Saturday, 23 January 2016 13:45

አያሻረው፤ “ጥላነቱ” የተንሰራፋ፣ “ስንቅነቱ” የተስፋፋ

Written by  አለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(6 votes)

ከተመኙ አይቀር ወንዝነት መመኘት፣
አገርን ሳይለቁ ሰው አገር መገኘት፤
ይሄ ግጥም የበዕውቀቱ ሥዩም ነው፡፡ ቀደም ሲል የግጥሙ እሳቦት እተሸኮረመመ፣ በመሸሽ፣ ያደክመኝ ነበር፡፡ ልከኛ ፍቺው የተገለጠልን ደራሲ አስማማው ኃይሉን (አያ ሻረውን) ከተዋወቅሁ በኋላ ነው፡፡ ደራሲ አስማማው አገርን ሳይለቁ እሰው ሀገር የመገኘት ዋነኛ ምሳሌ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያን የለቀቀው ከሰላሳ ስድስት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ በሱዳን በተለይም በአሜሪካን የተለያዩ ግዛቶች ያሳለፋቸው እነዚህ ጉልጥምት አመታት እንኳን ሊጫኑት ሲያልፉም የነኩት አይመስልም፡፡ በአነጋገሩ፣ በአፃፃፉ፣ በአለባበሱና በአስተሳሰቡ በኮሎምቦስ፣ በኦሃዮ፣ በሂውስተን፣ በቨርጂኒያ … እየተዟዟረ የኖረ ሳይሆን ከበለሣ፣ ከጭልጋ ወይም ከአርማጭሆ አሁን የመጣ ይመስለናል …
… አስማማው ሰግደድ ባለ ደልዳላ ሰውነቱ ላይ ካኪ ነክ ልብሶችን ያዘወትራል፡፡ እራሱ ላይ ጣል የሚያደርጋቸው ኮችያዎቹም ዳለቻዎች ናቸው፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ይመስለኛል እዚህ ቆይቶ ወደ አሜሪካን ሲመለስ፣ ለቸገራቸው ሰዎች እንዳከፋፍል አንድ ሻንጣ ሙሉ ልብስ ሰጥቶኝ ነበር፡፡ የከለር ምርጫው ያስገረመኝ ያኔ ነው፡፡ አስር የሚደርሱ ካኪ ሱሪዎች፣ አምስት ዳለቻ ጃኬቶች፣ ሦስት የካኪ ሸሚዞችና ሌሎች ጠያይም አራት ስስ ሸሚዝ አከል ቲሸርቶች፡፡ ሻንጣውን ስከፍተው የልብሶቹ መመሳሰል አንድ የእድር ድንኳን ተጣጥፎ የተከተተ እንጂ በተለያዩ ጊዜ ከብዙ አማራጭ የተገኙ ብዙ አይነት አልባሶች አልመሰሉኝም ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ ዳለቻና ካኪ ልብሶች ኖረውትም መንገድ ላይ ሲመለከት ደንገጥ ብሎ ዋጋቸውን የሚጠይቀው ዳለቾቹንና ካኪዎቹን አልባሳቶች ነው፡፡
“ለምን?” ስል ጠየኩት፡፡
“ለምን እንደሆን እንጃ” ብሎ በራሱ ላይ እያሾፈ እንዲህ አለኝ፤ “አሜሪካ ያሉ ወይዘሮዎች ባለቤቶቻቸው ካኪ መሰል ልብስ ከለበሱ ‹አያ ሻረውን ይመስላል› በማለት ይቃወማሉ”
ተሣሣቅን … ይሄንን አስታክኬ የእኔ ጎረቤቶች ምን እንደሚሉት ነገርኩት፡፡ መጥቶ፣ ደጃፌን ቆርቁሮ፣ አጥቶ ሲሄድ፤ “እኒያ ባላገሩ ዘመድህ መጥተው ነበር” ሲሉ መልዕክት ያቀብሉኛል፡፡
ዳግም ተሳሳቅን …
