Saturday, 23 January 2016 13:26

የሥራ ዕድል ፈጠራው ውጤታማነት በተጨባጭ የሚታይ የአደባባይ ሀቅ ነው!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

     ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነን ቅዳሜ ታህሳስ 23 ቀን 2008 ዓ.ም በአዲስ አድማስ የነፃ አስተያየት አምድ ላይ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ከ10.6 ሚሊዮን በላይ የሥራ እድል ተፈጥሯል የሚለውን የመንግስትን ሪፖርት፣ ከእውነት የራቀ ነው በሚል ለንባብ የበቃው የአቶ ዮሐንስ ሰ. ፅሁፍ ነው፡፡
ፀሐፊው በገለፁት መልኩ ጉዳዩ “ለመሳቂያና ለመቀለጃ ተዘጋጅቶ የተቀመጠ” ሳይሆን የጥቃቅንና አነስተኛ የሥራ ዘርፎችን ባህሪያትና የሚያስገኙትን ጠቀሜታ አስመልክቶ የዳበረ ግንዛቤ ካልነበረበት፣ በዘርፉ ስራዎች ላይ ከተሰማራው አስፈጻሚ አንስቶ በህብረተሰቡ መካከል ሰፊ የአመለካከት ክፍተት በነገሰበት፣ ሥራውን በታሰበው ልክ ሊፈፅም የሚችል አደረጃጀትና ብቁ የሰው ሃይል ባልተሟላበት ሁኔታ እጅግ ፈታኝ ተግዳሮቶችን በማለፍ የተገኘ ውጤት ነው፡፡
አሁን ያለንበት ወቅት የምንቀልድበት ሳይሆን እያንዳንዷ የእለት ተእለት እርምጃችን በህዝባችን የኑሮ ደረጃ ለውጥና በሀገሪቱ ቀጣይ እጣ ፈንታ ላይ የከበረ ዋጋ እንዳላት በእጅጉ ተገንዝበን፣ ከድህነት ጋር የሞት ሽረት ትግል የምናካሂድበት ነው፡፡
አቶ ዮሐንስ ሰ. ይህን ፅሁፍ ለመፃፍ ሲያስቡ፣ ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ባለስልጣን አገኘሁት ባሉት ቁንፅል መረጃ ላይ ብቻ ከመንጠልጠል ይልቅ የዘርፉን መረጃዎችንም ለማየት ቢሞክሩ፤ ከተቻለም ተፈጠረ የተባለው የሥራ እድል እንዴትና ለማን ተፈጠረ ብለው ሥራውን ወደሚመራው ተቋም ብቅ ቢሉ ኖሮ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራችን  ያስገኘው ውጤት የብዙዎችን ህይወት የለወጠ፣ የብዙዎች የድካም ፍሬ እንጂ ፌዝ እንዳልሆነ በተጨባጭ ይረዱ ነበር፡፡
ይህም ካልሆነ ሩቅ ሳይሄዱ በአካባቢያቸው በሚገኘው የዘርፉ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ጐራ ብለው ሥራ ፈላጊዎችን ለመለየት፣ ለማደራጀት፣ ሥራ ለማስጀመር፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና መንግስታዊ ድጋፎችን ለማመቻቸት የተሰሩ ሥራዎችንና ያስገኙትን ውጤት በተጨባጭ አስተውለው ቢሆን ኖሮ ይህን የተዛባ ጽሑፍ ለመጻፍ ባልበቁ ነበር፡፡
በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፍ በተለይም በስራ እድል ፈጠራው ባለፉት አመታት የተከናወነው ሥራ፣ በእርግጥም የተሳካ እንደነበር የፍሬወ ተቋዳሽ የሆኑ ዜጐች በተጨባጭ የሚመሰክሩትና እኛም በሙሉ መተማመን የምንናገረው፣ ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ አስፈጻሚ አካላት የአመታት ልፋትና ድካም ውጤት ነው፡፡ ከዘርፉ የአንደኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀም ለማየት እንደሚቻለው፣ ለ3.2 ሚሊዮን ዜጐች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ግብ ተጥሎ፣ በመደበኛው የኢንተርፕራይዞች ልማት ለ7,017,869 ዜጐች፣ በመንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለ3,637,786 ዜጐች፣ በጠቅላላው ለ10,655,655 ዜጐች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡
በተጠቀሰው የአምስት አመታት ጊዜ ውስጥ የተፈጠረውን የስራ እድል ዘርዘር አድርገን ስናየው፤ በቋሚነት 6‚029‚875 (56.6 ከመቶ)፣ በጊዜያዊነት 4‚625‚780 (43.4 ከመቶ) ሲሆን፣ በመደበኛው የኢንተርፕራይዞች ልማት ፕሮግራም ከተፈጠረው የስራ እድል በቋሚነት 4‚543‚240 (64.8 ከመቶ)፣ በጊዜያዊነት 2‚474‚629 (35.2 ከመቶ) እንዲሁም፣ በመንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶች በቋሚነት 1‚486‚635 (40.8 ከመቶ)፣ በጊዜያዊነት 2,151‚151 (59.2 ከመቶ) ነው፡፡
