Saturday, 13 February 2016 11:04

መንግሥት አዲስ የቤቶች ፕሮግራም እቅድ ይፋ አድርጓል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

በ5 ዓመት 1.7 ቢ የገጠር ቤቶች ለመገንባት ታቅዷል

በአዲስ አበባ፤ ቤት ፈላጊዎች 17 ቢ. ብር ቆጥበዋል ተባለ እስከዛሬ ቤት ያገኙት 143ሺህ ነዋሪዎች ብቻ ናቸው
የማህበራት የቤት ልማት ሙሉ ለሙሉ አልተሳካም

    መንግሥት ሰሞኑን አዲስ የቤቶች ልማት ፕሮግራም ይፋ አድርጓል - “የገጠር ማዕከላት ቤት ግንባታ” በሚል፡፡ ዕቅዱ ለብዙዎች አዲስ ቢመስልም በቀጣዮቹ 5 ዓመታት 1.7 ሚሊዮን የገጠር ቤቶች ይገነባሉ ተብሏል፡፡
በአዲስ አበባም ለዚህ ዓመት ብቻ በተመደበ 10 ቢ. ብር 171 ሺህ ቤቶች እየተገነቡና እየተጠናቀቁ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን በተለያዩ የቤት ፕሮግራሞች የተመዘገቡ ቤት ፈላጊዎች እስካሁን ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ እንደተቆጠበ ተጠቁሟል፡፡
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር፤ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ እስከ ዛሬ በቤቶች ልማት እንቅስቃሴ ዙሪያ የ3 ቀናት አገር አቀፍ ምክክር በማካሄድ ላይ ሲሆን በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ፤ 1.7 ሚሊዮን የገጠር ቤቶች እንደሚገነቡ ተገልጿል፡፡፡፡
የገጠር ቤቶችን መገንባት ያስፈለገው የገጠር ነዋሪው የተሻለ የአኗኗር ስልት እንዲከተል፣ የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆንና ሁሉም ፍላጎቱ ባለበት ተሟልቶ፣ ተረጋግቶ እንዲቀመጥ ለማስቻል መሆኑን የጠቆመው ሚኒስቴሩ፤ ገጠሩን በሂደት ወደ ከተሜነት ለመለወጥና በግብርና የሚተዳደረውም በሂደት ወደ ኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፎች እንዲገባ ለማድረግ ነው ብሏል፡፡ ቤቶቹ የገጠሩን ነዋሪ ፍላጎት መሰረት አድርገው እንደሚገነቡ የጠቆሙት የሚኒስቴሩ የስራ ኃላፊዎች፤ ቤት ፈላጊዎች ገንዘብ ቆጣቢ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡
አሁን ሊገነቡ የታቀዱት የገጠር ቤቶች መኝታ ቤት፣ መፀዳጃ ቤትና ኩሽና የሚኖራቸው ሲሆን  ደረጃቸውን የጠበቁ የውሃ፣ የመንገድና የመብራት አገልግሎት እንዲሁም የደረቅ ፍሳሽ ማስወገጃ እንደሚኖራቸው ተነግሯል፡፡
በ1999 የህዝብና ቤት ቆጠራ ሪፖርት መሰረት፤ 73.14 በመቶ የሚሆኑት የገጠር ቤቶች የተገነቡት ከእንጨትና ከጭቃ ሲሆን 61.43 በመቶዎቹ ጣሪያቸው የሳር ክዳን ነው፡፡ ከ54 በመቶ በላይ የሚሆኑት ቤተሰቦች በአንድ ክፍል ብቻ እንደሚኖሩም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
የከተማውን የቤት ፍላጎት ሳታሟሉ እንዴት ወደ ገጠር አካባቢ ትኩረት አደረጋችሁ? በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበው ጥያቄ የስራ ኃላፊዎቹ በሰጡት ምላሽ፤ “የከተማውም በተያዘለት እቅድ መሰረት ራሱን ችሎ በአግባቡ እየተሰራ ነው፤ ቤቶችን አጠናቆ በቶሎ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ ወሳኙ የቁጠባ አቅም ነው” ብለዋል፡፡  በአዲስ አበባ ከ3 ዓመት በፊት የተጀመሩ ቤቶችን በፍጥነት አጠናቆ ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ ያልተቻለበትን ምክንያት ኃላፊዎቹ ሲያስረዱም፤ ቀድሞ 80 በመቶ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ ቤቶች ይተላለፉ እንደነበር በማስታወስ፤ ይህ አሰራር በርካቶችን ለተጨማሪ ወጪና እንግልት የሚዳርግ በመሆኑ መቶ በመቶ አጠናቆ ለማስተላለፍ ሲባል ነው ብለዋል፡፡ ግንባታዎች በበጀት እጥረት እንዳይቆሙ ተጨማሪ በጀት ለመመደብ ውይይት እየተደረገ መሆኑንም ኃላፊዎቹ ገልፀዋል፡፡
