Saturday, 20 February 2016 09:47

በደብዳቤና በዘፈን የታጀበ ፍቅር

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

“እስካሁን 41 ዘፈኖችን ዘፍኜላታለሁ”

ለየት ያሉ ጥንዶች ናቸው፡፡ የፍቅር ታሪካቸውም ለየት ያለና አስደማሚ ነው፡፡ ከጅምሩ አንስቶ በደብዳቤና በዘፈን የታጀበ ፍቅር ነው፡፡ አቶ ተስፋዬ ድረሴና ወ/ሮ ሮማን ቱፋን ያገኘዋኋቸው  ባለፈው እሁድ በዋሽንግተን ሆቴል የፍቅረኛሞች ምሽት ላይ ነበር፡፡ ለጥንዶቹ በፍቅረኞች በዓል ላይ መታደም አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት እንደውም ወ/ሮ ሮማን የኢቶፒካሊንክ የጥያቄ ውድድር አሸንፈው የፍቅረኞች ምሽት ከእነ አልጋው በመጋበዛቸው፣ጥንዶቹ ሌሊቱን ከቤት ውጭ ነበር ያሳለፉት፡፡ ዘንድሮ ደግሞ በዋሽንግተን ሆቴል ተጋብዘው አስገራሚ የፍቅር ታሪካቸውን ለታዳሚው አጋርተዋል፡፡  በሶስዮሎጂ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ያገኙት አቶ ተስፋዬ፤ ሁለት የግጥም መድበሎችም አሳትመዋል፡፡ ከባለቤታቸው ጋር ከተገናኙበት ጊዜ አንስቶ 41 ዘፈኖችን ዘፍኜላታለሁ ይላሉ፡፡ በቅርቡ አልበም የማውጣት ዕቅድ እንዳላቸውም ነግረውኛል፡፡ ጥንዶቹ ሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት ልጅ አፍርተዋል፡፡ ፍቅራቸው ግን ከእነአጀቡ ቀጥሏል፡፡ እነሆ አስደማሚ የፍቅር ታሪካቸው፡-


መቼ ነው የፍቅረኛሞች ቀንን ማክበር የጀመራችሁት?
እኛ ሁሌም የፍቅረኛሞችን ቀን እናከብራለን፡፡ በቤተሰባችን ውስጥ ከሚከበሩ እንደ እናቶች ቀን፣ የአባቶች ቀን፣ የልጆች ቀን ሁሉ --- የፍቅረኛሞች ቀንንም እናከብራለን፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመትም ባለቤቴ በኢቶፒካሊንክ የጥያቄ ውድድር ላይ ተሳትፋ በማሸነፏ፣ የፍቅረኞች በዓል ዝግጅት ላይ ተገኝተን ነበር፡፡ ግብዣው አልጋንም ይጨምር ስለነበር ውጭ አድረናል፤ ዘንድሮም ተጋብዘን ነው የመጣነው፡፡
መድረክ ላይ ወጥታችሁ የፍቅር ታሪካችሁን ስትናገሩ እርስዎ ካገባኋት 31 ዓመት ተኩል ነው ይላሉ፡፡ ባለቤትዎ ወ/ሮ ሮማን ደግሞ ከተጋባን 25 ዓመታችን ነው ይላሉ፡፡ ጉዳዩ ምንድነው?
ሁለታችንም የምንለው ይሄንኑ ነው፡፡ እኔ ገና ያየኋት ቀን፣ “በቃ ሚስቴ ነሽ፤ ከዛሬ ጀምሮ አግብቼሻለሁ” አልኳት፤“ወላ ፍቅረኛ ይኑርሽ፤ በውስጥሽ የምታልሚውም ሰው ይኑር፤ በቃ ከዛሬ ጀምሮ ሚስቴ ነሽ” አልኳት፡፡ ግራ ገባት፤ ብልጣ ብልጥና አጭበርባሪም መስያት ነበር፡፡ እኔ ግን ከዚያን ቀን ጀምሮ አካሄዴ፣ አስተሳሰቤና ሁሉ ነገሬ እንደ ባልና እንደ ባለትዳር ሆነ፡፡ እኔ ጋብቻዬን የምቆጥረው ይሄን ነገር ከነገርኳት ቀን ጀምሮ ነው፡፡ እሷ ደግሞ በሰርግ ከተጋባንበት፣ ከተፈራረምንበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡
 ሁለታችሁም በየፊናችሁ ነው ማለት ነው የጋብቻ በዓላችሁን የምታከብሩት?
