Saturday, 06 February 2016 11:02

“ከአሜን ባሻገር”ን ስመዝነው

Written by  ተስፋ በላይነህ
Rate this item
(5 votes)

በውቄ “መጣሁ” “መጣሁ” ሲለን ሰነባብቶ “ከአሜን ባሻገር”ን እያስነበበን ነው…፡፡ ባጋጣሚ መጽሐፉ አዲሳባ በተለቀቀበት ወቅት ክፍለሃገር ነበርሁ፤ ካዲሳባ እንደየርቀቶቻቸው መጽሐፍቶች ዘግይተው የሚደርሱላቸው የክልል ከተሞች ልክ እንደ በረሃ ውሃ በጉጉት ሲጠበቅ እንደነበር አስተውያለሁ፤ ከጎንደር ባሕርዳር ስደርስም፣ ከጎንደር አንድ ቀን ፈጥኖ የደረሳት ባሕር ዳር በጥቂት ቦታዎች ጥቂት የማይባሉ ሰዎች መጽሐፉን እንደ ባለኣገር የቅቤ ቅል አንጠልጥለው ሳይ፣ ልክ ቅቤውን እንደጠገበ ረሃብተኛ ረክቻለሁ፤ ለመጽሐፍት ካለኝ ጉጉት የተነሳ፡፡
ኣዲሳባ ስገባ ቦሌ ብራስ ሆስፒታል ፊት ለፊት ያለችው የመጽሐፍ ውዷ መደብሬ “ቡክ ላይት” ገብቼ “ከአሜን ባሻገር”ን ፈለግሁ፡፡ አጣኋትም፡፡ እንዳልገባች መገመት ስለከበደኝ የሽያጭ መሪዋን ጠይቅኋት፤ “አልቋል” አለችኝ፡፡ ጠዋት ገብቶ ማታ ያለቀ መጽሐፍ…። በጀ!!
ሌላ 48 ሰዓታትን መጠበቅ ነበረብኝ፤ በነገው ጠዋት ስሄድ፤ የሽያጭ መሪዋ (ካሸር?) ቀጥታ ከጉያዋ አውጥታ አስቀመጠችልኝ፤ 63 ብር ገዛኋት፤ የመጽሐፍት አዟሪዎች አንድ መቶ ብር “እንደሚፈልጡን” ሌላኛው ገዥ ተናገረ። (“ፈላጭ” የዘመኑ ቋንቋ መሆኑንና ከተመጽዋጭነት ከፍ ያለ ሲል በገጽ 18 ህዳግ ማስታወሻ ላይ ጠቅሷል።) ነጋዴውም ከፈላጭ በላይ የሚገለጽበትን ቃል እየፈለግሁ ነው፡፡ 30 ብር የጨመረው መጽሐፍ አዟሪ፤ ትልቁ ቦርጫም ነጋዴ በሌሎች እቃዎች ላይ ስንት እንደሚጨምር ልብ በሉ!!
መጽሐፉን ለመመዘን በግሌ የተጠቀምኩት መንገድ ራሱ በውቄ በተጠቀማቸው ሐሳቦችና ለሐሳቦች ባስቀመጠባቸው ሌሎች ምክንያቶች፤ ወይም ራሱ በሌላኛው ማስታወሻው ላይ በጠቀሳቸው አንዳንድ ሐሳቦች በማጣቀስ ይሆናል። ይሕንን ምሳሌዎቼን ሳቀርብ አንባቢ የሚረዳው ይመስለኛል፡፡ በግሌ የምወቅሰውም የማወድሰውም ብዙም ሐሳብ አይኖረኝም፡፡
ሲጀመር በውቄ ላንባቢ ግድ እንደሚሰጠውና ኣንባቢን በሐሳብ ማዕረግ ደረጃ በደረጃ ከፍ አድርጎ ልዕልና ለማጎናጸፍ መጣሩን አልክድም። በቃል ሳይቀር “ላንባቢየ..” ሲል መጥቀሱን በገጽ 161 ማየት እንችላለን። “ጦርነት ደግሞ ምን በረከት ኣለው? የሚል ጥያቄ ካንባቢየ እንደሚወረወርልኝ እገምታለሁ” ሲል ጠቅሷል፡፡ በቅድሚያ ላንባቢ መጨነቁንና ግድ መስጠቱን የተረዳሁ ሲሆን ጥያቄ እንደሚወረወርለት ማስገንዘቡም መጽሐፉን በነጻነት አንብበን፣ ሐሳብ እንድንወራወርበት መፍቀዱን ተረድቻለሁ፡፡
‹‹ስለ ገብረ እግዚአብሔር” በሚለው መጣጥፉ ላይ የገብረ እግዚአብሔርን ጽሑፍ “እንመዝነው” ሲል በመጥቀሱ የዚሕ አጭር አስተያየት ጭብጥና ርዕስም በመመዘን ደረጃ ላይ ሊቆም ይችላል፡፡ “ከአሜን ባሻገር”ን ስንመዝነው- እንዲል ርዕሴ፡፡
በውቄ ምጡቅ አዕምሮ እንዳለው እኔ ገልቱው የምመሰክርለት ኣይደለሁም፤ የተሾሙና የተሸለሙ በአእምሮ ጉልበት የበሰሉ ታላላቆቼ ጉባኤ ይዘው ሲመራመሩበት ቢውሉ እመርጣለሁ፡፡ ከዚህ በፊት ባወጣቸው የግጥም ሐሳቦችም ሆነ መጣጥፎች በሁለት ኣይን ስመለከተው ኖሬያለሁ። “አምቢዘለንስ” የሚለውን ቃል ልብ በለልኝ፡፡ ቀዳሚው ጽሑፍ የምጡቅ ኣዕምሮ ባለቤት የሆነውን “በኗሪ ኣልባ ጎጆዎች” ያስደመመኝን ዘላለማዊውን በውቄን ሲሆን፤ በሌላኛው ኣይን የምመለከተው ደግሞ የግል ስብዕናውን ሙሉ ምድራዊ ነጻነት ይኖረው ዘንድ ልገድበውም ሆነ ልቃወመው የማይገባኝን ኢኣማኒውን በውቄን ነው፡፡
1- የምጡቅ አዕምሮ ባለቤት “ኗሪ ኣልባው” በውቄ፡፡
ፍልስፍናው፣ ማሕበረሰባችንን የሚያይበት ኃያል ሰይፉ፣ በደሳሳ ጎጆ የጠፍር አልጋ ላይ ተኮራምቶ፤ ዐለምን የሚያስሰውን በውቄን እጅግ አድርጌ ኣደንቀዋለሁ፤ ከማንኩሳ እስከ ካናዳ ከማርቆስ አዲሳባ የሚከንፍበትን “ክንፋም ሕልም” ባለቤት የሆነውን በውቄን ተገርሜ ተደምሜ ሁሌም አስበዋለሁ፤ በግጥሞቹ የሚወረውራቸውን ሐሳቦች ከእያሪኮ ጩኸት በላይ የሰውን ግዑዝ ሐሳብ የሚንዱ ናቸውና፡፡ ሐሳብ ግዑዙን ሲንድ እንደማየት ምን አስማት አለ?
ለአንድ ቤትና  ማሕበረሰብ ብሎም ለአገር እንዲሕ አይነት ፋና እንደሚያስፈልገን አጥብቄ እከራከር ነበር፡፡ አለሁም፡፡ ሐሳብ እንዲህ በደቀረበት- - - ተስፋ በሌለበት ተስፋ አድርግ የሚለውን በዓሉን እያሰብኩ!!
