Saturday, 23 January 2016 13:35

ከቤት ደላላነት እስከ ታክሲ ሹፌርነት

Written by 
Rate this item
(3 votes)

   ወ/ሮ ዘሃራ ኑረዲን በህይወት የተለያ ምእራች በአስቸጋሮ ሁኔታ ያለፉ ሴት ናቸው፡፡ ወ/ሮዋን የላዳ ሹፌር በመሆን ሁለት ልጆቻቸውን በብቸኝነት የሚያስተዳድሩ እናት ናቸው፡፡ ያለፉበትን የህይወት ውጣ ውረድና ስኬቴ ያሉትን የታክሲ ማሽከርከር ህይወት ለአዲስ አድማሷ ጋዜጠኛ ማህሉት ኪዳነወልድ በአጭሩ አውግተዋል፡፡
እስኪ ስለ አስተዳደግዎ ያጫውቱኝ?
የተወለድኩት አዲስ አበባ አባ ኮራን ሰፈር፣ ልዩ ስሙ ሐግቤስ አካባቢ ነው፡፡ ለቤተሰቦቼ አራተኛ ልጅ ነኝ፡፡ አሁን ሁለቱ በህይወት ስለሌሉ ሁለተኛ ልጅ ሆኛለሁ፡፡ በአጠቃላይ ግን 12 ነበርን፡፡ እናትና አባቴ ከዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል የሚመደቡ ነበሩ፤በእርግጥ ወደ መጨረሻ አካባቢ  በእናቴ ጥረት ነገሮች ተቀይረዋል፡፡  
የትምህርት ሁኔታስ?
ከ8ኛ ክፍል ነው ያቋረጥኩት፡፡ እንደነገርኩሽ ወላጆቼ ኑሮአቸው ጥሩ አልነበረም፤እናም እነሱን ለመርዳት በማሰብ ትምህርቴን አቋርጬ አረብ አገር ሄድኩኝ፡፡ ለ3 ዓመት ስሰራ ከቆየሁ በኋላ እዛው የነበረ ኢትዮጵያዊ አጨኝና ትዳር ተጀመረ፡፡ ሆኖም ትዳሬ ስኬታማ አልነበረም፤ እኔ የማደላው ለቤተሰቦቼ ነው፡፡ ሃሳቤ ሁሉ የእነሱን ህይወት መቀየር ነበር፡፡ እሱ ደግሞ ለቤተሰቤ ትኩረት መስጠቴን አልወደደውም፡፡ ይባስ ብሎም እንደ እህት ከምወዳት ጓደኛዬ ጋር ግንኙነት ጀመረ፡፡ አሁን እንደውም ተጋብተዋል፡፡ ያንን መቋቋም አልቻልኩም፡፡ የአንድ ዓመት ልጄን ይዤ ወደ አገሬ፣ወደ እናቴ ቤት ተመለስኩ፡፡
ከአረብ አገር ስትመጪ የቋጠርሽው ጥሪት ነበረሽ?
በጭራሽ ቤሳቤስቲ አልነበረኝም፡፡ እዚያ የኖርኩት ለቤተሰቤ ነው፡፡ በዚያ ላይ ልጅ ነበር፡፡ ንብረት ከተባለ የራሴ የጣትና የአንገት ወርቅ ብቻ ነው የነበረኝ፡፡
ታዲያ አዲስ አበባ እንዴት ተቀበለችሽ?
እሱ ነበር ከባዱ፡፡ እናቴ ጠንካራ ሴት ናት፤ጥንካሬን አውርሳኛለች፡፡ ያልሰራችው ነገር የለም፡፡ እንጀራ ጋግራ አከፋፍላለች፡፡ ሹራብ ሰርታ ሸጣለች፡፡ ከመጣሁ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ መረጋጋት አልቻልኩም፤እኔም ከነልጄ እሷ ቤት ነው የገባነው፡፡ ትንሽ ቆይቼ ግን የቤት ደላልነት ሥራ ጀመርኩ፡፡
የቤት ደላልነት ለሴት አልተለመደም፡፡ ወደዚያ ለመግባት ያነሳሳሽ የተለየ ምክንያት ነበር? ሥራውስ አልከበደሽም?
