Saturday, 23 January 2016 13:46

ካምቦሎጆ ወግ

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(0 votes)

    የሰንበት ጀምበር ብቅ ባለች ቁጥር ደርሶ የሚያበረኝ አባዜ አለ፡፡የካምቦሎጆ ካራማ እያዳፋ ከእቅፉ ሲከተኝ አፍታም አይፈጅበትም፡፡ሰርክ እንደእኔ ቀልቡ እየተሰለበ ከእልፍኙ የሚዶለው ምርኮ ወፈሰማይ ነው፡፡የልክፍቱ ቁራኛ ለመሆን እግር የሚያቀጥን ምልልስ ማድረግ መለኪያ አይደለም፡፡ለአንዲት ነጠላ ቀን  ፊትን ማስመታት በቂ ነው፡፡ሲለጥቅ እንደ መርግ ተጭና የኖረችው ሕይወት ወሃ የማታነሳ ገለባ መሆን ትጀምራለች፡፡ቧልቱ፣ግብብነቱ ሁሉ ከቅለት ዘረ-መል ተለንቅጦ ይበጃጃል፡፡ቅለት/simplicity/የካምቦሎጆ ዜጋ ብቻ የሚታደለው ስጦታ ነው፡፡
ካምቦሎጆ  እንዲህ እንደአሁኑ ሳይነፍስበት የአላፊ አግዳሚውን ቀልብ ለመስረቅ በኩራት ይገማሸር ነበር፡፡አሁን ያ ሁሉ ገርማ ሞገስ ደብዛው የለም፡፡በዙሪያው በተቀለሱት ቀውላላ ሕንጻዎች ምክንያት ወደ መጠነኛ ጉብታ ተቀይሯል፡፡በእኛ በካምቦሎጆ ቤተኞች ዘንድ ግን ይህ ሁሉ ቁመና ከቁጥር አይጣፍም፡፡በልባችን ንጣፍ ላይ ያኖረው የአብሮነት ሕንጻ ከሁሉም በላይ ልቆ ይታየናል፡፡በልክፍቱ ተጠልፈናል፣በሱሱ ናውዘናል፣በኹካታው ተጥበርብረናል፡፡ከእዚህ በላይ ዓይን የሚይዝ ትዕይንት ከወዴት ይገኛል፡፡
ዛሬም እንደወትሮው ማልጄ  ነው ከካምቦሎጆ እልፍኝ የደረስኩት፡፡ክብ ሠርተው የሚያውካኩ መሸተኞች አካባቢ ተጎራበትኩ፡፡እርስ በእርስ ክርክር ይዘዋል፡፡ፍሬ የሌለው እሰጣ ገባ ነው፡፡ጉንጭ አልፊ ክርክራቸውን ሊያመክን በመጽሓፍ ቁልል የተደበቀ መጽሓፍ አዟሪ ብላቴና ቀረባቸው፡፡ፊት ነስተው አበረሩት፡፡ በአልሸነፍ ባይነት ወደ እኔ አቅጣጫ ተንደረደረ፡፡ከቁልሉ መሀል አንዱን ጋበዘኝ፡፡አፈፍ አድርጌ ዙሪያ ገባውን ቃኘሁት፡፡ከፊት ለፊቱ ገጥ ላይ የታተመው የደራሲው ገጽታ ቅጭም ብሏል፡፡ጥቂት ገጾችን እንደገፋሁ የአንድ የምዕራፍ መግቢያ ላይ የሠፈረው ፍሬ ነገር ሁለመናዬን ረባበሸኝ፡፡
“ግመል የንዳድ ሰታቴን፣የሐሩር መቀመቀን የሙጥኝ ያለው አለነገር አይደለም፤የክብር ጉዳይ ሆኖበት እንጂ፡፡በጋራ፣በተረተሩ መሀል ምራቂ ከመምሰል፣ ምንም በሌለበት ኦና፣ አውላላ በረሃ ላይ እንደጅብራ ተገትሮ መመለክ አምሮት ቢሆንስ እንዲህ የሚማስነው……”ይላል
