Saturday, 12 March 2016 10:19

በደቡብ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በአርባምንጭ ሆስፒታል ከ140 በላይ ህሙማን ህክምና እየተሰጣቸው ነው

     በደቡብ ክልል አርባምንጭ ዙሪያ አማሮና አባያ ወረዳዎች በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን ገላን ወረዳና በሶማሌ ክልል ሞያሌ ወረዳዎች ላይ የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ ሰሞኑን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ እንዳደረገው፤ በሶስቱ ክልሎች በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ በአተት በሽታ የተያዘ ሰው አፋጣኝ ህክምና ካላገኘ የመሞት ዕድሉ ከፍተኛ ነው ያለው መግለጫው፤ህብረተሰቡ በሽታውን ለመከላከል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል ብሏል፡፡
የአርባ ምንጭ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ቀፀላ ለማ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት በሽታው በወረርሽኝ መልክ ከተከሰተበት ከአለፈው እሁድ ጀምሮ ከ140 በላይ ህሙማን በዚሁ በሽታ ተይዘው ወደ ሆስፒታሉ መጥተዋል፡፡ ለህሙማኑ የህክምና ማዕከል ተቋቁሞ ዕርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ዶ/ሩ ገልፀዋል፡፡ በበሽታው ሳቢያ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ስለመኖራቸው እንደማያውቁ የተናገሩት ዶ/ሩ፤ ወደ ሆስፒታሉ የመጡ ህሙማን ግን ተገቢው ህክምና እየተደረገላቸው በመሆኑ የሞት አደጋ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡  
ከሰሞኑ ዝናባማ የአየር ንብረት ጋር በተያያዘ በሚከሰተው ጐርፍ፤ ምንጮች፣ የውሃ ጉድጓዶችና ወንዞች ስለሚበከሉና ይህም በሽታውን በቀላሉ ለማስተላለፍ የሚችል በመሆኑ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል ያለው ጤና ጥበቃ ሚ/ር፤ ለመጠጥነት የሚውሉ ውሃዎች በአግባቡ ተፈልተውና ቀዝቅዘው አሊያም በውሃ ማከሚያ መድሃኒቶች ታክመው ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡   

Read 1813 times