Saturday, 30 January 2016 12:58

ነፍሰ ጡሮችን የሚያጠቃው “ዚካ” ቫይረስ የአለም ስጋት ሆኗል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

     - ፈውስም ሆነ ክትባት የለውም፤ እንደ ኢቦላ የከፋ ጥፋት ሊያደርስ ይችላል ተብሏል
                  - በ21 አገራት ተከስቶ፣ 1.5 ሚ ሰዎችን ተጠቂ አድርጓል
       ነፍሰጡር ሴቶችን በማጥቃት የጭንቅላት መጠናቸው አነስተኛ የሆኑና ውስን የአእምሮ እድገት ያላቸው ህጻናት እንዲወለዱ ምክንያት የሚሆነው “ዚካ” የተሰኘ ቫይረስ ወደተለያዩ አገራት በመሰራጨት ላይ መሆኑንና አስቸኳይ እርምጃ ካልተወሰደ እንደ ኢቦላ ቫይረስ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ የከፋ ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል ተዘገበ።
ዴይሊ ሜይል ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣ ካለፈው ግንቦት ወር ወዲህ በ21 የካረቢያን፣ የሰሜን አሜሪካና የደቡብ አሜሪካ አገራት የተስፋፋው “ዚካ” ቫይረስ ክፉኛ ካጠቃቸው አገራት መካከል ብራዚል በቀዳሚነት የምትጠቀስ ሲሆን፣ በአገሪቱ ካለፈው ጥቅምት ወር አንስቶ በቫይረሱ ሳቢያ 4ሺህ ያህል የጭንቅላት መጠናቸው አነስተኛ የሆኑ ህጻናት መወለዳቸው ተረጋግጧል፡፡
ቫይረሱን በምትሸከም ትንኝ አማካይነት ወደ ታማሚው የሚገባው “ዚካ” ቫይረስ፣ ምንም አይነት ፈዋሽ መድሃኒትም ሆነ ክትባት እንደሌለው የጠቆመው ዘገባው፣ አሜሪካና ሌሎች አገራት ቫይረሱ በስፋት ተሰራጭቶ የከፋ ጥፋት ከማድረሱ በፊት ክትባቱን ለማግኘት በአፋጣኝ ርብርብ እንዲደረግ ጥሪ ቢያቀርቡም፣ ክትባቱን የማግኘቱ ጥረት አስር አመት ያህል ጊዜ ሊወስድ ይችላል መባሉን ገልጿል፡፡ የአሜሪካ ሳይንቲስቶች የአለም የጤና ድርጅት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የአስቸኳይ ጊዜ የህክምና ባለሙያዎች ኮሚቴ በማቋቋም አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ የጠየቁ ሲሆን፣ በቫይረሱ ክፉኛ የተጠቃችው ብራዚል ፕሬዚዳንት ዲልማ ሩሴፍም የደቡብ አሜሪካ አገራት ቫይረሱን ለመግታት እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲነሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የመካከለኛውና የደቡብ አሜሪካ አገራት፣ ሴቶች በቫይረሱ ሊጠቁ ስለሚችሉ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የማርገዝ ዕቅድ ካላቸው እንዲያራዝሙት መምከራቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ የተለያዩ አገራት ነፍሰጡር ሴቶችም ወደ ደቡብ አሜሪካ አገራት እንዳይሄዱ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ ተነግሯል፡፡
እ.ኤ.አ በ1947 ለመጀመሪያ ጊዜ በኡጋንዳ እንደተገኘ የተነገረለት “ዚካ” ቫይረስ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአንዳንድ የአፍሪካና የእስያ አገራት ተወስኖ የቆየ ቢሆንም፣ ባለፈው ግንቦት ወር ላይ በብራዚል መከሰቱንና ወደሌሎች የላቲን አሜሪካ አገራት መስፋፋቱንና ከዚያ ጊዜ ወዲህም በአለም ዙሪያ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አይቢ ታይምስ ዘግቧል፡፡
የአውሮፓ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል በበኩሉ፤ “ዚካ” ቫይረስ በቱሪስቶች አማካይነት ወደ አውሮፓ መግባቱንና በቅርቡ በስዊድን አንድ ታማሚ መገኘቱን፣ ሰሞኑንም አንድ የዴንማርክ፣ 6 የእንግሊዝና 2 የጀርመን ዜግነት ያላቸው ሴቶች እንደተገኙ ጠቁሞ ሁለት ጀርመናውያን ሴቶችም በቫይረሱ መያዛቸውን ባለፈው ረቡዕ ማስታወቁን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡

Read 2398 times