Saturday, 20 February 2016 10:09

“መባ”- የሚያስቆጭ ፊልም!

Written by  ዶ/ር ዳዊት አሰፋ (ሳይካትሪስት፤ የአማኑኤል ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ)
Rate this item
(7 votes)

 መግቢያ
“መባ” በአእምሮ ሕሙማን ዙሪያ የተሰራ ፊልም ነው፡፡ አንድ ሐኪም በአእምሮ ሕመም ተጠቅቶ ቤተሣይዳ ወደተሰኘ የአእምሮ ሕክምና ማእከል ሲገባና ሌሎች ተኝቶ ታካሚዎችን በፍቅር ለመቅረብና ለመንከባከብ ሲሞክር ያሳያል፡፡ በአንፃሩ ዶ/ር ቤዛ የተባለች የማዕከሉ የሣይካትሪ ሐኪም በቁጣና አንዳንዴም በጥፊ የግቢውን ታካሚዎች አንቀጥቅጣ ስታክም/ስትገዛ ያላልኩት ሐኪም ስለተባለች ነው/ ይታያል፡፡ በመጨረሻም ፍቅር ያሸንፋልና ታካሚዎቹ ሁሉ “በፍቅር ድናችኋል” ተብለው መድኃኒታቸውን ጥለው ከማዕከሉ ሲሰናበቱ ፊልሙ ይጠናቀቃል፡፡
ፊልሙ ያቀረበልንን አንኳር ጉዳይ - ፍቅርን - የአብዛኛው ጽሑፌ ማጠንጠኛ አድርጌ የ“መባ” ፊልም ድርሰትና ዝግጅት ምን ያህል ጥናት ተደርጐበታል በሚለው ዙሪያ ደረጃ በደረጃ ለመተንተን እሞክራለሁ፡፡
ፍቅር…ምን አይነት ፍቅር?
ፍቅር አይነቱና መገለጫው ብዙ ነው፡፡ በፍቅር ጉዳይ ላይ ጥናት የሚያደርጉ ምሁራን በጥቅሉ ፍቅርን በሶስት ወይም በአራት ከፍለው ያዩታል፡፡ ጾታዊ መሳሳብን መሠረት አድርጐ ከሚነሳው “ኢሮስ” ከተባለው የፍቅር አይነት ጀምሮ አልፋና ኦሜጋ የሌለው፣ ወገንተኛ ያልሆነ፣ የፍቅሮች ሁሉ አውራ ፍቅር እስከሚባለው “አጋፔ” ድረስ የተዘረጋ የፍቅር መንገድ አለ ብለን ልንወስደው እንችላለን፡፡ እንግዲህ “አጋፔ” መጨረሻ በሌለው ነፃነት ወደ ላይ የሚመጥቅ መንፈሣዊ ይዘትን የተላበሰ ፍቅር መሆኑ ነው፡፡ የ “አጋፔ” ፍቅር መለያው ወዳጅን መውደዱ ላይ ሳይሆን፣ ጠላትንም እንደዚያው መውደድ መቻሉ ላይ ይሆናል፡፡ በመንፈሣዊ ቋንቋ ፈጣሪ ፍጡራንን የሚወድበት አይነት ፍቅር ማለት ነው…ጠላትንም እንደራስ መውደድ፡፡ በዚህ የፍቅር ከፍታ ላይ ለመድረስ ያልቻልን ሰዎች እንዴት ጠላትን እንደ ራስ መውደድ ይቻላል ብለን እንጠይቃለን፡፡ እንደዚህ ያለው ፍቅርስ ከምን ይመነጫል? በመጀመሪያ እንደዚህ ያለውን ፍቅር ለመሸከም የሚችል ልቦና ያስፈልጋል፡፡ ምናልባት “አጋፔ”ን ለመሸከም የሚችል የሥነ ልቦና አቅም የሚፈጠረው ያለቅድመ ሁኔታ ከመፈቀር /በፍቅር ከማደግ/ እና እራስን በጥልቀት ከማወቅ ይመስለኛል፡፡ (የሥነ ልቦና ጠበብቶች ሰልፍ - አክችዋላይዜሽን የሚሉት ከፍታ ላይ በመድረስ)
“ስላፈቀርኳት ገደልኳት”
እንደ ኳስ ያለ ፍፁም ድቡልቡል የሆነን ነገር በየትኛውም አቅጣጫ ብናዞረው ከራሱ በቀር የተለየ ነገር አናይም፡፡ “አጋፔ”ም በማንኛውም አይነት ሁኔታ ውስጥ ያው ፍቅር ነው፡፡ አዟዙረን ብንመለከተው የምናየው ፍቅርን ብቻ ነው፡፡ ከ “አጋፔ” ውጭ ያለው ፍቅር ግን መገለጫው ወገንተኝነቱ ይመስለኛል፡፡ ለምሣሌ በሀገራችን በስልሣዎቹ ውስጥ በሀገር ፍቅር ተቃጠልን ያሉ ወጣቶች በስሜት ግለው የተነሱበት ወቅት ነበር፡፡ መጨረሻው ግን የሚያሳዝን መጠፋፋት ሆነ፡፡ የሀገር ፍቅር እንዴት የእርስ በርስ ጥላቻን ይወልዳል? በልቦናችን ያለው ፍቅር ገደብ የለሽና ንፁህ ሳይሆን ሲቀር አጥር የተበጀለትና በቀላሉ ወደ ጥላቻ የሚሸጋገር ይሆናል፡፡ ያበጀነውን የፍቅር ድንበር በአንድ ጀምበር ተሻግረነው ሌላውን በጥላቻ እንገድላለን፡፡ የወገንተኛ ፍቅር ጣጣው ብዙ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ አይነቱ ፍቅር በጀርባው ጥላቻን አዝሎ ይዞራል፡፡ አዳነን ለመውደድ አብሴን መጥላት አለበት፡፡ በተለምዶ ፍቅር እውር ነው ይባላል፡፡ ይህ አባባል “አጋፔ”ን አይገልፀውም፡፡ በተቃራኒው “አጋፔ” የተበደቀውንም የሚያሳይ ብርሃን ነው፡፡ የፍቅረኛውን ሕይወት አጥፍቶ “ስላፈቀርኳት ገደልኳት” ለሚለው ሰው ግን በእርግጥም የእሱ ፍቅር እውር ነው፡፡ የዚህ ሰው ፍቅር በልቡ ላይ ያለን ሽንቁር መድፈኛው ነው፡፡  ፍቅረኛው የልቡን ሽንቁር ደፍናለት ሳለ - በድንገት ላጣት እችላለሁ ብሎ ሲያስብ እራሱን መቆጣጠር ያቅተዋል፡፡
ገደብ ያጣ መረበሽ ውስጥ ገብቶ ሕይወት እስከማጥፋት ይደርሳል፡፡ ይህንን ፍቅር ግለፀው ብባል በመጀመሪያ ጨለማ ነው እላለሁ፡፡ በመቀጠል ሰቀቀን ነው….ቀናተኛ ነው…ወገንተኛ ነው…ፈሪ ነው…ተጠራጣሪ ነው፡፡
ታዲያ ይሄን ማን ይፈልገዋል? ባንፈልገውም አብዛኞቻችን ከዚህ ዓይነት ፍቅር ጋር አብረን እንኖራለን፡፡ ግን ቢሳካ የምንፈልገው ዓይነት ፍቅር ከዚህ ተቃራኒ የሆነውን ነው፡፡ ጨለማ ሳይሆን ብርሃን የሆነውን…በልብ ሞልቶ የሚፈስ ሐሴት የሚሰጠውን … ደፋር … ትሁት … አማኝ… ዘወትር ጣፋጭ የሆነውን!!ስለዚህ “አጋፔ” እያለምነው ግን የማገናኘው አይነት ፍቅር ነው ማለት ነው? ምናልባት ለብዙዎቻችን የዚህ ጥያቄ መልስ “አዎ” ይሆናል፡፡ ምክንያቱም በልባችን ውስጥ ሽንቁር አለ፡፡ ወደ ልቦናችን ያስገባነውን ፍቅር አጣመንና አወላግደን ለሽንቁራችን መድፈኛ እናደርገዋለን፡፡ ኃያሉን ፍቅር አድክመንና አለስልሰን ተራ የስንጥቅ መለደሻ እናደርገዋለን፡፡ በአዋቂነት ዘመናችን ሽንቁር የበዛበት ልብ እንዳይኖረን በልጅነታችን ያለቅድመ ሁኔታ የተዘረጋን የረጋ የፍቅር ባህር መቅዘፍ ነበረብን፡፡
ይህ እድል ለእኛ “ለአዋቂዎቹ” አምልጦን ይሆናል፤ ልጆቻችን ግን እኛ ያጣነውን እድል እንዲያጡት መፍቀድ የለብንም፡፡