አዎ እኔም 31 ዓመት ነው ብዬ አመንኩኝ፤እሷ ደግሞ የለም እኔ ከተፈራረምኩበትና ከተሰረገበት ቀን ጀምሮ ነው የምቆጥረው አለች፤ ተስማምተን በየፊናችን ስናከብር አንዳችን አንዳችንን እንግዳ አድርገን እንጋብዛለን፤በዚህም ደስተኞች ነን፡፡
 እስኪ ስለ ትውውቃችሁ ያጫውቱን ------
የተዋወቅነው ፍቼ ተሀድሶ ፕሮግራም የሚባል ካምፕ ውስጥ ነው፤ፍቼ፡፡ ተሀድሶ ፕሮግራሙ ሥራ አጦችንና ጎዳና ተዳዳሪዎችን አሰልጥኖ፣ አምራች ዜጎች የሚያደርግ ነው፡፡ ወቅቱ 1976 ዓ.ም ነበር፡፡ የአንድ ዓመት ፕሮጀክት ሲሆን በሶስት ዙር የሚጠናቀቅ ነበር፡፡ የተገናኘነው በመጀመሪያው ዙር ነው፡፡ እኔ የማህበራዊ አገልግሎት ሰራተኛ ሆኜ ስሄድ፣ እሷ 12ኛ ክፍል ተፈትና ውጤት እስኪመጣ ድረስ ቤተሰቦቿ ፍቼ ስለነበሩ ክረምቱን ለምን አልሰራም ብላ ስትወዳደር አለፈችና መጣች፤ እዚያ ነው የተገናኘነው፡፡ ፕሮጀክቱ በሶስት ወር ተዘጋ፡፡ በነገራችን ላይ በወቅቱ ስራ አጦችና በየጎዳናው ላይ የነበሩት ሰዎች ተሰብስበው ወደ ማሰልጠኛው የገቡት 10ኛውን የአብዮት በዓል ለማክበር ሽር ጉድ ይባል በነበረ ጊዜ  የከተማዋን ገፅታ ለመጠበቅና እዛም እዚህም እንዳይታዩ ታስቦ ነው፡፡ ሐምሌ ገብተን መስከረም ላይ ሰልጣኞቹ ወደየእርሻ ጣቢያው ሄዱ፤ እኔም ሄድኩኝ፡፡ እኔ ከሀዋሳ ነበር የሄድኩት፤አዲስ አበባ ለመግባት ጉጉት ስለነበረኝ በፍቃደኝነት የሰለጠኑትን ሰዎች ይዤ ወደ ሻይ ተክል ሄድኩኝ፡፡ በሪፖርቱ መነሻነት አዲስ አበባ የመግባት እድል ነበረኝ፡፡ ከዚያ አሪፉ ታሪክ ምን መሰለሽ? ከእርሷ ጋር ሳንገናኝ ግን ደብዳቤ ልንፃፃፍና ደብዳቤው ላይላክ ተስማምተን ነው የተለያየነው፡፡
እንዴት ማለት---?
እሷም ባለችበት ደብዳቤ እንደ ዲያሪ እየፃፈች ልትቀጥል፣ እኔም እንደዚያው እያደረግሁ ቆይቼ ከዘመቻው ስመለስ ደብዳቤዎቻችንን ልንቀያየር ነበር ስምምነታችን፡፡ ከዚያ በፊት ካምፕ እያለን በየቀኑ የምንፅፈውን እየተለዋወጥን እንናበብ ነበር፡፡ እኔ ወደ እርሻ ሰልጣኞች ስሄድ ግን ተለያየን፤ያኔ ዲያሪ መፃፉ እንዲቀጥልና ስንገናኝ የተጠራቀመውን ተቀብለን ልናነብ ነበር ስምምነታችን፡፡ ዲያሪያችንን ስም ሰይመንለት “ጌጥ” እንለዋለን፡፡ እኔም ጉመሮ፣ ውሽውሽና በበቃ ሻይ ቅጠሎች የሚመረቱበት ሄጄ ስመጣ እሰጣታለሁ ብዬ ነበር አልሆነም፡፡
ምን ተፈጠረ -----?