በእርግጥም አባባሉን በምናቤ መነጽር መረመርኩት፡፡በኢጎ፣ በእኔነት ስነልቦና ላይ ቅኔ እየተቀኘ ነው፡፡በልኬ ነው ያስታጠቀኝ፡፡ጥቂት ከውሃው ካልወሳሰድኩ ሕይወት እንደ አቀበት ታስቃስተኛለች፡፡በሌጣዬ ሆኜ ሕይወትን ስጋፈጣት ትንሽነቴ፣ እዚህ ግባነቴ ይጋረጥብኛል፡፡ግዝፈቴን፣ የሰማይ ቅራፊነትን ለማወጅ የሞቅታውን ዓለም ለመወዳጀት በብርቱ እጣደፋለሁ፡፡የጥበበኛውን ምልከታ በራሴ ቁመና ልክ ለማጥለቅ ተውተረተርኩ፡፡
ጊዜውን ያለአግባብ ለፈጀሁበት መጽሓፍ አዟሪ የምለው ጠፋኝ፡፡ጥቂት ገጾችን አንብቦ ፈረንካ የሚወረወረው ለጋዜጣ እንጂ ለመጽሓፍ እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ከኪሴ ያለው ንዋይ ብዙም የሚያወላዳ አይደለም፡፡ ከሁለት የብር ቅጠሎች ጋር መጽሓፉን ጀባ አልኩት፡፡ግራ በተጋባ ስሜት ተሰናብቶኝ ወደ ሌላ አቅጣጫ በረረ፡፡
ጉሮሮዬን ላረሰርስ የድራፍት ብርጭቆውን አፈፍ እንዳደረግሁ ኑሮ ግራና ቀኝ ያላጋው መዳፍ ከፊት ለፊቴ  ተነጥፎ አደናቀፈኝ፤ ተማጽኖውን የሚያቀርቡት ነዳያ አንድ ዓይና ናቸው፡፡ጎስቋላ ኩታራ ይመራቸዋል፡፡ ሽልንግ አኑሬ መልሱን ከመደፋቸው ላይ መልቀም እንደጀመርኩ ቀና ብዬ ዙሪያ ገባዬን ሰለለልኩት፡፡ ከአንድ ስለታም ፊት ጋር ተላተምኩ፡፡ እንደ ብርንዶ ሥጋ ውስጤ በላለተው፡፡የምንተፍረቴን፣ የቆጠርኳቸውን ሳንቲሞች መልሼ  በመዳፋቸው ላይ እንዳኖርኳቸው የአዛውንቱ አንደበት ውዳሴ ለማዝነብ መፍታታት ጀመረ፡፡
የስሜት ሽግግር
አሁን የስሜት ሽግሽግ የማደርግበት ቅጽበት ላይ ደርሻለሁ፡፡ከካምቦሎጆው አውድ ውስጥ ለመከተት በመጣደፍ ላይ ነኝ፡፡በጉያው ከተሸሸጉት መሸታ ቤቶች ተስፈንጥሬ እደረቱ ላይ በተነጠፈው መስክ ዘንድ ቅሪላ ሲላፋ ለመታዘብ ከታዳሚው መሃል ተመስግኩ፡፡የካምቦሎጆ መታደሚያ ካምፖች ከትከሻቸው ላይ ያኖሩት ማዕረግ የመደብ ክፍፍል ይንጸባረቅበታል፡፡ክቡር ትሪቡን፣ከማንአንሼ፣ሚስማር ተራ…………..፡፡ በክብር ትሪቡን አፋፍ ላይ ተኩኖ ከማንአንሼን ማማተር፣የጠራራ ጠሐይ አድባሯን ሚስማር ተራን ተገን አድርጎ ጥላ ፎቅን፣ዳፍ ትራክን፣ካታንጋን መገርመም ወግም፣ልማድም ነው፡፡
