Saturday, 23 January 2016 13:27

የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ባህርያትና የፖለቲካ-ኢኮኖሚ አንድምታዎች

Written by  ሀብታሙ ግርማ (ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ)
Rate this item
(34 votes)

    መግቢያ
ኢትዮጵያን ላለፉት ሩብ ክፍለ ዘመናት የመራውና እየመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) መመሪያው ያደረገው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም፣ በብዙ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኞችና ምሁራን ሲተች ይደመጣል፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች እንዲህ የሚባል ርዕዮተ ዓለም በዓለም ታይቶ አያውቅም፤ ምንም አይነት የፖለቲካ-ኢኮኖሚ አስተምህሮና (Thoughts) ሀልዮቶች (theories) ድጋፍ የሌለው ነው ብለው ይከራከራሉ፡፡ በእርግጥም ስለ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ምንነት ብዙዎች ግራ ይጋባሉ፤ እንዲያውም የራሱ የኢህአዴግ አባላት ሳይቀሩ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ የላቸውም ሲባል መስማት እንግዳ አይደለም፡፡ ሌላው ደግሞ ግልጽ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አቅጣጫዎች አያስቀምጥም የሚል ነው፡፡ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ገጾች መስተጋብርን የሚፈትሸው ይህ መጣጥፍ፣ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ይሞከራል፡‹-
•    አብዮታዊ ዲሞክራሲ ምንድነው?የኢኮኖሚና ፖለቲካ ገጾቹስ?
•    የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ባህርያት ምንድናቸው? መነሾዎችስ?
•    የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ባህርያት የፖለቲካ-ኢኮኖሚ አንድምታዎች ምንድናቸው?
•    ላለፉት ሃያ አምስት አመታት በተለያዩ የጊዜ ማዕቀፎች ኢትዮጵያ የተመራችበት የኢኮኖሚ ፍልስፍናዎች ማለትም የነጭ ካፒታሊዝም አስተምህሮ (ከ1983 እስከ 1997 ገደማ) እና የልማታዊ መንግስት አስተምህሮ (ከ1998 ወዲህ) የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ግቦችን ከማሳካት አንጻር ውጤታማነታቸው እንዴት ይታያል? በሌላ አማርኛ ነጭ ካፒታሊዝም ወይም ልማታዊ መንግስት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ዋነኛ የኢኮኖሚ  ግቦችን ለማስፈጸም ትክክለኛ አማራጮች ናቸው?
ታዲያ እነዚህን ጥያቄዎች መርምሮ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል መሰረታዊ የሆኑ ጽንሰ ሃሳቦችን ማንሳትና ማብራሪያ መስጠት ያሻል፡፡ አብዮታዊ ዲሚክራሲ ከሶሻሊዝም እና ከካፒታሊዝም ርዕዮተ ዓለማት የተወሰኑ ጽንሰ ሃሳቦችን  ስለሚወርስ በቅድሚያ ስለ  ርዕዮተ ዓለም ምንነትና ባህርያት፣ ስለ ሁለቱ ዋነኛ አማራጭ ርዕዮተ ዓለም አይነቶች ማለትም ካፒታሊዝምና ሶሻሊዝም በአጭሩ ለማለት እሞክራለሁ፡፡