ከሄድኩ በኋላ እዛ የሻይ ቅጠል እርሻ አድርሰውን የመጡት ሹፌሮች ሲመለሱ፣ ከፍቼ እዛ እስክደርስ የፃፍኩትን 25 ገፅ ደብዳቤ ላኩላት፡፡ የአንድ ወር ፕሮጀክት ነበር፤ ወደ ሁለት ወር ተራዘመና እዚያው ቆየሁ፡፡ ከዚያ ደግሞ ሰልጣኞቹን ሊገመግሙ ኃላፊዎች ወደ እርሻው ሲመጡ እስከዚያን ቀን ድረስ የተፃፉ ደብዳቤዎችንና አንድ ካሴት ላኩላት፤ካሴቱ ዘፈን የተቀረፀበት ነበር፡፡ ዘፈኑን ቀድቼ ላኩላት፡፡ ከእርሷ በኩል አንድም የተላከልኝ ደብዳቤ አልነበረም፤ለምን? የሚመጣ ሰው አላገኘችም፡፡ ከዚያ ወደ አዲስ አበባ ሪፖርት ላደርግ ስመጣ ፍቼ ጎራ አልኩኝ፤ ተገናኘን ምክንያቱም አማች ነኝና፡፡ ከዚያ ስመጣ 68 ገፅ ደብዳቤ በስኩየር ሉክ ፅፌላት ነበር፡፡
ከዚያ በፊት ቤተሰቦቿ ቤት ገብተው ያውቃሉ እንዴ?
እንዴታ! የሚገርምሽ አግብቼሻለሁ ያልኳት ቀን ቤተሰቦቿ ቤት ሄጃለሁ፡፡ ኧረ ምን ልትል ነው እያለች ስትፈራ፣ የወንድ ጓደኛዋ ነኝ እላለሁ ብዬ አብሬያት ሄድኩኝ፡፡ እዚህ ፕሮጀክት የተዋወቅኳት ጓደኛዋ ነኝ፤ አልኩና ሄድኩኝ፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ በተለይ ከዳኛው አባቷ ጋር ጓደኛሞች ሆንን እልሻለሁ፡፡
መጀመሪያ ወደሷ እንዲሄዱ አዝማች ነበረዎት የሚባል ነገር ሰምቻለሁ -----
በደንብ አዝማች ነበረኝ፡፡ አዝማች ተካ ጣሴ ይባላል፡፡ ተካ የኔ ጓደኛ ነው፡፡ ሶስዮሎጂስት ነው፡፡ እኔ ቁጭ ብዬ እፅፋለሁ፤ እሱ ወደኔ መጣና “አንዲት ቆንጂት መጥታ ህዝቡ ይተራመሳል÷ አንተ እዚህ ቁጭ ብለህ ትሞነጫጭራለህ?” አለኝ፡፡ እዛ ያለው ጎረምሳ ሁሉ ይረባረባል አልኩሽ፤ተካ ደግሞ “ሂድ አንተ ስማርት ስለሆንክ ታሸንፋቸዋለህ” አለኝ፡፡ እኔ የሄድኩት እነሱን ለማሸነፍ ነው፤ግን ልክ ሳያትና አይኗን ክድን አድርጋ ስትገልጠው መሽቶ የነጋ ነው የመሰለኝ፡፡ በጣም ደነገጥኩኝ፡፡ ያኔ ነው “ከዛሬ ጀምሮ አግብቼሻለሁ” ያልኳት፡፡ እሷም እሺም እምቢም የለ ዝም ብላ ስታጠናኝ ኖረች፡፡ ትምህርቴን ሳልጨርስ የወንድ ጓደኛ አልይዝም  አለች፤እኔም ሀሳቧን አልተጋፋሁም፤ እንደውም ክራር እየተጫወትኩ፣ ዘፈን እያንጐራጐርኩ፣ ግጥም እየፃፍኩ ማላመድ ቀጠልኩኝ፡፡ እሷም ሚስቴ ነሽ ብዬ በአንዴ አገባሁሽ ስላት የነበራት ጥርጣሬና መጥፎ አመለካከት እየተቀየረ መጣ፡፡ በቃ ለማዳ አደረግኋት፡፡ ይሄው ለዚህ በቃን፤ የሁለት ወንዶችና የአንዲት ሴት ልጅ ወላጆች ሆነናል፡፡ የመጀመሪያ ልጃችን 24 ዓመቱ ነው፤ በኮምፒዩተር ሳይንስ ድግሪውን ይዟል፡፡ በጣም ተፅዕኖ የፈጠረብኝ አስተዋይና ምርጥ ልጄ ነው፡፡ ሁለተኛውም ጥሩና ደስተኛ ልጅ ነው፡፡ ሶስተኛዋ የ14 ዓመትና የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ በግልጽነትና በፍቅር አጥለቅልቀን ነው ያሳደግናቸው፡፡
ወደ ኋላ ልመልስዎትና አግብቼሻለሁ ያሏት ቀን ወዲያው አንድ ግጥም ጽፈው ሰጥተዋት ነበር፡፡ ግጥሙ ምን ነበር የሚለው?  