 ስለዚህ ልጆቻችንን ያለቅድመ ሁኔታ ፍቅር እንስጣቸው፤ የእኛን ፍቅር ለማግኘት ከክፍላቸው አንደኛ መውጣት ግዴታ እንዳልሆነ…የእኛን ፍቅር ለማግኘት እኛ የምንወደውን ብቻ ማድረግ ግዴታ እንዳልሆነ… የእኛን ፍቅር ለማግኘት አፍንጫቸው ቀጥ ያለ፣ ጥርሳቸው ሀጫ በረዶ የመሰለ መሆን ግዴታ እንዳልሆነ…የእኛን ፍቅር ለማግኘት እንግዳ ቤት ሲመጣ አለመረበሽ ግዴታ እንዳልሆነ…የእኛን ፍቅር ለማግኘት ምንም፣ ምንም ግዴታ እንደሌለባቸው……እንንገራቸው፡፡ አዎ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደምንወዳቸው ይወቁት፡፡ ያን ጊዜ “አጋፔ”ን መሸከም የሚችል ሥነልቦና እየፈጠርንላቸው ነው፡፡
“መባ” ፊልምና “አጋፔ”
“መባ” ፊልም ስለ “አጋፔ” ፍቅር እያወራ፣ የአእምሮ ሕሙማንን በፍቅር ስለመንከባከብ እየለፈፈ የመድኃኒት ሕክምናን ማቆም አስፈላጊ እንደሆነ አስመስሎ ይሰብካል፡፡
ይህ አንዱን ለመውደድ ሌላውን የመጥላት ሥነልቦና አይነተኛ መገለጫ ነው፡፡ የዛሬ አሥር ዓመት ገደማ በጠቅላላ ሐኪምነት በአንድ ሆስፒታል ውስጥ አገለግል ነበር፡፡ በመጀመሪያ ተመድቤ እሰራ የነበረውም የኤችአይቪ/ኤድስ ታካሚዎች የመድኃኒት ሕክምናና ምክር የሚያገኙበት ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ በወቅቱ በተደጋጋሚ ያጋጥመን የነበረው ችግር ከበርካታ ታካሚዎች ጋር መድኃኒት በመውሰድ ዙሪያ የሚደረገው ክርክር ነው፡፡
 አንዳንዶች “ፀበል ስለጀመርን መድኃኒት መውሰድ አቁመናል” ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ እንዲያውም “ኤችአይቪ/ኤድስ የሚመጣው በሰራነው ሐጢያት ወይንም ነውር ምክንያት ለቅጣት ተብሎ ስለሆነ በፀሎት እንጅ በመድኃኒት ሊድን አይችልም” ይሉ ነበር፡፡
እኛም እንጠይቃለን፤ “ሁሉንም ማድረግ አይቻልም ወይ? በፀበል ለመዳን መድኃኒት ማቆም ግድ ነው ወይ?” ደግነቱ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ትልልቅ የሐይማኖት አባቶች በይፋ “መድኃኒት አታቁሙ” እያሉ መምከር ጀመሩ፡፡ በአንዳንድ የፀበል ቦታዎችም የሕክምና መስጫ ጣቢያዎች ተከፈቱ፡፡ ይህም ለውጥ የብዙ ሰዎችን ሕይወት በከንቱ ከመቀጠፍ የታደገ ይመስለኛል፡፡ ለማንኛውም በርካታ አማራጮችን መሸከም የሚያስችል ታጋሽና በሳል ልቦና ያስፈልገናል፡፡
“መባ” ፊልምም እንደ “አጋፔ” ፍቅር ሰባኪነቱ ከወገንተኝነት የፀዳ፣ ጥልቀት ያለው ፍቅር መሠረት አድርጐ ቢሰራ ኖሮ የአእምሮ ሕሙማንን ከመገለልና ከአእምሮ ስቃያቸው የሚታደግ መንገድ ለተመልካች ለመጠቆም የሚያበቃ ሰፊ እድል ነበረው፡፡ ግን አልሆነም…እናም ለእኔ እጅግ የሚያስቆጭ ፊልም ሆኖብኛል፡፡ እንደ ባከነ እድልም እቆጥረዋለሁ፡፡ መልካም ነገር ይዞ ተነስቶ በግድየለሽነት ሲበላሽ የመመልከትን ያህል የሚያስቆጭ ነው፡፡ አንድ ሰው ወርቅን ያህል ተወዳጅና ውብ ነገር ይዞ ሊያጌጥበት ሲገባ ወርውሮ ሲማታበት ምን ይባላል?
