Saturday, 12 March 2016 11:30

የፍርሐት ወግ

Written by  መሐመድ ነስሩ
Rate this item
(1 Vote)

 ሰዎች ነን፡፡
እንፈራለን፡፡
በሰዎች ህይወት ውስጥ አንድ እውነት የሆነ ስሜት አለ፡፡ እሱም ፍርሃት ነው፡፡ እንደ ሳቅ እንደ ለቅሶ፤ እንደ ሀዘን፣ እንደ ደስታ ሁሉ ፍርሃትም ከውስጣችን ይሰርፃል ወይም ከውጪ ወደ ውስጥ ይሰርጋል፡፡ የፍርሃት መነሻው ከየት እንደሆነ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ሊከብድ ይችላል፡፡ ምንጩ ከውስጥ ወይም ከውጪ ሊሆን ይችላል፡፡ ብቻ ግን ፍርሃት በዕለት ተዕለት ኑሯችን ውስጥ ክሱት መሆኑ እርግጥ ነው፡፡
የምንፈራው ለምንድን ነው? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ የተለያየ ነው፡፡ እንዳንታመም እንፈራለን፡፡ እንዳንከስር እንፈራለን፡፡ እንዳንራብ እንፈራለን፡፡ እንዳንጠማ እንፈራለን፡፡ እንዳንታረዝ እንፈራለን፡፡ እንዳንሞት እንፈራለን፡፡ ፍቅረኛችን እንዳትከዳን እንፈራለን፡፡ ትዳራችን እንዳይፈርስ እንፈራለን፡፡
ለልጆቻችን አስፈላጊውን ነገር አላሟላንላቸውም ብለን እናስባለን፡፡ እናስብና አስተዳደጋቸው ላይ ተፅዕኖ እንዳናሳድር እንፈራለን፡፡ ማህበራዊ ፍትህ ለማስፈን ተቀናቃኞቻችንን እንፈራለን፡፡ ፖለቲካ ውስጥ ከገባን እንዳንታሰር እንፈራለን፡፡ እንፈራለን… እንፈራለን… እንፈራለን….
ፍርሃታችን ፈርጀ ብዙ ነው፡፡ ፍርሃት ሁለት መልክ አለው፡፡ በጐና መጥፎ! አንዳንድ የስራ አመራር ሊቃውንት ፍርሃትን በበጐነቱ ይጠቅሳሉ፡፡ ፍርሃትን የፈጠራ ቆስቋሽ ሀይል አድርገው ያቀርባሉ። የውድቀት ፍርሃት ጠንቃቃ እንድንሆንና ወደ ስኬት ዓለም እንድንቀላቀል ይረዳናል፡፡ ፍርሃት ፈጠራን ያበረታታል፡፡ ይህ የሚሆነው ፍርሃቱ እጅና እግርን ሸብቦ የሚያቆራምት፣ ልብና አዕምሮን የሚያደንዘዝ ካልሆነ ነው፡፡ ፍርሃቱ ላለመውደቅ መፍጨርጨርን የሚፈጥር ከሆነ የስኬትን በር ማንኳኳታችን አሌ የሚባል አይደለም፡፡ ፍርሃት ወርቅ ነው፤ ህይወት እንድንዘራ፣ ወልደን እንድንስም፣ ዘርተን እንድንቅም ያደርገናል፡፡ ከምድር ላይ ሙሉ ለሙሉ መጥፋትንና መሞትን ስናስብ በልጅ በኩል ህያው እንድንሆን እንወልዳለን፡፡ በረሃብ እንዳንጠቃ ስንፈራ አርሰን እንዘራለን፡፡
በዕውቀቱ ስዩም “እንቅልፍና ዕድሜ; በተሰኘ መጽሐፉ እንዲህ ይላል፤
“የስልጣኔ መነሻ ፍርሃት እንጂ ጀግንነት አይደለም፡፡ መስጠም የማይፈራ ሰው የዋናን ጥበብ አይፈለስፍም፡፡ ፈሪው በጦርነት ውስጥ ወደ ኋላ ይሸሻል፡፡ ወይም ራሱን ከአደጋ የሚከላከልበት ያበጃል፡፡ ያረጀ ርስቱን ለጠላቶቹ ጥሎላቸው ሌላ ያልታሰሰ መሬት ይፈልጋል፡፡ ጠፉን መሬት ያለማል። (በዓለም ያለውን አዳዲስ መንገድ ሁሉ ፈሪዎች ይቀይሱታል፤ጀግኖች ይሰየሙበታል፡፡)”
በዕውቀቱ ይቀጥላል፤
“የራስ ቁሮች እና የደረት ጡርሮች፣ የጐበዙ ፈጠራዎች አይደሉም፡፡ ፈሪው ከጦርና ከሰይፍ ራሱን ለመጋረድ ሲል የፈለሰፋቸው ናቸው፡፡ የስልጣኔ ውጤት ሁሉ የፍርሃት ግርዶሽ ነው፡፡”
በሌላ መልኩ ፍርሃት አውዳሚ ሊሆን ይችላል። እንደ ደማሚት ስጋና ነፍስ የሚያፈርስ ክስተት። በፍርሃት ስለተፈጠርን ብቻ ያመለጡን ዕድሎች ስንት ናቸው? ፍርሃት መብቶቻችንን እንዳንጐናፀፍ ምን ያህል ተፅዕኖ አሳደረብን!?
