Saturday, 27 February 2016 11:43

ግብፅ ለድርቅ ተጎጂዎች 20 ሚ. ብር ለገሠች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

ቀይ መስቀል 1 ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ አቅዷል
   በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የግብፅ መንግሥት በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል የ1 ሚ. ዶላር (20ሚ. ብር ገደማ) እርዳታ ለገሠ። ግብፅ እርዳታውን የለገሰችው የሁለቱን ሃገራት ህዝቦች ወንድማማችነትና ለችግር ደራሽነት ለማረጋገጥ መሆኑን የግብፅ መንግስት የልማት ትብብር ዋና ፀሐፊ ሃዚም ፋሃሚ በከል የገለፁ ሲሆን እርዳታው ሙሉ ለሙሉ ለሶማሌ ክልል የድርቅ ተጎጂዎች እንዲውል የተወሰነው በክልሉ ሰፊ የግብረ ሰናይ ተግባር እያከናወነ የሚገኘው የአለም የምግብ ፕሮግራም ባወጣው እቅድ መሰረት ነው ተብሏል፡፡
ህብረተሰቡን በማስተባበር የድርቁን ተጎጂዎች ለመርዳት እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በበኩሉ፤ እስካሁን ወደ 20 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ገንዘብ በአፋርና በሱማሌ ለሚገኙ ተጎጂዎች ድጋፍ ማድረጉን ያስታወቀ ሲሆን ሰሞኑን ከተለያዩ ለጋሽ ተቋማት ከ1.4 ሚሊዮን ብር በላይ እርዳታ መለገሱን አስታውቋል፡፡
ከትላንት በስቲያ ዘመን ባንክ 500 ሺ ብር፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን 500 ሺህ ብር፣ አቢሲኒያ ባንክ 150 ሺ ብር፣ ኢስት አፍሪካ ታይገርስ ብራንድ 50 ሺ ብር እንዲሁም በለንደን ነዋሪ የሆኑ “የእኛው ለኛ” የሙዚቃ ቡድን አባላትና ወጣት ተማሪዎች 127 ሺ ብር የሚገመቱ 9 የውሃ ፓምፖችን ለግሰዋል ብሏል ማህበሩ፡፡ ቀይ መስቀል በዋናነት ለእናቶችና ለህፃናት በሚቀርቡ አልሚ ምግቦች ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን ያስታወቁት የማህበሩ አመራሮች፤ 100 ሺህ የሚደርሱ ህፃናቶችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
ከጥር ወር ጀምሮ ህብረተሰቡ በያለበት ሆኖ ከ3 እስከ 50 ብር እንዲለግስ በተዘረጋው የሞባይል የአጭር መልዕክት ፕሮግራም በ15 ቀን ውስጥ 160 ሺህ ብር ብቻ መገኘቱን የጠቆሙት አመራሮቹ፤ በቂ የቅስቀሳ ስራ ባለማከናወኑ በታሰበው መጠን እርዳታው ሊገኝ እንዳልቻለ ጠቅሰው ህብረተሰቡ በህይወት አድን ስራው እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ማህበሩ በአጠቃላይ ድርቁን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ለመወጣት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የተናገሩት አመራሮቹ፤ በዚህ ግብረ ሰናይ ፕሮግራሙ በቅርቡ እስከ 200 ሚ. ብር ለማሰባሰብ ያቀደ ሲሆን ተቋማት እርዳታ እንዲለግሱ ከሚደረገው ቅስቀሳ ጎን ለጎን የ1 ቢ. ብር ማሳሰቢያ ሰፊ ፕሮግራም ለማከናወን ማቀዱንም ጠቁመዋል፡፡
ኦክስፋም አሜሪካ እንዲሁ 160 ሺ ያህል የድርቅ ተጎጂዎችን በቀጥታ እየረዳ መሆኑን ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫው ጠቅሶ፤ ትኩረት አድርጎ በሚንቀሳቀስበት በሶማሌ ክልል ስቲ ዞን ብቻ ግማሽ ሚሊዮን የቤት እንስሳት በድርቁ ማለቃቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ቋሚ ገቢ የሚያገኙት ከእንስሶቻቸው በመሆኑ መልሶ ለመቋቋም ይቸገራሉ ሲል ስጋቱን ገልጿል፡፡ በአሁን ወቅት በአካባቢው ለ100 ሺህ ሰዎች የእለት ተዕለት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የገለፀው ኦክስፋም፤ በአጠቃላይ ድርቁን ለመቋቋም ያስፈልጋል ከተባለው 1.4 ቢሊዮን ዶላር ግማሽ ያህሉ እንኳ ከለጋሾች አለመገኘቱን አመልክቷል፡፡
በቀጣይ እስከ 777ሺህ የድርቅ ተጎጂዎችን በእርዳታው ለማዳረስ አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ኦክስፋም በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

Read 3871 times