Saturday, 20 February 2016 09:35

“ጎንደር የህልሜ ከተማ ናት”

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(6 votes)

     “አንዳንድ በህይወታችን የሚያጋጥመን አስገራሚ ነገር አለ፡፡ ለሰው ብንነግረው አያምነንም፡፡ ልቦለድ አስመስለን ብንናገረው ደሞ “ኢ-ተአማኒ ነው አይታመንም” ይላል፡፡ ፈጣሪ ግን አያልቅበትምና ኢ-ተአማኒ የምንለውን እሱ በህይወታችን እንዲደርስ አድርጎ ያሳየናል፡፡”
ይሄን ያለው ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ነው፡፡ “መይሳው ካሳን ፍለጋ” በተሰኘ መጣጥፉ መግቢያ ላይ፡፡ እውነትነት አለው፤ የህይወት ምስጢርነት ከሰው ልጅ አምክኑያዊ መረዳት በላይ የሚሆንበት ጊዜ ጥቂት አይደለም፡፡ በሌላ ሰው ቀርቶ በራሳችን ላይ የደረሰን ትንግርታዊ ሁነት ፍቺ ስለምናጣለት ለታዛቢ መንገር ይቅርና እራሳችን አምነን ለመቀበል ሲያዳግተን ያታያል፡፡ ስብሐት እንዳለው፤ “ፈጣሪ ግን አያልቅበትምና ኢ-ተአማኒ የምንለውን እሱ በህይወታችን እንዲደርስ አድርጎ ያሳየናል፡፡”
በእኔ ህይወት የደረሰውን (ባታምኑትም) ልንገራችሁ … ከአስራ ሁለት ወይም ከአሥራ ሦስት ዓመቴ ጀምሮ አንድ አስጨናቂ ህልም በተደጋጋሚ አይ ነበር፡፡ ህልሙ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ይጎበኘኛል፡፡ ከህልሙ ላይ የሚቀነስ ወይም የሚጨመር አንዳች ነገር አልነበረም፡፡ ህልሙን እንዳደኩበት መንደር አጥርቼ አውቀዋለሁ፡፡ ሂደቱ ስለማይዛነፍ ቀጥሎ የሚሆነውን አውቀዋለሁ፡፡ ህልሙ በውሃ ድምፅ የታጀበ ነው፡፡ ውሃው ሰው ሰራሽ ፏፏቴ ሆኖ የፏፏቴውን ግራና ቀኝ ይዘው የተገነቡ መንትያ ደረጃዎች አሉ፡፡ ደረጃዎቹ ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ያለውን ሰባ ደረጃ ይመስላሉ፡፡ እኔ የሚያሳድደኝን ላሳውቅ በፍርሃት የድንጋይ መወጣጫዎቹን፡፡ እንደ እባብ በደረቴ እየተሳብኩ ለመውጣት እጣጣራለሁ፡፡ አይሆንልኝም፡፡ ደረጃዎቹ አልጌ እንደጠገቡ ሁሉ እያሟለጩ ይከዱኛል፡፡ እፍጨረጨራለሁ የፏፏቴው ውኃ እየተፈነጣጠረ በድምፁና በጤዛው ያጅቡኛል፡፡ … ይሄንን ህልም ቢያንስ ለሃያ ዓመታት አይቼዋለሁ፡፡ በሣምንት አንዴ እንዳየሁት ቢሰላ እንኳን ከአንድ ሺህ ሰማኒያ ጊዜ በላይ ተመላልሼበታለሁ፡፡ ፈጣሪ ካላጣው ህልም ስለምን በህልም ድግግሞሽ ያሰክረኛል? ስል ጠይቄአሁ፡፡ ፍቺ ለማግኘትም ደክሜያለሁ፡፡ ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ያሉትን የድንጋይ ደረጃዎች መርምሬአለሁ፡፡ አንዳቸውም ከህልሜ መወጣጫዎች ጋር አልገጠሙልኝም፡፡ ምንድነው? ለምንድነው? ፍቺ አለው? … ምንም!
