Saturday, 13 February 2016 11:12

100 ዓመት ያስቆጠረው የጋዜጣ ታሪክ

Written by  ባዩልኝ አያሌው
Rate this item
(2 votes)

“People care about what newspapers tell them to care about.” ይላል የታሪካዊ ልቦለዶች ጸሐፊው Delia Parr፡፡… በዓለም ታሪክ ውስጥ የሰው ልጅ መረጃዎችን ከተቀባበለባቸውና ሐሳቡን ካቀበለባቸው ቀደምት መንገዶች አንዱ ጋዜጣ ነው፡፡ በዘመናት ሂደት የሰው ልጅን የአእምሮና አስተሳሰብ ዕድገት፣ በዚህም የደረሰበትን የሥልጣኔ ከፍታ ተከትሎ ጋዜጣ አሁን ከደረሰበት (በቅርጽም በይዘትም) መራቀቅ በፊት፣ ያለፈበት መንገድ እጅጉን አስደማሚ “ገድል” ነው፡፡ ይሆናል ተብሎ የማይታሰብ፤ ግን ደግሞ የሆነ ገድል!
በዓለም ላይ የጋዜጣ ታሪክ ከአምስት ምዕተ ዓመት በላይ አስቆጥሮአል፡፡ ጠንሳሾቹም አውሮፓውያን መሆናቸውን ጥናቶች ይገልጻሉ፡፡ ጋዜጣ በማተሚያ ማሽን ለመታተም ወግ፣ ከመብቃቱ በፊት ተወልዶ ዳዴ ያለው በእጅ በመጻፍ ነበር፡፡… ከጦርነት ወሬ እስከ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣ ከባህላዊ ክንውኖች እስከ ማህበራዊ ወጎች… በእጅ እየተጻፈ በነጋዴዎች አማካይነት ይሰራጭ ነበር፡፡
በኋለኛው ዘመን ጋዜጣን በማሳደግ ለወግ ካበቁት ሀገሮች መካከል አሜሪካን፣ እንግሊዝና ህንድ ቢጠቀሱም ቅሉ፣ በ14ኛው ክፍለ ዘመን ጋዜጣን ለመጀመሪያ ጊዜ በማሽን ያተመችው ሀገር ጀርመን እንደሆነች ተመዝግቦአል፡፡ ቀጥሎም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነው ዓለም ቅርጹንና ይዘቱን እያዘመነ፣ ስርጭቱንም እያሰፋ ጋዜጣን ለወግ አበቃው፡፡ በዚህም እንግሊዞች በ1666 ትክክለኛ ጋዜጣ ሊባል የሚችለውን “London Gazette”ን በማተም ቀጣይ ጉዞውን ቀይሰዋል፡፡…
እንደ አውሮፓውያኑ ሁሉ የማተሚያ ማሽን ያልነበረባቸው ሀገሮችም ጋዜጣን የጀመሩት እጅግ ጥቂት ቅጂዎችን በእጅ እየጻፉ በማሰራጨት ነው፡፡ በኢትዮጵያም የሆነው እንዲሁ ነው፡፡ ጋዜጣ በሀገራችን መሠረቱን የጣለው በአጼ ምኒልክ ዘመን ነው፡፡ መሠረቱንም የጣሉት (በተለይ የአማርኛ ጋዜጣን) ብላታ ገብረ እግዚአብሔር ጊላ የተባሉ በዘመኑ የነበሩ የሥነጽሑፍ ሰው ናቸው፡፡ (ከእሳቸው በፊት ከ1860-1893 በነበሩት ዓመታት በሐረር ከተማ በጣሊያንኛና በፈረንሣይኛ ቋንቋዎች ሁለት ጋዜጦች ይዘጋጁ እንደነበር ሳንዘነጋ) ብላታ ገብረ እግዚአብሔር በየሳምንቱ 50 ቅጂዎችን በእጅ ጽፈው ለመኳንንቱ ያድሉ ነበር፡፡
