Saturday, 27 February 2016 11:46

የህይወት ጀንበር፤ በፀሐይ መጥለቂያዋ ሀገር

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(1 Vote)

በውልብታ መሰል ዕይታ እንተዋወቃለን፡፡ የእሷን እንጃ እንጂ የእኔ የውልብታ ወለምታ ለአመታት አብሮኝ አለ፡፡ ለነገሩ ከተማ - ከተማ ናት፡፡ እንኳን ለተሸጋጋሪው፣ ለዕድሜ ገባሪውም መመዝገቢያ ልቡና የላት፡፡ ሐውልት ብታቆምላት፣ መታሰቢያ ብታኖርላት፣ ትውስታ ብትሰፍርላት… ከልቡናዋ መኖሩን እንጃላት…
…በውልብታ መሰል ዕይታ የሞሸርኳት ጋምቤላ ናት፡፡ አይኔ ሀይቅ ሆኖ ያስመጣት፣ ልቡናዬ ጥሪት አድርጐ የቋጠራት… የአሥራ አምስት አመት ቀለቤ ናት፡፡ በፊት፣ ገና በፊት ልጅ ሳለሁ ሰሜኖች ከደቡብ ሱዳን እስኪወጡ ኙዌሮች መንደሬ ድረስ መጡ፡፡ እነ ሚስተር ሄኖክ፣ አንቶኒ፣ ኦኬሎ፣ ኡጁሉ…የሚባሉ፡፡ አንድ ሰሞን ይጠፋሉ፤ ደግሞ ተዋግተው ነው ተብሎ ይመጣሉ፡፡ ሲያሻቸው ሱዳን፣ ካልሆነም ኢትዮጵያዊ ይሆናሉ እየተባሉ ይታማሉ፡፡ ለእነሱ አዲስ አበባ አንድ መላ ሳይኖራት አልቀረም እያልኩ አስባለሁ፡፡ ብዙ መከራ ማቅጠኚያ ጥቂት ደስታ የሚሸምቱባት ቦታ ናት፡፡ መጠጥ፣ ጭፈራ፣ ሴት… መጠጥ፣ ጭፈራ፣ ሴት… ከዚያ ጦርነት፡፡
ሕይወት በእነዚህ ምሕዋር ላይ የምትሽከረከር ናት፡፡
ወደ ጋምቤላ ስሄድ በኙዌርኛ ሠላምታ ሲያቀርቡልኝ ድንግርም አላለኝ፡፡
“ማለ”
“ማለ”
“ማለ ሙጋ”
“ማለ ቾምቾም”
ያኔ፤ አገራችን ከሻዕቢያ ጋር ጦርነት ላይ ስለነበረች ጋምቤላ አውሮፕላን ማረፊያ ለመድረስ አስር ደቂቃ ሲቀረን መስኮቶቻችንን እንድንዘጋ ተጠይቀን ነበር፡፡ እንኳን ለገና ገና የአየር ላይ ጉዞ፣ መሬት የተቆናጠጠ ቤት መስኰት ሲዘጋ እንዴት እንደሚጨንቅ አስቡት፡፡ ማረፋችንን በመንገጫገጭ አውቀን ወረድን፡፡ አውሮፕላን ማረፊያው ከጋምቤላ ከተማ አስራ ስድስት ኪሎ ሜትር ይርቃል፡፡ የሚገርመው ምንም አይነት የትራንስፖርት አቅርቦት አለመኖሩ ነበር፡፡ ጥቂት የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ሰው ለመውሰድ ሲመጡ ሌሎቹንም መንገደኞች አጭቀው ይመለሳሉ፡፡
የያኔዋ ጋምቤላ ከተማዋም፣ ትራንስፖርት የላትም፡፡ ታክሲ፣ ባጃጅ፣ አውቶቡስ፣ ሎንቺና…ምንም አልነበራት፡፡ አንዳንድ የመንግሥት መኪኖች የኋላ እግራቸው እንደተሰነከለ ውሻ ዝልል፣ ዝልል እያሉ ያልፋሉ፡፡ መንገዱ እንደ ገበጣ መጫወቻ በጉድጓድ የተሞላ ነበረአ! በዚያ በተቅለጠለጠ ሙቀት፣ መሣፈሪያ ማጣት፣ ለደጋ ሰውነት እንዴት?... ግራ ተጋብቼ ነበር፡፡ ብቸኛው የኪራይ ተሽከርካሪ ብስክሌት ነበር፡፡
አልጋ “ፓርክ ሆቴል” ያዝኩ፡፡ ቀጫጭን የበረሃ ዛፎች በርብራብ ላይ ተሰድረው ዳስ የሆኑበት ሰፊ ክፍት ቦታ አለው፡፡ ዳሱ ከፀሐይ ቀጥተኛ ጥቃት እንጂ ከወበቁ አይከላከልም፡፡ የውኃ ጥያቄ ለአፍታም አይገታም፡፡ እየጠጡ ይጠማሉ፣ ሆድ በውኃ ተቆዝሮ እርካታ ይሰንፋል - ምን ይባላል?