በዚሕኛው በ”ከኣሜን በሻገር” ያስተዋልሁት ነገር ቢኖር፤ በውቄ ከወትሮም በምናውቀው የልግጫና በየጥጋጥጉ ጣል በሚያደርጋት ዋዛ ለበስ ቁምነገር ቀልዶቹ በመሆኑ ይመስለኛል፤ አሁን ላይ ግን ታሪክ እና ቁምነገራዊ ምክር ኣዘል ሐሳቦችን ይዞ ስለተነሳ ቅር የተሰኙ “የባርጩሜ ጸሐፊያን”ም ሆኑ አንባቢያን ጥቂት አይደሉም፡፡
በውቄ “የባርጩሜ ጸሐፊያን” ሲል የተጠቀመው አገላለጽ ከምንም በላይ ለአሁን ጸሐፊያን የሚገድ ሐሳብ ነው፡፡ የጉዞ ማስታወሻዎች ይቅሩና፤ በእግር በተንቀሳቃሽ ኃይሎች ተዟዙረን መጻፍን ጨምሮ ወደኋላ እየሄድን መጽሐፍትን፣ ዜና መዋእሎችን፣ ታሪክ ነገስትን እያጣቀሱ መጻፍ ልምድን በውቄ አሳይቶናል፡፡ ለዛሬ ሕመማችን፣ የማሕበረሰባዊም ሆነ የፖለቲካ ቅጥኣምባራችን በውቄ በምጡቅ ሐሳቡ ወደ ኋላ እተጓዘ የዘመንን መንፈስ እየቃኘ፤ ሲያሻው እንደ መሰንቆ ቅኝት ላይ ላዩን እየሞሸረ እንድንማር፣ እንድንገነዘብ አልፎ ተርፎም ዘንድሮን እንድናድን ሲለፋ ተመልክቸዋለሁ፡፡ በተለይ ኣሁን ኣሁን ከሚወዛወዙት የብሔር ፖለቲካ ቅብብሎሽ ንውዘት እናገግም ዘንዳ በውቄ ሲቦዝን ኣላየሁትም። ይሕንንም የራሱን ዘር ሐረግ ለመጻፍ በተመላለሰበት ጽሑፍ ውስጥ እንዲሁም የመጽሐፉን ሙሉ ገጽ አንብበን ስንጨርስ የምናገኘው ሐቅ ነው፡፡ ‹‹በእውቀቱ -ስዩም -በዳዳ- ደስታ-ወየሳ›› መባሉን በገጽ 98 ሲነግረን፤ ለብሔር ሽኩቻው ውርዋሮሽ የማለዘቢያ መስዋዕትነቱን ሲጠቅስልን ነው ብዬ አምኛለሁ፡፡
አሁን አሁን እየተዛቡ የሚቀርቡልንን የታሪክ ቁርቁሶች፤ በኃይልና ልክ እንደ በርጩሜው ጸሐፊ ተቀምጦ መከላከል እንደማይቻል የተገነዘበው በውቄ፤ የተስፋዬ ገብረኣብንና ሐሳቦ, “የተፈበረኩ” አሊያም “አፍራሽ አስተያየት” ሲል ከገለጸ በኋላ ምጡቅ አዕምሮውን በመጠቀምና ስለዘመኑ የተጻፉ መጻሕፍትን በመፈተሽ ተስፋዬን ሲሞግት እንመለከታለን፡፡
በዚህ ዘመን በአሁን ሰዓት የሚያስፈልገን እንዲህ አይነት ጸሐፊ፣ እንዲህ አይነት ሐሳብ አራማጅ እንጂ ብሔርተኛ ልክፍቶች በሚያዜሙት የተምታታ የቁራ ጩኸት መነዳት አይደለም፡፡ በውቄ በዘንድሮ ውሰጥ “ድሮ” /ገጽ 9/ መገኘቱን የመግለጽና የማየት አቅሙ እንዲሁም ለነገሮች የሚሰጠው አመክንዮያዊም ሆነ አካሚ ሐሳብ ይበል የሚያሰኘው፣ አርኣያ ሊሆንበት የሚገባ፣ ሊያስመሰግነውም የሚያስችል ስብዕና  ተላብሶ አግኝቸዋለሁ፡፡
