Saturday, 30 January 2016 12:36

“...ፕሮጀክቱ ቢያበቃም ግንኙነቱ አይቋረጥም”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

   የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከተለያዩ አጋዥ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የተፈጸመባቸው ወገኖች የህክምና፣ የስነልቡና እና የህግ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚችሉባቸውን ሞዴል ክሊኒኮችን እያቋቋመ አገልግሎት እንዲሰጥ ሲያደርግ ቆይቶ ፕሮጀክቱ በመጠናቀቁ ምክንያት ክሊኒኮቹን ለየሆስፒታሎቹ አስረክቦአል፡፡ ይህንን በሚመለከት የኢሶግ ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሰላማዊት ክፍሌ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
“...የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር  ESOG ጾታዊ ጥቃት የሚደርስባቸውን ወገኖች ተገቢውን ሕክምናና የህግ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያስችሉ ሞዴል ክሊኒኮች ማቋቋም የጀመረው እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2001ዓ/ም ጀምሮ ነው፡፡  ማህበሩ ይህንን ፕሮጀክት ሲያካሂድ የቆየው ከተለያዩ አጋዥ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ነው፡፡ አጋዥ ድርጅቶቹም በመጀመሪያ የአለም አቀፉ ጽንስና ማህጸን ሕክምና ማህበራት ፌደሬሽን ሲሆን በመቀጠልም ላለፉት 6/አመታት  በተለያዩ መስተዳድር ክልሎች ካሉ ሪፈራል ሆስፒታሎች ጋር በመተባበር ሞዴል ክሊኒኮቹ እንዲቋቋሙ እገዛ ያደረገልን አጋዥ ድርጅት ም/ነው፡፡ በዚህ መስሪያ ቤት በተደረገልን ድጋፍም ከጋንዲው ተሞክሮ በመነሳት በአዋሳ እና አዳማ ሪፈራል ሆስፒታሎች ሞዴል ክሊኒኮችን በማቋቋም እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2010-2013 ድረስ  ሰርተን ፕሮጀክቱ በመጠናቀቁ ለሆስፒታሎቹ አስረክበናል፡፡ ከዚያም በመቀጠል ከዚሁ ከ ም ጋር በመተባበር በመቀሌ በጎንደር እና በጅማ ሪፈራል ሆስፒታሎች የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የተፈጸመባቸው ወገኖች ተገቢውን እርዳታ የሚያገኙበት ሞዴል ክሊኒኮች አቋቁመን በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱ ጊዜውን ውጤታማ በሆነ መልኩ በማጠናቀቁ ሞዴል ክሊኒኮቹን ለሆስፒታሎቹ አስረክበናል፡፡ ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበርም የወሲባዊ ጥቃት የህክምና መመሪያ የሚል ሰነድ አዘጋጅተን በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር በኩል አገርአቀፍ ሰነድ ለመሆን በቅቶአል፡፡”
እንደ የአለም የጤና ድርጅት ዘገባ በአለም አቀፍ ደረጃ 35 ኀየሚሆኑ ሴቶች በሕይወት ዘመናቸው በሚያውቁትም ይሁን በማያውቁት ሰው የወሲብ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። የጥቃቱን አድራሽ ማንነት በሚመለከትም ዘገባው እንደሚያስረዳው 30 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ድርጊቱ የደረሰባቸው በቅርባቸው ካለ ሰው ወይንም ከቤተሰብ እና ዘመድ አዝማድ ሲሆን ድርጊቱ ለስነተዋልዶ ጤና ወይንም ሌላ ተያያዥ ለሆኑ የጤና እክሎች ኤችአይቪ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡
በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በትክክለኛ መረጃ ይህን ያህል ነው ለማለት ባይቻልም ከተለያዩ ሆስፒታሎች በሚገኘው መረጃ ግን በሴቶች ላይ የሚደርሰው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን ድርጊቱ በሴቶች ላይ ብቻ ተወስኖ የቀረ ሳይሆን ወንዶችንም እንደሚያካትት የተረጋገጠ እውነታ ነው፡፡
“...  ሰውየው አብሮኝ ለነበረው ሰው እንዲህ አለው፡፡...ያንን ጥቁር ልጅ ሌሊት አስር ሰአት ላይ ስራ ስለአለኝ ለዛ ጉዳይ ስለምፈልገው ጥራልኝ...አለው፡፡ እኔም ላነጋግረው ስወጣ አስቀድሞ እጄን ነበር የያዘኝ፡፡ ጊዜው እኮ መሽቶአል ስለው...ግድየለም... ዋጋ እንነጋገራለን...በለሊትም ሰው ከምንቀሰቅስ ከእኔ ጋር ብታድር ይሻልሀል አለኝ፡፡ እኔም ግድ የለም ዋጋ ንገረኝና እመለሳለሁ ብዬ ተከተልኩት፡፡ ከዚያ በሁዋላ እቤቱ አስገብቶ በቃ...ልብስህን አውልቅ...ተኛ...የሚል ትእዛዝ ነው የሰጠኝ፡፡ በቃ...ስለፈራሁኝ ብቻ ልብሴን አውልቄ ተኛሁ.............”