1.1    ርዕዮተ ዓለም (አይዲዮሎጂ) ምንድነው
ርዕዮተ ዓለም (አይዲዮሎጂ) የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በማህበራዊ ሳይንስ መዝገበ ቃላት የሰፈረው በ18ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ገደማ ኮንት ትሬሲ (Count Destott De Tracy) በተባለ  ሊቅ አማካኝነት ነው፡፡ ትርጉሙም ጽንሰ ሃሳቦችን የሚያጠና ሳንይስ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ትርጓሜው እምብዛም አይታወቅም፤ ከዚህ ይልቅ አይዲዮሎጂ የጥናት መስክ ሳይሆን የተለያዩ ተያያዥነት ያላቸው ሀሳቦችንና ሃሳቦቹ ስለሚወልዱት ወይም ስለሚያመላክቱት ጉዳይ(ዮች) የሚገልጽ አንድ ቃል (term) ተደርጎ ይታያል፡፡
ስለ ርዕዮተ ዓለም ስናነሳ ሊሰመርበቸው የሚገባ አራት መሰረታዊ ጉዳዮች አሉ፡-
1.    በመሰረቱ ርዕዮተ ዓለም ወይም አይዲዮሎጂ ሁለት ፈርጆች አሉት፤ እነዚህም የፖለቲካና ኢኮኖሚ ገጾች ናቸው፡፡ ፖለቲካና ኢኮኖሚ በጥብቅ የተቆራኙ ናቸው፤በእርግጥም የፖለቲካ ኢኮኖሚ ምሁራን እንደሚሉት፤ ዘጠና በመቶ የሚሆነው ኢኮኖሚክስ ፖለቲካ ሲሆን ዘጠና በመቶ የሚሆነው ፖለቲካ ደግሞ ኢኮኖሚክስ ነው፡፡ ለዚህም ነው የትኛውም ርዕዮተ አለም (አይዲዮሎጂ) የፖለቲካና ኢኮኖሚ ገጾች አሉት የምንለው፡፡ እነዚህ ገጾች ታዲያ የማይነጣጠሉ፤ ማለትም ተመጋጋቢ ናቸው፡፡ የካፒታሊዝም ርዕዮተ ዓለም የግለሰብ መብቶችን መሰረት ያደረገ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ፍልስፍና ሲኖረው  በኢኮኖሚ ገጹ ደግሞ ዋነኛ የምርት ሀይሎች የሆኑት መሬት እና ካፒታል በግለሰቦች ሊያዙ ይገባል ይላል፡፡ ሶሻሊዝም በአንጻሩ በፖለቲካው ገጹ ከአንድ ፓርቲ የበላይነት ውጭ ምንም አይነት የፖለቲካ አማራቾችን የማያስተናግድ፣ በኢኮኖሚ አስተምህሮው ደግሞ የምርት ሀይሎች በጋራ ባለቤትነት (common ownership of means of production)እንዲያዙ ዓላማው አድርጓል፡፡
2.    አንድ ርዕዮተ አለም የማይነጣጠሉ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ገጾች አሉት ካልን ታዲያ የትኛው ገጽ ይቀድማል፡ የኢኮኖሚ ወይስ የፖለቲካ፣ በሌላ አነጋገር የኢኮኖሚ ፍልስፍናው የሚመራው በፖለቲካ ፍልስፍና ወይስ በተቃራኒው ነው› ብዙ ሊቃውንት  በተወሰነ ደረጃ ለኢኮኖሚ ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የየትኛውም ፖለቲካዊ ቡድን (ሀይል) በዋነኝነት የቆመለትን መደብ ለኢኮኖሚ የበላይነት እንዲኖረው ማድረግ ነው፤ ፖለቲካ ወደዚያው የሚወስድ መንገድ (means) ወይም ማስፈጸሚያ መሳሪያ ነው፤ ለማስፈጸምም የኢኮኖሚ መሰረቶች ሊኖሩት ይገባል፡፡ እናም የትኛውም ርዕዮተ ዓለም በዓላማ (ግብ) ሆነ በማስፈጸሚያ መሳሪያው ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዘው የኢኮኖሚ ፍላጎት (Economic interest) ስለሆነ የኢኮኖሚ ገጹ መሪ ነው ማለት ይቻላል፡፡