መስጊድን አፍርሶ ቤተክርስትያን ሰራ የሚልን ዘገባ ከመቃወም፤ ቤተክርስትያንም ፈርሶ መስጊድ የተሰራበትን የታሪክ ገጽ አውጥቶ በማሳየት፤ አሁን ላይ ከመቂያቂያም ይልቅ ካለፈው ተምረን አሁንንና ነገን “ቤት” እንድንገነባ የበኩሉን ጡብ ሲያቀብል የሚውልን ቀን-በሌ ግንበኛ ሆኖ አይቼዋለሁ፡፡
ተስፋዬ ገብረአብ ዐማራ ሲመጣ ጭካኔው በዛ የሚለውን ሕግ ወደ አንድ ብሔር ትንኮሳ ለማቀጣጠል፣ ሲሞክር፤ በውቄ ወደኋላ የነበረውን ድርሳን ተመልክቶ  ታዋቂው የሀረር አሳሽ ሪቻርድ በርተንን በማስረጃ በማስቀመጥ ይሞግታል፡፡/ገጽ 175ን አንብብ/
በውቄ ቃላት ይታዘዙለት ዘንድ የተፈቀደለት ጸሐፊም ነው፡፡ ሐሳቦች በቃላት እንደትንፋሽ ተንቀልቅለው፣ ልክ ሸምበቆ የሰውን ትንፋሽ ሲያገኝ እንደሚያላዝነው ሁሉ፤ ብሎም ደስታን እንደሚገልጽ ጭምር፤ በውቄ ቃላቶችን በሐሳብ ትንፋሽ ሲያዛቸው ተመልክቻለሁ። የምዕራባዊውን ዝናብ በፍጥነት መውረድ “እንደ ወፍ አይነምድር ሿ” ሲል የገለጸበት መንገድና ተያያዥ አገላለጾቹ ከምጡቅ አዕምሮው እንጂ ከኪሱ እንደማይወጡ ልብ እንላለን፡፡
ከምጡቅ አዕምሮ ብዙ ነገሮች ይወጣሉ፡፡ በዚህ መጽሐፍ ብቻ በአጭር በአጭር የተቀመጡ ሐሳቦችን ብንወስድ ከመማር፤ ከመመራመር አልፈን ዘመን ተሻጋሪ ብሂሎችን አንጥረን እናወጣለን፤ አንጣሪ አንባቢ ግን ግድ ይለናል፡፡
እስኪ ጥቂቶቹን እንካችሁ፤
ድል በዘር አይተላለፍም- ገጽ 11፤ በጉብዝናህ ወራት በእርጅና ላይ ያሉትን ሐውልቶች ጎብኝ- ገጽ 31፤ ስልጣኔ ማለት ተፈጥሮን መከርከም ነው- ገጽ 42… ልክ እንደዚህ በወፍ በረር እየተመለከትን ገጾችን ብንናቅኝ መሠረት ያላቸውን ሐሳቦች እንሸለማለን፡፡ ሆኖም ማንበብ በጥልቀትና በማስተዋል መሆኑን መዘንጋት እንደሌለብን አሁንም ግልጽ ነው፡፡
በውቄ ዋዛና ፌዝ አሊያም ልግጫ አያቅተውም፤ በውድቅት ለሌሊት እያነበብኩ የነበረውን የገጽ 41 አንቀጽ ከት ከት ብዬ እንድስቅና የተኙትን እንድቀሰቅስ አስገድዷል፡፡ ብቻዬን ብሆን ማንም ባላየኝና እብድ ባላለኝ ነበር፡፡ የተኙ ሰዎች እንኳ በድንገት ነቅተው እብድ የማለት ብቃት እንዳላቸው አስመስክሬያለሁ፡፡ በገጽ 41 የተቀመጠው “ሰው አለቅጥ ሲደነግጥ እንዲህ ያለውን የጥንቃቄ ዝርዝር ይቅርና በሽንት ቤትና በሱሪው መካከል ያለውን ልዩነት እንኳ ይረሳዋል፡፡” ሲል ከነበረው ሐሳብ ጋር ተዳምሮ በጣም አስቆኛል፡፡ እብድ እስከመባል፡፡ ብቻዬን ብሆን እብድ አልባልም ነበር…፡፡
