Saturday, 30 January 2016 12:30

የኪነ - ህንፃው አዳም ረታ እና ፎቅአዊ “መረቅ”

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(1 Vote)

 አንድ ጠማማ ጎረቤት አለኝ፡፡ ሰው አይደለም፣ ግዑዝ ሕንፃ ነው፡፡ በግትርና በእንቅስቃሴ አልባ ሕይወቱ ስለ ዘመናችን ብዙ የሚናገር ይመስላል፤ (ይቅርታ ይመስለኛል) አንድያ ልጇን ሞት እንደቀማት እናት ወደ መቃብር ጉድጓዱ አዘቅዝቆ እርምን የሚያወጣ አይነት ነው፡፡ ሰግደድ ብሎ እንባው ጉንጮቹን ሳይነካ ሲንጠባጠብ ይታየኛል፡፡ እራሱን ወደ ቀብሩ ጉድጓድ እንዳይጥል ከበስተኋላው አንቆ የያዘው ደባል ሕንፃ አለው፡፡ ባይያዝ ድፍት፣ ክንብል እንደሚል የሚያሳምን ሁኔታ ይረብብናል፡፡ ብዙ ምስሎች ወደ አእምሯችን እንዲመጡ ግድ ይለናል። ኢየሱስና እናቱ ማርያም ከወንጌል፣ በዛብህ፣ እናቱና አባቱ ከፍቅር እስከ መቃብር፣ የቀይ ሽብር ዘመን እናቶች ከቅርብ ታሪክ፣ አፄ ቴዎድሮስና ሟች ሚስታቸው ከሩቅ ታሪክ …
በካዛንችስና በፊት በር ድንበር ላይ ያለው ይሄ ጠማማ ጎረቤቴ፤የብዙዎች ግርምት መጫሪያ ነው። እንደውም አንዳንዱን የፎቁ የውጭ ይዘት የውስጥ ሁናቴው ላይ ጥርጣሬ እንዲጭር ስለሚያደርገው ያለ ሥራ ወደ ሕንፃው እንደሚዘልቅ አውቃለሁ፡፡ እውነት ነው፤ ፎቁ ፊት ለፊት ወይም ከጎን በኩል ያለ ሰው፣ ውስጣዊ ክፍሉ ማዕበል እንደሚያናውጣት መርከብ ያጋደለ ተንሸራታች ወለል ያለው ቢመስለው እውነት አለው፡፡ ጠረጴዛው፣ ፀሐፊዋ፣ ኮምፒዩተሩ፣ የቆሻሻ ቅርጫቱ፣ የፋይል ካቢኔቱ … አንዱ ባንዱ ላይ ተነባብሮ ዘቅዛቃው ላይ የተጠራቀሙ የሚመስል ግንዛቤ ይረታናል፡፡ እኔ ራሴ ገብቼ እንዳረጋገጥኩት እንደዚያ አይደለም - ሊሆን አይችልም፡፡ እዚሁ ጠማማ ጎረቤቴ ሦስተኛ ፎቅ ላይ የባህል ቡና አፍልታ የምታቀርብ ቤት አጋጥማኝ ሊሆን የሚችለውን እያሰብኩ ስቄአለሁ፡፡ የጠማማ ጎረቤቴ ውጫዊው አኳኋን ውስጣዊ ጠባዩን አይወክልም፡፡ ውስጡ ሆነን ሐዘነተኛነቱን አናውቅም፡፡
ኪነ-ህንፃ (Architecture) እንደ ሌሎቹ ጥበቦች ማለትም ሥነ-ፅሁፍ፣ ሙዚቃ፣ ሥነ-ሥዕልና ቅርፃ ቅርፅ ሁሉ ሐሳብና ፍልስፍናዊ አቋም የሚገለፅበት እንጂ የግብር ይውጣ መዳረሻ አይደለም፡፡ አንድ ሕንፃ ወረቀት ላይ ከሰፈረ ግጥም፣ መድረክ ላይ ከቀረበ ቴአትር፣ አቡጀዲ ላይ ከገዘፈ ሥዕል፤ ቋጥኝን ካንበረከከ ሀውልት … ያልተናነሰ ማንነትና ዘመንን ይዘግባል፡፡ ህንፃ የመጠለያ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን በሒደት ላይ ያለ ሥነ - ቃል፣ ታሪክና እምነት ነው፡፡ እንደዚህ ዘመን ባልተናቀበትና ከካርቶን በማይታነፅበት በጥንቱ ዘመን የነበሩ ግንባታዎች ከየትኞቹም ታሪክን ማስተላለፊያ ስልቶች በተሻለ ቋሚ ሆነው፣ እላያቸው ላይ የሰፈሩትን ሀሳቦች ለዚህ ዘመን አድርሰዋል፡፡
ህንፃ እንደ ሌሎቹ ጥበቦች ሁሉ የሚበላለት ስልት ያለው ኪን እንደሆነ ያወቅሁት አሁን በቅርቡ ነው። “Four Stages of Renaissance Style” የተሰኘ መፅሀፍ እጄ ገብቶ ሳገላብጥ አንድ ህንፃ እንደ ግጥምና ሙዚቃ ምት (Rhythm)፣ እንደ ልቦለድ ቅርፅና ጭብጥ፣ እንደ ሥዕል ህብርና ንፅፅር (Contrast) የመሳሰሉ አላባዎች (Elements) እንዳሉት ገባኝ፡፡ ህንፃዎች በእነዚህ አላባዎች ስለ ዘመኑ የሰው ልጅ እሳቤና የኑሮ ፍልስፍና ተመዝግቦባቸው የሚተነተን መረጃ ለትውልድ ያቀብላሉ፡፡ እንደ ሌሎቹ ኪኖች ሁሉ የሰው ልጅ በተለያየ ዘመን የተለያየ የኪነ ህንፃ አቋም ላይ እየደረሰ፣ የተለያየ የአገነባብ ሥልት ተከትሏል፡፡ ባሩክ (baroque)፣ ጎቲክ (Gothic)፣ ማነሪዝም፣ ረነሰንስ (renaissance)፣ ሮማንቲሲዝም፣ ዘመናዊነት (modernism) እና ድህረ ዘመናዊነት  (post-modernism)… በዓለም ላይ ከተለዋወጡት የኪነ ህንፃ ስልቶች (style) ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በግሪክ ዘመን የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ተፈጥሮን በመቅዳት ለሰው ልጅ እንደ ግብ የተቀመጠው ሥነ - ምግባራዊ ታላቅነት ማሳየት ነበር፡፡ በግሪክ ውስጥ የሚካሄዱ ግንባታዎች ሁሉ በማያፈናፍን ሥሌት ህብር እንዲኖራቸው ይደረግ ነበር፡፡ “Of Men and Numbers” የተሰኘ መፅሀፍ ላይ ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ የሚል ውርስ ግንዛቤ የሚሰጥ ሀሳብ አለ÷ “የአቴናው ቤተ መቅደስ የፓርቴኖን ዙሪያ፣ ፓርቴኖን የተገነባበት የአክሮፖሊስ አካባቢ (ዳግም የተመሰረተው ከተማ) ቅፅሮቹና መደቦቹ ሁሉ በጂኦሜትሪ መሞገቻ ነጥቦች ግልፅ የሆነ አንድነት ይንፀባረቅባቸዋል” (It may be said that all parts of the Parthenon, the Acropolis, the city as rebuilt, the walls, and the port, are expressible in terms of a geometrically unity.) ግሪኮች ፕሌቶ፤ “God ever geometrizes” ያለውን ሲተረጉሙ እንደ ማለት ነው፡፡
ኪነ-ህንፃ ዘመንና የዘመኑን ሰዎች ተርጓሚ የግንባታ ቅኔ ከሆነ፣ የእኛ ህንፃዎች ስለኛ ምን ይሉ ይሆን? ጠማማው ጎረቤቴስ ምን በመናገር ላይ ነው? ኧረ ከተማውን ሁሉ ያጥለቀለቁት ኮሽኮሼ ፎቆች እኛን በምናቸው ወከሉን?------
በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢንጂነር ጌታሁን ሄራሞ ጋር እንደተጨዋወትን ትዝ ይለኛል፡፡ እሱ ጥሩ የሚባል የኪነ-ህንፃ ግንዛቤ አለው፡፡ “ጠማማው ጎረቤትህ በድህረ-ዘመናዊነት ስልት የተገነባ ነው” ብሎኛል፡፡ የኪነ-ህንፃው አዳም ረታ የደረሰው ፎቅአዊ “መረቅ” መሆኑ ነው፡፡ እዚህ ግንባታ ላይ የሚታየው እውነታን ገልብጦ የመተርጎም ፈጠራ የድህረ ዘመናዊነት ስልትን መሰረት ያደረገ ነው ማለት ነው፡፡ ኢንጂነር ጌታሁን፤ ድህረ ዘመናዊነት ስልትን ተከትለው የተገነቡ ህንፃዎችን ከኢንተርኔት አውርዶ አሳየኝ፡፡ አንዳንዶቹ ህንፃዎች የመሬት ስበትን ተቋቁመው ወደ ሰማይ በመምጠቅ ላይ ያሉ መስለው ተገንብተዋል፡፡ ከእውነታና ከተለምዶ በተቃራኒው መምጣት የድህረ ዘመናዊነት ጠባይ ነውና ህንፃዎቹ በዚህና በተለያዩ መለኪያዎች በስልቱ ውስጥ የተካተቱ ሆነዋል፡፡
ሌሎቹ ኮሽኮሼዎችስ?----
… የዘመንና የዘመነኞችን ገመና በጥበብ ሳይሆን በግልብ መንገድ የሚገልፁ ናቸው፡፡ ሱሪን ከባት በታች ዝቅ የማድረግን ዘመን አመጣሽ ፋሽን፣ ኮሽኮሼዎቹ ህንፃዎች የሽንት ቤት መፍሰሻን በውጭ ግድግዳ ላይ በመለጠፍ ከዘመኑ ጋር ህብር ይፈጥራል፡፡
ገመናን አደባባይ አውሎ በመኩራራት አባዜ አንድ ናቸው፡፡ ዘመን አመጣሹ ገመና ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ አይን ያወጣ መስገብገባችንና ማጋበሳችን በእነዚሁ ኮሽኮሼ ህንፃዎች ቦታ አያያዝና አጠቃቀም ተተርጉሞ ይታያል፡፡ የፎቆቹ መወጣጫዎች እንደ ጀጎል የውስጥ ለውስጥ መንገድ ሁለት ሰዎችን በአንድ ላይ የሚያስተናግድ ከመሆኑም በላይ የአንዳንዶቹ ህንፃዎች ደረጃ በውጭ በኩል በብረት የተቀጣጠለ ነው፡፡ ዓይንና መንፈስን አጨናንቆ ጥቅምን ብቻ ማንሰራፋት ከህንፃዎቻችን  ባሻገር የዘመናችንም የኑሮ ፍልስፍና አይመስላችሁም?  

Read 2348 times