3.    ርዕዮተ ዓለም መሰረታዊ መገለጫዎቹን (ስሪቱን) በማይቃረን መልኩ እንደየጊዜውና ማህበረሰቡ፣ የማህበረ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ገጽታዎችና ነባራዊ ሁኔታዎች የተለያየ ትርጓሜና የቅርጽ ለውጥ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ሶሻሊዝም የተለያዩ ዝርያዎች አሉት፡- የሶቭየት ህብረት ሶሻሊዝም፣ የቻይና ሶሻሊዝም፣ የአልባንያ ሶሻሊዝም ወዘተ… ካፒታሊዝም እንዲሁ ታላላቅ ኩባንያዎች መር ካፒታሊዝም (Big-firm led capitalism) ፣ መንግስት-መር ካፒታሊዝም (State- led capitalism)፣ ልሂቃን መር ካፒታሊዝም (Oligarchic capitalism)፣ ኢንተርፕርነሮችን መሰረት ያደረገ ካፒታሊዝም (Entrepreunerial capitalism) ተብሎ ሊከፋፈል ይችላል፡፡
4.    የትኛውም ርዕዮተ ዓለም በዋናነት የሚደግፈው (ጥቅሙን የሚያስጠብቅለት) መደብ አለው፡፡ ለአብነትም ካፒታሊዝም የከበርቴው መደብን መሰረት ያደረገ ነው፤ ሶሻሊዝም በአንጻሩ ለሰራተኛው (ለወዛደሩ) መደብ ፍላጎቶች ቅድሚያ ይሰጣል፡፡
1.2    የካፒታሊዝም እና ሶሻሊዝም (ኮሚኒዝም) መሰረታዊያን
1.2.1    ካፒታሊዝም
እ.ኤ.አ በ1750 ዓ.ም የፈነዳው የኢንዱስትሪ አብዮት፣ የምርት ሂደትና ስርዓት ወለደ፡፡ በሰው ልጅ ታሪክ ታይቶ የማያውቅ የምርት እድገት በግብርናውም ሆነ በማምረቻ ክፍለ ኢኮኖሚ ተፈጠረ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የመደብ ስርዓቱም ተለወጠ፤ በዚህም ኢኮኖሚውን በዋናነት የተቆጣጠረ የኢንዱስትሪያሊስት ከበርቴ መደብ ተፈጠረ፡፡ ይህ መደብ የኢኮኖሚ ጥንካሬውን ወደ ፖለቲካ መንዝሮ አዲስ የፖለቲካ አኮኖሚ ፈጠረ፤ ይህ ስርዓት ካፒታሊዝም ይባላል፡፡
የካፒታሊዝም አስተምህሮ ሶስት ምሰሶዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው የሰዎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚመራበት መርህ የግል ጥቅምን መሰረት ያደረገ ነው የሚለው ነው፡፡ ይህም ለግል  ጥቅም ቅድሚያ መስጠት (Self-interest) ይባላል፡፡ በካፒታሊዝም አስተምህሮ መሰረት የሰው ልጆች በተፈጥሯቸው ሁለት ተቃራኒ መንፈስ አላቸው፡፡ አንደኛው የፉክክር መንፈስ  ሲሆን ሁለተኛው የትብብር መንፈስ ነው፡፡ በሰዎች የኢኮኖሚ ውሳኔ ሂደት ውስጥ ታዲያ የፉክክር መንፈስ ከትብብር መንፈስ አይሎ ይገኛል፡፡ ቀሪዎቹ ሁለት የካፒታሊዝም ምሰሶዎች ፣ የምርት ሀይሎች በግለሰቦች ቁጥጥር ስር መሆን (Private ownership of means of production)፣ እና ነጻና በውድድር መርህ የሚመራ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ (Free Competition)፡፡ ከሶስቱ ምሰሶዎች ካፒታሊዝም ለግል ጥቅም መርሁ የተለየ ቦታ ይሰጣል፡፡ በእርግጥም ያለዚህ መርህ ደጋፊነት ሌሎቹ ሁለቱ ምሰሶዎች ሊቆሙ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም  ሰዎች ሀብት ለማፍራት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለግል ጥቅም መትጋት ትልቁና ወሳኙ ሀይል በመሆኑ ነው፡፡ ታዲያ ሁሉም ሰው የግሉን የኢኮኖሚ ጥቅም ለማሳካት በሚያደርገው ሩጫ ደግሞ ውድድር ውስጥ መግባቱ አይቀርም፡፡ የካፒታሊዝም አስተምህሮን መሰረት የጣለው ስኮትላንዳዊው አዳም ስሚዝ እንደሚለው፤ የሰው ልጅ ፍላጎት መቆሚያ የለውም፤ በመሆኑም በካፒታሊዝም ስርዓት ሰዎች ሁልጊዜ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ከማሳካት ባለፈ ሌላ ግብ ያስቀምጣሉ፤ ሁልጊዜ ፈላጊ ናቸው፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ታዲያ ሁልጊዜም በውድድር ውስጥ ይኖራሉ፡፡
ካፒታሊዝም በዋናነት የከበርቴውን መደብ ጥቅም ለማስከበር የቆመ ስርዓት ነው፡፡ የከበርቴው መደብ ሲባል ግን ሁሉም የንግድና ኢንዱስትሪ አንቀሳቃሽ ግለሰቦችን ያጠቃልላል ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ ቀደም ሲል የተጠቀሱት መሰረታዊ የካፒታሊዝም መርሆች እንደተጠበቁ ሆነው አገራት ካላቸው ተጨባጭ የማህበረ ፖለቲካ ከባቢ መሰረት የሚከተሉት የካፒታሊዝም አይነት ሊለያይ ይችላል፡፡ ከዚህ አንጻር አራት የካፒታሊዝም ዝርያዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው መንግስት- መር ካፒታሊዝም (State-led capitalism) ነው፡፡ በዚህ የካፒታሊዝም ዘር መሰረት መንግስት ለተመረጡ ስትራቴጂክ ዘርፎች ኢንዱስትሪ) የግል ባለሃብቱ እንዲሳተፍ የተለየ ድጋፍ ያደርጋል፡፡
መንግስት ከግል ባለሃብቶች ጋር በአክሲዮን ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችን ይቆጣጠራል፡፡ በቻይና የምናየው የኢኮኖሚ ሥርዓት በአብዛኛው የመንግስት መር ቅርጽ ያለው ነው፡፡ ሌላኛው የካፒታሊዝም አይነት የልሂቃን-መር ካፒታሊዝም (Oligarchic capitalism) ነው፡፡ በእንዲህ አይነቱ የካፒታሊዝም ስርዓት ዋነኛው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾችና የምርት ሀይሎችን የሚቆጣጠሩት ጥቂት በጥቅም ትስስር የተባደኑ እና/ወይም በስጋ ዝምድና የተሳሰሩ ግለሰቦች ናቸው፡፡
ሶስተኛው የካፒታሊዝም አይነት በግዙፍ የግል ኩባንያዎች የሚመራ (Big-firm led capitalism) የኢኮኖሚ ስርዓት ነው፡፡ ይህ አይነቱ የካፒታሊዝም ሞዴል ዋነኛ የኢኮኖሚ ሀይል በጥቂት ታላላቅ ኩባንያዎች የተያዘ ነው፤ የፖለቲካው ስርዓትም በዋነኛነት የኩባንያዎቹን ጥቅም ለማስቆም ይሰራል፡፡ በአራተኛ ደረጃ የምናገኘው ኢንተርፕነር-መር (Entrepreunerial capitalism) ካፒታሊዝምን ነው፡፡ በኢንተርፕርነር መር ካፒታሊዝም መሰረቱ በተወሰነ መልኩ ሰፋ ይላል፡፡ በዚህ አይነቱ ካፒታሊዝም ዋነኛ የኢኮኖሚው ሀይሎች ተደርገው የሚወሰዱት በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ እንዲሁም በቴክኖሎጂም ሆነ በስራ አመራር የቢዝነስ ፈጠራቸው በላቁ ድርጅቶች ነው፡፡
እንደ መንደርደሪያ ይህን ያህል ካነሳን ወደ ዋናው ነጥባችን እንግባ፡፡ እንግዲህ እያንዳንዱ ርዕዮተ ዓለም የራሱ ተመጋጋቢ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ፍልስፍናዎች አሉት ካልን፣ አንድ አገር የምትመራበት የፖለቲካ ፍልስፍና እና የኢኮኖሚ ፍልስፍና ተመጋጋቢ (complementary) መሆን አለበት፡፡ በዚህ አንጻር የተቃኘ የፖለቲካና ኢኮኖሚ አስተዳደር ግልጽ ራዕይ ያለው፣  ፖሊሲዎቹም እንዲሁ ግልጽና አቅጣጫቸውን የሚያውቁ፣ እንዲሁም በኢኮኖሚና ፖለቲካ ሀልዮቶች የዳበሩና የሚደገፉ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ የማህበረ-ኢኮኖሚ እንዲሁም ፖለቲካዊ ዕድገት ለማስፈንም ቁልፉ ጉዳይ ይህ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አብዮታዊ ዲሞክራሲን ርዕዮተ ዓለም እንመርመር፡፡
1.2.2    ሶሻሊዝም (ኮሚኒዝም)
ካፒታሊዝም ስር በሰደደባቸው አገራት የሰራተኛው መደብ በከበርቴው መደብ ይደርስበት የነበረው ጭቆና የከፋ፣የሀብት ክፍፍሉም ኢ-ፍትሃዊ ነበር፡፡ በሁለቱ የካፒታሊዝም መደቦች ማለትም በከበርቴውና በሰራተኛው ክፍል መካከል የነበረው ተቃርኖ እየሰፋ መጥቶ፣ በ19ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ገደማ ጀምሮ ዋነኛ የካፒታሊስት አገራት ማለትም እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እንዲሁም አሜሪካ የኢንዱስትሪ አመጾች ተደጋግመው ይነሱ ነበር፡፡ ከጊዜው ማህበረ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ቀውስ ለመውጣት  ካፒታሊዝምን ማደስ ያሻል ያሉ ሊቃውንት፤ መፍትሄ ብለው የተለያዩ ሃሳቦችን መሰንዘር ጀመሩ፡፡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ይመጣ ዘንድ ካፒታሊዝም ስርዓት ሊወገድ ይገባል ያሉ ሊቃውንቶችም በርካታ  ነበሩ፡፡ ከኋለኞቹ መካከል ካርል ማርክስ አንዱ ነው፡፡ ካርል ማርክስ ካፒታሊዝምን በማከም ከማህበረ ኢኮኖሚ ምስቅልቅል መውጣት አይቻልም፤ ምክንያቱ ደግሞ ካፒታሊዝም በራሱ ሂደት በሶሻሊዝም ይተካ ዘንድ ግድ ይላል፤ ለዚህም ታሪካዊ (historical)፣ ማህበራዊ (social)፣ እና የፖለቲካ-ኢኮኖሚ (political economy) መሰረቶችን አስረጅ በማድረግ ያቀርባል፤ ይህ የካርል ማርክስ አስተምህሮ ሳይንሳዊ ሶሻሊዝም ይባላል፡፡
ሶሻሊዝም የምርት ሀይሎችን (ማለትም መሬትና ካፒታል) ከከበርቴው መደብ አላቆ በሰራተኛው መደብ  ቁጥጥር ስር ማድረግ ዓላማው ያደረገ ነው፡፡ ለዚህም ሰላማዊ፣ ሲያሻ ደግሞ ሀይል የተቀላቀለበት አብዮት ግድ እንደሚል ያስተምራል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉና ኢንዱስትሪ ባልተስፋፋባቸው፣ በዚህም የካፒታሊዝም መሰረት በሌላቸው አገራት ሶሻሊዝምን ማስፈን እንደማይቻል የካርል ማርክስ ትንታኔ ይገልጻል፡፡ ነገር ግን ሌኒን ከዚህ የማርክስ ሃሳብ በተቃራኒ ካፒታሊዝም ባልተስፋፋባቸው አገራት