እብድ መባልን የገለጸበት መጣጥፍም ብዙ ያስተምረናል። በድጋሜ በውቄ የታደለው ነገር ቢኖር ትናንትን ሙሉ በሙሉ ከማምለክም ይሁን ከመጥላት ጋር አለመቆራኘቱ ነው፡፡ ዛሬንም ቢሆን ከትላንትና ከነገ ጋር መዝኖ ማስቀመጥ እንጂ የሙጥኝ ሲል አላጋጠመኝም፡፡ “ጤዛዊነት” የምትለው ብኂሉ የገባኝን ያክል ሳደንቀው ብኖርም፤ ዘላለማዊነትን የሚጻረር ዛሬነትን ግን አልደግፈውም፡፡ ዛሬ ዘላለማዊ ነው፤ ዘላለማዊም ሕያው ነው፡፡ ሕያውነት ካለ ዘላለማዊነት የግድ ነው፡፡ “ሕያው ወንድሙ” ሲል የጠቀሰውን ድርብ ቃል ከመጽሐፉ ማግኘት ይቻላል፡፡ ራሱን በራሱ ሐሳብ መግለጽ ስል የተጠቀምኩበት መንገድ እንዲህ አይነቱን እንደሆነ አንባቢ ልብ ይበል፡፡
ወደዚህኛው ሐሳብ የተሸጋገርኩት ከላይ እንደጠቀስኩት በውቄን የምመለከተው በሁለት አይን መሆኑን ባስቀመጥኩት መሰረት ነው፡፡ ስለ ምጡቁ አዕምሮው ባለቤት በውቄ እና ኢአማኑ በውቄ፡፡
በሚቀጥለው ሳምንት ስለ ሁለተኛው በውቄ ለመጻፍ ቃል በመግባት እንሰነባበት፡፡ የአምስት ኪሎውም ሆነ የፒያሳው ክሩ(crew) እንዲሁም የፌስቡኩ ማዕበል የበውቄን “ከአሜን ባሻገር” የወደደው አልመሰለኝም፡፡ በቡድን ማሰብ ቀርቶ በየግል ሚዛናችን አንብበን የግል አረዳዳችን መስጠት የሚበጅ ይመስለኛል። በውቄ ከዚህ በፊት የወጡ ጽሑፎችን ደግሞ ማውጣቱን ከበጎ ሕሊና ከተረዳነው የሚታፈኑ መጽሔቶችንም ሆነ በኢንተርኔት የማያነበውን ሰፊው ሕዝብን በማሰብ የተቸረ መሆኑን መገንዘብ ብቻ ለኔ በቂ ነው፡፡
በተጨማሪ በዚህ የመጣጥፍ ንዑስ ጋርዮሽ ሥራውም ሳንቲም ቢሰበስብ የምቃወም መሆን ለብኝም፤ ሰው ዘርፎ ሐብት ካላባበተ(ከብት ከሚለው ቃል መጣ ሲል ገልጾታል -በውቄ)፤ ወይንም ገድሎ ካልተፎከረ በቀር ጀግንነት እንደማይገኝ የሚያስብ አዕምሮ በውቄን ቢያማው አልደነቅም፡፡ ከበጎ ሕሊና ግን በውቄን ሐብትም ከብትም ብንሸልመው የሚያንስው ይመስለኛል፡፡
የ“ደብተራው” ጸገየ ወይን ገብረ መድህን ‹‹ናስተማስለኪ›› የኮሌጅ ቀን ግጥምን በመጋበዝ፤ ኢኣማኒውን በውቄን ለመቃኘት ሳምንት ወደ ዝርዝሩ እንደምመለስ አስታውቃለሁ፡፡ የሳምንት ሰው ይበለን!!


Read 5882 times