.. አያ ሻረው በአለባበስ ብቻ ሳይሆን በወግም ወደ አሜሪካን ጎራ የሚለው አልፎ አልፎ ነው፡ በጭብጥ አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን በለዛም ቁጭ በለሶችን፣ ጭልጎችንና አርማ ጮሆችን ነው፡፡ ፅሁፎቹንና መፃህፍቶቹን በአካል ማግኘት ሥለምትችሉ ያመለጣችሁ ወጎቹን እንደቻልኩ ላውጋችሁና በገደምዳሜም ቢሆን ለመዳኘት ሞክሩ፡፡
አንድ
በለሣ የትግል ሥፍራ ነው፡፡ የተለያዩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ነበሩበት፤ እነዚህ ድርጅቶች ለአርሶ አደሩ የፖለቲካ ትምህርት እየሰጡ የራሳቸው ደጋፊ ለማድረግ ብዙ ይጥራሉና የአካባቢው ሰዎች የርዕዮተ - ዓለም ንቃት የሚሰማቸው አይነት ናቸው፡፡ በተለይ ከሌሎቹ የአካባቢው ወረዳ አርሶ አደሮች ጋር እራሳቸውን ሲያነፃፅሩ ኩራት ቢጤም ይዳዳቸዋል፡፡ አልፎ - አልፎ የጋራ መድረክ ተፈጥሮ የፖለቲካ ውይይት ከተጀመረ አንዳንድ የፖለቲካ ማስተጋቢያ ቃላቶቻቸውን እየረገጡና እየደጋገሙ ሐሳባቸውን ያራቅቃሉ፡፡ አንድ ጊዜ ነው አሉ፤ የበለሣ አርሶ አደሮች በፖለቲካ ትንታኔያቸው መካከል “አንጣር፣ ሲነጣጠር፣ ሲንጠባረቅ …” የሚሉ ቃላትን ቢደጋግሙ፣ አንዱ አርሶ አደር ተነስቶ እንዲህ አለ፡-
“ተውኒ በለሶይ አታንጠባርቁብነ”
ሁለት
ኢሕአሦ (የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሠራዊት) የራሱ ሰንደቅ ዓላማ እንዲኖረው ወስኖ አዘጋጀ አሉ፡፡ ነገር ግን አርሶ አደሩ ባንዲራውን ሲመለከት፣ የማያውቀው ሆኖ ይቆጣ ጀመር፡፡ ሌሊት ገበያ መካከል ተሰቅሎ ያድርና ጠዋት አርሶ አደሩ ሲያይ፡-
“የምን የቱርክ ባንዲራ ነው?” እያለ ያወርደዋል፡፡ ሰንደቅ አላማውን እንደተፈለገ ማውለብለብ ሳይቻል ቀረ፡፡ ቢቸግር አንድ ተራማጅ አመለካከት ያላቸው ፊታውራሪ በማግባባት እግቢያቸው ውስጥ እንዲሰቀል ተደረገ፡፡ ፊታውራሪ አካባቢው ላይ ተሰሚነት ያላቸው  ባለብዙ ወገን ናቸው፡፡ እሳቸው ምድረ - ግቢ የመጣ ወዳጅ ዘመድ ያቺን ባንዲራ ይገረምማታል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሰንደቅ አላማው ገበያ ላይ ተሰቅሎ እንዲሞከር በመወሰኑ እንዲውለበለብ ተደረገ፡፡ አርሶ አደሮቹ አሁንም አልተበገሩም፡፡
“የቱርክ ባንዲራ ተሰቀለ፣ አውርዱት!” አሉ፡፡
በዚህ መካከል አንድ የፊታውራሪ ወገን የሆነ አርሶ አደር ጠበንጃውን አቀባብሎ እንዲህ አለ፡-
“እስቲ የአጎቴን ባንዲራ ማነው የሚነካ? ሱሪ የታጠቀ የአጎቴን ባንዲራ ያውርድ!!” ባለብዙ ወገን ነውና ማን ይድፈር? ባንዲራው እንደተሰቀለ እየተውለበለበ ቀረ፡፡
ሦስት
የአባ ኃይሉ (የአስማማው አባት) እና የጎረቤት ኮርማዎች ተጣሉ፡፡ ሁለቱም በደንብ የተቀበሉ ናቸውና በቀላሉ የሚሸነፍ ታጣ፡፡ የሁለቱ ኮርማዎች ፀብ የአካባቢው ዋነኛ ጉዳይ ሆኖ ውጤቱን ጠያቂ በዛ፡፡
“የማን ኮርማ ተቸነፈ? የአባ ኃይሉ ወይስ …”
“ገና ናቸው፣ መች ለየ?”