ጋዜጠኛ ሆኜ ለመጀመሪያ ጊዜ የተወለድኩበትን አዲስ አበባ አልፌ የተለያዩ አካባቢዎች መሄድ ጀመርኩ፡፡ ድሬደዋ፣ ጋምቤላ፣ ሰመራ፣ አዋሳ፣ ዲላ፣ ደሴ፣ ባህርዳር፣ ጎንደር፡፡ ህልሜን ጎንደር አገኘሁት፡፡ አገር ለማየት ስዘዋወር ፒያሣ አካባቢ ከሃያ ዓመታት በላይ እየደጋገምኩ የዳሁበትን መንታ የድንጋይ መወጣጫና ፏፏቴ እዚያ አገኘሁት፡፡ ድንጋጤ ምንድነው? ከተወለድኩ አንስቶ ከአዲስ አበባ ወጥቼ አላውቅም፡፡ የድንጋይ ላይ ጌጡን፣ የፏፏቴ ቁመናውን ሁሉ አጥርቼ የማየው ይሄ ህልሜ እንዴት ውስጤ ገባ? አሁንም ምስጢር ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ያንን የጎንደር መንትያ ደረጃ ካየሁ በኋላ ህልሜ፣ ለአንዴ እንኳን ብቅ ሳይል መጥፋቱ ነው፡፡ ህልሜ ተልዕኮውን ፈፀመ? ወይስ ምን? …
… ባለፈው አርብ ወደ ጎንደር ሄጄ እዚያ የህልሜ ሰገነት ፊት ቆምኩ፡፡ ከበስተኋላዬ አዲሱ የአፄ ቴዎድሮስ ሀውልትና ቋራ ሆቴል አሉ፡፡ ፊት ለፊቴ ሁለቱ መወጣጫ የድንጋይ ደረጃዎች መካከላቸው ላይ መናፈሻ ተገንብቷል፡፡ ጋሽ አበራ ሞላ ነው አሉ እንዲህ ያደረገው፡፡ መናፈሻው “ሰማዕታት” ተብሏል፡፡ የህልሜ አንዱ አካል ፏፏቴው ተነስቷል፡፡
ጎንደር የህልሜ ከተማ ናት፤ ምናልባትም ከልደት በፊት-በፊት የማውቃት፤ ለአንዱ ጀግና አድሬ የተዘዋወርኩባት፣ ወይም በክፋት ያስጨነኩባት … ከመረገዜ በፊት የሞትኩባት፤ ከመወለዴ አስቀድሞ አፈር የቀመስኩባት፡፡ የእኔ የልጅ ልጆች እዚያ አሉ፣ አሁን ጓደኞቼ የሚሆኑ፣ የያኔውን ፎቶዬን ሙጥኝ፣ ያሉ፡፡ ቀብሬን የሚጎበኙ … ነፍሴ የገባት አንዳች ነገር አለ፤ ለሰው ቢያወጉት እንግዳ የሆነ፡፡ ሥጋዬ የተኛ ነው፤ ነፍሴ ቢጓጉጠው - ቢጓጉጠው ሩሁን ያላገኘው፡፡ አሁን ይሄ ለሰው የሚነገር ነው? ያውም ቁስ ለናጠጠበት ለዚህ ዘመን ሰው? … እንደ ስብሐት “አንዳንድ በህይወታችን የሚያጋጥመን አስገራሚ ነገር አለ” ብለን እንቀጥል …
ከክርስቶስ ልደት 570 ዓመታት በፊት የኖረው ጲፃጎራስ (Pythagoras) ነፍስን በጊዜአዊ አካል ውስጥ የምትኖር ሕያውት አድርጎ የሚመለከትበት እምነት ነበረው፡፡ ነፍስ አንዱን የዘር ሐረግ ለቅቃ ሌላውን እየተንጠላጠለች … አንዱ ጊዜአዊ ቤት (አካል) ሲፈርስ፣ ሌላ አዲስ ቤት ውስጥ እየገባች ዘላለማዊነቷን ትቀጥላለች ይላል፡፡ “የሥጋ ቤት” መልቀቁና መከራየቱ በሰውና በእንስሳት መካከል ለመከናወን የሚያግደው ነገር እንደሌለ ይሄው የጥንት ፈላስፋ ያስተምራል፡፡ በቀለ ተገኘ መኮንን “የምዕራባውያን ፍልስፍናና ሥልጣኔ ታሪክ (፩)”  በተሰኘ መፅሐፋቸው ስለ ጲፃጎራስ እምነት እንዲህ ይላሉ፡-
“… ጲፃጎራስ ለማስጨበጥ የሞከረው እምነት ይህን መሳይ ነበረ፡- ከሁሉ አስቀድሞ ነፍስ ለዘለዓለም ኢመዋቲት (ሕያውት) ነገር መሆንዋንና ከአንድ አይነት ፍጥረት ወደ ሌላ እንደምትጋባ፣ ከዚሁም ተያይዞ ማንኛውም ሕያው ፍጥረት መተካኪያ ጊዜውን እየጠበቀ እንደገና በመውለድ ከህልውና ህልውና ሲሸጋገር ይኖራል እንጂ ፈፅሞ ሌላ አዲስ ነገር እንደማይመጣ፤ ማንኛውም ህያው ፍጥረት ሁሉ ከሌላው ጋር እንደ ቤተ ዘመድ - ወይም እንደ አንድ አምሳልና አካል መተያየት እንደአለበት ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ አይነቱ የተነሣ ጲፃጎራስ ቅዱስ ፍራንሲስ ዘአሲስ ያደርግ እንደነበረው ዐይነት በእንስሳቱ  መሀል በየጊዜው እየተገኘ መንፈሣዊ ቃሉን ያሰማቸው ነበር ይላል፡፡”
ይሄን የነፍስ ከሥጋ ወደ ሥጋ መንጦልጦል ሕንዶች “ሳም ሳራ” (Samsara) ሲሉት ምዕራባውያን ደግሞ ሜተምሳይኮስስ (metempsychosis) ወይም ዳግም ልደት (reincarnation) በሚል ሰይመውታል፡፡ በዚህ አዙሪት የተጠመደችው ነፍስ፤ አልፎ አልፎ በትውስታ ካለፈ ህይወቷ የምትጎትታቸው ሁነቶች እንዳለ እነ ጲፃጎራስ ይናገራሉ፡፡
እናስ?