በአጠቃላይ ከተፈጠረው የስራ እድል ውስጥ ተጠቃሚ የሆኑ ሴቶች 4‚387‚701 (41.2 ከመቶ) ሲሆኑ ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ በዘርፉ ልማት 766‚990 ኢንተርፕራይዞችን ለማፍራትም ተችሏል፡፡ በእነዚህ ኢንተርፕራይዞች አማካኝነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጐችን ተጠቃሚ ያደረገ ቋሚና እንደ ስራው ባህሪ የቅጥር ጊዜው ተለዋዋጭ የሆነ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡
የማእከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ፤የከተማ ነዋሪዎችን ቁጥር አስመልክቶ ያወጣውን መረጃ ከላይ ከቀረቡት የዘርፉ መረጃዎች ጋር በማነጻጸር የቀረበው የአቶ ዮሐንስ ጽሑፍ፣ ስህተት አንድ ብሎ የጀመረው በዚህ መልኩ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸውን ዜጐች ማንነት በጥልቀት መቃኘት ካለመቻል የተነሳ ነው፡፡ ከላይ እንደተገለፀው በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት፣ የሥራ ዕድል የተፈጠረው በሁለት መልኩ ነው፡፡ አንደኛው በዘርፉ መደበኛ የኢንተርፕራይዞች ልማት ፕሮግራም በምንለው ሥር ባሉ የስራ ዘርፎች ማለትም በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በንግድ፣ በአገልግሎትና በከተማ ግብርና ንዑስ ዘርፎች ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚያከናውናቸው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ነው፡፡ ጸሐፊው ከመሰረቱ የሳቱት ጉዳይ በእነዚህ ዘርፎች የሚሰማሩ ሥራ ፈላጊ ዜጐች፣ የግድ በከተማ ነዋሪነት ብቻ የተመዘገቡ ናቸው ብለው መነሳታቸው ላይ ነው፡፡
የዘርፉን ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ ከተዘጋጁ መመሪያዎች መካከል አንዱ በሆነው የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፣ በከተማ በሚፈጠሩ የስራ ዕድሎች ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን የሚፈልግ ማንኛውም ዜጋ፣ ከሚኖርበት የገጠር ቀበሌ ሥራ ፈላጊነቱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ በማቅረብ፣ በሚኖርበት ወረዳ ውስጥ በሚገኝ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ በስራ ፈላጊነት ሊመዘገብ ብሎም ከሚፈጠሩት የሥራ እድሎች ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ በአጭሩ፣ባለፉት ዓመታት በተፈጠረው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች በከተማዋ ነዋሪነት የተመዘገቡ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡
በመደበኛው የኢንተርፕራይዞች ልማት ፕሮግራም የሥራ ዘርፎች ከተፈጠረው የሥራ ዕድል በተጨማሪ የመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች በምንላቸው የስኳር ፋብሪካ፣ የህዳሴ ግድብ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የባቡርና የገጠር መንገድ ግንባታ፣ የኤሌክትሪክና የቴሌኮሙኒኬሽን ስራዎች፣ የቤቶች ልማትና የከተማ ማስዋብ፣ የኮብል ስቶን፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታን ጨምሮ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ዜጎች በርካታ መሆናቸውን በተጨባጭ ማስተዋል ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባን ባለፉት ዓመታት የተፈጠረው የሥራ ዕድል ከመደበኛው የኢንተርፕራይዞች ልማት ፕሮግራም በተጨማሪ በእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ በሚሰሩ ኢንተርፕራይዞች አማካኝነትና በግለሰብ ደረጃ በቋሚነትና  በጊዜያዊነት፣ በየጊዜው ለአጭር ጊዜ ሊሆን ይችላል /ከ1 ዓመት ያልበለጠ/ ወደ ሥራ የገቡ ዜጎችንም ጭምር የሚያካትት ነው፡፡
