Saturday, 05 March 2016 11:02

ጥበብና የነፍስ ፀሎት!

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

  ሁሉም የማነባቸው መጽሐፍት እያስጠሉኝ ነው፡፡ ጥሩ ናቸው በሚል በማምናቸው “አዋቂዎች” የተጠቆሙትም ወደ እምፈልገው የነብስ ጥልቀት ዘልቀው የሚያስተጋቡ አልሆኑልኝም፡፡
ብቻ በአጠቃላይ እራሴ እየፃፍኩት ባለሁበት አቅጣጫም ሆነ በሌሎች ፀሐፊዎች አቅጣጫ ደስተኛ አይደለሁም፡፡ ሲሲፈስ ድንጋይን ያለመዳረሻ እንደሚያንከባልለው እኔ ደግሞ ያለ አቅጣጫ የብዕሬን እድሜ እየገፋሁ መሰለኝ፡፡
ምን ይሆን ምክንያቱ እያልኩ ስብሰለሰል፤ “ጊታንጃሊ” እጄ እንዳጋጣሚ ገባ፡፡ ወይንም እንዳጋጣሚ ገዝቼ እንዲገባ አደረኩት፡፡ “ሚስቴሲዝም” ላይ የሚፃፉ መጽሐፍትን ማንበብ ካቆምኩ ጥቂት ጊዜ አልፎኝ ነበር። በስጋ አለም ላይ እየኖሩ ስጋን መርሳት… ደካማ እያደረገ አስቸገረኝ። ወደ ጐን አድርጌያቸው ቆየሁ፡፡ ወደ ጐን አደረኳቸው ማለት ግን ከመጽሐፍ መደርደሪያዬ ላይ አስወገድኳቸው ማለት አይደለም፡፡ አለሙና የታሰርንበት ካቴና እንደሆነው ባይሆን መጽሐፍቱማ የእውነት መንገድ ናቸው፡፡ መከተል ስላልቻልኩ ላስወግዳቸው አልፈልግም፡፡
ጊታንጃሊ የኦሮምኛ ቃል አይደለም፡፡ ከህንድ የመጣ የመጽሐፍ አርዕስት ነው፡፡ ራባንዲያራስ ታጐር የመጽሐፉ ባለቅኔ ሲሆን፣ መጽሐፉ በልሙጥ ስንኝ የተፃፈ ግጥም ነው፡፡ ገጣሚው ከሙልኤ ኩሉው ፈጣሪው ጋር በዜማና ጥበብ (በፍልስፍና) ለመድረስ የሚለማመጥበት ፈጠራ ነው፡፡
ካህሊል ጅብራንም መንፈሳዊ ጠቢብ ነው፡፡ ግን ካህሊል እንደ መካሪም ነው፡፡ “ነብዩ” በተባለው መሰረታዊ ስራው ለህዝቡ ያስተምራል፡፡ የራሱን የነፍስ ልዕልና ያገኘ ገፀ ባህርይ ወደ መጨረሻው የህይወቱ ጀልባ ከመሳፈሩ በፊት በአሕዛቡ ጥያቄ ይቀርብለታል፡፡ ነብይን ሆኖ ወይንም መስሎ ለጥያቄዎቹ ጥልቅና መንፈሳዊ መልሶች ይሰጣል፡፡ ግን በመሰረቱ በመንፈሳዊ ገፀ ባህርይ ላይ ያጠነጠነ የጥበብ ስራ ልንለው እንችላለን፡፡
የታጐር “ጊታንጃሊ” ግን የጥበብ ስራ አይደለም፤ የነፍስ እውነተኛ ፀሎት ነው፡፡ ፀሎቱ ደግሞ ከገጣሚው ወደ ፈጣሪው በዜማና ግጥም ታሽቶ የቀረበ ነው፡፡ ፀሎት ጥበብ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳ ይሆናል፡፡ ለምን እንዳልሆነ የሚያስረዳ ከሌለ መንፈሳዊ እምነትና ጥበብ እስከአሁንም ተለያይተው የቆዩት በሌላ ስውር ደባ ምክንያት እንጂ በተፈጥሮአቸው ምክንያት አይደለም ማለት ነበር፡፡
