Saturday, 20 February 2016 09:21

ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ጀኔሬተር ሊገዛ ነው

Written by 
Rate this item
(16 votes)

ሠኞ እለት አንድ ሰው በባቡር አደጋ ህይወቱ አልፏል የኢትዮ - ጅቡቲ መስመርን ሁለቱ ሃገራት በጋራ ያስተዳድራሉ  

    በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ እያጋጠመ ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ለመቋቋም ጀነሬተር ሊገዛ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ባቡሩ ባለፈው ሠኞ ሥራ ከጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በደረሰ አደጋ የአንድ ሠው ህይወት ጠፍቷል፡፡
የጀነሬተር ግዢውን ለማከናወን የምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በጋራ አጥተነው ወደ ሂደት እየተገባ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ የኮሚኒኬሽን ኃላፊ ገልፀዋል፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎቱ ዋነኛ ችግር የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፤ የሚገዙት ጀነሬተሮች መብራት እንደጠፋ ወዲያው የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ ትራንስፖርቱ ሳይቋረጥ ያለ እንከን አገልግሎቱን ለመስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡
የከተማዋ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ከጀመረ ወዲህ አንድም አደጋ ደርሶ እንደማያውቅ የጠቀሱት ኃላፊው፤ ባለፈው ሠኞ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ በኡራኤልና መገናኛ መሃል ባለው መስመር አጥሩን በመዝለል ቀጥታ የባቡሩ መስመር ላይ የገባ ግለሰብ ህይወቱ ማለፉን  ገልፀዋል፡፡ ግለሰቡ የአዕምሮ ህመምተኛ ሳይሆን እንደማይቀር መጠርጠሩንና በህክምና ለማረጋገት እየተሞከረ እንደሆነ የጠቀሱት ኃላፊው፤ ባቡሩን ማቆም በማይቻልበት ቅርብ ርቀት ላይ የነበረ በመሆኑ ህይወቱን ማትረፍ ሳይቻል መቅረቱን ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡ ባቡሮቹ ጠዋት 12 ሰዓት ስራ ከመጀመራቸው በፊት በየቀኑ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ ተሳፋሪ ሳይጭኑ ሙከራ እንደሚያደርጉና አጠቃላይ የቴክኒክ ፍተሻ ተደርጎላቸው የሚጀምሩ በመሆኑና ህብረተሰቡ ለአደጋ ያለው ግንዛቤ እያደገ በመምጣቱ፣ የተፈራውን ያህል አደጋ አለመከሰቱን ተናግረዋል ኃላፊው፡፡
በአሁን ሰዓት ለከተማዋ ትራንስፖርት በሁለቱ መስመሮች 28 ባቡሮች የተመደቡ ሲሆን 10 ባቡሮች በቅርቡ ይጨመራሉ ተብሏል፡፡ አሁን ያሉት በቀን እስከ 120 ሺህ ሰው በማጓጓዝ በቀን እስከ 4 መቶ ሺህ ብር ገቢ እያስገቡ መሆኑንም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ለአካል ጉዳተኞችና ለአቅመ ደካሞች ታስበው በተወሰኑ ባቡር ጣቢያዎች የተዘጋጁ ሊፍቶችና ስካሌተሮች ቀደም ብሎ አገልግሎት እንዲሰጡ በተደረገበት ወቅት በጥንቃቄና በአጠቃቀም ችግር ጉዳት አጋጥሟቸው እንደነበር ያወሱት አቶ ደረጃ፤ ጥገና ከተደረገላቸው በኋላ በዚህ ወር መጨረሻ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ብለዋል፡፡ የወረቀት ቲኬቶች ለመጭበርበር ምቹ መሆናቸውን የጠቀሱት ሃላፊው፤ የኤሌክትሮኒክስ ቲኬት አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ ቲኬቶቹ በውጭ ሃገር እንዲዘጋጁ መታዘዙንና የሂሳብ መሙያ ማሽኖች ተከላ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ በቅርቡ አገልግሎቱ ይጀምራል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ሲጀምር 58 በመቶ ያህሉ የባቡር ሠራተኞች ቻይናውያን፣ 42 በመቶ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ያስታወሱት ኃላፊው፤ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያውያኑ በረዳትነት በስፋት ባቡሩን እየዘወሩ መሆኑንና ከ3 ዓት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ከቻይናውያኑ እንደሚረከቡ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
የድርጅቱ ባለሙያዎች ተቋሙ ያለውን አቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ ደሞዝ እንደሚከፈላቸውና ጥቅማ ጥቅም እንደሚያገኙ የጠቀሱት አቶ ደረጀ፤ በቃሊቲና በሃያት የባቡር ማሳደሪያዎች አካባቢ የመኖሪያ ቤት እንደተሰጣቸውና የምግብ አገልግሎት እንዲያገኙም ተደርጓል ብለዋል፡፡   
የአዲስ አበባ - ጅቡቲ የባቡር መስመርን የስራ ክንውን በተመለከተ የተጠየቁት ኃላፊው፤ አጠቃላይ ስራው ከ90 በመቶ በላይ መጠናቀቁን፣ በአሁን ሰዓት የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና ከባቡር ጣቢያዎች ወደ ዋና አውራ ጎዳናዎች የሚያደርሱ መንገዶች እየተገነቡ መሆኑን በመጥቀስ ባቡሩ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ከተባለው ጊዜ የዘገየ ቢሆንም በዚህ ሰዓት ሙሉ ለሙሉ ሰራ ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡ አንገብጋቢ ለሆነው የድርቁ ችግር ሲባል ይፋዊ የሙከራ ስራ አለመጀመሩን ያወሱት አቶ ደረጀ፤ ከህዳር 11 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ለ14 ጊዜ ያህል በዲዝል በሚሰሩ ባቡሮች የእርዳታ ስንዴ እስከ አዳማ ድረስ መጓጓዙን አስታውቀዋል፡፡
ባቡሩን ሥራ ለማስጀመር የጅቡቲና የኢትዮጵያ መንግስታት ስምምነት እንደሚያስፈልግ ያወሱት አቶ ደረጀ፤ የባቡር አገልግሎቱን የሚያስተዳድር ኩባንያ ለማቋቋምና የማናጅመንት ኮንትራት ለመስጠት በሁለቱ ሃገራት መካከል ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር የሁለቱ ሃገራት የጋራ ንብረት መሆኑንና የትርፍ ክፍፍልንና የእዳ አከፋፈልን በተመለከተም ሀገራቱ እየተወያዩ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ለወደፊት በመስመሩ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችም ከሁለቱ ሃገሮች የተውጣጡ ይሆናሉ ተብሏል፡፡

Read 11110 times