ውይ ---- በጣም ከምነግርሽ በላይ አድካሚ ነው፡፡ አንዳንዱ ሰው ሊከራይ ሳይሆን ሊገዛ ነው የሚመስልሽ፡፡ እኔን ወደ ስራው እንድገባ ያበረታቱኝ አብረውኝ የተማሩ ሁለት ልጆች ሙያው ላይ ስለነበሩ ነው፡፡ እነሱ ያግዙኝ ነበር፡፡ የሰዎች ስሜትና ፍላጎት የተለያየ ነው፡፡ ቤት እየዞርሽ አሳይተሽ የማይፈልግም ይኖራል፡፡ አንዳንዴ አከራዮቹ እራሳቸው መንገድ ላይ ያገኙሽና በዚህን ያህል ብር የሚከራይ ቤት አለ ይሉሽና፣ ተከራዩ ደግሞ ስፋቱን ስንት ነው፣ ግድግዳው በሩ --- ይልሻል፡፡
በስራው የገጠመሽ ገጠመኝ ከአከራይ ወይ ከተከራይ
ብዙ ነገር ይገጥምሻል፤ ቀብድ ሰጥቶ የሚቀር አለ፡፡ በመሃል ካልገባሁ ብሎ የሚያስጨንቅ አለ፡፡ ጥሩው ነገር ግን ሴት ስለሆንኩ ነው መሰለኝ ሰዎች እኔን በጣም ያምኑኝ ነበር፤ የምላቸውን ይሰሙኛል፡፡  
 የድለላውን ሥራ እንዴት ተውሽው?
ድካሙን አልቻልኩም፡፡ ኩላሊቴን አመመኝ፡፡ ግን አሁን አሁን ሳስበው ድካሙን ችዬ ብቆይ ኖሮ ያዋጣኝ ነበር እላለሁ (ሳ---ቅ--)
ከዚያስ ምን መስራት ጀመርሽ ?
ለትንሽ ጊዜ የምኖርበት የቀበሌ ቤት ጥግ ላይ ውሃና ለስላሳ መሸጥ ጀምሬ ነበር፡፡ እሱም አልተሳካም፡፡ በመሃል በእናቴ እርዳታ 2ኛ መንጃ ፍቃድ አወጣሁ፡፡ ሆኖም እጅ የምፈታበት መኪና አላገኘሁም፡፡ በመሃል ትዳርም ሞክሬ ነበር፤ከሁለት ዓመት በላይ አልዘለቀም፡፡ ግን ከሁለቱም ትዳሬ ሁለት የሚያማምሩ ሴት ልጆችን አፍርቼበታለሁ፡፡  
የልጆቹ አባቶች ይረዱሻል?
በጭራሽ አንድ ቀንም አይተዋቸው አያውቁም፡፡ አሁን ሁለቱም ሌላ ሚስት አግብተዋል፡፡ ነፍሷን ይማረውና ልጆቼን በማሳደግ በኩል ብኩን እናቴ ሁሉ ነገሬ ነበረች፡፡
ባወጣሽው 2ኛ መንጃ ፍቃድ ሰራሽበት ?