ጭምር ሶሻሊዝምን ማስፈን እንደሚቻል ገለጸ፡፡ በሩሲያ የፊውዳል ስርዓትን በሶሻሊዝም የተካውና በዓለም የመጀመሪያው የሶሻሊስት አብዮት የሆነው 1917ቱ  የጥቅምት አብዮትን በተሳካ ሁኔታ የመራው ሌኒን በእርግጥም ይህን በተግባር አሳየ፡፡ ካፒታሊዝም ባልተስፋፋባት ቻይናም እንዲሁ የገጠር ነዋሪውን መሰረት ያደረገ የሶሻሊዝም አብዮት በማዖ ዜ ዱንግ ቀዳማይ መሪነት ተካሄዶ በስኬት ተጠናቀቀ፡፡ እነዚህ ታሪካዊ ክስተቶች ሶሻሊዝም የኢንዱስትሪ መሰረት በሌላቸው ደሃ አገራት የሲሻሊዝም ስርዓትን ማስፈን እንደሚቻል ያሳዩ ነበሩ፡፡
እንደማንኛውም ርዕዮተ ዓለም፤ ሳይንሳዊ ሶሻሊዝም የፖለቲካና ኢኮኖሚ ገጽታዎች አሉት፡፡ የሶሻሊዝም ፖለቲካዊ ገጽታ የሳይንሳዊ ሶሻሊዝምን መሰረት የጣሉት ካርል ማርክስና ፍሬደሪክ ኤንግልስ “The Communist Manifesto” በተሰኘው መጽሀፋቸው አብራርተዋል፤ በዚህም የሳይንሳዊ ሶሻሊዝም የፖለቲካ ስርዓት ከአንድ ፓርቲ ውጭ ብዝሃ ፓርቲ ስርዓትን አይፈቅድም፤ የፖለቲካ መሰረቱም የሰራተኛውን መደብ ነው፡፡ የሶሻሊዝም የኢኮኖሚ ገጽታ መመሪያ እንደሚለው፤ የሚመሰረተው ኢኮኖሚ የዕዝ ኢኮኖሚ ነው፤ በሶሻሊዝም የመንግስት ዋነኛ ተልዕኮ የሚሆነው ህዝብን በጋራ እንዲኖር ማለማመድ ነው፡፡ በዚህም የከተማው ህዝብን በከተማ ማህበራት፣ ገበሬውን በገበሬ ማህበራት፣ ሰራተኛውን በሰራተኛ ማህበራት፣ ወጣቱን በወጣት ማህበራት፣ ሴቶችን በሴቶች ማህበራት ወዘተ…. ያደራጃል፤ ከዚያም ካፒታሊዝም ወደሚቀጥለው እርከን ይሸጋገራል፡፡ በዚህም ሶሻሊዝም ራሱን ቀይሮ (አሻሽሎ) የኮሚኒዝም ስርዓት ዕውን ይሆናል፡፡ በኮሚኒዝም የመንግስት ሚና በኢኮኖሚው ላይ አነስተኛ ነው፤ ምክንያቱም በሶሻሊዝም በተለያዩ አደረጃጀቶችና ማህበራት ህዝብ ራሱን በራሱ መምራት ተለማምዷል ስለሚባል ነው፡፡ በተግባር ግን ኮሚኒዝም ደረጃ የደረሰ አገር የለም፤ ዋነኛዋ የሶሻሊስት አይዲዮሎጂ መሪ አገር የነበረችው ሶቭየት ሀብረት እንኳ ኮሚኒስት አገር አልነበረችም፡፡
በሶሻሊዝምም ሆነ ኮሚኒዝም አስተምህሮ መሰረት፤ የሀብት ክፍፍል በዋናነት መሰረት የሚያደርገው ችሎታን አይደለም፡፡ በሶሻሊዝም የሀብት ክፍፍሉ መመሪያ ‹‹ከእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ለእያንዳንዱ እንደ ስራው›› የሚል ነው፤ የኮሚኒዝም ደግሞ ለሁሉም ዜጎች እንደየፍላጎታቸው መከፋፈል አለበት ይላል፤ መመሪያውም ‹‹ከእያንዳንዱ እንደችሎታው፣ ለእያንዳንዱ እንደፍላጎቱ›› ነው፡፡

2.    አብዮታዊ ዲሞክራሲ
2.1    አብዮታዊ ዲሞክራሲ ምንድነው?
በዚህ ክፍል ለሚከተሉት ጥቄዎች መልስ ለማፈላለግ ይሞከራል፡፡
•    የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተምህሮ ዋነኛ ምሰሶዎች ምንድናቸው?
•    አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከተለምዶዋዊው ዲሞክራሲ በምን ይለያል?
•    የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ እሳቤዎች ምንድናቸው? የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መሰረታዊ መገለጫዉስ?