ቆይቶም በብላታ ገብረ እግዚአብሔር የተጣለው የጋዜጣ መሠረት፣ የግሪክ ተወላጅ በሆነው እንድርያስ ኤካቫዲ አማካይነት ለማደግ ዳዴ ማለት ጀመረ፡፡ ኤካቫዲ በ1880ዎቹ መጨረሻ በተሻለ የእጅ ጽሑፍና ቅርጽ፣ አራት ገጾች ያለው ጋዜጣ እያዘጋጀ በየሳምንቱ 24 ቅጂዎችን ማዳረስ ጀመረ፡፡ ይህ ጋዜጣ በአማርኛ ቋንቋ ይዘጋጅ የነበረ ሲሆን ስሙም “አእምሮ” (የሰየሙት አጼ ምኒልክ እንደሆኑ ይነገራል) ይባል ነበር፡፡… እንግዲህ እስካሁን ባለን መረጃ የመጀመሪያው የአማርኛ ጋዜጣ “አእምሮ” መሆኑ ነው፡፡ (“አእምሮ” በአፍሪካ ቋንቋ የታተመ የመጀመሪያው ጋዜጣም ነው፡፡) በኋላም ኤካቫዲ የማባዣ መሳሪያ ከአውሮፓ አስመጥቶ የቅጂው ቁጥር እንዲጨምር አደረገ፡፡
የብላታ ገብረ እግዚአብሔርን እና የኤካቫዲ ትጋት በተለይም የጋዜጣውን ጥቅም ልብ ያሉት ምኒልክ ነገሩን በቸልታ አላዩትም፡፡ ከፈረንሣይ ሀገር የማተሚያ ማሽን እንዲገዛ አደረጉ፡፡ በመሆኑም “አእምሮ” ጋዜጣ በማሽን ለመታተም በቃ፡፡ አዘጋጁም አብዝቶ ያለመታከት የደከመው እንድርያስ ኤካቫዲ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ጋዜጣው ጥቂት (አራት) ገጾች የነበሩት ቢሆንም፣ ርዕሰ አንቀጽን፣ የሀገር ውስጥ ዜናዎችን፣ ልዩ ልዩ አስተያየቶችንና ማስታወቂያዎችን ይዞ ይታተም ነበር፡፡ በመጀመሪያው ዕትም ርዕሰ አንቀጹም፣ “ይድረስ ለአልጋ ወራሽ ኢያሱ” በማለት ለወቅቱ አልጋ ወራሽ መልዕክት አስተላልፎአል፡፡
የጋዜጣው ታትሞ (200 ቅጂዎች ድረስ ይታተም ነበር) መሰራጨት፣ ለሥነጽሑፍ ሰዎችም ሆነ ለአንባቢያን ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም የጋዜጣው ጉዞ እንደ ጅማሬው አልቀጠለም፡፡ የራስ ተፈሪን የአልጋ ወራሽነት ሥልጣን መቆናጠጥ ተከትሎ፣ አልጋ ወራሹ ማተሚያ ቤት እስኪያቋቁሙ ድረስ የ“አእምሮ” ሕትመት ተቋረጠ፡፡
በ1914 ዓ.ም. የብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት (የመጀመሪያ ስሙ “አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ ማተሚያ ቤት” ነበር፡፡ የ“ብርሃን እና ሰላም” ጋዜጣ መታተም መጀመርን ተከትሎ ነው ስሙን ከጋዜጣው የወሰደው) መቋቋም የኢትዮጵያ የጋዜጣ ጉዞ ሌላው ምዕራፍ ሆነ፡፡… በ1917 ዓ.ም. በማተሚያ ቤቱ “ብርሃን እና ሰላም” የተባለ አዲስ ጋዜጣ መታተም ጀመረ፡፡ ተቋርጦ የነበረው “አእምሮም” በዚሁ ማተሚያ ቤት ይታተም ጀመር፡፡ (በወቅቱ በማተሚያ ቤቱ እየታተሙ ከሚወጡት ከእነዚህ ሁለት ሳምንታዊ የአማርኛ ጋዜጦች ሌላ፣ አንድ በፈረንሣይኛ ቋንቋ የሚታተም ጋዜጣም ነበር፡፡)
በዘመኑ መድረሻቸውን የሀገሬው አንባቢ ባደረጉት ሁለቱ (“አእምሮ” እና “ብርሃን እና ሰላም”) ሳምንታዊ ጋዜጦች መካከል የነበረው ሙግትና “እሰጥ አገባ” ትኩረትን የሚይዝ ነገር ነበረው፡፡  በጊዜው “አእምሮ” ጋዜጣ የሚያወጣቸው ጽሑፎች ይዘት፣ አልጋ ወራሹን የሚቃወሙና የሚተቹ ሲሆን የ“ብርሃን እና ሰላም” ጋዜጣ የሚያትማቸው ጽሑፎች ደግሞ በአንጻሩ አልጋ ወራሹን የሚደግፉ ነበሩ፡፡ ይህም በጋዜጦቹ የቅጂ ብዛት ላይ የጎላ ልዩነትን የፈጠረ ነበር፡፡