ሮጦ ሁሉም መጣ ወዳንቺ ከነፈ
 ማን ቢልከው ይሆን እንዲህ የተጣደፈ
 ንገሪኝ ልወቀው ልቤ ተንሳፈፈ---- ይላል፡፡
የስንኞቹ የመጀመሪያ ቃላት ወደ ታች ሲነበቡ ሮማን ይላል፡፡ ያን ጊዜ እንደዚህ መፃፍ ፋሽን ነበረ፡፡ የዛሬ 30 ዓመት ተኩል ነው የተፃፈው፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ግጥምና ዘፈን አልተቋረጠም፡፡ ስምንት ጊዜ ከፃፍኩላት በኋላ በስንት መከራ ፃፈችልኝ፡፡ “ጉዳዩ መልስ የሌለው ደብዳቤ ሆነብህ ወይ? ደብዳቤውን ካነበብክ በኋላ ያለህን ጊዜ ጠቁመኝ” ይላል፡፡ ኧረረረ አልኩና እኔም ቀጠልኩበት፡፡ ያለ የሌለ ተሰጥኦዬን ተጠቅሜ ለእሷ የተቀኘሁትን ---- በግጥም፣ በሙዚቃ ብቀኝ ኖሮ ኦስካር፣ ግራሚ፣ ኖቤልና ሌሎች ሽልማቶች እቀዳጅ ነበር፡፡ ግን እሷ ከሁሉም ትበልጣለች፤ አይገርምም!!
ባለፈው ጥር ወር 25ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላችሁን ባለቤትዎ አዘጋጅታ፣ሰርፕራይዝ አድርጋዎታለች ይባላል
የጋብቻችንን 25ኛ ዓመት በዓል እንደምታዘጋጅ ነግራኝ ነበር፤ግን ብዙ ነገር አዲስ ሆነብኝ፡፡ ለምሳሌ ቬሎ እንደምትለብስ አላውቅም ነበር፡፡ በራስ ሆቴል ነው ያከበርነው፤እንግዳ አድርጋ ጠርታኝ፡፡ ልብስ ለመግዛት ስዘጋጅ፣በተር ፍላይ እንዳትረሳ ትለኝ ነበር፤ለካ ቬሎ ስለምትለብስ  እኔም በተር ፍላይ እንዳደርግ አስባ ነው፡፡ ማመን አቃተኝ፤ ብዙ እንግዶች ነበሩ፤ሳያት ልወድቅ ምንም አልቀረኝ፡፡ ከዚያ በኋላ እንደ አዲስ ሰርግ መልስ ሁሉ ስንጠራ ነበር፡፡ ብቻ በቃላት ተዘርዝሮ አያልቅም፤ በጣም ጥሩ ህይወት ያለኝ እድለኛ ሰው ነኝ፡፡
41 ዘፈኖችን ለባለቤትዎ ዘፍነውላታል፡፡ የፍቅረኞች ቀን በዓል ላይም በዋሽንግተን ሆቴል “አብረን እንጨርጭስ; የሚለውን አቀንቅነዋል፡፡ እስኪ ስለሱ ዘፈን ይንገሩኝ?