አብዮታዊ ዲሞክራሲ መሰረቱ ከቻይናዊው የሶሻሊስት አብዮት መሪ ማዖ፤ ‹የአዲሱ ዲሞከራሲ› መጽሀፍ የተቀዳ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ካፒታሊዝም ባልተስፋፋባቸው አገራት ሶሻሊዝምን እንዴት ማስፋፋት እንደሚቻል የሚያብራራው ይህ የሊቀመንበር ማዖ ፍልስፍና፤ አርሶደሩን መሰረት ያደረገ የሶሻሊስት አብዮትን ማቀጣጠል አላማው ነው፡፡ በመሆኑም አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከፊውዳሊዝም ወደ ሶሻሊዝም በሚደረገው ሽግግር ፖለቲካው የሚመራበት አስተምህሮ ነው፡፡
2.3    የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ
የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲን በመቅረጽ ረገድ የፓርቲው የረጅም ጊዜ መሪ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ በትጥቅ ትግሉ ዓመታት የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍልስፍና ከማዖ ‹የአዲሱ ዲሞከራሲ› ፍልስፍና ጋር የሚመሳሰል ነበር፡፡ ማለትም በኢኮኖሚ ግቡ ሶሻሊዝምን ማስፈን፤ በፖለቲካ ግቡ ደግሞ  የአንድ ፓርቲ የበላይነት የነገሰበት ስርዓት ዕውን ማድረግ ነው፡፡  ነገር ግን ፓርቲው ስልጣን ሊይዝ በተቃረበበት ዓመታት የአለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ ስርዓት ወደ ዲሞክራሲና ካፒታሊዝም በማጋደሉ፣ ኢህአዴግ ይህን ያገናዘበ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ፍልስፍና ለውጥ አደረገ፡፡ እከተለዋለሁ የሚለው አብዮታዊ ዲሞክራሲ በፖለቲካ ግቡ ሊበራሊዝምን ማስፈን፤ በኢኮኖሚ ግቡ ደግሞ ኢንዱስትሪ (ካፒታሊዝም) እንደሆነ ገለጸ፡፡ እናም የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከሶሻሊዝም ወደ ካፒታሊዝም በሚደረግ ሽግግር ፖለቲካው የሚመራበት ስርዓት ነው፡፡
አብዮታዊ ዲሞክራሲ ለፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግቦቹ መሳካት የሚሰራ ጠንካራ የፖለቲካ አመራር (ፓርቲ) መገንባት ያስፈልጋል ይላል፡፡ የመሪ ድርጅቱ አወቃቀርም በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ የተቃኘ ይሆናል፤ በዲሞክራሲ ማዕከላዊነት መርህ መሰረት የፓርቲ ውሳኔዎች የሚተላለፉት ከፓርቲው የበላይ አመራሮች ሲሆን ሌሎች የፓርቲ አባላት ሃላፊነት መመሪያውን ተቀብለው ማስፈጸም ነው፤ በዚህም ለውስጠ ፓርቲ ዲሞክራሲ ብዙም ግምት አይሰጥም፡፡
የኢህአዴግ አብዮታዊ አስተምህሮ እንደሚለን፤ ዲሞክራሲን ለማስፈን የህዝብ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን መመለስ ያስፈልጋል፤ ይህም ከዲሞክራሲ (ከነጻነት) ዳቦ ይቀድማል የሚል ዕምነት የያዘ ይመስላል፡፡ በጥቅሉ የዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት  ጠንካራ የመካከለኛ ገቢ ያለው መደብ መፍጠር ቅድሚያ ሊሰጠው ያስፈልጋል፡፡ የኢኮኖሚም ሆነ ፖለቲካዊ ፍልስፍናውን እንደየጊዜውና ሁኔታው የሚቀያይር መሆኑ የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ዋነኛ መለያ ባህሪ ነው፡፡  
2.2    ምሁራንና የፖለቲካ ሰዎች ስለ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ምን ይላሉ?
ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ‹የኢትየጵያ የታሪክ ፈተናዎች እና የሚጋጩ ህልሞች፡ የኢህአዴግ ቆርጦ ቀጥል ፖለቲካ› በሚለው መጽሃፋቸው (ገጽ 73-75) ላይ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የፖለቲካ ገጾችን እንደሚከተለው ቃኝተዋል፡-
•    (የአብዮታዊ ዲሞክራሲ) ፍልስፍና መሰረት ስልጣን ላይ መምጫው መንገድ የማኦው ፍልስፍና የሆነው ‹‹ ስልጣን የሚመጣው ከጠመንጃ አፈሙዝ ነው” የሚለው ነው፡፡
•    የመሪ ድርጅትና የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ጽንሰ ሃሳቦች የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ዋነኛ መሳሪያዎች ናቸው፡፡ ዓላማውም የመንግስትን ስልጣን ጨምድዶ ለመያዝና ከመንግስት ስልጣን የሚመነጩትን ጥቅሞች ብቻ ዓላማዎቹ አድርጎ ለሚንቀሳቀስ ሃይል ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡
•    በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አንድ ገዥ ፓርቲ የመሪነት ሚና ይኖረዋል፡፡
ሌሎች ፓርቲዎች እንዲኖሩ ባይከለክልም የሚሰጣቸው ሚና የይምሰል እንጂ ጠንካራ ፓርቲ ሆኖ በመውጣት ስልጣን እንዲይዙ አይፈቅድላቸውም፡፡ የፓርቲዎቹ ሚና የገዢው ፓርቲ አገልጋይ መሆን እንጂ ተቀናቃኝ መሆን አይደለም፡፡
•    የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አሰተሳሰብ በፓርቲና  በመንግስት መካከል ፍጹማዊ አንድነትን ይፈቅዳል፡፡ (በዚህም) ልዩ ልዩ የመንግስት ተቋማትም የገዢው ፓርቲ ጉዳይ አስፈጻሚዎች መሆን አለባቸው፡፡……ሁሉም የመንግስት ተቋማትና ሰራተኞቻቸው የገዢው ፓርቲ ፍጹማዊ አመራር መቀበል አለባቸው፡፡….. ይህ ማለት ለሲቪል ሰርቪስ የተቀጠሩ ሰራተኞች የዲሞክራሲያዊ ስርዓት በዳበረባቸው ሀገሮች እንደሚደረገው፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክር ነጻ መሆን አይችሉም፡፡ እንደዚህም በመሆኑ ‹አብዮታዊ ዲሞክራሲ› ለታማኝነት እንጂ ለዕውቀትና ችሎታ ብዙም የማይጨነቅ የካድሬዎች አስተዳደር ይሆናል፡፡
•    (በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተምህሮ መሰረት ነጻ የመንግስት ተቋማት እንዲጠናከሩ ስለማይፈለግ የዘመናዊ የውክልና ዲሞክራሲ መሰረተ ድንጋይ የሆኑት የስልጣን ክፍፍል እና አንዱ የሌላውን ስልጣን መቆጣጠር () አይኖሩም፡፡
•    በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ነጻ የሲቪል ማህበራት እንዲያብቡ አይፈቀድም፡፡ ነጻው ፕሬስ የአድሃሪ ሃይሎች ስለሚሆን ቢታፈን ችግር የለውም፡፡… እንደ ዶ/ር መራራ ትንተና፤ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ሶስቱም የመብት ክፍሎች ማለትም የፖለቲካ፣ የንብረት ባለቤትነት እንዲሁም የሲቪል መብቶች አይከበሩም፡፡
አንጋፋው የህወሃት ታጋይ አቶ ገብሩ አስራት ‹ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ. በተአኘውና በ2007 ዓ.ም ለህትመት በበቃው መጽሃፋቸው ገጽ 148 ላይ አብዮታዊ ዲሞክራሲንና ሊበራል ዲሞክራሲን ሲያነጻጽሩ እንዲህ ነው፡-
‹……….አ.ብዮታዊ ዲሞክራሲ መደባዊ ይዘትንና ወገንተኝነትን ሲያመለክት ሊበራል ዲሞክራሲ ደግሞ ዜጎች ሁሉ ያለምንም አድልዖ እኩል ናቸው ይላል፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የአንድን አገር ዜጎች እንደጠላትና ወዳጅ ይከፋፍላል፤ በሊበራል ዲሞክራሲ አይን ደግሞ ሁሉም ዜጎች እኩል ናቸው፡፡አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጨቃኝ መደቦች መብትና ነጻነት ሊነፈጉ እንደሚገባቸው ሲያመላክት፣ ሊበራል ዲሞክራሲ ደግሞ ነጻነትና መብት ለሁሉም ዜጎች እኩል መሰጠት እንዳለበት ያስረግጣል፡፡ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተምህሮ ማንኛውም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ በመሪ ድርጅት ቁትጥር ስር መሆን አለበት ሲል፤ ሊበራል ዲሞክራሲ ደግሞ ብቃት ያላቸው ዜጎች
ተወዳድረው ፖለቲካውን፣ ኢኮኖሚውንና ማህበራዊ እንቅስቃሴውን እንዲመሩ ያደርጋል፡፡
(ይቀጥላል)
ጸሃፊው፤ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ሲሆኑ በኢ-ሜይል
አድራሻቸው E-Mail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ; ወይም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 17230 times