Saturday, 05 March 2016 12:00

ሉሲዎቹ ከአልጄርያ አቻቸው ይገናኛሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በ2016  ካሜሩን ወደምታስተናግደው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ጉዞውን ነገ ይጀምራል፡፡ ሉሲዎቹ በሁለት ዙር 4 የደርሶ መልስ ጨዋታዎች የሚያደርጉ ሲሆን፤ ሁለቱን በአንደኛ ዙር ማጣርያ  ከአልጄርያ ጋርእንዲሁም ሁለቱን ከኬንያ ብሄራዊ ቡድን ጋር ይሆናል፡፡ የመጀመርያ ጨዋታቸው ነገ ከአልጄርያ አቻቸው የሚገናኙበት ሲሆን ለዚህ ወሳኝ ጨዋታ ሐሙስ ምሽት ወደ ስፍራው ተጉዘዋል።  የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን   ለሶስት ሳምንታት ዝግጅት ቢያደርግም ጠንካራ የወዳጅነት ጨዋታ አላደረገም፡፡ ዋና አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው በመጀመርያ ምርጫው 30 ተጫዋቾችን በመያዝ በሱሉልታ ልምምድ ሲያሰራ የቆየ ሲሆን ከዚያም 5 ተጨዋቾችን በመቀነስ  ካለፈው ሳምንት ጀምሮ 25 ተጫዋቾችን በመያዝ በአዲስ አበባ ስታድየም ዝግጅቱን ቀጥሏል፡፡ ወደአልጄርያ ያቀናው 20 ተጫዋቾችን በመያዝ ሲሆን ከአሰልጣኞች፣ የህክምና ባለሙያዎች ፣ የቡድን መሪ እና ጋዜጠኛን ያካተተው  የልኡካን ቡድን ብዛት 26 ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ   ብርሃኑ ግዛው ከሶከርኢትዮጵያ  ድረገፅ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ …ተጫዋቾቹ ከክለብ ውድድሮች እንዲሁም ከ17 እና 20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች እንደተውጣጡ  ገልፆ፤ ለ20 ቀናት የሰሩት የዝግጅት  በቂ እንደሆነ በማብራራት  ማጣርያዎችን በድል በመወጣት ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለመመለስ ጠንክረን እየሰራን እንገኛለን፡፡›› ብሏል
 ‹‹ በአልጀርስ በሚገባ እየተከላከልን በሚገኙ ክፍተቶች ግብ ለማስቆጠር የሚረዳንን አጨዋወት እንተገብራለን፡፡ እቅዳችን ጨዋታውን አሸንፈን አልያም ለመልሱ ጨዋታ የሚረዳንን ውጤት ይዘን መመለስ ነው።›› በማለትም  ለሶከርኢትዮጵያ  ተናግሯል፡፡ ብርሃኑ ግዛው የሴቶች አግር ኳስ ቡድን  አሰልጣኝ ሆኖ  በመስራት ከ17 ዓመታት በላይ ልምድ ያለው ሲሆን ብሄራዊ ቡድኑን ከአራት ዓመታት በላይ እንዳሰለጠነና  ለአፍሪካ ዋንጫ ባሳለፈበት ውጤቱ ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድኑን በኦሊምፒክም ማጣርያዎችም ከፍተኛ ተፎካካሪ አድርጎታል፡፡ በአሰልጣኝነት በሰራባቸው ዓመታት  የየካ ክፍለ ከተማ፣ ሴንትራል የጤና ኮሌጅ እንዲሁም አሁን ባለበት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን በሃላፊነት በመምራት አሰልጣኝ ብርሃኑ ባጠቃላይ 20 ዋንጫዎችን መሰብሰብ ችሏል።
የአልጄርያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ  ደረጃ በዓለም 77ኛ በአፍሪካ 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በውድድር ታሪኩ 4 ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ  ያለፈ ከመሆኑም በላይ የቅርብ ጊዜ ውጤቱ ባለፈው አመት የአረብ ሊግ ዋንጫን ያገኘበት ነው፡፡ የአልጄርያ ቡድን በስብስቡ በፕሮፌሽናል ደረጃ ፈረንሳይ ውስጥ የሚጫወቱ 11 ተጨዋቾችን አካትቷል፡፡

Read 3718 times