አዎ እኔ ከግጥም ጋር በተያያዘ ብዙ ታሪክ አለኝ፡፡ አርባ አንድ ዘፈኖችን ለሚስቴ ሰርቼ ሰጥቻታለሁ፡፡ ለተለያዩ ዘፋኞችም ግጥምና ዜማ እሰራለሁ፡፡ አሁን እንደውም በደንብ ስቱዲዮ ገብቼ፣ አልበም ሰርቼ ለገበያ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ነኝ፡፡ የቫላንታይንስ ዴይ ላይ የዘፈንኩላትን ዘፈን በእሷ አቆጣጠር በተጋባን በ20ኛ አመታችን፣ በ2003 ዓ.ም ሁለቱን የግጥም መፅሀፌን በብሄራዊ ቴአትር ለማስመረቅ ከፍተኛ ፕሮግራም አድርጋ ነበር፡፡ በርካታ ትልልቅ እንግዶች ተገኝተው ነበር፤ ለምርቃቱ፡፡ እኔ ደግሞ “አብረን እንጨርጭስ” የሚለውን ዘፈን ከዳዊት ፅጌ ባንድ ጋር ሰርቼ ሰርፕራይዝ አደረግኋት፡፡ ግጥሙ በከፊል እንዲህ ይላል፡-
ያሳለፍነው ጊዜ በጣም ረጅም ነው
ፍረጅ የኔን ያህል ያፈቀረሽ ማነው
ሩብ ምዕት ሞላኝ ሳፈቅርሽ የምሬን -----
ታናሼ ብትሆኙም አብረን እናርጅ ባክሽ- ---
ልውደድሽ ውደጂኝ እስክንረሳሳ
ፀጉራችን በእድሜ ደመና ይምሰል ጭስ
በፍቅር እንዳለን አብረን እንጨርጭስ ---
አሁን ይህንን እንዲሁም ከአርባዎቹ ዘፈኖች የተመረጡትንና አዳዲሶቹን ጨምሬ በአልበም እሰራቸዋለሁ ብያለሁ፡፡
ባለቤትዎ ሙያቸው ምንድን ነው? እርሰዎስ?
ባለቤቴ መጀመሪያ ኮሜርስ፤ ከዚያ ማኔጅመንት፤ ቀጥሎ ህግ ተምራለች፡፡ በአሁን ሰዓት በዲዩቲ ፍሪ በኃላፊነት ላይ ናት፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት እየሰራች ነው፡፡፡ እኔም ለ15 ዓመታት ከሰራሁበት ኖርዌይ ህፃናት አድን ድርጀት ወጥቼ፣ ተስፋዬ ድረሴ አድቨርታይዚንግ የተሰኘ የማስታወቂያ ድርጅት ከፍቼ በርካታ ስራዎችን እየሰራሁ ነው፡፡
“የበሬ ውጊያ” የተሰኘ ለህትመት የተዘጋጀ መፅሀፍ እንዳለዎ ነግረውኛል፡፡ በምን ጉዳይ ላይ ያጠነጥናል?
 “የበሬ ውጊያ” የተሰኘው መፅሀፌ፣ የገበሬ ውጊያ ድሮና ዘንድሮ ምን ይመስል ነበር፣ ዘንድሮ በሬ ይዋጋል ወይ? ድሮ ለምን ነበር የሚዋጋው? አሁንስ ለምን ተወ? የሚሉ ሀሳቦችን ከስነ ምህዳር ለውጥ ጋር በማያያዝ፣ ለውጡ የእንስሳትን ህይወትና ባህሪ እንዴት እንደሚቀይረው የሚያስቃኝ ነው፡፡ ፅሁፉን ክብረመንግስት እያለሁ ከብት ስጠብቅ ከነበረበት ትዝታዬ ተነስቼ ነው የፃፍኩት፡፡
 በፎቶ ለማስደገፍ የሚዋጋ በሬ አጥቼ፣መፅሀፉ ሳይታተም ብዙ ጊዜ ቆየ፡፡ ለስራ የተለያዩ መስኮች ስወጣ አልፎ አልፎ የሚዋጉ በሬዎችን ሳይ፣ አንድ ሁለት ፎቶ ሳነሳ አሁን ሞልቶልኛል፤በጣም የምጓጓለት መፅሀፍ ነው፡፡ በየጠጅ ቤቱ፣ በየጠላ ቤቱ እየገባሁ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ሞክሬያለሁ፡፡ ለህትመት ተዘጋጅቷል፡፡ ሌላው እኔ አባትነትና ባልነት የሙሉ ሰዓት ስራዬ ስለሆነ፣ ስለ ባልነት ስለ አባትነት የተሰሩ ጥናቶችን፣ መፅሀፎችን አነባለሁ፡፡ ብዙ መፅሀፍትን አንብቤያለሁ፡፡ እድሜ ከሰጠን ብዙ የተጀመሩ ስራዎችን ለመስራት እቅድ አለኝ፡፡ በስኬቴ ሁሉ ከጎኔ የነበረችዋን ባለቤቱን ሮሚን፣ ልጆቼን፣ ጓደኞቼን፣ የስራ ባልደረቦቼን ሁሉ አመሰግናለሁ፡፡



Read 5838 times