ተዋጉ፣ ተዋጉ .. ሰዓታት ተቆጥሮ በመጨረሻ የአባ ኃይሉ በሬ አቸነፈ፡፡ ያኛው ቀንዱ ተሰብሮ ሸሸ፡፡ የተቸናፊው ኮርማ ባለቤት እጅግ አድርጎ ከፋቸው፡፡ ተቸንፎ ቤቴ አላስገባም አሉ፡፡ አማላጅ ተላከ፡፡ የተቸናፊው ጌታ ለአማላጆቹ እንዲህ ሲሉ ስሞታ አሰሙ፡-
“ከአባ ኃይሉ ኮርማ አሳንሼ ይዤዋለሁ? አልተንከባከብኩትም? ያጓደልኩበት ነገር ነበር? ዛዲያ እንዴት ሁኖ ተቸነፈ? ከእንግዲህ እኔና እሱ አንድ ጣሪያ ሥር አንኳኳንም፡፡ አይኔ የማያይበት ወስዳችሁ ሽጡት፤ በጨሌ እንዳይጎዳ፣ የሚያርደው ሰው እጅ እንዳይገባ ተጠንቀቁለት፤ ተዚያ በላይ አበቃ!”
አራት
ራስ ዳኜ (ሥማቸው የተቀየረ) ለአንድ ታማኝ ሎሌያቸው ልጃቸውን ድረውለት፣ ቀኛማችነት ሾመው ያስደሰቱት መስሏቸው ሲቀመጡ ቅር እንዳለው ሰሙ፡፡ “ለልጃቸው ደጃዝማችነት ሰጥተው ለእኔ ቀኛማች?” አለ፡፡ አሉ ራስ ተበሳጩና ሎሌያቸውን አስጠሩ፡-
“ቀኛማችነት አነሰህ? ሚስቱንም ሹመቱንም ከእኔ ያገኘህ መስሎኝ? ቀኛማችነቱን ሽሬሃለሁ፣ ልጄንም አፋትቼሃለሁ” ወደ ሌላኛው ሎሌያቸው ዞረው፤ “ቀኛማችነቱን ላንተ ሾሜያለሁ፣ የልጄን እጅ ሰጥቼሃለሁ” አሉ፡፡
ተሻሪው ሎሌ በመባረሩ ካካባቢው ጠፋ፡፡ ከአምስት ዓመታት በኋላ ራስ አንድ ወሬ ደረሳቸው፡፡  ያ ሎሌያቸው አካባቢው ላይ ታየ፡፡ “በቅሎዬን ጫኑ” ብለው ወደ ተጠቆሙት ቦታ ሄዱ፡፡ እውነትም የሻሩት ሎሌ ጀርባውን ለእሳቸው ሰጥቶ፣ ማዶ ማዶውን እያየ ቆሟል፡፡ ቀስ ብለው ከበቅሎዋ ወረዱ፣ ተጠጉ ድንገት ያዝ ሲደርጉት፤
“የራስ ዳኜ አሽከር!!” ብሎ ፎከረ፡-
“አንተ አልረሳኸኝም?” አሉ ራስ “ነይ” ልጃቸውን ጠሩ “ከባልሽ አፋትቼሻለሁ፣ ለዚህኛው ድሬሻለሁ፣ ቀኛማችነትህንም መልሻለሁ”
*          *            *
የጊዜ ንብርብሮሽ የደደረ ተስፋ መቁረጥ ቢፈጥርም ማንነትን ቀብሮ አለማስቀረቱ አስገራሚ ጉዳይ መሆኑ አልቀረም፡፡ ደራሲ አስማማው እንደዚያ ነው፡፡ እንደ ሰለስቱ ደቂቆች ለእሳት ተዳርጎ ቁልጭ እንዳለ የተገኘ “ይድረስ ከአያ ሻረው” በሚል ርዕስ የአማርኛ ሥነ - ፅሁፍን የተቀላቀለበት የግጥም ስራው የሚያተኩረው በባህል ግጭት (Culture Shock) ላይ ነው፡፡ ለተራኪው ገፀ ባህርይ “ጭልጋ” የተሰኘችው የገጠር አካባቢ የዓለም ሁሉ ማንፀሪያ አስተውሎቱ የሆነችበት ቱባ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ድንገት ተነቅሎ በሱዳን በኩል ወደ አሜሪካ ቢሄድም በጭልጋ መለኪያነት የምዕራቡን አለም ባህልና ልምድ ይተቻል እንጂ በንፅፅር ጭልጋ አንሳ አትታየውም፡፡ ደራሲ አስማማው የዚህን ገፀ ባህርይ ስም እንዲወርስ ያደረጉ ሰዎች፤ ያስተዋሉት አንድ ነገር እንደነበር ግልፅ ነው፡፡ ያም - ነገር ደራሲውና ገፀ ባህሪው የሚቃዱት አንዳች ተመሳሳይ ጠባይ መኖሩ፤ በመሆኑም የደራሲ አስማማው ኃይሉ የቅንፍ ሥም (አያ ሻረው) መሆኑ ልከኝነት አለው ማለት ይቻላል፡፡