ባለመናገር ደጃዝማችነት እንደሚባለው፣ በፍርሃታችን ምክንያት ብቻ አቅሙና ብቃቱ እያለን ስንቱን በረከት አጣን?!... ፍርሃት ከልክ በላይ የገነነበት ሰው የሚከተለው የደበበ ሰይፉ ግጥም ቁስሉን ሊያክለት ይችላል፡-
ፍርሃት አዶከብሬ
አያ እናት አይምሬ
የቁም መቃብሬ
የቅዠት ሀገሬ
ከሥጋ ከነፍሴ ከደሜ ቆንጥሬ
ከአጥንቴ ሰንጥሬ፤
ምስህን ሰጥቼህ ላመልህ ገብሬ፤
ያው ነህ አንተ ግና
ልንምህ አይላላ፡፡
ትጋልበኛለህ በእሾህ በቆንጥር ላይ
ጨለማ እንደ ግራር በቅሎበት የሚታይ
አንዲት ዘሀ-ጮራ
ለማትደፍርበት
እውነት- ፍቅር- ውበት
በተቀበሩበት፡፡
ገፀ ባህሪውን ፍርሃት ሙሉ ለሙሉ የተቆጣጠረው የፍርሃት ምርኮኛ ነው፡፡ ፍርሃታችንን በአግባቡ ካልያዝነውና ለመልካም ስኬት እንደገፊ ምክንያት ካልተጠቀምነው መጥፊያችን ሊሆን ይችላል፡፡ የፍርሃት አጋዥ የሆኑ በርካታ ተረቶች አሉን፡፡ መናገር ስንፈራ፣ “ዝም አይነቅዝም” እንላለን። እንደገና “ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባም” እንላለን፡፡ አሁንም እንደገና “ዝምታ ወርቅ ነው” እንላለን፡፡
እነዚህ ከፍርሃት ግርግም ውስጥ መውጣት ሲሳነን ፍርሃታችንን የምናፀድቅባቸው አባባሎቻችን ናቸው፡፡ የፍርሃታችን ቃፊሮች ብንልም እንችላለን። ፍርሃትን የሚያበረታ አንድ ተረትም አለን፡፡ “ፈሪ ለእናቱ” ስንል እንደመጣለን፡፡ “ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም; ይባላል፡፡ እኛ ደግሞ “ፈሪና እርጥብ እንጨት በቀላሉ አይነድም” ልንል እንችላለን፡፡ ፈሪ በፍርሃቱ እየተመራ ሰላማዊ አውድማዎች ላይ ይሰፍራል፡፡ ጦርንና ጦረኝነት በሩቁ ይሸሻል፡፡ እና በህይወት የመቆየት ዕድሉን ይጨምራል፡፡
በተቃራኒው ደግሞ ፍርሃቱ መጥፊያው ሊሆን ይችላል፡፡ ልቡ በፍርሃት የተቀየደበት ሰው እጁም ሽባ መሆኑ አይቀርም፡፡ ልቡን ፍርሃት ሲረታው እጅጉን ድካም ይገታዋል፡፡ ድካሙ የፍርሃት ልጅ ነው፡፡ ፍርሃታችን ስር ሰዶ አላንቀሳቀስ፣ አላላውስ ሲለን እንደ ዮሐንስ አድማሱ “ፍርሃት የኛ ጌታ” እያልን እንለማመን ይሆናል፡፡
ፍርሃት የኛ ጌታ
ፍርሃት የገዛን እኛ የፍርሃት ሀገር ዜጋ
በፍርሃት ብቻ መቸም መውጫ መግቢያችን የተዘጋ፣
ያለንበትም ቤቱ ሁሉ መላው አየሩ ተነፈገ፣
በውስጡም ያለነው እኛ ሰውነታችን ጠወለገ፡፡
ተው ልቀቀን ተው እባክህ እንደምን እንሁን ያንተ ዜጋ
እስኪ ሙትልን እስኪ ጥፋ ሕይወታችንን አትዝጋ፤
እስከአሁን ድረስ እስከዛሬ እንዲያው ተክዘን ብናየው
መች ነው ሰዓቱ ይህ ያንተ ጊዜ የሚያልፈው?
እስኪ ተጠየቅ እንጠይቅህ ፍርሃት የኛ ጌታ፣
እኛን ብቻ ነው ወይስ አሉ ያደረግሃቸው አውታታ?
ኧረ ምንድን ነው ምስጢሩ ያገዛዝህ ውል መሰረቱ?
ከቶ ምንድን ነው ስልጠትህ ይህ ሁሉ ፍጡር መራቆቱ?
ብርታት ድፍረትን ጥሎ ወኒ መቁረጥን አሽቀንጥሮ፣
ላንተ ብቻ እንዲህ መገዛቱ ዕራቁን ሁኖ ተዘርዝሮ፡፡
የፍርሃት ባሪያ ከሆንን ብዙ ነገር ሊጎድልብን ይችላል፡፡ ፍርሃት ተጭኖ ያጐብጠናል፤ ረግጦ ያስጐነብሰናል፣ ገፍትሮ ይጥለናል፡፡ መድኃኒቶች ህመም ከሚያስከትሉ ተውሳኮች ይሠራሉ፡፡ ፈውስ ህመሙን ከሚፈጥር መርዝ የሚቀመምበት ጊዜ አለ።
ፍርሃትም እንዲሁ ነው፤መልካምና መጥፎ ገጽታዎች አሉት፡፡ እነዚህ የፍርሃት መንታ መልኮች በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ህልው የሆኑ ነገሮች ናቸው፡፡ መልካም የሆነው ፍርሃት ባለቤት እንድንሆን እየተመኘን ወጋችንን ቋጨን፡፡    

Read 2124 times