እናቴ አንድ ቀን የሆነ ዱቄት ፋብሪካ ወሰደችኝና መንጃ ፍቃዴን ኮፒ አድርጌ ለባለቤቱ ሰጠሁት፡፡ መጀመሪያ ሴት በመሆኔ ደስ ብሎት፣ አንቺ የልጆቼ ሹፌር ትሆኛሽ፤ ጎበዝ ልጅ ነሽ፤በርቺ አለኝ፡፡ በኋላ ቢሮ ቀጥሮኝ ፈተና ሲፈትነኝ ግን እጄን ስላልፈታሁ ትንሽ አቃተኝ፡፡ እሱም ለልጆቹ ስላጨኝ ፈራ፡፡ በቃ ትንሽ ጊዜ እጅ እስክትፈቺ ብሎ የዱቄት ፋብሪካው የስምሪት ክፍል ኃላፊ አደረገኝ፡፡ እኔ ግን ህልሜ መንዳት ነበር፡፡ የሚገርምሽ በልጅነቴ እቤት ውስጥ ወደፊት የአንበሳ አውቶቡስ ሹፌር ነው የምሆነው ስል እናቴ ትናደድ ነበር፡፡ አንቺ ከልጆቼ ፈጣን ነሽ፡፡ ትልቅ ተስፋ ያለኝ ባንቺ ነው፤እንደዚህ አትበይ ትለኝ ነበር፡፡ በስምሪት ሰራተኝነቱ ብዙም አልገፋሁም፤ ደሞዜም ከ500 ብር የማይበልጥ ነበር፡፡
በዚህ መሃል 3ኛ መንጃ ፍቃድ አወጣሁ፡፡ ግን ስራ ማግኘት ቀላል አልነበረም፡፡ ያልሞከርኩበትና ማመልከቻ ያላስገባሁበት መስሪያ ቤት የለም፡፡ ግማሹ ሴት መሆኔን ሲያይ ቦታ የለም ይለኛል፡፡ እንደ በፊቱ እንዳልቸገርም የሰፈራችንን የታክሲ ሹፌሮች እየለመንኩ እጄን በደንብ ፈታሁ፡፡ በዚህ መሀል እናትና አባቴ ተከታትለው ሞቱ፡፡ ልጆቼን ይዤ የምገባበት አጣሁ፡፡ የቀበሌውም ቤት ብዙ ታሪክ አለው፤ ብቻ ተወሰደ፡፡ ግን ሁልጊዜ የምፅናናበት እናቴ ከእኔ ስምንት እጥፍ ችግሮችን ተቋቁማ ያሰበችበት መድረሷ ነበር፡፡ በኋላ ላይ እኔም የላዳ ታክሲ ሹፌር ሆንኩ፡፡
 የላዳ ሹፌርነት አልፈተነሽም ? ሴት በመሆንሽ የሰው አቀባበል እንዴት ነበር?
 አዲስ አበባ ውስጥ ያለነው ሴት ላዳ ሹፌሮች ሁለት ወይ ሦስት ብንሆን ነው፡፡ ያው ሰው በተለያ አይነት መንገድ ነው የሚቀበልሽ እንዳመጣጡ መቀበል ነው፡፡ አንዳንዴ በተለይ ከመሸ አፏጭተው አስቁመው ሴት መሆኔን ሲያዩ ደንግጠው ጥለውኝ የሚሄዱም አሉ፡፡
በታክሲ ሹፌርነት ህይወትሽ በበጎነት የምትጠቅሻቸው ገጠመኞች ይኖሩሻል ብዬ እገምታለሁ----
ሰው በጣም ያዝናል፡፡ እንደምታይው ትንሽ ወፍራም ነኝ፡፡ ቀን ቀን ከሙቀቱ ጋር ላቤ በጣም ይወርዳል፡፡ እንደውም አንዱ ተሳፋሪ፣ አባይ መገደብ የነበረበት ከአንቺ ነው ብሎ ቀልዶብኛል፡፡ እናም ከተነጋገረው ክፍያ በላይ ጨምሮ የሚሰጥሽ ብዙ መልካም ሰው አለ፡፡ ያው እንዴት ስራውን ጀመርሽ ምናምን እያለ የሚያደርቅሽም አይጠፋም፡፡  
መጥፎ የምትያቸው ገጠመኞችሽ?