ከላይ ያነበባችሁት ምስክርነት በአዳማ ሞዴል ክሊኒክ ለስራ በተጉዋዝንበት ወቅት ተገዶ መደፈር የደረሰበት የ18/አመት እድሜ ያለው ልጅ ምስክርነት ነው። የልጁን ማንነትና ድርጊቱ እንዴት እንደተፈጸመ በጊዜው ያነጋገርናቸው የስነልቡና ባለሙያ አቶ መኮንን በለጠ የሚከተ ለውን ገልጸዋል፡፡ “...የዚህ ልጅ ታሪክ...እድሜው 18 አመት ሲሆን ተወልዶ ያደገው ባሌ ሮቤ አካባቢ ነው። የዚህ ልጅ ወላጅ አባት በበሽታ ምክንያት በመሞቱ ምክንያት እናትየው ካገባችው ሰው ...ማለትም ከእንጀራ አባቱ ጋር መግባባት ስላቃተው ...ማለትም ከእንጀራ አባቱ ለተወለዱ ልጆች የሚደረገው እንክብካቤ እና ቤተሰቡ ለእርሱ የሚሰጠው ግምት ከፍተኛ ልዩነት ስለነበረው በበጎ ፍቃድ አሳዳጊዎች ምክንያት ወደ አዳማ መጥቶአል፡፡ ይህ ልጅ ወደ አዳማ ከመጣ ገና አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የወንድ ለወንድ አስገድዶ መድፈር ሰለባ ሆኖአል። አስገድዶ የደፈረው ሰው የልጁን ታሪክ በማጥናት እና በማባ በል ...እኔ ሆል አለኝ...ስራ አስገባሀለሁ...በማለት ሊያግባባው ሞክሮአል፡፡ ከዚያም ባገኘው እለት አስገድዶ ሲደፍረው ልጁ የነበረውን ጉልበት ተጠቅሞ በላዩ ላይ የተቀዳደደ ልብሱን በእጁ ይዞ ... አምልጦ ...ማመን በሚያቅት ሁኔታ ነበር ወደነበረበት የሄደው.....”
እንግዲህ ከላይ እንዳነበባችሁት በወሲብ ተገዶ የመደፈር አደጋ በሴቶች ላይ ብቻም ሳይሆን በወንዶችም ላይ የሚሰነዘር ጥቃት መሆኑን ነው ፡፡ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በመቀሌ ባቋቋማው ሞዴል ክሊኒክ አገልግሎት ፈልገው ከመጡት 379/ ተገልጋዮች 12/ወንዶች ሲሆኑ በጅማም ከ239/ ተገልጋዮች 2/ ወንዶች ናቸው፡፡ ይህ የሚያመላክተው በትክክል ወደ ሕክምናው ወይንም ወደህግ ድጋፍ ደፍረው ባለመውጣታቸው እንጂ ተጎጂዎቹ እነዚህ ብቻ እንዳልሆኑ ነው፡፡
ይህንን ጥቃት የሞዴል ክሊኒኮቹ ባሉበት ቦታ ሁሉ ተዘዋውረን የተመለከትን ስለሆነ ለትውስታ ጥቂት ምስክርነቶችን ከየሆስፒታሎቹ ከተገኙት ተገልጋዮች ለናሙና የመረጥነውን ታነቡ ዘንድ ጋበዝናችሁ፡፡
“...እዚህ ላይ አንድ የሚያሳዝን ክስተት ተፈጽሞአል። መምህሩ ሕጻኑዋን ከጥቅም ውጭ አድርጎ በመድፈሩ ምክንያት የልጅቱ ገላ እንዳይሆን ሆኖአል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ...መምህሩ ኤችአይቪ ቫይረስ በደሙ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ህጻኑዋንም በቫይረሱ እንድትያዝ አድርጎአታል፡፡ መምህሩ ዛሬ በህግ የተያዘ ቢሆንም የህጻኑዋ የወደፊት የህይወት እጣ ፈንታ ግን ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ እጅግ ...ያሳዝናል፡፡ መምህርማ በእናትና አባት የሚመሰል አይደለምን? ይህንን ድርጊት ይፈጽማል ብሎ መገመት እጅግ ያስቸግራል፡፡ እንደዚህ ያለው መምህር የሌሎች መልካም ስነምግባር ያላቸውን መምህራን በጎ ተግባር የሚያጠፋ ስለሆነ ተገቢው እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል፡፡”
