Saturday, 12 March 2016 11:15

በዕውቀቱና ድፍረቱ

Written by  በጌታሁን ሄራሞ (ኬሚካል መሐንዲስ)
Rate this item
(33 votes)

ክፍል 1
አዲሱን የበዕውቀቱ ስዩምን መፅሐፍ (ከአሜን ባሻገር) መገምገም እንደ ንባቡ አዝናኝ አይደለም,,,በጥቂቱ ሁለት ምክንያቶች ይኖሩኛል፡፡ የመጀመሪያው ከመጽሐፉ የትረካ መዋቅር ቅርጽ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ከጭብጦቹ ብዛት አንጻር ደራሲው ለተደራሲያኑ ሐሳቡን ለማስቃኘት የመረጠው ቅርጽ ቀጥተኛ ሳይሆን ባለ ብዙ መስኮት (Multiple frames) ነው፡፡ በዚህ ቅርጽ አማካይነትም በመጽሐፉ ጥቂት ገጾች ውስጥ አያሌ ክፍልፋይ ተረኮች (Fragmented stories) ሰፍረዋል፡፡ በክፍልፋይ ተረኮች ላይ የተጠነሰሰ ድርሰትን መገምገም ደግሞ ግምገማውንም ክፍልፋይ ማድረጉ የማይቀር ነው፡፡ ሐያሲው በደራሲው ከቀረቡለት ተረኮች ውስጥ አንዱን ብቻ መዝዞ ሊገመግም ይችላልና፡፡ ይህ ደግሞ በአንባቢያን ዘንድ ለገምጋሚው አተያይ አሉታዊ ትርጉምን አላብሶ የሂሱን ደረጃ ወደ  ፀጉር ስንጠቃነት አሊያም ስህተት አነፍናፊነት ሊያወርደው ይችላል፡፡
ሁለተኛው ምክንያቴ ከደራሲው የኮሜዲያንነት ባህርይ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ አንድ የኮሜዲያንነት ዝንባሌ ያለው ጸሐፊ ኮስታራ ጭብጥ ያላቸውን ሐሳቦችን ለማስተላለፍ ወደ እውነታው ዘውግ ዘው በሚልበት ቅጽበት በተደራሲያኑ ዘንድ የሚኖረው የቅቡልነት ደረጃ አጠያያቂ ነው፡፡ ይህ በኮሜዲያን የዕለት ተዕለት ማህበራዊ ሕይወት ላይ እንኳን ሳይቀር የሚንጸባረቅ እውነት ነው፡፡ የቀልደኛው እረኛ ምሳሌን በማንሳት ሐሳቤን ለማስረዳት ልሞክር…ይህ እረኛ ለሁለት ጊዜ ያህል ቀበሮ ሳይመጣበት እየጮኸ የመንደሩ ሰው ላይ ቀልዶ ተሳካለት፤በሦስተኛው ግን ቀበሮው የምር መጥቶበት ቢጮህ  የደረሰለት አልነበረም፡፡ እንግዲህ እረኛው ለሁለት ጊዜ ያህል የተወነው በኮሜዲው ዘውግ ሲሆን ሶስተኛው ግን በእውነታ(Realist) ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ በእውነታው ዘውግ ትወና ወቅት እረኛው ዕርዳታ ያላገኘው ጩኸቱ ሳይሰማለት ቀርቶ አልነበረም፡፡ ይልቅ በሰሚዎቹ ዘንድ የጩኸቱ ዘውግ እንደ ወትሮው በኮሜዲ ዘውግ በመመደቡ (Genre mis-catagorization) ነበር፡፡ ለእንደዚህ ዓይነቱ የዘውጎች ንብርብሮሽ (genre juxtaposition) በእጅጉ የተጋለጠ በመሆኑ ቀልደኛን ማሄስ በጣም ከባድ ነው፡፡
በዕውቀቱ በተለይም ፖለቲካ ቀመስ መጣጥፎቹን በተመለከተ ከላይ የጠቀስኩት ዓይነት ችግር እንደሚከሰት ገምቶ ገና ከጅምሩ ገፅ 8 ላይ ጥንቃቄ ሲያደርግ እንመለከታለን “…..ጠንከር ያለ የርዕዮተ ዓለም ትንታኔ ማንበብ የሚወድ ሰው በፖለቲካ ቀመስ መጣጥፎቼ ውስጥ የሚፈልገውን ማግኘቱን እጠራጠራለሁ፡፡ መጣጥፎቼ የእንጉርጉሮና የልግጫ ድብልቅ ናቸው” ይለናል፡፡ ይህች መልዕክት ከአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ተልዕኮ ጋር ተመሳሳይነት ያለውን ዓላማ ያነገበች ትመስላለች…. ፖለቲካ ቀመስ መጣጥፎቹ ላይ ጠንከር ያለ ሂስ ለመሰንዘር የሚያኮበክቡ ሐያሲያንን እዚያው በረራው ጣቢያ መሬት ላይ አጣብቃ የምታስቀር! እንዲሁም መጣጥፎቹ በሙሉ በ”ቀመስ” ጀምረው በ”ቀመስ” የመጠናቀቃቸውም ጉዳይ የሆነ ስነ ልቦናዊ ጨዋታን የሰነቁ ይመስላሉ፡፡ ለምሳሌ ደራሲው በመጽሐፉም ሆነ በሌሎች ሚዲያዎች ላይ ሥራዎቹ በምርምር የተቃኙ እንደሆኑ አብስሮልን ነበር፡፡ ምናልባትም   ይህ ገለጻው ወደ ታሪክ መጣጥፎቹ ያመላክት ይሆናል፡፡ ግን እርሱም ቢሆን “ቀመስ” ተብሎ ተቀምጧል፡፡ በምርምር የተደገፈና ጥናታዊ እንደሆነ የተነገረን ጽሁፍ ወደ “ቀመስነት” ደረጃ የወረደበት አግባብ ሊገባኝ አልቻለም፡፡
ስለ ሂስ ሲነሳ በብዙዎቻችን አዕምሮ ፈጥኖ የሚከሰተው የአፍራሽነት ሚናው ነው፡፡ የሂስ ምሁራን ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ ብዙዎቹ የሂስን ሚና የሚያነጻጽሩት እንክርዳድን ከስንዴው ከመለየት ጋር ነው፡፡ ስለዚህ የሂስ መኖር በግልባጩ የስንዴውን መኖርንም ያመለክታል ማለት ነው፡፡ እናም በዕውቀቱም በመጽሐፉ ውስጥ ብዙ ጠቃሚ ሐሳቦችን ማንሳቱን መካድ አይቻልም፡፡ በተለይ ታሪክ ነክ መጣጥፎቹ ላይ በደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ የታሪክ ሰነድ አጠቃቀስ ላይ አስተዋልኩ ያላቸው  ችግሮች በራሱ ላይ እንዳይደገሙ ያደረገው ጥንቃቄ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ይህን ጥረቱን እያደነቅሁ ይዘቱን በተመለከተ ግን ዳኝነቱን ለታሪክ ባለሙያዎች ትቼአለሁ፡፡
  ያም ሆነ ይህ በዕውቀቱ በሕብረተሰቡ የተለመደውን አተያይ ለማፍረስ በእጅጉ ከሚተጉት ደራሲያን ተርታ ይመደባል፡፡ በዚህም ሂደት ውስጥ ሊገጥመው የሚችለውን ተቃውሞ ከቁብ ሳይቆጥር በጥረቱ መቀጠሉን አደንቅለታለሁ “…በሐሳቤ ምክንያት የሚመጣውን መዓት ለብቻዬ ራሴን ችዬ ልጋፋጠው ዝግጁ ነኝ” ብሎን የለ? ስለዚህም የእርሱም ምልከታዎች ተራቸው ሲደርስ መፍረስ የሚችሉበት (Deconstructing deconstruction) አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል አስልቶ ሥነ ልቦናዊ ዝግጅት ማድረጉን ከዚሁ አባባሉ መገመት ይቻላል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ የተከበበው በውይይት በማያምን ትውልድ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚያነሳ ደራሲ የእርሱም አመለካከቶች ለውይይት ሲቀርቡ  በሆደ ሰፊነት በማስተናገድ ትውልዱን በኮነነበት ርዕሰ ጉዳይ ላይ አርአያነቱን በተግባር ማስመስከር ይጠበቅበታል፡፡ ለነገሩ የበዕውቀቱን  የውይይት ግብዣ ሁሌም በጥርጣሬ ዓይን እንደተመለከትኩት ነው፡፡ ለምን ቢባል እኔ እስከገባኝ የውይይት ጽንሰ ሐሳብ  ሀሁ የሚጀምረው የሌሎችን ሐሳብ ከማክበርና ስህተቶችን በጨዋ ደንብ ከማረም ነው፡፡ በዕውቀቱ ግን…. የሃይማኖት አባቶችን “የሃይማኖት እበቶች”፤ የምልክት ቋንቋን “የዱዳ ቋንቋ”፤ቤተመቅደስን “አዳራሽ”… እያለ በተቃራኒው ደግሞ የውይይት መድረክ ጠፋ ብሎ ቡራ ከረዩ ማለቱን ምን አመጣው? ስለዚህ እውነቱን እንነጋገር ካልን የበዕውቀቱ ጥሪ የሚያመዝነው ከውይይት ይልቅ ለልግጫና ለስድብ ነው፡፡ ለምሳሌ በገጽ 91 ላይ “አንድ ፍሬ ሽንብራ የሚያክል ቄስ ባንዲት ቃል “አሠርሁ ፈታሁ” እያለ ሀገር ሊያምስ ይችላል፡፡” ስሙ ይለያይ እንጂ አንድ ሰው ሲያጠፋ መወሰድ የሚገባቸው ዲሲፕሊን እርምጃዎች አንተ ቀደም ሲል ከነበርክበት ቤተ እምነት ውጪ በሌሎችም አቢያተ ክርስትያናት የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ ሊገባኝ ያልቻለው ጉዳዩ የሥልጣን ሆኖ እያለ የቁመት እጥረትን ከግዝት ጋር እንዴት እንዳገናኘኸው ነው፡፡ ለዚህ ለዚህማ በጣም አሪፍ ገጣሚ የሆኑ  ግን የሽምብራ ፍሬ የሚያካክሉ ገጣሚያን ስለመኖራቸው ስም ጠቅሼ ማስረዳት ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ ግን ግን ሚልኪ ባሻ በፌስ ቡክ ገጹ እንዳስቀመጠው፤ ትልቁ ችግርህ የ”Poetic Licence” ማሊያህን እንደለበስክ ወደ እውነታው ዘውግ ሜዳ መግባትህ ነው፡፡
 በጣም ያስደመመኝ ደግሞ እርሱ በሌላ ሰው እምነት ላይ እንደዚህ እየቀለደ በዘር ጉዳይ ግን ብዙ ርቀት ሄዶ “ቀልድ ክልክል ነው” የሚል አዋጅ መሰል ማስጠንቀቂያ ይሰጠናል… “መሳቅና መዝናናት መልካም ነው፤ግን ለመዝናናት ሲባል አብሮ መኖራችንን የመስዋእት በግ አድርገን እንዳናቀርብ መጠንቀቅ አለብን፡፡ በእንዲህ ዓይነት ቀልዶች ምክንያት የሚመጣውን መዘዝ ‘እንዴ ምን ታካብዳለህ?’ ‘ቀልድ አይደል እንዴ?  በሚል ማቅለያ ማብረድ የሚቻል አይደለም” ውድ ወዳጄ፤ ይህን ለማለት ድፍረቱንና ሞራሉን ከየት እንዳገኘህ ነው ግራ የገባኝ!
በሰው ዘር ስለአለመቀለድ ይህን ያህል አምርረህ የመከርከን ዘር በማንነት፤በህይወት ትርጉምና ማህበረሰባዊ ፋይዳዎች  ( Identity,Meaning and Community) ላይ መሠረት እንደሚጥል ስለገባህ ይመስለኛል፡፡ በሃይማኖት ጉዳዮች እስከ ወዲያኛው ጥግ እየቀለድክ በዘር ጉዳይ ግን ቀልድን የተቃወምከው በዘርና በሃይማኖት መካከል ምንም ዓይነት ቁርኝት የሌለ መስሎህ ከሆነ “Ethnicity and Religion : Intersections and comparisons, Edited by Joseph Ruane and Jennifer Todd” መጽሐፍ ፈልገህ አንብበው፡፡ መፅሐፉ ላይ ምናልባትም ጨርሶ ባልጠበከው ሁኔታ ዘርና ሃይማኖት ምን ያህል ቁርኝት እንዳላቸው ታጤናለህ፡፡ ገና ከመግቢያው ያለውን ብቻ ላስቀምጥልህ “…Religion has regained political prominence in the twenty first century and not least for the manner in which it intersects with ethnicity. Many ethnic conflicts have a strong religious dimension, and religion appears as a powerful force of mobilsation, solidarity, and violence. Religion and ethnicity can each other act as base of identity, group formation and communal conflict, They can also overlap, with ethnic and religious boundaries coinciding, partially or completely, internally nested or intersecting”