በጊዜው “አእምሮ” ጋዜጣ 200 ቅጂዎች ብቻ ይታተም የነበረ ሲሆን፣ የአልጋ ወራሹ ደጋፊ የነበረው “ብርሃን እና ሰላም” ግን በየሳምንቱ 500 ቅጂዎች እየታተመ በስፋት ይሰራጭ ነበር፡፡… ምንም እንኳን ለዚህ ዕድል መፈጠር በወቅቱ የነበረው የሥልጣን ሽኩቻና መሰል ጉዳዮች ምክንያት ቢሆኑም፣ በዚያን ዘመን ይህን መሰል የመቃወምና ሐሳብን የመግለጽ (ባይዘልቅም) መንፈስ መኖሩም በራሱ ትኩረትን የሚስብ ነገር አለው፡፡  
እንዲህ እንዲህ እያለ፣ (በመንግሥት ሙሉ ቁጥጥር ሥር ቢሆንም) መሠረቱን እያጠበቀ ጉዞውን የቀጠለው ጋዜጣ፣ ከጣሊያን ወረራ በፊት (1928) በነበሩት ጥቂት ዓመታት የጋዜጦች ቁጥር ሰባት (አራት የአማርኛ፣ ሁለት የፈረንሳይኛ፣ አንድ የጣሊያንኛ) ደርሶ የነበረ ቢሆንም የሀገሪቱ በጣሊያን መወረር የጋዜጣን ጉዞ መልሶ ቀጨው፡፡
በጊዜው በሰፊው እየታተመ ይሰራጭ የነበረው የኢጣሊያ መንግሥት ልሣን የሆነው “የቄሣር ልሣን” የተባለው ጋዜጣ ብቻ ነበር፡፡ (ጋዜጣው የወራሪውን ኃይል መልካምነት የመስበክና ለነጻነታቸው በዱር በገደል የሚዋጉትን አርበኞች ወኔ የመስለብ ዓላማ ነበረው) ሆኖም እንደ ኢትዮጵያውያኑ አርበኞች ሁሉ “እንቢኝ” ብሎ በሱዳን ሀገር እየተዘጋጀ ወደ መሀል ሀገር ይሰራጭ የነበረ “ባንዲራችን” የተባለ አንድ የአማርኛ ጋዜጣ መኖሩ የጋዜጣን ጉዞው ከምንም ታድጎታል፡፡
ከነጻነት በኋላ ጋዜጣ እንደገና ሌላ የጉዞ ምዕራፉን ጀመረ፡፡ ለዚህም በሀገሪቱ የተፈጠረው አዲስ የነጻነት መንፈስና ዘመናዊ ትምህርትን የተማሩና የሥነጽሑፍ ችሎታው የነበራቸው ሰዎች ወደ ጋዜጣ መምጣታቸው ምክንያት ሆኖአል፡፡… ይህም በቅርጽም ሆነ በይዘት የተሻሉ ሁለት ጋዜጦች ብቅ እንዲሉ አደረገ፡፡ እነዚህም በዘመኑ ከተፈጠረው አዲስ መንፈስ ስሙን ያገኘ የሚመስለው “አዲስ ዘመን” (1933) ጋዜጣ እና ከዓመታት በኋላ (በ1940) መታተም የጀመረው የእንግሊዝኛው “Ethiopian Herald” ጋዜጣ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን እነዚህም ጋዜጦች እንደ ቀዳሚዎቹ ሁሉ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የነበሩና ዘውዳዊውን  መንግሥት የሚያገለግሉ ቢሆንም፣ በወረራው ዘመን ተገትቶ የነበረውን የጋዜጣን ጉዞ በአዲስ መንፈስ አስቀጥለዋል፡፡…
እንግዲህ በቁጥርና በአይነት በርክቶ፣ በቅርጽና በይዘት ዘምኖ… አሁን ላይ የደረሰው የሀገራችን ጋዜጣ መሠረቱን የጣለው በእንዲህ ባለ ምስቅልቅልና አድካሚ መንገድ ነው፡፡ አሁንም ግን ከድካሙ አላረፈም፡፡ ከመቶ ዓመታት በኋላ ዛሬም ዕድገቱን የሚጎትቱ ጋሬጣዎች፣ ማበቡና መንሰራፋቱ የሚረብሻቸው አጥሮች… እግር በእግር ይከተሉታል፡፡… እነሆ “ቀዝቃዛ ሳንሱርም” የስጋት ምንጭ ከመሆን ገና አልተገታም፡፡   
መልካም ሰንበት!





Read 3098 times