Saturday, 16 January 2016 10:23

4ኛው ቻን ዛሬ በሩዋንዳ ይጀመራል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

     4ኛው የአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ሻምፒዮንሺፕ (ቻን)  በሩዋንዳ አዘጋጅነት ዛሬ የሚጀመር ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለፈው ሐሙስ  ተጉዟል። አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በተሳትፏቸው ከምድብ ማለፍን እንደውጤት ግብ አስቀምጠዋል፡፡ ቡድናቸው ግብ በማስቆጠር ያሉበትን ችግሮች ያሻሻለበት ዝግጅት ማድረጉን የተናገሩት ዋና አሰልጣኙ፤ የሴካፋ ተመክሮና የሊጉ ውድድር ጠንካራ ቡድን ለማዋቀር እንዳገዛቸው ተናግረዋል፡፡
በዋልያዎቹ  ስብስብ ስምንቱ ተጨዋቾች በሴካፋ  ተሳትፈው የነበሩ ሲሆን የአፍሪካ ዋንጫና የቻን የተሳትፎ ልምድ ያላቸውም ተጨዋቾች ተይዘዋል፡፡ ከግብ ጠባቂው አቤል ማሞና ከአጥቂው ታፈሰ ተስፋዬ ቀላል ጉዳት በስተቀር ወቅታዊ ጤንነታቸው አስተማማኝ መሆኑን የገለፁት አሰልጣኝ ዮሐንስ ፤ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን እንዳካተቱ በመጥቀስ ከምድብ ለማለፍ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ተስፋ ማድረጋቸውንና በምድባቸው የሚገኙትን ቡድኖች  አቅም በተወሰነ መልኩ መረዳታቸውንም አስታውቀዋል፡፡  ኢትዮጵያ በምድብ ሁለት ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፣ አንጎላና ካሜሩን ጋር መደልደሏ ይታወቃል፡፡
  4ኛው ቻን ዛሬ  በዋና ከተማዋ ኪጋሊ በሚገኘው አማሃሮ ስታድዬም በምድብ 1 የመጀመሪያ ጨዋታዎች የሚከፈት ሲሆን ሩዋንዳ ከአይቬሪኮስት እንዲሁም ጋቦን ከሞሮኮ ይገናኛሉ፡፡  ነገ ደግሞ የምድብ 2 የመጀመሪያ ጨዋታዎች የሚካሄዱ ሲሆን በቡታሬ ከተማ በሚገኘው ሁዬ ስታድዬም ዲ.ሪ ኮንጐ ከኢትዮጵያ እንዲሁም አንጐላ ከካሜሮን ይጫወታሉ፡፡
በብሔራዊ ቡድኑ የሚስተዋለውን ግብ የማስቆጠር ክፍተት ለማሻሻል መሀል ላይ ተጭኖ ማጥቃት ላይ የተመሰረተ የጨዋታ ስልት በመቀይስ በቂ ዝግጅት አድርጊያለሁ በማለትም ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ4ኛው ቻን ባደረገው ዝግጅት በቂ የአቀም መፈተሻ አላደረገም ማለት ይቻላል፡፡  ከኒጀር ጋር ባደገው ብቸኛ የአቋም መፈተሽ ጨዋታ 1ለ1 አቻ ተለያይቷል፡፡ሌሎቹ የምድብ 2 ብሔራዊ ቡድኖች ግን ከ1 በላይ የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ ችለዋል፡፡ ሌሎቹ የምድብ 2 ብሔራዊ ቡድኖችና የቻን ተሳታፊዎች ግን ከ1 በላይ የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ ችለዋል፡፡