የበዕውቀቱ የአላዋቂነት ድፍረት ከላይ ብቻ በተጠቀሰው የሚያበቃ አይደለም፡፡ በተለይም ከክርስትና ጋር ፍቺ ፈጽሜአለሁ እያለ ክርስትናን በተመለከተ መጽሐፉ ላይ የፈፀማቸውን ስሕተቶች ስናጤናቸው ቀደም ሲል ከእምነቱ ጋር ጋብቻ ስለመፈፀሙ እንድንጠራጠር ያደርጉናል፡፡ ለምሳሌ በገጽ 97 ላይ  “ስምና ማንነት” በሚለው መጣጥፉ፤  በኢትዮጵያ  ውስጥ የነበረውን የስም ለውጥን ሂደት መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሰው የስም ለውጥ ታሪክ (ከሳውል ወደ ጳውሎስ) ጋር እያነጻጸረ ሊያስረዳን ይሞክራል፡፡… “በቀደሙት ንጉሠ ነገሥታት ዘመን የማእከላዊው መንግስት ርእዮተ ዓለም ክርስትና ነበር፡፡ ክርስትና መነሳት የሙሉ ዜግነት መሥፈርት ነበር ሊባል ይችላል፡፡…ሳውል የተባለ ይሁዲ ወደ ክርስትና ሲመጣ አሮጌ ስሙን ካሮጌ እምነቱ ጋር አራግፎ ጳውሎስ የሚል አዲስ ስም እንደተቀበለ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ተተርልኮናል፡፡” ይለናል፡፡ በዕውቀቱ በቀደሙት ንጉሠ ነገሥታት ዘመን ክርስትና በመንግስት ደረጃ የነበረውን ሚና በሐዋርያት ዘመን ከነበረው ጋር ተመሳሳይ አድርጎ ማቅረቡ አደረኩ ያለውን ጥናቱን ገደል የሚከት ነው (ይህን ግድፈት በፌስ ቡክ ገጹ ከማንም በፊት ግልጽ ያደረገው  ሚልኪ ባሻ ነው.)፡፡ ውድ ወዳጄ፤ ሳውል ወደ ጳውሎስ በተቀየረበት ዘመን የማእከላዊው መንግስት እምነት የነበረው የይሁዲ እምነት ነበር፡፡ ክርስትና የአናሳዎቹ እምነት ነበር፡፡ በጊዜው የሳውል የስሙ ለውጥ በመንግስት የሚያሸልመው ወይም የዜግነት መብት የሚያሰጠው ሳይሆን (እንደ ኢትዮጵያዊ ማለቴ ነው)  ለከፍተኛ ስደትና እንግልት የሚዳርገው ነበር፡፡ ከክርስትና ጋር ጋብቻ ፈጽሜ ነበር ከሚል ሰው እንደዚህ ዓይነት ተራ ስሕተት አይጠበቅም፡፡
ሌላው የበዕውቀቱ የአላዋቂነት ገለፃው፣ በገጽ 216 የሚገኘው ነው፡፡ እዚህ ጋ ደግሞ በዕውቀቱ በክርስትናና በእምነቱ ተከታዮች መካከል ያለውን ልዩነት ማጤን አቅቶት የመሰለውን ሲጽፍ እንመለከታለን፡፡ “ክርስትና በጥንታዊው ቁመናው እንደ ማንኛውም የአንድ አምላክ ሃይማኖት ሌሎችን አምላኮችና ሌሎችን ባህሎች የሚችልበት ሆደ ሰፊነት አልነበረውም፡፡ እምነቱን ባስፋፉት ሰዎች አስተያየት የክብር የእውነት እና የቅድስና ምንጭ አንድ ሃይማኖትና አንድ ጥምቀት ሲሆን ከዚያ ውጪ ያለው የሚናቅና የሚነቀፍ ነበር፡፡ ክርስትና የነገሮች መስፈሪያ በሆነበት ዘመን ላይ የዋቄፈታና የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነውን ዜጋ በአረሚነት መፈረጅ የተለመደ ነበር፡፡”  ልብ በሉ፤ ልጁ ይህን ሁሉ የክስ መዓት እያዘነበ ያለው ክርስትያኖች ላይ ሳይሆን የክርስትና አስተምህሮት ላይ ነው፡፡ የክርስትና አስተምህሮ ደግሞ ጥንታዊ፤ ወቅታዊ ምናምን የሚባል ቁመና የለውም፡፡  እስቲ በየትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው ክርስትና ጥንትም ሆነ አሁን ሰውን (ማንኛውንም) ስለ መናቅና ስለ መንቀፍ የሚያስተምረው? (የእምነቱ ተከታዮች የሚሰሩት ስሕተት የለም እያልኩ ግን አይደለም።) እንዲያውም እርሱ  በእምነቱ ላይ እንደልቡ መናገሩ  የሚያመለክተው የእምነቱን ሆደ ሰፊነት መሰለኝ፡፡ ደግሞ የምን ብልጣ ብልጥነት ነው? “እንደ ማንኛውም የአንድ አምላክ ሃይማኖት” ያልካቸውንም እስቲ እንደ ክርስትናው ለመወረፍ ሞክር!  ምርምር እንደ ወለደው የነገርከን ጽሑፍህ ሚዛናዊነትን ሲጠብቅ ማየት አልቻልንም!
የሚገርመው ከላይ ያየነውን የበዕውቀቱን ማጠቃለያ የሚቃረን ነገር በገጽ 220 ላይ መስፈሩ ነው፡፡ በዚህ ክፍል ደራሲው የሚያወሳን ስለ አንድ የካቶሊክ ሐዋርያና (አባ ማስያስ) ሞቲ አባ ባጊቦ ስለተባለ የኦሮሞ ተዋላጅ ነው። በዕውቀቱ፤ ሞቲ በልማድ የእስልምና እምነት ተከታይ ሲሆን ውስጡን ግን እምነቱ ወደ ዴይዚም ይጠጋል ይለናል፡፡ የአቡነ ማስያስ ዋና ዓላማ ሞቲን ማጥመቅ ቢሆንም ሞቲ ግን ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ እንግዲህ ቀደም ሲል በዕውቀቱ ስለ ክርስትና ሆደ ሰፊ አለመሆን “ያስተማረንን” ተግባራዊ ብናደርግ ሞቲ አባ ባጊቦን መከተል የነበረበት ንቀት መሆን ነበረበት፡፡ እዚህ ጋ ግን በዕውቀቱ የሚነግረን ታሪክ ፈጽሞ ተቃራኒውን ነው። አቡነ ማስያስ የክርስትናን እምነት ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነውን ሞቲ አባ ባጊቦን ያደነቀው እንደዚህ በማለት ነበር፡፡ “ኢትዮጵያ ውስጥ በቆየሁባቸው ዓመታት ልኡላንና ነገሥታትን የማግኘት ዕድል ገጥሞኛል፡፡ የአባ ባጊቦን ያክል ያስደነቀኝ  ግን አልነበረም፡፡ እሱ ታላላቅ ተሰጥኦዎች የታደለ ነበር፡፡ ከአፍሪካ ከስንት አንድ የሚገኝ ዓይነት ሰው ነው፡፡ …ተወዳጅ አልፎ አልፎም ጨካኝ፤ በፍርዱ ቀጥተኛ ቀልጣፋ….ብሩህ አዕምሮ የታደለ በመሆኑ አባ ባጊቦ ትክክለኛ ትምህርት የማግኘት እድል ቢያገኝ ኖሮ ኢምፓየር መምራት የሚችል የተዋጣለት ፈላስፋ ይሆን ነበር፡፡”
ሌላ ጉድ ደግሞ በገጽ  228 ላይ ይገኛል፡፡ ደራሲው በገጽ 216 ላይ “ክርስትና በጥንታዊው ቁመናው እንደ ማንኛውም የአንድ አምላክ ሃይማኖት ሌሎችን አምላኮችና ሌሎችን ባህሎች የሚችልበት ሆደ ሰፊነት አልነበረውም፡፡” ያላለውን ያህል በገጽ  228 በተቃራኒው በክርስትና እምነታቸው የሚታወቁት ራስ ጉግሳና ወራሹ ራስ ዓሊ የቱን ያህል ሆደ ሰፊ እንደነበሩ ያብራራልናል። የሚገርመው ይህ ማብራሪያው ቀደም ሲል ካለው ጋር እንዳይጋጭበት የታሪክ መዘውሩን ወደ ራሱ አቅጣጫ ለማሾር ሲል ሆደ ሰፊነታቸውን ከክርስትና ጋር ሳይሆን ከሰብዕናቸው ጋር ለማዛመድ ይዳክራል፡፡ ራስ ጉግሳና ራስ አሊ ክርስትያን ካልነበሩ አሮሞዎችና እስላሞች ጋር ተቻችለው ለመኖራቸው የሰጠው ምክንያት የራሶቹ ልዩ ችሎታ እንጂ የክርስትና ባሕርይ እንዳልነበረ ነው። አንባቢያንን ይቅርታ ጠይቄ በእንግሊዝኛ ደግሞ እንደዚህ ላስቀምጠው… (This guy is attempting to cheat us! When he finds something wrong within Christian leaders, he will attribute that blame to Christianity, when he finds something good within them he invests all his might to internalize such qualities as an outcome of personal achievement) ውድ በዕውቀቱ፤ በተሰጥዖህ የምትጽፋቸውን መጣጥፎችህን (ግጥሞችህን አጫጭር ልብ ወለዶች፤ዘና-አድርጌ(Humor) ጽሑፎች፤ወግ-ነክ መጣጥፎች) እንዴት እንደምወዳቸው ልነግርህ አልችልም፡፡ ለምሳሌ በአዲሱ መጽሐፍህ “አሜሪካን ዐየን” መጣጥፍህ ምርጥ ነው..በተለይ አሜሪካንን ለማየት ዕድሉን ላላገኙት! ከተሰጥኦህ ውጪ ለሆኑ ዘውጎች ግን ….እኔ እንጃ!