የአእምሮ ሕሙማንን ችግር ለማሣቂያነትና ለመቀለጃነት ሥናውለው፣ ፍቅር እየሰጠናቸው ሳይሆን ዱላ እያሳረፍንባቸው ነው፡፡ “መባ” ፊልምን ዘወር አድርገን ስናየው የተደበቀው ዱላ ብቅ ይላል…”አጋፔ” አይደለም፡፡
ፊልሙ ሲሰራ በቂ ጥናት ተደርጓል ወይ?
ማንኛውም የጥበብ ሥራ ለማህበረሰቡ በጥበብ ሊገልጠው ያለመውን ጉዳይ በተለያዩ መንገዶች መርምሮ ያቀርባል፡፡ ጥበብ በጥበብነቱ ብቻ ሌላ የተለየ ዓላማ ሣይኖረው ሊሰራ ይችላል (Art for art sake) ብንል እንኳን እንዲሁ ያለ እውቀት በዘፈቀደ ይፈጠራል ማለት ግን አይመስለኝም፡፡
በአንድ ወቅት የአእምሮ ህመምተኛን የወከለ ገፀ ባህሪ ያለበት የትያትር ሥራን ተመልክቼ አስተያየት እንድሰጥ ተጋብዤ ነበር፡፡ ገፀ ባህሪው ሕጻን ልጅ እንጂ እኔ የማውቀውን ዓይነት የአእምሮ ሕመምተኛን አይወክልም ስል አስተያየቴንም ቅሬታዬንም ሰነዘርኩ፡፡ “አይ ዋናው አርቱ እንዳይበላሽ አስበን ነው” የሚል ምላሽ ተሰጠኝ፡፡ “Art for art sake” /ኪነ ጥበብ ለኪነ ጥበብነቱ ብቻ /እንጂ ስለ አእምሮ ሕመም ለማስተማሪያነት ታስቦ የተዘጋጀ ስላልሆነ ችግር የለውም የሚል ዓይነት ማብራሪያ ታከለበት፡፡ ምን ማለት ነው? የፈጠራ ሰው የመሳሳት መብት አለው ማለት ነው? የአእምሮ ሕመም ላይም ይሁን ሌላ ጉዳይ ላይ የማስተማር ዓላማ አይኑረው እንበል፡፡ ነገር ግን የአእምሮ ሕመምተኛን ገፀ ባህሪ የወከለ ተዋናይ እንደ ሕፃን ልጅ ሆኖ እየከወነ ከሆነ፣ የደራሲው ሐሳብና ስሜት በተተለመለት አቅጣጫ ሳይሆን በሌላ መንገድ ለታዳሚ እየቀረበ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ አይንን ለመዳበስ የላከ እጅ አፍንጫን ሲይዝ አይነት ነገር ነው፡፡ ለማንኛውም በስንፍናም ይሁን በሁሉን አውቃለሁ ስሜት ለሚፈጠሩ ስህተቶች ማንኛውም ሰው ኃላፊነት ሊወስድ ይገባዋል እንጂ ሌላ ሰበብ ማብዛት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ “Art for art sake” የኪነ ጥበብን ውበት፤ ውበትም በራሱ ግብ ሊሆን እንደሚችል ለማጉላት እንጂ ስንፍናችንን ለመሸፈን ልንጠቀምበት አይገባም፡፡
በአጠቃላይ እውነተኛ የፈጠራ ሥራ ከጥልቅ እውቀትና ፍቅር የሚመነጭ ይመስለኛል፡፡ በአንድ ጉዳይ ላይ የሚኖረን ጥልቅ ፍቅር ስለጉዳዩ በየእለቱ እንድናስብ፣ እንድንጠይቅ፣ እንድንመራመርና በጉዳዩ እንድንጠመድ ያደርገናል፡፡ እንደዚህ ያለው ያለመታከት፣ በጉዳዩ ላይ መጠመድና ይህንንም ተከትሎ የሚመጣው የመጠየቅና የመመራመር ጉዞ ደግሞ ወደ ተለያዩ የፈጠራ አጋጣሚዎች ይመራናል፡፡ በአጭሩ ፍቅር የጥበብ /ፈጠራ/ መነሻ ነው፡፡ ምክንያቱም ፍቅር ወደ እውቀት ይመራናል፣ በመጨረሻም የጥበብን ፍሬ ያሳየናል፡፡ “መባ” ፊልም በዚህ አይነት መንገድ ተጉዞ የመጣ አይመስልም፡፡ በአእምሮ ህሙማን ችግር ዙሪያ በመጨነቅ የተጠመደ ሰው በፍቅር የፈጠረው የኪነ ጥበብ ሥራ ነው ብዬ ለማሰብ እቸገራለሁ፡፡ ከአንደኛው ገጸ ባህሪ ውጭ ያሉት በርካታ የአእምሮ ሕሙማን እንደ ጅል ተደርገው መሳላቸው በሥራው ላይ ጥልቅ ፍቅርን አሳድሮ፣ በቂ እውቀት ለመገብየት የተደረገው ሙከራ አናሳ መሆኑን ያሳያል፡፡
የፊልሙ ደራሲና ዳይሬክተር ለስድስት ወራት ያህል በአማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ ጥናት እንዳደረገች ለመገናኛ ብዙሀን ተናግራለች፡፡ ሆስፒታሉ የጥበብ ስራዎችንም ሆነ ሌሎች ድጋፍ የሚሹ ጉዳዮችን ለማስተናገድ የሚያስችል አሰራር አለው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ይህ ፊልም በዚህ መንገድ አልተጓዘም፡፡ ምናልባት ያለ ባለሙያ ድጋፍ በራሳችን አጥንተን መስራት እንችላለን ከሚል በራስ መተማመን ስሜት የመነጨ ይሆናል፡፡ ውስብስብ የሆነውን የሥነ አእምሮ ጉዳይ ያለአግባብ አሳንሶ ከማየት አባዜ የመጣም ሊሆን ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ እንደ አንድ ባለሙያ ስመለከተው፣ በቂ የባለሙያ ድጋፍ ባለማግኘቱ አፍራሽ ተፅእኖው ጎልቶ ወጥቷል፡፡
ማጠቃለያ
በመጨረሻ በፊልሙ ላይ የወደድኳቸውን ነገሮች ጠቅሼ ጽሁፌን አጠቃልላለሁ፡፡ “መባ” ፊልም በአእምሮ ሕሙማን ዙሪያ እንድናወራ፣ እንድንከራከር ወይንም እንድንወቃቀስ እድል መፍጠሩ የሚያስመሰግነው ነው፡፡ የአእምሮ ሕመም ጉዳይ ሙሉ አጀንዳው አድርጎ መስራቱ በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ምንም እንኳን ባልበሰለና በተንሻፈፈ መንገድም ቢሆን ፍቅርን ከአእምሮ ሕመም ጉዳይ ጋር አስተሳስሮ ለማቅረብ መሞክሩም በራሱ የሚያስደስት ነው፡፡ በቀጣይ ሚዛናዊ የሆነ ጥናት ላይ ተመርኩዞ የአእምሮ ሕሙማንን ዓለም ለመዳሰስ ቢሞከር ተአማኒና ጠንካራ የሆኑ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ለታዳሚ ማቅረብ እንደሚቻል አምናለሁ፡፡ ፊልሙ ግን በህዝብ እይታ ውስጥ ሆኖ እስከሚቆይበት ጊዜ ድረስ የአእምሮ ሕመም ጉዳይ ተቆርቋሪ ወገኖችና ባለሙያዎች ሁሉ ታዳሚው ሚዛናዊ እይታ ይኖረው ዘንድ በተገኘው የመገናኛ አማራጭ ሁሉ በመጠቀም የማስተማር ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል እላለሁ፡፡

Read 3349 times