“ሻይ ወይም ቢራ ጠጣ” አለኝ የታዘበኝ፡፡
እውነትም ተሻለኝ፡፡
ጋምቤላ ላይ ሌላ የገረመኝ የጠለስ ዝናብ ጉዳይ ነበር፡፡ ከወደ ሰማይ ወረቀት ተቃጥሎ ሲያልቅ የሚቀረውን የመሰለ ጠለስ ይወርዳል፡፡ ሸሚዝ ላይ ሲያርፍ ከላብ እርጥበት ጋር ተዋህዶ ጥላሸት ይሆናል፡፡ ለሁለት ቀን ሚስጥሩ አልገባኝም ነበር፡፡ አንድ አመሻሽ ላይ ወደ ኢትዮጵያ ሆቴል እየሄድኩ ሳለ፣ አሥር እርምጃ ያህል እግራችን አንድ ላይ የተራመደብንን ልጅ ጠየኩ፡፡
“ይሄ ምንድነው?”
ልጅቷ ፈገግ ብላ አየችኝና “የደጋ ሰው ነህ?” አለችኝ፡፡
“አዎ” አልኳት
“ይኸውልህ፤ ከከተማው ውጭ ረጃጅም የበረሃ ሣሮች አሉ፡፡ በሰደድ እሣት ሲቃጠሉ ወደ ሰማይ ይወጡና ከተማው ላይ ይወርዳሉ፡፡”
ልጅቷን ልብ ብዬ አየኋት፡፡ ፀጉሯ ዞማ ነው፤ መልኳ ለጥቁረት የሚያደላ ጠይምነት አለው። አይኖቿና ጥርሶቿ ሃጫ - በረዶ የመሰሉ ናቸው። “አንቺ የጋምቤላ ልጅ ነሽ?” ስል ጠየኳት፡፡ በጭንቅላቷ “አዎ” አለችኝ፡፡ አፍንጫዋንና አይኖቿን የጨቆነ ወፍራም ጉንጭ አላት፡፡
“አንተስ?”
“አዲስ አበባ”
“እዚያ አክስት አለኝ”፤ በአመት፣ በአመት እመጣለሁ”
ምን ይባላል? ዝም! ጥቂት ተራመድን፡፡ በድልድዩን አልፈን ወደ ኢትዮጵያ ሆቴል አንድ ላይ ታጠፈን፡፡
“ተማሪ ነሽ?” (ቢገባኝም)
“አዎ”
“ሰፈርሽ እዚህ ነው?” (ቢገባኝም)
“አዎ”
ይቺ ናት ጨዋታ መጥፋት፡፡
“እኔ አለማየሁ እባላለሁ፤ ጋዜጠኛ ነኝ፡፡”
“ኘዋል እባላለሁ”፤ ኘዋል ሳይመን”
“የምን ሥም ነው?ማለቴ…”
“የኙዌር ነው፡፡ አባቴ ኙዌር ነው፡፡ እናቴ የትግራይ ሴት ናት”
“ኙዌርኛ ትችያለሽ?”
“አዎ”
“ትግርኛም?”
“አዎ”
“አማርኛ በደንብ! ታድለሽ?”
ሽኩርምሚታም ሣቅ አስተናገደች፡፡ ኢትዮጵያ ሆቴል ስለደረስን ለመሰናበት ቆም አለች፡፡ ሰውነቷም እንደ ጉንጮቿ ሞላ ያለ ነው፡፡
“እንኳን ተዋወቅን” አልኳት፡፡
“እሺ” አለችኝ፡፡
“እሺ አይባልም፤”
“ታዲያ?”