የቦታን ሥነ ክስተትና የኪነ ሕንጻን ስነ ልቦናን (Place Phenomenology and Psychology of Architecture) ዲሲፕሊኖችን በዕውቀቱ በጅምላ ጨራሽ ድፍረቱ የቱን ያህል እንዳደቀቃቸው ለማየት ወደ ገጽ 171 ልመልሳችሁ ነው፡፡ በዚህ መጣጥፍ በዕውቀቱ ስለ አምልኮ ቦታዎች መፍረስ እንደዚህ ይላል፡፡ “ቤተክርስትያን ወይም መስጊድ ሲቃጠል የሚጎዳው እምነቱን አይደለም። እምነቱማ በምዕመናን ልብ ውስጥ በእልክ ይበልጥ እየተንቀለቀለ ይኖራል፡፡
የእምነት ሥርዓቱ ጠላት ባልደረሰበት ሀገር ውስጥ በሚገኝ ቤተ አምልኮ ውስጥ ይቀጥላል፡፡” እንዲሁ ላይ ላዩን ስናየው በዕውቀቱ የሚለው ነገር ልክ ይመስላል፡፡ ቦታ በእምነትም ሆነ በሰው ስሜት ላይ ስለሚፈጥረው ስነ ክስተታዊም ሆነ ስነ ልቦናዊ ጫና ግን ምንም መረጃ እንደሌለው ድፍረቱ ያሳብቅበታል። በአንድ ወቅት ሊኮርቡዛየር የተባለ ዘመናዊው የኪነ ህንጻ አጋፋሪ እንደ በዕውቀቱ የቦታና እምነት ቁርኝትን ከቁብ ሳይቆጥር በአንድ የካቶሊክ ቤተክርስትያን ውስጥ አዲስ የዲዛይን ዕቅድ አወጣ። በዚህም እቅድ መሠረት ቤተመቅደስ ውስጥ ያለው የድንግል ማርያም ምስል በአንድ ቦታ ከመሆን ይልቅ ተንቀሳቃሽ ይሆንና በውጪ ላሉትም ምዕመናን ለዕይታ ይበቃል ብሎ ሐሳብ ሰጠና ሞከረ፡፡ ንድፉ ወደ ተግባር ተቀይሮ ለምዕመኑ ይፋ በሆነበት ወቅት ግን ከሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው፡፡ የህዝቡ ምላሽ “እመቤታችንን ለምን በኮንቬየር ላይ ታንከራትታላችሁ? የኛ ጸሎት የሚሰማው እዚያው በክብር ባለችበት ነው። እኛ ተንቀሳቅሰን እርሷ ወዳለችብት ሄደን እንማጸናታለን፤ ጸሎታችን የሚደመጠው የበፊቱ ቦታዋ ስትሆን ነው“ የሚል ነበር። ቦታም ሆነ ኪነ ሕንፃ  በትውስታ አጋፋሪነት በሰው አስተሳሳብም ሆነ እምነት ጫና ይፈጥራል። ከዚህ ባሻገር ኪነ ሕንጻ የድንጋይና የሲሚንቶ ክምር ብቻ አይደለም፡፡ የድንጋይ ክምር ብቻ በሚመስለን ነገር ውስጥ ትውስታ አለ፤  የዘመኑ ዕውቀት፤ መንፈስና  ሥልጣኔም አርፎበታል፡፡ በዕውቀቱ ከልክ ባለፈ ድፍረት ገዳፊና  (Reductionist) እርግጠኛ  ሆኖ “ቤተክርስትያን/መስጊድ ሲፈርስ እምነት አይጎዳም” ያለው የእርሱን  አባባል ልጠቀምና “ሙልጭ ያለ ኢ-አማኒ” ስለሆነ መሰለኝ፡፡    
ኪነ ሕንጻ ለበዕውቀቱ የቁስ ቁልል ብቻ ነው፤ለዚህም ነው ህንጻውን አድንቆ ለህንጻው መከሰት ምክንያት የሆነውን እምነት በቅርቡ ይጠፋል በማለት ስንቶች ተመኝተው ያልሆነላቸውን ትንቢት አርፍዶ መጥቶ የሚያወራልን! እንደዚህ ይለናል በገጽ 171 “ …ተወደደም ተጠላም ነገ ከነገ ወዲያ ሣይንስ ሲጎለብት ሐብት እየተትረፈረፈ ሲሄድ የአምልኮ መንፈስ እየቀዘቀዘ እንደሚሄድ አያጠራጥርም፡፡ እምነት የሚባለው ነገር ጨርሶ እንከዋ ባይወገድ አምልኮ ቦታን የሙጥኝ የሚል እምነት