስድስት ወራት ውስጥ ሶስት ነገሮችን መፈፀምና አክሲዮን ማህበሩን ስራ ማስጀመር ነው፡፡
እነዚህ ሶስት ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
የመጀመሪያው ቅድሚያ የተሰጣቸውን ሳይቶች ማስነሳት፣ ሁለተኛው እቅድ የብድርና የእዳ ጉዳይ ያለባቸውንና የሶስተኛ ወገኖችን ጉዳይ መጨረስ፣ ሶስተኛው ደግሞ ሶስተኛ ወገን ጋ የሚገኘውን ብር መሰብሰብ ነበር፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ይሄ ተከናወነ የምንለው አንድም ነገር አላገኘንም፡፡ ይሄ ማለት አንዳቸውም ሳይቶች አልተነሱም፣ ምክንያቱም ሳይት ለማስነሳት ገንዘብ መገኘት አለበት፡፡ ገንዘብ አመጣለሁ ያሉት ደግሞ አብሬያቸው የምሰራው የውጭ ኮንትራክተር ኩባንያዎች አግኝቻለሁ ብለው ነበር፡፡ ነገር ግን አንዳቸውም መጥተው እንሰራለን ያሉ ወይም በተግባር ስራ የጀመሩ ኩባንያዎች የሉም፡፡ ሌላው ከሶስተኛ ወገኖች ጋር ያሉ ጉዳዮችን በድርድር እጨርሳለሁ አንድም በድርድር ያለቀ ጉዳይ የለም፡፡ ሶስተኛው 300 ሚሊዮን ብር አሰባስባለሁ ብለው ነበር፡፡ እንኳን ይሄን ገንዘብ አንድም ብር ወደ አክሲዮን ማህበሩ አካውንት አልገባም፡፡ ይህ የስድስት ወር እቅድ መጋቢት 14 ቀን 2007 ዓ.ም ነው የቀረበው፡፡ አብይ ኮሚቴውም ያፀደቀው ያን ጊዜ ነው፡፡ እስከ መስከረም 30 ቀን 2008 መከናወን ነበረበት፤ ምንም የተጀመረ ነገር ግን የለም፡፡ እንደገና ጥቅምት 18 ቀን 2008 ዓ.ም በመንግስት የተዋቀረው ኮሚቴ ሌላ አቅጣጫ ዘረጋ።
ምን አይነት አቅጣጫ?
ሌላው ወዲያ ወዲህ ይቅርና ቢያንስ ከአክሲዮን ማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ጋር ተስማምታችሁና ተግባብታችሁ መስራት መቻላችሁን እንድናረጋግጥ፣ በተለምዶ ኒያላ ሞተርስ የተባለውን ሳይት ለማስጀመር ቅድመ ሁኔታዎችን ጨርሳችሁ አምጡልን አልናቸው፡፡ ሆኖም እስከ ህዳር አጋማሽና ከዚያ በኋላም ምንም እንቅስቃሴ አልጀመሩም፡፡ ይህን ሁሉ እድል ሰጥተን ታግሰንም የእኛ ሪፖርት፤ ካቀረቡት እቅድ ውስጥ አንዱንም እንዳልሰሩ ያረጋግጣል፡፡
እሺ አቶ ኤርሚያስ በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ቤት ለማግኘት ጓጉቶ የሚጠብቀው ቤት ፈላጊ እጣ ፋንታ ምን ይሆናል ይላሉ?
የአቶ ኤርሚያስ መታሰር የህግ አግባብ ጥያቄ ነው፡፡ መጀመሪያም ከውጭ ሲመጡ የህግ ከለላ ተሰጥቷቸው ሳይሆን ያሉት በርካታ ክሶች ባሉበት ተቋርጠው የመፍትሔው አካል እንዲሆኑ ነው እንጂ ከህግ ተጠያቂነት ነፃ ሆነው አይደለም፡፡ ይህንን ስምምነት ማሳየት ይቻላል፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት አንቀጽ መሰረት፣ የተመሰረቱባቸው ክሶች ባሉበት ተቋርጠው የመፍትሔው አካል ይሆናሉ ተብሎ ነው የመጡት፡፡ ነገር ግን እርሳቸው ባቀረቡት እቅድና በተሰጣቸው እድል መሰረት መፍትሔ ማምጣት ስላልቻሉ ቀደም ብለው የተቋረጡት ክሶች እንደገና ተንቀሳቀሱት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የህግ ጥያቄ እንጂ ከቤት ፈላጊዎቹና ከአክሲዮን ማህበሩ ጉዳይ ጋር የተገናኘ አይደለም፡፡
የህዝቡን ጥያቄ በተመለከተስ?
ቤት ፈላጊ ህዝቡን በተመለከተ አክሲዮን ማህበሩ 1.4 ቢሊዮን ብሩን ከበላና ያ የተበላው ብር መሬት ላይ ነው የዋለው ከተባለ የአክሲዮን ማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ ያ ብር በምንና እንዴት ያሉ ጉዳዮች ላይ እንደዋለ እንዲያሳይ ነው የሚደረገው፡፡ ቤት ፈላጊዎቹ በኮሚቴ ተደራጅተዋል፡፡ ቤት የሚሰሩ ሰዎች የሚደራጁበት አካሄድና የህግ አግባብ አለ፡፡ በዚያ መልኩ ህጋዊ ቁመና ፈጥረው፣ አክሰስ ያለው መሬት ወደ እነሱ የሚዞርበትን መንገድ እያመቻቸን ነው ያለነው፡፡ የተባለውን ብር በተመለከተ ከአክሲዮን ማህበሩ ጋር እየተደራደሩ በህግ እየተከታተሉ ይቆያሉ፡፡ የመሬት ጉዳይ ግን በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙና በህጋዊ መንገድም የአክሰስ ሪል ስቴት የሆኑ መሬቶች አሉ፡፡ እነሱን ካሰባሰብን በኋላ ለቤት ፈላጊዎቹ እናደላድላለን፡፡
ቤት ፈላጊዎቹ መሬት ቢያገኙም የመስሪያውን ገንዘብ ከማውጣት አይድኑም ማለት ነው?
1.4 ቢሊዮን ብሩን በህግ ሂደት የሚያገኙበት መንገድ እንደተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን መንግስት የቤት ፈላጊዎቹን ችግር ለማቃለል ቢያንስ መሬቱን እንዲያገኙ ያመቻችላቸዋል፤ ስለዚህ በራሳቸው ገንዘብ ይሰራሉ ማለት ነው፡፡

Read 3188 times