Saturday, 30 January 2016 12:56

የአፕል የአይፎን ሽያጭ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀነሰ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

           በአሜሪካ ኩባንያዎች ታሪክ ከፍተኛውን የሩብ አመት ትርፍ አግኝቷል
     ታዋቂው የቴክኖሎጂ ምርቶች አምራች ኩባንያ አፕል፣ ዝነኛውን የስማርት ፎን ምርቱን አይፎንን ለገበያ ማቅረብ ከጀመረበት እ.ኤ.አ ከ2007 ወዲህ ሽያጩ ለመጀመሪያ ጊዜ መቀነሱን ማስታወቁንና ይሄን ተከትሎም የኩባንያው የአክሲዮን ድርሻ ዋጋ እንደቀነሰ ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡ ኩባንያው በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት የመጨረሻዎቹ ሶስት ወራት 74.8 ሚሊዮን አይፎኖችን በመሸጥ በታሪኩ አነስተኛውን የአይፎን ምርቶች የሽያጭ እድገት ማስመዝገቡንና በቀጣይም ሽያጩ እየቀነሰ እንደሚሄድ ማስታወቁን ዘገባው ገልጧል፡፡
ይሄም ሆኖ ግን፣ አፕል ኩባንያ ምንም እንኳን የአይፎን ምርቶች ሽያጩ ቢቀንስም፣ ባለፈው ሩብ አመት ባገኘው የ18.4 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ትርፉ በአሜሪካ ኩባንያዎች ታሪክ ከፍተኛውን የሩብ አመት ትርፍ ሊያስመዘግብ መቻሉን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
አፕል ኩባንያ የአይፎን ምርቶቹ ሽያጭ መቀነሱን በይፋ ማስታወቁን ተከትሎም፣ ባለፈው ረቡዕ በኩባንያው የአክስዮን ድርሻ ዋጋ ላይ የ4 በመቶ ቅናሽ መመዝገቡንም ዘገባው አብራርቷል፡፡
አይፎን ባለፉት አመታት በስማርት ፎን ገበያ መሪነቱን ይዞ የዘለቀ የአለማችን ታዋቂ ስማርት ፎን መሆኑን ያስታወሰው ዘገባው፣ አፕል ኩባንያ ከአጠቃላይ ገቢው ሁለት ሶስተኛ የሚሆነውን የሚያገኘው ከአይፎን ሽያጩ እንደሆነም ጠቁሟል፡፡

Read 1508 times