Saturday, 27 February 2016 11:18

የእንግሊዙ ጠ/ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል

   የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍሊፕ ሃሞንድ በእንግሊዝና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ በማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረገ ጉብኝት ለማድረግ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ ከትናንት በስቲያ በድረ-ገጹ አስታወቀ፡፡ባለስልጣናቱ ኢትዮጵያን የመጎብኘት እቅድ እንዳላቸው ያስታወቁት፣ ባለፈው ረቡዕ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የመከሩት የእንግሊዝ የአገር ውስጥ ጉዳይ ቢሮ ሁለተኛ ቋሚ ጸሃፊ ኦሊቨር ሮቢንስ መሆናቸውን ቢገልጽም፣ ጉብኝቱ የሚከናወንበትን ጊዜ በተመለከተ ግን ያለው ነገር የለም፡፡ ሁለቱ የእንግሊዝ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙትና እንግሊዛዊ ዜግነት ያላቸው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈቱና በቆንስላ ተወካዮች የሚጎበኙበት ሁኔታ እንዲመቻች የሚጠይቅ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ቢልኩም መንግስት ግን ይህ ነው የሚባል ምላሽ አለመስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ጉብኝቱ ዴቪድ ካሜሩን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ላይ ከወጡ ወዲህ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡበት የመጀመሪያው ጉብኝት ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር እ.ኤ.አ በ2004 ኢትዮጵያን ጎብኝተው እንደነበር ይታወሳል፡፡

Read 4676 times