በምድብ 2 የምትገኘው የ2009 የመጀመሪያው ሻምፒዮን ዲ.ሪ ኮንጐ በብሔራዊ ቡድንና በክለብ ደረጃ በአፍሪካ ከፍተኛ ልምድ ያለውን ስብስብ ይዛለች፡፡  የዲ.ሪ ኮንጐ ብሄራዊ ቡድን በ4ቱም የቻን ሻምፒዮናዎች በመሳተፍ  ከፍተኛ ልምድ ያካበተ ከመሆኑም በላይ የመጀመርያውን የቻን ሻምፒዮንሺፕ ያሸነፈበት ታሪክም አለው፡፡ የዲ.ሪ ኮንጎ ቡድንን  በዋና አሰልጣኝ የሚመሩት ፍሎረንት አቤንጌ ናቸው፡፡ በተጨዋቾች ስብሰባቸው በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ያሸነፉ እና ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የቲፒ ማዜምቤ እና የኤ ኤስ ቪታ ክለብ ተጨዋቾችን አካተዋል፡፡ ስምንቱን ተጨዋቾች ከኤኤስ ቪታ 3 ከቲፒ ማዜምቤ የተቀሩትን ከሌሎች 4 ክለቦች ሰብስበዋል፡፡ በቻን ውድድር ለሶስተኛ ጊዜ የሚሳተፈው የአንጐላ ብሔራዊ ቡድን ሱዳን ባዘጋጀችው 2ኛው ቻን ለፍፃሜ የደረሰና በቱኒዚያ 3ለ0 ተሸንፎ 2ኛ ደረጃ ያገኘበት ታሪክ አለው፡፡ በ3ኛው ቻን በተሳተፈበት ወቅት ደግሞ ከምድቡ ማለፍ አልቻለም ነበር፡፡ የአንጎላ ቡድን በጊዜያዊ አሰልጣኙ ጆሴ ኪሊምባ የሚመራ ቢሆንም አሰልጣኙ የካፍ የስልጠና ደረጃ ፍቃድ ባለመያዛቸው ከቡድኑ ጋር መጓዛቸው አጠያያቂ ነበር፡፡ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሮሚዮ ፋይሌሙን በእግድ ላይ ናቸው፡፡ የአንጎላ ቡድን ዝግጅት ባደረገበት ደቡብ አፍሪካ በመጀመርያ የወዳጅነት ጨዋታ ከናይጄርያ ጋር 1ለ1 አቻ ከተለያየ በኋላ በሁለተኛው የወዳጅነት ጨዋታ ከዛምቢያ ጋር ተገናኝተው 2ለ1 ተሸንፈዋል፡፡ የመጨረሻ  የወዳጅነት ግጥሚያ ከጊኒ ጋርም ለማረግ ሞክረዋል፡፡
ከምድብ 2 ከፍተኛ ግምት የተሰጠው የካሜሮን ብሄራዊ  ቡድን እንደ ኢትዮጵያ ለ2ኛ ጊዜ በቻን የሚሳተፍ ይሆናል፡፡ ካሜሮን ከ4ኛው ቻን መጀመር በፊት በአቋም መፈተሻ ከአዘጋጇ ሩዋንዳ ጋር 1ለ1 ከተለያየች በኋላ የመጨረሻ የአቋም መፈተሻ ግጥሚያ ከኡጋንዳ ጋር በማድረግ በድጋሚ 1ለ1 አቻ ተለያይታለች፡፡
የምስራቅ አፍሪካዋ ሩዋንዳ የ4ኛው ቻንን መስተንግዶ  የተሳካ ለማድረግ በመሰረተ ልማትና ሌሎች  እንቅስቃሴዎች ከ21.4 ሚሊዮን ዶላር በላይ አውጥታለች። በ4ኛው ቻን 3.2 ሚሊዮን ዶላር ለሽልማት ተዘጋጅቷል፡፡ ለሻምፒዮን 750ሺ ዶላር ለ2ኛ ደረጃ 400ሺ ዶላር ይበረከታል፡፡በ3ኛ እና 4ኛ ደረጃ የሚጨርሱ ቡድኖች እያንዳንዳቸው 250ሺ ዶላር ሲታሰብላቸው፤ ለሩብ ፍፃሜ 175ሺ ዶላር፤ በምድባቸው በ3ኛ ደረጃ የሚጨርሱ 125ሺ ዶላር እንዲሁም በምድባቸው በ4ኛ ደረጃ ለሚያጠናቅቁ 100ሺ ዶላር የሽልማት ገንዘብ ይታሰብላቸዋል፡፡
በ4ኛው ቻን የዋልያዎች ስብስብ የተካተቱት 23 ተጫዋቾች
ግብ ጠባቂዎች
አቤል ማሞ፣ ይድነቃቸው ኪዳኔና ደረጀ ዓለሙ
ተከላካዮች
ሥዩም ተስፋዬ፣ አሉላ ግርማ፣ ተካልኝ ደጀኔ፣ ሱለይማን መሀመድ፣ ወንድይፍራው ጌታሁን፣ አስቻለው ታመነ፣ አንተነህ ተስፋዬ፤ ያሬድ ባዬ፤ ወንዲፍራው ጌታሁን
አማካዮች
ጋቶች ፓኖም፣ አስራት መገርሳ፣ ተስፋዬ አለባቸው፣ ቢንያም በላይ፣ ታደለ መንገሻ፣ በኃይሉ አሰፋ፣ ኤሊያስ ማሞ፣ ሳምሶን ጥላሁንና ታፈሰ ሰሎሞን
አጥቂዎች
ታፈሰ ተስፋዬ፣ ራምኬ ሎክና ሙሉዓለም ጥላሁን

Read 2352 times