የካምቦሎጆ ቤተኛ ዛሬ ነቅሎ ነው የመጣው፡፡ጠጠር መጣያ የለም፡፡፡፡ፍልሚያውም ቢሆን እንዲህ  በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ በከተማዋ ከታወቁት ተፋላሚዎች  መካከል በቀዳሚነት የሚሰለፉ ናቸው፡፡ቡኒዎቹና ቢጫዎቹ፡፡
ድሮ ድሮ ምድርን ቁና የሚያደርግ ግጥሚያን ለመመልከት እንዲህ እንደዛሬው የኮምቦሎጆ ድግስ ብቻ አይጠበቅም፡፡በእየሰርጓጉጡ የሚፋለሙ የቅሪላዋ ምርኮዎችን ለመተፎዝ ችምችም ብሎ የሚሰለፍ የሸገር ነዋሪ ቁጥሩ የትየለሌ ነበር፡፡ አሁን ግን ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆኗል ፡፡ከተማዋ ለልማት እንጂ ለቅሪላ ማልፊያ የሚባክን ባዶ መሬት የላትም፡፡የበሬ ግምባር የምታክል መጫወቻ ሥፍራ ብርቅ ሆኖባቸው፣ ከአውራ ጎዳና ላይ ውር ውር የሚሉ ጨቅላ ቅሪላ አልፊዎችን ጎዳናው ይቁጠራቸው፡፡
//ጨዋታው ተጀመረ//
ቢጫ ለባሽና ቡኒ ለባሽ ቡድን አንዲት ቅሪላን ለማባረር ማዶ ለማዶ ተሰየሙ፡፡እኔ የቡኒው ለባሽ ደጋፊ ነኝ፡፡ፍትሕ ለጋሹ ፣ፍትሕ ነሺው ዳኛ መንቁሩ ላይ በመለጋት በፊሽካ ልፊያውን አደብ ማስገዛቱን ጀመረ፡፡ ቅሪላዋ በሰማይ፣በምድር አበሳዋን እያየች ነው፡፡
ከሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሲሶው ደቂቃ በረረ፡፡
ድንገት ከቢጫው ወገን ያለ የቅሪላዋ ቀበኛ፣ ቅሪላዋን በቃሪያ ጥፊ መቶ ከመረብ ላይ ያለርህራሄ መለጋት፡፡ ፍትሕ አንጋሽ ባለበት አውድ፣ በጠራራ ጠሐይ ሕግ ተጣሰ፡፡ ሐቅ መንምና ተበጠሰች፡፡ ካምቦሎጆው ከመቅጽበት ጉራማይሌ ገጽታን ተጎናጸፈ፡፡ በአንድ ወገን ምድር ቁና ስትሆን በሌላ ወገን እንደመቃብር ሥፍራ የሚደብት ፀጥታ አረበበ፡፡ ምስማር ተራ ላይ ጠሐይ ጠለቀች፡፡ ሁሉም ነገር …ፀጥ…ረጭ ..አለ፡፡
“ይህ ዲስኩራም …ነገ ጠዋት ብድግ ብሎ….እንደማንትስ…የእግዜር እጅ…እያለ ሊመጻደቅብን እኮ ነው፣” አለ ከእኔ ወገን ያለ የነደደው ተመልካች፡፡
“የእግዜር እጅ …..የጥሬ ጓደኛ ነው እንዴ….” ከሌላ ተመልካች የተሰጠ ተመጣጣኝ ምላሽ ነበር፡፡
“እንካ ሰላንቲያውን ትታችሁ……ለልፊያው ቀልባችሁ አውሱ.?” አለ ጎበዙ ጨዋታ አድማቂ፡፡
