Saturday, 20 February 2016 09:19

አቃቤ ህግ የፖለቲካ አመራሮቹ ላይ ከብሔራዊ ደህንነት የሰነድ ማስረጃ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

      ከእስር እንዲለቀቁ በተባሉት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ላይ አቃቤ ህግ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ያመጣውን የሰነድ ማስረጃ ረቡዕ እለት ያቀረበ ሲሆን 367 ገፆች ያሉት የሰነድ ማስረጃ ላይ ተከሳሾች መልስ እንዲሰጡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
ከእስር ይለቀቁ ከተባሉት ተከሳሾች መካከል የአንድነት ፓርቲ የቀድሞ አቶ ሃብታሙ አያሌውና መምህር አብርሃም ሰለሞን ማክሰኞ እለት የተለቀቁ ሲሆን የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲ አመራሮቹ አቶ የሸዋሽ አሰፋ፣ አቶ ዳንዴል ሺበሺና አቶ አብርሃ ደስታ ቀደም ሲል ፍ/ቤት በመድፈር የተላለፈባቸውን ከ14 እስከ 16 ወራት እስራት ታሳቢ ተደርጎ እስካሁን አለመለቀቃቸው ታውቋል፡፡ ሶስቱ ተከሳሾች በማረሚያ ቤቱ በደል ደርሶብናል ሲሉ ለጠቅላይ ፍ/ቤቱ ያመለከቱትን አቤቱታ ከቀረበባቸው ክስ ነፃ ሆነው ከእስር እንዲለቀቁ ብይን የሰጠው የከፍተኛው ፍ/ቤት ነው ወይስ በአቃቤ ህግ ይግባኝ መሰረት ጉዳያቸውን እየተመለከተ ያለው ጠቅላይ ፍ/ቤት ነው የሚለውን መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠትም ፍ/ቤቱ በእለቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በሌላ በኩል አቶ ዳንኤል ሺበሺ ህክምና እንዳያገኙ መደረጉን፣ ጠበቃቸው ለፍ/ቤቱ ያመለከቱ ሲሆን ቤተሰቦቻቸው ከአርባ ምንጭ አዲስ አበባ ድረስ መጥተው እንዳይጠይቋቸው በመደረጉ ሳያገኟቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ፍ/ቤቱ በአቃቤ ህግ ለቀረበው የሰነድ ማስረጃ፣ ተከሳሾቹ ምላሽ ይዘው እንዲቀርቡና ከላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለየካቲት 18 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Read 3315 times