Saturday, 06 February 2016 10:51

ጃፓን የሰሜን ኮርያን ሮኬት እንደምትመታ አስጠነቀቀች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አሜሪካ፣ ደ/ ኮርያና ቻይና የሰ/ ኮርያን ዕቅድ አውግዘዋል
    ሰሜን ኮርያ ለምርምር ተግባር የሚውል ያለችውን ሳተላይት ወደ ጠፈር ለማምጠቅ መዘጋጀቷን ባለፈው ማክሰኞ በይፋ ማስታወቋ በአካባቢው አገራት ውጥረት የፈጠረ ሲሆን ጃፓን፤ ሰሜን ኮርያ ይህንን እቅዷን እንድታቋርጥ መክራ፣ ካልሆነ ግን ሮኬቱን መትታ ለመጣል የጦር ሃይሏን ዝግጁ እንዳደረገች ማስታወቋን ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
የጃፓን መከላከያ ሚኒስትር ጄኔራል ናካታኒ፤ የሰሜን ኮርያ ሚሳየል የአየር ክልሏን ጥሶ የሚገባ ከሆነ፣ የባህር ሃይሏ በሮኬቱ ላይ ጥቃት ለመፈጸም መዘጋጀቱን ያስታወቁ ሲሆን፣ በጃፓን ባህር ላይ የጦር መርከቦች መሰማራታቸውና የባላስቲክ ሚሳኤል መከላከያዋም በተጠንቀቅ ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ሰሜን ኮርያ ለምርምር ተግባር አውለዋለሁ ያለችውን ሮኬት በመጪዎቹ ሳምንታት ወደ ጠፈር እንደምትልክ ለተመድ ማስታወቋን ተከትሎ፣ ጃፓን፣ አሜሪካ፣ ቻይናና ደቡብ ኮርያ የአገሪቱን እቅድ የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳየል ለመሞከር የታቀደ ስውር ደባ ነው በማለት እንደተቃወሙት ተነግሯል፡፡
የደቡብ ኮርያ መንግስት ሰሜን ኮርያ ዕቅዷን ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነ ትልቅ ዋጋ ትከፍላለች ያለ ሲሆን፣ ቻይናም ጉዳዩ እንደሚያሳስባት በመግለጽ ሰሜን ኮርያ ከድርጊቷ እንድትታቀብ ጥሪ አቅርባለች፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰሜን ኮርያ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡
አገራቱ ሰሜን ኮርያን ከድርጊቷ እንድትታቀብ ቢያስጠነቅቁም፣ የአገሪቱ መንግስት ግን ሮኬት በማምጠቅ የጠፈር ምርምር ማድረግ ሉአላዊ መብቷ እንደሆነ በመግለጽ ነቀፋውን አጣጥላዋለች ተብሏል፡፡

Read 2952 times