እንደሚወገድ መገመት ይቻላል፡፡ ለጥንታዊ ስነሕንጻዎች እና ለብራናዎች ያለን አድናቆት ግን በቀላሉ አይበርድም፡፡ ስነ ውበት ከእምነት የተሻለ ዕድሜ ይኖረዋልና፡፡ ይህን ስናስብ መስጊዱን በማፍረስ ፈንታ ቤተክርስትያን አድርገው ያቆዩንን፤ቤተክርስትያንን በማቃጣል ፈንታ ወደ መስጊድ ቀይረው ያስተላለፉልንን አባቶቻችንን እናመሰግናቸዋለን፡፡” ይህ ምን የሚሉት ትንተና ነው? ጸሐፊው ዕውን የስነ ውበትና የሥነ ጥበብ አፍቃሪ ነው? ብራናውን ያደንቅና ብራናው እንዲከሰት መንስኤ የሆነው እምነት ድራሹ እንዲጠፋ “አማልክቱን” (ሳይንስም ሆነ የሀብት መትረፍርፍ) ይማጸናል፡፡ ወንዙን እያደነቀ የወንዙ መነሻ የሆነው ምንጭ እንዲደርቅለት ይጎመጃል፡፡ ውድ ወዳጄ፤ ጣልያን ሀገር የሚገኘውን “Sistine Chapel” በዓመት ወደ 25 ሚሊየን ቱሪስቶች እንደሚጎበኙት ሳታውቀው አትቀርም፡፡ ውስጡ ሲገባ ድንቅ ከሆኑ የሚካኤል አንጀሎ የጥበብ ሥራዎች የተነሳ እምነትን ከቤተመቅደሱ መለየት በማይቻል ደረጃ ተዋህደው ታገኛቸዋለህ፡፡ Andrew Graham የተባለ ጸሐፊ በ ““Michelangelo And The Sistine Chapel”  መጽሐፉ ላይ እንደ አንተ ስነ ውበትን ብቻ አድንቆ አላቆመም፡፡ ለጥብብ ሥራው ምክንያት ለሆነው ለሚካኤልአንጀሎ እምነትም ዋጋ (Credit) ሰጥቶአል፡፡…” These works go to the heart of Michelangelo’s intensely powerful, idiosyncratic spirituality and reveal the full extent of his genius as a painter.”  ደግሞ ..ሳይንስ ሲጎለብት..ሀብት ሲትረፈረፍ.. ያለው ነገር እጅግ የሚያስደምም ነው፡፡ ደግሞ ሳይንስ የሚጎለብተው ነገ ከነገ ወዲያ ነው ይለናል፡፡ ውድ ወዳጄ፤ ምነው ዛሬ የሳይንስ መጎልበት አልታይህ አለ? ሳይንስ በጣም ጎልብቶአል… የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን አልፎ እኮ ወደ ኢንፎርሜሽን አብዮት ዘመን ከገባን እኮ ሰነባበተ። እምነት ግን አሁንም አለ፡፡ ደግሞስ ነገ ከነገ ወዲያ ሀብት ሲትረፈረፍ አምልኮ ድራሹ ይጠፋል ትለናለህ፡፡ እና ዛሬ ሀብት የተትረፈረላቸው ማህበረሰቦች የሉም ማለትህ ነው? ውድ በዕውቀቱ፤ ማተብህን ያስበጠሰው ፍሮይድ እንኳን የአንተን ያህል ድፍረት የተሞላበትን ትንታኔ በእምነት ላይ አልሰጠም፡፡
አንተ በጣም አሳንሰህ እንደተመለከትከው የእምነት ጉዳይ ከድህነት አሊያም ከዕውቀት ማነስ ጋር ተያይዞ የሚሄድ ነገር አይደለም፡፡ ዛሬ አንትሮፖሎጂስቶችን በጣም የደነቃቸው ጉዳይ በማንኛውም የሥልጣኔና የዕድገት እርከንና ደረጃ፣ ሃይማኖት ከሰው ልብ ውስጥ ሊጠፋ አለመቻሉ ነው፡፡ ይህንኑ በተመለከተ ማክስ ቻርልስዎርዝ የተባሉ ምሁር በ”Philosophy And Religion” መጽሐፋቸው ገጽ 4 ላይ እንደዚህ ይላሉ፡- ..”Despite Nietzsche’s prophesy of impending death of God and the confident prediction by Max Weber and other sociologists of the increasing secularization of western societs,philosophy of religion is now a flourishing industry”…”ከኒቼ እግዚአብሔር ይሞታል ትንቢት ማክስ ዌቤርና ሌሎች የማህበረሰብ ሳይንስ ባለሙያዎች ካስቀመጡት የዓለማዊነት መስፋፋት ግምት (በምዕራቡ ዓለም) በተቃራኒ ዛሬም የሃይማኖት ፍልስፍና ዘርፍ በማደግ ላይ ያለ ዘርፍ ነው”  እንግዲህ ትናንት ከትናንት ወዲያ እነ ኒቼ ልክ ዛሬ አንተ እንዳልከው “ነገ ከነገ ወዲያ…” እያሉ ስለ ሃይማኖት መጥፋት ብዙ ብለው ነበር፡፡ ግን እየሆነ ያለው ተቃራኒው ነው፡፡     
በመጨረሻም “ከአሜን ባሻገ”ር በዕውቀቱ ከመቼውም በበለጠ ግልጽነት በእርሱ አገላለጽ “ሙልጭ ያለ ኢ-አማኒነቱን” ይፋ ያደረገበት መጽሐፉ ነው። ሁሌም እንደምንለው እንደዚያ መሆኑ መብቱ ነው፡፡ ለዚያውም በውይይት የሚያምን ማህበረሰብ በሚኖርበት በምድረ አሜሪካ ቀርቶ እዚህም እያለ የግል ውሳኔው ይከበርለታል፡፡ ከዚህም ባለፈ በዕውቀቱ በመጽሐፉ ውስጥ ኢ-አማኒነቱን ብቻ ሳይሆን እንዴት ኢ-አማኒ ሊሆን እንደበቃም እኛ ሳንጠይቀው በራሱ ተነሻሽነት በገጽ 40 ላይ እንደዚህ በማለት አውግቶናል። “….የ3ኛ ዓመት የሳይኮሎጂ ተማሪ እያለሁ  “The Futrure of Illusion” የተባለውን የሲግመንድ ፍሮይድን መጽሐፍ አነበብኩና ከሃይማኖት ጋር ፍቺ ፈፀምኩ፡፡” በዕውቀቱ ያለእኛ ጥያቄ የኢ-አማኒነት የጉዞ ተረኩን ሊያካፍለን ፈቃደኛ ከሆነ፣ እኛ ደግሞ የትረካውን አግባብነት (Narrative Validity) በተመለከተ የመጠየቅ መብታችን መጠቀም ግድ ሊሆን ነው፡፡ ለመሆኑ ሲግመንድ ፍሮይድስ ማነው? የበዕውቄን ማተብ በብርሃን ፍጥነት ያስበጠሰው የፍሮይድ መጽሐፍ (“The Futrure of Illusion”) ዋና ይዘቱስ? ከ88 ዓመታት በፊት የተጻፈው የዚህ መጽሐፍ ወቅታዊ ምልከታ (contemporary view) ምን ይመስላል? አንድ ነገር ግን ከወዲሁ ማለት እፈልጋለሁ። ሲግመንድ ፍሮይድ እዚሁ መጽሐፉ ላይ ማንም ሰው መጽሐፉን ካነበበ በኋላ ከእምነቱ ጋር ፍቺ እንዲፈጽም አላደፋፈረም፡፡ በተለይም ከእምነታቸው ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ይህን ለማድረግ እንደማይደፍሩ አስምሮአል፡፡ ደፍሮ የሚያደርግ ሰው ካለም እሱ ጨካኝ ነው ብሎ ይደመድማል፡፡ በዕውቄ አልሰማ ያለው የአጎቱን ምክር ብቻ አይደለም…የሲግመንድ ፍሮይድን ጭምር እንጂ.. “በዕውቀቱና ድፍረቱ ክፍል 2” ሳምንት ይጠብቃችኋል፡፡ በቸር ያገናኘን!



Read 13355 times