… የፒያሣው መንትያ የድንጋይ መወጣጫ፣ ያለፈው ሕይወቴ ቃርሚያ ትዝታ ይሆን? ከሆነስ ያንን ደረጃ ብቻ ምን ሙጥኝ አሰኘኝ? … የልሜን አጋዥ የትውስታ ፍርፋሪ ባገኝ ብዬ ከተማዋን ለማሰስ ተነሳሁ፡፡ አጠገቤ የ “ትንሳኤ ናፋቂዎች” ደራሲ ተስፋ በላይነህ አለ፡፡ የጎንደር ልጅ ነው፡፡ ከአርበኞች አደባባይ ጀርባ “ከቡልኮ” ተነስተን በቀድሞ ልዕልት ተናኘወርቅ፣ በአሁኑ ህብረት ትምህርት ቤት በኩል ቁልቁል ወረድን፡፡ ከፎገራ ሆቴል በስተግራ የአንገረብ ወንዝን ታክከን ወደ ደብረ ብርሃን ሥላሴ አቀናን፡፡ የነፍሴን ትውስታ የሚያግዝ አንዳች ነገር አላገኘሁም፡፡ ደብሩ ጥንታዊ አሰራሩ ያስደምማል፡፡ ቅፅሩ በምስጢራዊ የዋርዲያ ማማ የተከበበ ነው፡፡ መወጣጫው የድንጋይ ሆኖ ከሩቅ ለመቃኘት እንዲያስችል ከፍ ተደርጎ ተገንብቷል፡፡ ያንን ነፍሴ አላወቀችውም፡፡ ከቅፅሩ ወደ ቤተክርስቲያኑ ማተርኩ፡፡ በጥንታዊ ስዕላት አሸብርቋል፡፡ ቅድስት ድንግል ማሪያም የአንገት ላይ የንቅሳት ውቅሯ እንዳማረ ሆኖ፣ ፊት ለፊት ትታያለች፡፡
 ነፍሴን ፈተሽኩ፣ ሽራፊ ትውስታ አጣሁ፡፡ የተመለስነው በባጃጅ ነው፡፡ ጎንደር በባጃጅ “ዝንብ” ተወርራለች፡፡ ጥዝዝዝዝ … የሚሉት የመሬት ለመሬት ዝንቦች የጎንደርን ግርማ ይፃረራሉ፡፡
 እንደተግለብላቢ መጤ ከተማ ሞተር በተገጠመለት ዝንብ መወረሯ ያስቆጫል፡፡ ጎንደር ጭራ ያሻታል፡፡ ጥዝዝዝ - ጧ! በምትኩ ቁመናው ባማረ ፈረስ የሚጎተት ሰረገላ ይበዛላታል፡፡ ጎንደር የጥሞና ከተማ ናት፡፡ ተንጦዝጧዥ ነገር ሁሉ ይፃረራታል፡፡
ነፍሱን ይማርና ፋሲል ሆቴል የነበረበት ጋ ስንደርስ ከባጃጅ ወረድን፡፡ “ላቭ ስትሪት” መጤ ድርጊያና ቃሉን ከጥንታዊው “ቆብ አስጥል” ጋር በጉራማይሌ አዋህዶ አየነው፡፡ የራስ ሚካኤል ስሁልን ህንፃ ቃኝተን በ“ሰማዕታት” መናፈሻ አናት ብቅ አልን፡፡
በህልሜ ሃያ ዓመት የዳህኩበትን የድንጋይ ደረጃ በእግሬ ቁልቁል ወረድኩበት፡፡ ምን አዛመደን? ምን አገናኘን? ምን አቆራኘን? … “ፈጣሪ ግን አያልቅበትምና ኢ-ተአማኒ የምንለውን እሱ በህይወታችን እንዲደርስ አድርጎ ያሳየናል” ከማለት ውጭ ምን መተማመኛ አለን?

Read 3480 times