ውይ እነሱ ብዙ ናቸው፡፡ ብዙ ችግሮች አይቻለሁ፤አሁን አሁን ሥራ ካልጠፋ አላመሽም፡፡ በፊት ግን ለሊትም እሰራ ነበር፡፡ ያው ገቢ ማስገባት አለብሽ፤የቤት ኪራይም አለ፡፡ የልጆች ቀለብ ምናምን --- ወጪዎች ስላሉ አመሽ ነበር፡፡ ታዲያ ሰክሮ የሚሳደብ ብዙ ነው፡፡ አንዱ ጉራንጉር ሰፈር ውስጥ ካላስገባሽኝ ሂሳብ አልከፍል ብሎ፣በፖሊስ ኃይል ያመለጥኩበት ግዜም አለ፡፡ ከኋላ ጭነሽው ድንገት ተነስቶ የሚደበድብም አለ፡፡ ሰክሮ ብር ሳይዝ ገብቶ ቦታው ሲደርስ አልከፍልም የሚልም ያጋጥማል፡፡ ብዙ አላስፈላጊና ጭንቅላት የሚነኩ ቃላቶችን የሚናገርሽም አለ፡፡ በተለይ እኔ ሙስሊም እንደመሆኔ፣ሙስሊም ደንበኞቼ ስራሽ ከእምነት ጋር አይሄድም፣በሚል ይቃወሙኛል፡፡ ከብዙ ወንዶች ጋር ስለሚያገናኝሽ አቁሚ የሚሉኝም አሉ፡፡ እንደውም አንድ ደንበኛዬ፤ባለፈው “ይሄን ስራ ከአሁን ጀምሮ አቁሚ” ሲለኝ፤ “ነገ ተቸግሬ አስር ብር ስጠኝ ብልህ፣እግር አለሽ ሰርተሽ ብይ ነው የምትለኝ፤በዚህ አልጠራጠርም፡፡ በዲናችንም የሚያስጠላው የሰው እጅ ማየት ነው” በማለት መልሼለታለሁ፡፡ ለእኔ ስራዬ ኑሮዬን አሸንፎልኛል፤እዚህ ጋ ለመድረስ ያልፈነቀልኩት ድንጋይ የለም፡፡ የታክሲ ስራ ለእኔ ትልቁ ስኬቴ ነው፡፡ ህልሜን ነው የሞላሁት፡፡ በእኔ አእምሮ ጥሩ ስራ ነው፡፡ የሰው ፊት ከማየት ገላግሎኛል፡፡ የአበራና የተሰማ ሀሳብ ለኔ ዳቦ አይሆንም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ መልካም ሰው አለ፤ወርጄ ጎማ ስቀይር የሚያየኝ ሹፌር ሁሉ ካላገዝኩሽ ይላል፡፡ አንዳንድ ደንበኞችም፤“ትንሽ ትንሽ ብር የሚያዋጣልሽ ፈልጊና ደህና መኪና ግዢ፤እኛም እናግዝሻለን” ይሉኛል፡፡
ላዳዋ ያንቺ ናት ወይስ ተቀጥረሽ ነው የምትሰሪው?
አሁን አይደለችም፤ግን ትሆናለች፡፡ አሁን የያዝኳት ላዳ አሮጌ ብትሆንም፣ ጥረቴን ያየ አንድ መልካም ሰው ሰርቼ እንድከፍለው የሰጠኝ ነው፡፡ አሁን ግማሽ ያህሉን ከፍያለሁ፤ስጨርስ ስሙን ያዞርልኛል፡፡
ወደፊት ስንገናኝ ከአንቺ ምን ልጠብቅ?
በየቦታው የማያቆመኝን የራሴን ላዳ ታክሲ ይዤ! (…ሳ…ቅ….) ያኔ አንቺንም እሸኝሻለሁ  (ሳ…ቅ…)

Read 3090 times