“እንኳን ለመተዋወቅ በቃን ነዋ”
“እሺ እንደሱ፣ በቃ ልሂድ…”
“ሁልጊዜ እዛች ዛፍ ሥር እቀመጣለሁ፤ ስታልፊ ሰላም በይኝ” አልኳት፡፡
“እሺ ቻው”
“ቻው”
እራሴን ከኢትዮጵያ ሆቴል ጋር ማቆራኘቴ የታወቀኝ ቆይቶ ነው፡፡ ቁርስ እዚያ እበላለሁ፤ ለምሳ እሄዳለሁ፤ ከእራት ሰዓት ቀደም ብዬ ቦታው ላይ እገኛለሁ፡፡ ኘዋል ሦስት ቀን ዝር አላለችም። ሆን ብላ የምገኝበትን ሥፍራ ሸሽታዋለች፡፡ የቀኑን ጥበቃ የማበቃው በአብሪ ነፍሳት ሲታጀብ ነው። በጨለማው ውስጥ እንደገና አምፑል ብልጭ ድርግም እያሉ ሲጓዙ አቅጣጫቸውን ለመለየት በአይኔ እከተላቸዋለሁ፡፡ በቅቶኝ ወደ ፓርክ ሆቴል ሳመራም በእነዚሁ ነፍሳት ታጅቤ ነው፡፡ አይን ያጫውታሉ፡፡ ብልጭ ብላ የያዘችውን አቅጣጫ ተፍታ ትቀይረዋለች፡፡ ቀኝ፣ ግራ እያሰቡ እስክትበራ መጠበቅ፣ አነሁላይ ጨዋታ ነው፡፡
በሦስተኛው ቀን ለዘገባ የማመራው ወደ ጋምቤላ ትምህርት ቢሮ ነበር፡፡ የጋምቤላ መምህራን አንድ ያቋቋሙት ማህበር አለ፡፡ ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ዘመድ አልባ ተማሪዎችን ማህበሩ ከአባላት በሚዋጣ ገንዘብ እየረዳ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ያደርጋል፡፡ የአባላቱን ቃለ መጠይቅ እንደጨረስኩ ወደ ከተማው ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሄድኩ፡፡ ተረጂ ተማሪዎችን ፍለጋ ነበር፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ለእረፍት ተደውሎ አንድ ሁለት ተማሪዎች እንዳነጋገርኩ ከሩቅ ኘዋልን አየኋት፡፡ እሷም አይታኛለች፡፡ አፍራ ትደበቃለች ስል ያለማንገራገር ወደ እኔ መጣች፡፡
“እንኳን ለመተዋወቅ በቃን” አለችኝ
“እንደሱ አይባልም” አልኳት
“እህስ?” አለች
“እንኳን ዳግም ለመገናኘት በቃን”
“እሺ እንደሱ”
“ለምን ጠፋሽ? ስጠብቅሽ…”
“ለምን ጠበከኝ?”
“እንድናወራ”
“ኢትዮጵያ ሆቴል አይሆንም፡፡ እዚያ ቤቴ አለ” አለች፡፡
“ታዲያ የት?”
“ፓርክ ሆቴል ግቢ ውስጥ ይሻላል”
“ጥሩ፣ አልጋ የያዝኩት እዚያ ነው” ካልኩ በኋላ ቆጨኝ፡፡ ሌላ ነገር ይመስላት ይሆን?
“አልጋ ውስጥ አይደለም፤ ውጭ ነው”
“እሺ” አባባሏ አሳቀኝ፡፡
እውነትም አመሻሽ ላይ መጣች፡፡ የበረንዳው ደፍ ላይ ተቀምጠን ያዘዘችውን ለስላሳ መካከላችን አኑረን አወራን፡፡ አስተዋይ ናት፡፡ ለእንግዳ ሰው የሚሆን ገለፃ አላት፡፡ የጋምቤላን ጠለስ ተከትላ ስለ ሣር ቃጠሎው አወራችኝ፡፡
“ሣሩ በሰደድ እሣት ሲቃጠል እዚያ የተሸሸጉት ሁሉ ወደ ጥርጊያው መንገድ ይወጣሉ፡፡ እባብ፣ እንሽላሊት፣ አይጥ… ብዙ፡፡ አሞራዎች ደግሞ ከጥርጊያው ላይ እየጠለፉ ይዘዋቸው ይከንፋሉ፡፡ አየር ላይ ለመነጣጠቅ እርስ በእርስ ይጣላሉ። አንዱ የለቀቀውን ሌላው ይቀልበዋል፡፡ ሁኔታው የሚያስፈራ ቢሆንም ግን ደስ ይላል፡፡ አባቴን እዚያ ይዞኝ እንዲሄድ እለምነውና ሲወስደኝ ወዲያው እንመለስ እለዋለሁ፡፡”
“ለምን?”
“ያስፈራል፤ ግን ህይወት ነው አይደል?...”
ብቀጥል ውስጤ የማይበርድ ሐዘን ለመቀስቀስ የምትሰንፍ ልጅ አይደለችምና ፈርቼ ተውኩት፡፡ ግን አልቀረም፡፡ በራሷ ህይወት በኩል መጣች፡፡
“እናትህና አባትህ በፍቅር አንድ መሆናቸውን የበለጠ የሚያረጋግጡት አንተን ሲወልዱ ነው፡፡ ግን…”
“ግን ምን?”
“ለእናትህና ለአባትህ ዘመዶች ግማሽ ዘመድ ነህ”፤ ሁለቱም ዘመዶች ልጆቻቸው የራሳቸውን እንዲያገቡላቸው ስለሚፈልጉ ከሌላ ጋር በመሆናቸው ይናደዳሉ፡፡ ሲወልዱ ደግሞ በቃ በአንተ ምክንያት ተቆራርጠው እንደቀሩ ያስባሉና አይወዱህም፤ አይጠሉህም፡፡ ዘመድ ነህ፤ አይደለህም ለማለት ይቸገራሉ፡፡ እንዴት ያምማል መሰለህ”፤
ለሰሚው ለእኔም ያምማል…
(ይቀጥላል)    



Read 1988 times