                ከመቀሌ/
በዚያው በመቀሌ ያገኘነው አንድ እውነታ አለ። አንዳንድ የቤተሰብ አባላት የተደፈሩ ሴት ልጆችን ወደህግም ሆነ ወደሆስፒታል የሚያመጡአቸው በትክክል መብታቸውን ለማስከበር እና ሕክምናም እንዲያገኙ ሲሆን በአብዛኛው ግን ሽምግልና አልሳካ ሲላቸው መሆኑ ነው፡፡
“...እኔ በእርግጥ እስከአሁን ሽምግልና አልሞከርኩም። እንዲያውም ሰውየው ሳያየኝ እና ሁኔታውን ሳይጠረጥር ነው ልጄን ከአካባቢው ይዤ የተሰወርኩት፡፡ ምክንያቱም መጀመሪያ ህግ ይይልኝ...ከሰውየው ጋር መደራደሩ በሁዋላ ይደርሳል ብዬ ነው፡፡ መጀመሪያ መደፈርዋ ከተረጋገጠልኝ...የትም አያመልጠኝም...አገኘዋለሁ፡፡ መቼም እንግዲያውማ ሽምግልና...ሰው ሰውን ገድሎስ ይሸማገል የለ?”
የተደፈረች ልጅ አባት
ይህ ግን ጉዳት እንዳለው የህክምና ባለሙያዎቹ ይመሰክራሉ፡፡
    “...አንዲት ሴት ስትደፈር መረጃውን በትክክል ማግኘት የሚቻለው በፍጥነት ወደሐኪም ስትቀርብ ነው። ከአንድ ወር በላይ ከቆየች ግን ህጉዋ የተወሰደው መቼ እንደሆነ ለማረጋገጥ ያስቸግራል፡፡”
ሲስተር አበባ ከበደ
በሴቶች ላይ የሚደርስ ወሲባዊ ጥቃት ጉዳቱ የአካል፣ የስነልቡናና የፍትሕ መሆኑን ማንም በግልጽ የሚረዳው ስለሆነ ለእርምጃው መረባረብ ምንም ቅድመ ሁኔታ የማይመቻችለት ነው፡፡ በጅማ በነበረው ርክክብ ላይ የጅማ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ድሪባ ፉፋ የሚከተለውን ብለዋል፡፡
“...ይህ ሞዴል ክሊኒክ በጣም ጥሩ ስራ የሰራ መሆኑን እናምናለን፡፡ በስራ ላይ በቆየበት አንድ አመት ከአራት ወር ወደ 239/ ተገልጋዮችን ማስተናገዱ ትልቅ ቁም ነገር ነው። ይህንን እድል ያልተጠቀሙ ብዙ ሰዎች በየቤታቸውም እንዳሉ ስለምናምን እነርሱንም ወደአገልግሎቱ ለማምጣት ብዙ ስራ መስራት እንደሚጠበቅብን ተገንዝበናል፡፡ በእርግጥ የወሲብ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እና ህጻናት የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ይህንን ሞዴል ክሊኒክ አቋቁሞ በተለይ ጉዳቱ የደረሰባቸው ሰዎች በተደራጀ መልክ  መታከም እንዳለባቸው ያመላከተ በመሆኑ በጣም እናመሰግናለን፡፡ ሆስፒታሉም ይህንን ድርጊት አጠናክሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን መግለጽ እወዳለሁ፡፡”
የስራውን ቀጣይነት በመመልከት ረገድ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ድርሻው ምን እንደሆነ ወ/ሮ ሳላማዊት ክፍሌ የኢሶግ ዋና ስራ አስኪያጅ ሲገልጹ”...ሁልጊዜም የሞዴል ክሊኒኮቹ ሲቋቋሙ የመግባቢያ ሰነድ የሚኖር ሲሆን በሰነዱ ላይም የስራውን ሂደትና ወደፊት ቀጣይ ስለሚሆነው ግንኙነት ያወሳል፡፡ በዚሁም መሰረት በየሶስት ወሩ ከኢሶግ እንዲሁም ሞዴል ክሊኒኩ ካለበት ቦታ ባለሙያዎች ተውጣጥተው ስራውን ይመለከታሉ ፡፡ ሙያዊ ምክርም ይሰጣሉ፡፡ስለዚህም ፕሮጀክቱ ቢያበቃም ግንኙነቱ ግን ይቀጥላል፡፡ “

Read 2308 times