የኦሪቱ ዳዊት በበገናው እየዘመረ መንፈሳዊ ግጥም ለመጽሐፍ ቅዱስ አበርክቷል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሰነዱት የጥበብ ስራዎቹ ናቸው፡፡ ታዲያ እነዚህ የኦሪት ንጉሳን ጥበብን ከመንፈሳዊነት ጋር አዋህደው ከፈጣሪያቸው ጋር መነጋገር ከቻሉ ለምን እኛ፣ ጠቢቡ ሰለሞንም … ዘመነኞቹ ይሄንን ከማድረግ ተቆጠብን፡፡
ታጐር እነ ዳዊትና እነ ሰለሞን ያደረጉትን ነው ያደረገው፡፡ ግን በሂንዱ ሃይማኖት ውስጥ ፀሎቱ እንዲካተትለት ፈልጐ አይደለም፡፡ ከሃይማኖታዊ ፕሮፖጋንዳ ነፃ ሆኖ ነው ነፍሱን ወደ እውነትና የፈጣሪ ዕውቀት በእምነቱ ፍላፃ ወደ ፈጣሪው ጆሮ ያስወነጨፈው፡፡
እና በካህሊል ጂብራን ድርሰት ውስጥ ያላገኘሁትን አዲስ አይነት መነካት ፈጠረብኝ፡፡ አዲስ የሆነብኝ እውነተኛ ጥበብን ከእውነተኛ ፀሎት ጋር ቀላቅሎ ስለተቀኘ ሳይሆን ይህንን ያደረገው ተከታይ ለማፍራት ወይንም አድማጭ ለማግኘት ብሎ አለመሆኑም ጭምር ነው፡፡
የራሱን ነፍስ እንጂ የሚገስፀው እናንተም እንደኔ አድርጉ እያለ አይደለም፡፡ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሀገሩና ህዝቦቹም ይፀልያል፡፡ ፀሎቱ ግን ስብከት አይደለም፡፡ እውር ፀሎትም ግን በፍፁም አይደለም፡፡ ስለሚፀልየው ነገር ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ከእውቀት በኋላ ነው እምነቱን ወደሚሰማ አምላክ የሚያዜመው፡፡ በዜማው ፍልስፍና እውቀትና እምነት በተመጣጣኝነት ሳይረባበሹ ተካተውበታል።
እንዲህ ይፀልያል በሰላሳ አምስተኛው አንቀጽ -
Where the mind is without fear and the head held high,
Where knowledge is free
Where the world has not been broken up into fragments by narrow domestic walls
Where words come out from the depth of truth,
Where tireless striving stretches is arms towards perfection where the clear stream of reason has not lost its way into the desert sand of dead habit;
Where the mind is led forward by thee into ever winding thought and action into the hearer of freedom let my country wake.
