Saturday, 12 March 2016 10:12

ከእነመላኩ ፈንታ ጋር በሙስና ከተከሰሱት፣ ሶስቱ በእስራት ተቀጡ

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(0 votes)

- ከ3 ዓመት እስከ 7 ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል
- በሙስና ወንጀል ያፈሩት ሃብትን ንብረት ታግዷል

   ከቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣናት፣ ከእነመላኩ ፋንታ ጋር የሙስና ወንጀል ክስ ከተመሰረተባቸው ውስጥ የአዳማ ገቢዎችና ጉምሩክ ስራ አስኪያጅ የነበሩትን አቶ ተመስገን ጉላልን ጨምሮ ሶስት ተከሳሾች ላይ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከ3 ዓመት እስከ 7 ዓመት በሚደርስ እስራትና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡
የፀረ ሙስና ኮሚሽን የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው፤ አንደኛ ተከሳሽ ተመስገን ጉላል ከ1999 እስከ 2004 ዓ.ም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በተለያየ የስራ ኃላፊነት በሚሰሩበት ወቅት በመንግስት ስራ ወይም በሌላ መንገድ ከሚያገኙት ወይም ሲያገኙ ከነበረው ህጋዊ ገቢ ጋር የማይመጣጠን ሀብት በማፍራታቸው ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡  ተከሳሹ በወንድማቸው ካህሳይ ጉላል ስም በባንክ በተለያዩ ጊዚያት ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ በማስቀመጥና በማንቀሳቀስ፤ በ 2003 ዓ.ም በ2ኛ ተከሳሽ ወልደ ሚካኤል ኃለፎምና በ4ኛ ተከሳሽ በአቶ ብርሃኑ ዝናቡ አማካኝነት ከባንክ 10 ሚ. 500 ሺ ብር በመበደርና ከራሳቸው 10 ሚ. 500ሺ ብር በመጨመር በ21 ሚሊዮን ብር ጓደኛቸውና 4ኛ ተከሳሽ በሆኑት አቶ ብርኑ ስም ስድስት ቦቴ መኪኖች ከእነተሳቢያቸው መግዛታቸውን የክስ መዝገቡ ያስረዳል፡፡
ተከሳሹ በ2005 ዓ.ም ቦቴ መኪኖቹን በመሸጥ በወንድማቸው ተከሳሽ ካህሳይ ጉላይ ስም በ15 ሚሊዮን ብር ሁለት ዶዘሮችን መኪኖችን መግዛታቸውን የክስ መዝገቡ አብራርቷል፡፡
በተጨማሪም አቶ ተመስገን በ2ዐዐ4 ዓ.ም. በቦሌ ክ/ከ 325 ሜ.ካ ቦታ ላይ የተሰራን የመኖሪያ ቤት ወንድሙማቸው በሆነው በ5ኛ ተከሳሽ ካህሳይ ጉላል ስም በመግዛት ተከሳሹ በተለያየ ጊዜያት በድምሩ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ማስቀመጣቸውና ማንቀሳቀሳቸው ታውቋል፡፡
ተከሳሾቹ በተመሰረተባቸው በሙስና ወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብና በወንጀል በመርዳት የሙስና የወንጀል ክስ ጥፋተኛ መሆናቸው በማስረጃ በመረጋገጡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽ ተመስገን ጉላል፤ በ 7 አመት ከ6 ወር እስራትና በ35 ሺህ ብር እንዲቀጣ ውሳኔ ተላልፏል። 5ኛ ተከሳሽ ካህሳይ ጉላል፤ በ5 አመት ከ6 ወር እስራትና በ15 ሺህ ብር እንዲሁም 4ኛ ተከሳሽ ብርሃኑ ዝናቡ በ3 ዓመት ከ3 ወር እስራትና በ3ሺህ ብር እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ኮሚሽኑ በሙስና ወንጀል የተገኘውን ገንዘብና ንብረት በፍርድ ቤት ትእዛዝ እንዲታገድ ያደረገ ሲሆን ገንዘብና ንብረቱን የማስመለስ ስራም በሂደት ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

Read 2261 times