ደራሲ አስማማው ከግጥም ሥራው ባሻገር ልቦለዶቹም እንዲሁ በባህል ግጭት ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡ “ከደንቢያ ጎንደር እስከ ዋሽንግተን ዲሲ” የተሰኘው በሁለት መፅሐፍ የቀረበው ልቦለድ፤ ገፀ ባህርይ፣ የደራሲውን የህይወት ውጣ ውረድ “ወንጌል” አድርጎ የሚኖር ደቀ - መዝሙር ነው፡፡ ገፀ ባህሪው የደራሲው አስተውሎት ቀኖናው ነው፡፡ ገፀ ባህሪው በደራሲው፣ ደራሲው በገፀ ባህሪው ውስጥ የተወሰወሱ ናቸው፡፡ በአጭሩ ሥራው “ግለታሪካዊ ልቦለድ” (autobiographical Novel) ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሌላው የአያሻረው ሥራ በሁለት ቅፅ የቀረበው “ኢህአሠ” (የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሰራዊት) የታሪክ መፅሐፍ ነው፡፡ በእዚህ ሥራ ዘመን እንደ ሳሙና አረፋ አኩረፍርፎ ዕድሜያቸውን አፍታ ያደረገው ብዙ ታጋዮች ወደ ህያውነት ተሸጋግረውበታል፡፡ እነ መሐመድ ማኀፉዝ፣ ቢኒያም አዳነ፣ ያዕብዮን፣ ዳዊት ወደ ቀሽ … ሌሎችም እንደ አልአዛር የመረሳትን ትቢያ አራግፈው፣ መና የመቅረትን ከፈን በጣጥሰው፣ ወደ “ህይወት” የሚመለሱት በእነዚህ መፃህፍት ነው፡፡
አያሻረው ከታተሙት ሥራዎቹ ውጪ አንድ ልቦለድ “ውለታ”) እና ሌላ አንድ የግጥም መድበል አለው፡፡ ልቦለዱን የማንበብ ዕድል ገጥሞኛል፡፡ መቼቱን ደጎላ ማርያም ላይ አድርጎ ስለፊታውራሪ መርሶ ዘር የ“ፌሽታ” እና የ “ዘለሰኛ” ቅልቅል ዜማ ያዥጎደጉዳል፡፡ ተደራሲም በአመዛኙ እየሳቀ፣ ከአለፍ አገደም ደግሞ እያዘነ፣ ከ“ውለታ” ጋር የሚቆይበት ሥራ ነው፡፡ መቼ፣ በማን ይታተም ይሆን?
አያሻረውን በዚች ፅሁፍ መቀንበብ አስቸጋሪ ነው፡፡ ከሥራዎቹ ባሻገር እርሱን በአካል በሚያውቁት ሰዎች ዘንድ የተከለው ሀውልት ይገዝፋል፡፡ አያሻረውን በተደጋጋሚ ቀርቶ ለአንዲት አፍታ ያገኘው ሰው የቀሪ ህይወቱ ስንቅ የሚያደርገውን ሳይዝ አይለይም፡፡ አያሻረው፤ “ጥላነቱ” የተንሰራፋ፣ “ስንቅነቱ” የተስፋፋ የትየለሌ ነበር፡፡ … ታዲያ፣ ታዲያ ..
.. ታዲያ ፣ ታዲያ … በዚህ ዓመት ወርሃ ጥቅምት መጀመሪያ ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶ፣ እዚያው አሜሪካ የደብረገነት ቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስቲያን የቀብሩ ሥነ - ሥርዓት ተፈፀመ፡፡ አያሻረውን በሚወክል የኑረዲን ዒሣ ግጥም ልቋጭ፡-
አንድ ትልቅ ሀገር፣ ካንድ ትንሽ መንገድ ላይ
                       ተጣጥፎ ተኝቶ፣
ሲጨናነቅ አየሁ ለእግሮቹ መዘርጊያ
                  ሽራፊ ቦታ አጥቶ፤

Read 1755 times