ወደ ታጐር ስመለስ የራሴም የመነሻ ጥያቄዬ ተመልሶ ይከሰትብኛል፡፡ ማለትም ጥበብን ከእውነተኛ የመንፈስ ልዕልና ጋር አዋህዶ ከፍ ወዳለ ጆሮ (ለፈጣሪ አይነት) ለመሰደድ የጣረ ሚስቲክ እንዴት የለንም? ግጥማችን ሁሉ ለሆነ ጫና የማካካሻ የመልስ ምት ነው፡፡ ለሚሰማን የኑሮ ወይንም ፍላጐታችን ጫና አፀፌታዎች ናቸው፡፡
በዕውቀቱ፤ “ዶሮውን ከዶሮ ወጥ ለይተን መመልከት አንችልም” ሲል፤ ተዕለት ታለት ፍላጐታችን የሚሆን ግጥም ብቻ ነው የምናልመው ማለቱ ነው፡፡ ዶሮዋ ጥሬዋን፣ ገጣሚውም ጥሬና ዶሮ ማግኛውን ብቻ አልሞ ነው የሚቀኘው፡፡ ግን ይህንን እውነት የነገረን እሱም በአፀፌታ ነው፡፡ ዶሮን ከዶሮ ወጥ ለይቶ ገጥሞ አላሳየንም፤ ማየት ለእኛ ተስኖናል የሚል ኩርፊያን ነው የነገረን፡፡ ለእኛ ሌላ መንገድ መኖሩን ያወቀው መጠቆሙ በመንገዱ ተጉዞ መድረስ ማለት አይደለም፡፡ በንፅፅር መንገዱ መኖሩን ከናካቴው ከማያውቁት ግን በጣም የተሻለ ነው፡፡
የተሻለ ገጣሚ የሆነውም በዚህ ብልጫው ነው፡፡ ከተሻለው በላይ ጥበብን መንፈሳዊ አድርጐ ከፈጣሪው ጋር መገናኘት የቻለው (ለእኔ ችሏልና) ታጐር ግን ከበዕውቀቱም የበለጠ አስቀንቶኛል፡፡
የመንፈስ ንጥረ ነገሮች በቁሳዊ ንጥረ ነገሮች የተተኩባት አለም ላይ ነው ያለነው፡፡ ነፍስ ሳይሆን የቁስ ግዝፈትና በአምስቱ ስሜት ህዋሳችን ብቻ የሚሰሙንን ነገሮች በዋናነት መግለጽ ላይ ነን፡፡ እምነታችንም በእነዚህ ነገሮች ላይ ድርሻ ስለማግኘት ነው እንጂ ከዚህ ባሻገር የሰው ግዛት እንዳለ መናፈቅ አቁመናል፡፡
እርስበርስ የምንገናኘው በኤሌክትሪክና በዜና አማካኝነት ነው፡፡ እውነተኛ የነፍስ ዜና በራሳችንም ላይ ይሁን በሌሎች ላይ አይነበበንም፡፡
ምናልባት ይህ ይሆን እንዴ በማገላብጣቸው መጽሐፍት ላይ የጐደለኝ ነገር? ኮተትና ግንብ ስንገነባ፣ በገነባነው ቁስ ጥላ ውስጥ የተከለለችው ነፍሳችን ፍርሐት - ፍርሐት፣ ጥርጣሬ - ጥርጣሬ፣ ተስፋ ማጣት - ተስፋ ማጣት የሚመላለስበት ምክንያቱ ይኼ ይሆን
`I am ever busy building this wall all round, and as this wan go up into the sky day by day I lose sight of my true being in its shadow` ይላል ታጐር፡፡ እያወራ ያለው ስለራሱ ቢሆንም፣ እያወራ ያለው የራሱን እውነት ከአምላኩ ጋር ቢሆንም፣ እኔም ማውራት የምፈልገውን እውነትና ከማን ጋር ማውራት እንዳለብኝ ያስታውሰኛል፡፡
በቀን ውስጥ፣ ድሮ ሊታሰብ በማይችል መጠን፣ በተለያዩ ሶሻል ሚዲያ የብዙ የጓደኞቻችንን ሃሳብና ግጥሞች እናነባለን፡፡ በቴክኖሎጂ የሰበሰብናቸው ጓደኞች በአንድ ላይ ተጨምቀው አንድ የእውነት ጓደኛ አይወጣቸውም፡፡ በፌስ ቡክ አመት ሙሉ የደረሱን ግጥምና ዜናዎች አንዳቸውም ወደ ነፍሳችን በቋት አይደርሱም፡፡ ግን ነፍስ መዘናጋት የለባትም። መንገዱን አግኝታ ከፍ ወዳለው እውነት መድረስ አለባት፡፡ ታጎር ጥበብና ዜማን እንደ መንገድ ተጠቅም ራሱን አውቆ ፈጣሪው እንዲመለከተው ፀለየ፡፡ ፀሎቱ ማህበረሰቡን ለማስተማር፣ ማወቁ እንዲታወቅ የሰበከበት አይደለም፡፡ ከፍ ወዳለው ፀጋ እንዳይወጣ ያገደውን የሆነውን የኢጐ እኔነኛዊነት ሰብሮ በመንፈሳዊ አይን የፈጣሪውን ልቦና ለመግዛት የሞከረበት ነው፡፡