ይህን ሁኔታ ከግምት በማስገባት፣ የመንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶች በሚገኙባቸው አካባቢዎች፣ ሥራ ፈላጊ ዜጎች የሚመዘገቡበትና ወደ ሥራ እንዲገቡ ሁኔታዎች የሚመቻችበት የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ከግንዛቤ በመግባቱ፣ በተለያዩ የመንግስት ፕሮጀክቶች ላይ ጣቢያው ተቋቁሟል፡፡ ጸሐፊው ሩቅ ሳይሄዱ በአዲስ አበባ በቤት ልማት ፕሮጀክቶችና የኮብልስቶን መንገድ ሥራዎች ላይ በቋሚና በጊዜያዊነት የተሰማሩ ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ ያልያዙ ዜጎችን እጅግ ከፍተኛ በሚባል መጠን ማግኘት የሚችሉ ሲሆን በየክልሉ በሚካሄዱ ፕሮጀክቶች የሚሰሩ ዜጎች የየአካባቢው የገጠር ቀበሌ ነዋሪ ወጣቶችንም ጨምሮ እንጂ የከተማ ነዋሪዎች ብቻ አለመሆናቸውን በቀላሉ ማረጋገጥ የሚችሉት ነው፡፡
ምንም እንኳን የዘርፉ የሥራ እድሎች የሚፈጠሩት በከተማ ውስጥ እንደሆነ በስትራቴጂው ላይ ቢገለፅም ባለፉት ዓመታት የአርሶ አደሩ የአኗኗር ሥርዓት ላይ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በገጠር ቀበሌዎች እንደ ንግድ፣ አገልግሎትና የከተማ ግብርና የመሳሰሉ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እንዳለ ተስተውሏል፡፡ በዚህም መሰረት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፍ፣ “የገጠር የሥራ ዕድል ፈጠራ” በሚል ራሱን ችሎ በተከናወነ ፕሮጀክት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ተችሏል፡፡ እነዚህ ዜጎች በከተማ ነዋሪነት የተመዘገቡ ባይሆኑም ከሀገሪቱ ሀብት በፍትሃዊነት የመካፈል መብት ያላቸው ኢትዮጵያውያን እንጂ ጸሀፊው እንደሚሉን ከቅርብ የጎረቤት ሀገራት አልያም ከባህር ማዶ የመጡ ባዕዳን አይደሉም፡፡
በዘርፉ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ነገር ግን የግድ የከተማ ነዋሪ መሆን ከማይጠበቅባቸው ዜጎች መካከል ከተለያዩ የቴክኒክና ሙያ እንዲሁም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚወጡ ዜጎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ መንግስት ለምሩቃን የሥራ ዕድል ፈጠራ በሰጠው ትኩረት፣ እስከ ሰኔ 2007 ዓ.ም ድረስ ለ407, 682 ምሩቃን የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ምሩቃንን ወደ ሥራ ለማስገባት በተዘጋጀው መምሪያ ላይም ማንኛውም ምሩቅ በሚፈልገው የሥራ ዘርፍ፣ በመረጠው የሀገሪቱ ክፍል ከትውልድ ሥፍራው ከዚህ በፊት በዘርፉ ተደራጅቶ እየሰራ አለመሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ በማቅረብ፣ የዘርፉ የሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ መሆን ይችላል፡፡
የሥራ ፈጠራችን ዋነኛ ግብም ለኢንዱስትሪ ሽግግሩ መሰረት የሚሆኑ ኢንተርፕራይዞችን በስፋት ከማፍራት በተጨማሪ አቅም በፈቀደ መጠን በመደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆኑ የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶች፣ በቋሚነት ይሁን በጊዜያዊነት፣ የከተማ ነዋሪዎችም ሆኑ በሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ ለመሆን የሚሹ ማናቸውም ዜጎች፣ ሰርተው ራሳቸውንና ሀገራቸውን ሊለውጡ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ይህንን መሰረት በማድረግም ባለፉት አመታት በዘርፉ ልማት ያከናወናቸው ሥራዎች ወደ ሥራ መግባት ከሚገባቸው ዜጎቻችን አንጻር ስንመዝነው በቂ ነው ማለት ባይቻለንም፣ ጸሐፊው እንዳጣጣሉት ከእውነት የራቀና የማይጨበጥ ሳይሆን የበርካቶችን ህይወት የለወጠና በየአካባቢያችን የምናየው ሀቅ ነው፡፡
በመሆኑም አቶ ዮሐንስ፤ እንደ ዜጋ በሀገራቸው የልማት ሥራዎች ላይ ግልጽ ያልሆኑላቸውን ነገሮ የመጠየቅ መብታቸውን የምናከብር በመሆኑና በጽሁፋቸው ያሰፈሩት ጉዳይም ምን አልባትም በቂ መረጃ ካለመያዝ የመነጨ ይሆናል ብለን ስለምንገምት፣ወደፊት ተጨማሪ ማብራሪያ የሚሹ ከሆነ በራችን ሁሌም ክፍት መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
የፌደራል የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ
የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

Read 4615 times