አዲስ የታቀደው የቤት ፕሮጀክት የክልል ከተሞችንም የሚያካትት ሲሆን ከዚህ ቀደም በክልል ከተሞች የኮንዶሚኒየም ቤት ፍላጎት አነስተኛ ነው ተብሎ ፕሮጀክቶች እንዲቋረጡ መደረጉ ይታወሳል፡፡ አሁንስ ምን ተገኝቶ ይሆን? የስራ ኃላፊዎቹ መልስ አላቸው፡፡ “አሁንም በክልል የሚኖረው የቤት ፍላጎቱ በዝርዝር ተጠንቶ ነው ተግባራዊ የሚደረገው፤ ቤቶቹ የቆጣቢውን አቅም መሰረት ያደረጉ ይሆናሉ”፡፡
የኮንዶሚኒየም ቤቶችት ልማት ፕሮግራም ይፋ ከተደረገ ወዲህ ባሉት 10 ዓመታት ገደማ ድሬደዋን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች 69 ሺህ ቤቶች መገንባታቸውን የጠቀሰው የሚኒስቴሩ ሪፖርት፤ 61 ሺዎቹ ለቤት ፈላጊዎች የተላለፉ ሲሆን ስለቀሪዎቹ 8ሺ ቤቶች የጠቀሰው ነገር የለም፡፡
 በህብረት ስራ ማህበራት በኩል፤ በአዲስ አበባ ከ1996 በፊትና በኋላ የተቋቋሙ 100ሺህ አባላትን የያዙ 5,599 ማህበራት የነበሩ ሲሆን በተለያየ ምክንያት ማህበራቱ ስኬታማ አልሆኑም ተብሏል፡፡ ከ1997 በኋላ የነበሩ 499 ማኅበራትም እስካሁን የተሟላ መስተንግዶ አግኝተው ወደ ተግባር አለመግባታቸውን የሚኒስቴሩ ሪፖርት ያመላክታል፡በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ግን በህብረት ስራ ማህበራቱ በየዓመቱ 34 ሺህ ቤቶች እንዲገነቡ የታቀደ ሲሆን በ5 ዓመቱ መጨረሻ ላይ 174 ሺህ ቤቶች ተገንብተው እንደሚጠናቀቁ ይጠበቃል፡፡
መንግስት በአዲስ አበባ የቤት ልማት ፕሮግራምን ተግባራዊ ካደረገበት 1996 ዓ.ም ወዲህ ከ3 አመት በፊት የተካሄደውን ምዝገባ ጨምሮ ወደ 1ሚ. የሚጠጉ ነዋሪዎች በቤት ፈላጊነት የተመዘገቡ ሲሆን እስካሁን 143 ሺህ ቤቶች ብቻ ለነዋሪዎች እንደተላለፉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በመጀመሪያው እቅድ 150ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት 171 ሺህ ቤቶች በመገንባትና በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን የጠቆመው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ በሁለተኛው የእድገት እቅድ ደግሞ 430 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ያቀደ ሲሆን በየአመቱም 86 ሺህ ቤቶች ይገነባሉ ብሏል፡፡ ከዚህም ውስጥ 60 ሺዎቹ በአዲስ አበባ የሚገነቡ ሲሆን ቀሪዎቹ በክልል እንደሚገነቡ ተጠቁሟል፡፡ በአጠቃላይ በተለያዩ የመንግሥት የቤት ልማት ፕሮግራሞች፤ በማህበራትና በሪል ስቴቶች 750 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት መታቀዱን የሚኒስቴሩ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ በመንግስት ዕቅድ መሰረት፤ በ5 ዓመት ውስጥ 12ሺ 700 ቤቶች በግለሰቦች የሚገነቡ ሲሆን በሪል እስቴት 70ሺህ፤ በህብረት ስራ ማህበራት 174 ሺህ፣ በገጠር ማዕከላት ቤት ግንባታ 1.7 ሚሊዮን ቤቶችን የሚገነቡ ይሆናል፡፡ በሀገሪቱ የገጠር ከተሞችም ከ2.4 ሚሊዮን በላይ ቤቶች ለመገንባት ታቅዷል፡፡
በቤቶች ግንባታ ላይ የውጭ ሀገር የኮንስትራክሽን ኩባንያዎችን ለማሳተፍ በመንግሥት በኩል ታቅዶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታቸው ሃይለማርያም ስለጉዳዩ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ “ቀድሞም ቢሆን የታቀደው የውጭ ኩባንያዎች በስራው ላይ በቀጥታ እንዲሰማሩ ሳይሆን መንግስት ትኩረት ለሰጠው የኮንስትራክሽን ዘርፍ የአቅም ግንባታ አጋዥ እንዲሆኑ ነው” ብለዋል፡፡ የአቅም ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ የሀገር ውስጥ ተቋራጮችን አቅም በመገንባት በኩል በትኩረት እንሰራለን ብለዋል፤ አቶ ጌታቸው፡፡ የውጭ ኮንትራክተሮች የሚያስፈልጉት ለአቅም ግንባታ ነው እንጂ ስራው እንዲሰራ የሚፈለገው በሀገር ውስጥ ተቋራጭ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በአሁን ወቅት በዘርፉ ከ60 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡    

Read 3043 times