በእኔ እምነት፤ ይህ አንድ ልዕለ ሰብ ሊያደርገው የሚገባው ብቸኛውና ዋነኛው ነገር ነው፡፡ እኔን የሰለቹኝ መጽሐፍት መነሻቸው ራሱ ደራሲው፣ መድረሻውም መልሶ ደራሲው ላይ መሆናቸው ነው። ይኼኔ ደራሲው፣ እኔ ዘንድ ሊደርስ ይቅርና ራሱም ዘንድ ሳይጠጋ ይቀራል።
ይኼንን መሰል ደራሲ የሚተቸውም ድራሸ ቢስ የሆነን ተጓዥ ተከትሎ ለመነዝነዝ የራሱን የነፍስ መንገድ የዘነጋው ነው፡፡ ሁለቱም ስተዋል፡፡ እኔ ግን ራሴን ማግኘት እፈልጋለሁ፡፡ ለማግኘት ደግሞ ጥሩ ምሳሌዎች ያስፈልጉኛል፡፡ ምሳሌዎቼን ለማወቅ የሰው ጥቆማን መጠቀምም ብክነት ነው፡፡ ሰው የሚጠቁመኝ ወዳልደረሰበት ወይንም ወደተሳሳተ ቅያስ ገብቶ ወደተቀረቀረበት ነው፡፡
የነፍሴን ጥያቄ ተከትዬ መጓዝ አለብኝ፡፡ ጥያቄዬና ጥያቄአቸው ተመሳሳይ የሆኑትን መንፈሳዊያን የጉዞ ካርታ በመጽሐፋቸው አሻራ እያጠናሁ… የራሴን አድራሻ ጥርጊያ ለመስራት ከእንግዲህ እጥራለሁ፡፡
ኦማር ካያም ከእንግዲህ አያገለግለኝም፡፡ እሱ እንቢታ ላይ ነው፡፡ “ይሄ ግልብጥ ቆሪ /ሰማይ የምንለው ከስሩ ተደፍተን ጭረን የምናድረው/ እጅህን አታንሳ እሱም የሚኖረው እንደኔ እና እንዳንተ ሲገለባበጥ ነው” የሚል የጉዞ መረጃ አልፈልግም፡፡
ለጥበበኛ ከመጠጥ እና ሴሰኝነት በላይ የሚታይ ግብን መፈለግ አለበት፡፡ ተቃራኒን እየጋጩ ከንቱነትን በተለያየ ዘርፈ እይታ ከማዋለድ ባሻገር የሚታሰስ እውነተኛ አድራሻ ለሰው ልጅ ነፍስ ያሻዋል፡፡
ጥበብ የቁሳዊ ተድላ ማዳመቂያ፣ የፈጣሪ ፍትህን ለመንግስት ጭቆና ማመቻቻ ሆኖ ስመለከት ጥበብ የሰይጣን ናት ብዬ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ “ጊታንጃሊን” ስመለከት… የፈጣሪንም የእውነት መንገድ ለነፍስ እውቀት ጥበብ ልታመቻች ትችላለች ብዬ ተደሰትኩኝ፡፡
እናም ካህሊል ጂብራን እንዴት “ነብይ” መሆን እንደሚችል በገፀባህርይው ቀርፆ እንዳሳየን ሁሉ፤ ታጐር ደግሞ ተራ ግለሰብ ሆኖ ፈጣሪን በጥበብ እና በዜማ ማናገር መቻሉን ለእኔ አሳየኝ፡፡ በስተመጨረሻ እንደ ታጐር፤
“The song that I came to sing remains unsung to this day
I have spent my days in stringing and in unstringing my instrument
The time has not come true, the words have not been rightly set
Only there is the agony of wishing in my heart”
ብዬ እስካሁን ዜማ ፍለጋ እውቀት እና እምነቴን ሳፈርስ እና ስቀልስ ያጠፋሁት ጊዜ መጥፎ አለመሆኑን እንድቀበል ያባብለኛል፡፡

Read 3179 times