እኛ የፍትሕ ምንዱባኖች ግን አንደበታችንን መለጎም ተስኖናል፡፡መንቁራችንን በአንድነት ከፍተን ጩኽታችንን ለቀቅነው፡፡ የካምቦሎጆን ዓየር ባሰገምጋሚ የሕብር ድምጻችን ገረሰስነው፡፡ ጩኸታችን ግን የኢያሪኮ ሆነ፡፡ እንደ ገደል ማሚቱ መልሶ መላልሶ እያስተጋባ ተቀባይ አጥቶ መስሚያችንን አደነቆረን፡፡መላ ያመጣል ያልነው መውተርተር ሌላ መዘዝ ይዞ በቅ አለ፡፡ዓሳ ጎርገሪ ሆነ ነገሩ፡፡ቅጥ ያጣው እሮሯችንን አደብ ሊያስገሱ መለዮ ለባሾች እየተሽቀዳደሙ ወደ እኛ አቅጣጫ ተንደረደሩ፡፡ ትዕግስቴ፣ ብርታቴ ሲሟጠጥ ይሰማኛል፡፡ ድግሱን ረግጬ በረርኩ፡፡
ረሃብ ቢጤ ተሰምቶኛል፡፡ በእዚህ ጊዜ የከርሴን ውትወታ አደብ የሚያስገዛ ፈጥኖ ደራሽ ያስፈልገኛል፡፡ ፈጥኖ ደራሾቹን ጥንድ ኪስታ ሳምቡሳዎች ወደ ጎተራዬ ሰደድኳቸው፡፡ ነፍሴ ትንሽ መለስ አለች፡፡
በዓይኔ በብረቴ ያየሁት አድልዎ የእግር እሳት ሆኖ እያንገበገበኝ ነው፡፡በውስጤ ከማጉተምተም አልቦዘንኩም፡፡ከሚንኳተተው ባቡር ላይ ለመሰቀል ወደ ቲኬት መቁረጫው ተጣደፍኩ፡፡ ድብልቅል ያለ ጩኸት ስሰማ በእርምጃዬ ብዙም አልገፋውም ነበር፡፡ ቅሪላዋ ከመረብ ስትመሰግ የሚሰማ ዓይነት ድምጽ ነው፡፡ሚስማር ተራ በአንድ እግሯ ቆመች፡፡ የምይዘውን የምጨብጠውን አጥቼ ወደ መግቢያው በር ተመልሼ በረርኩ፡፡ የደመነፍስ መውተርተር ሆኖብኝ እንጂ የካምቦሎጆ በር እንደሆነ ተከርችሟል፡፡ የውስጥ ጉጉቴ አለቅጥ አሻቀበ፡፡ በኤሌክትሪክ ምሰሶ ላይ ተንጠላጥሎ ለመቅረፁ ምስል የበቃው ብላቴና ትውስ አለኝ፡፡ በትክክል ስሜቱን ተጋራሁት፡፡እንደርሱ ልሞክረው ብል ዕድሜዬ ለእዚህ የሚያበቃ አይደለም፡፡
መግቢያ ትኬት አጥተው በዓይናቸው መለዮ ለባሾችን የሚማጸኑ ልጅ እግር ወጣቶችን ተቀላቀልኩ፡፡ ኃይለኛ ጩኽት ተደገመ፡፡በደመነፍስ ከአጠገቤ ቆሞ ከነበረው ሥጋ ቅብ መለዮ ለባሽ ላይ ጥምጥም አልኩበት፡፡ በሁኔታው ግር የተሰኙት ባልደረቦቹ የቆመጥ መንጋ በላዬ ላይ አዘመቱብኝ፡፡
የዘመተበኝ ቆመጥ የሰውነት መገጣጠሚያዎቼን ክፉኛ ጎድቷቸዋል፡፡ ሥጋዬ ቢታመምም ስሜቴ ግን ሰንጋ ፈረስ ነው፡፡የእኔ ቡድን ድልን ተጎናጽፏል፡፡አያ…..ሆሆ……ማታ ነው ድሌ.. እያለ የሚያዜም …..የሕዝብ ደራሽ ተግተልትሎ የቆምኩበትን ምድር ሲወራትና እኔም እንደ እምቦሳ ስዘል አንድ ሆነ፡፡

Read 1429 times