Saturday, 12 March 2016 11:35

“በፊልም ሙያ መዝለቅ የሚቻለው ሥራውን ከወደድነው ብቻ ነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

ተወልዶ ያደገው ደሴ ከተማ ውስጥ ነው። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እዚያው ደሴ ተምሮ አጠናቅቋል፡፡ በ1995 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ የመጣው ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) ለመማር ነበር፡፡ ነገር ግን የIT ትምህርቱን ወደ ጎን ትቶ ማስተር የፊልም ትምህርት ቤት በመግባት ካሜራ ኤዲቲንግና ሌሎች ተያያዥ ሙያዎችን ተማረ፡፡ ለምን ይሆን? “አይራቅ”፣ “ሰኔ ሰላሳ”፣ “አምራን” እና “እኔ እና አንቺ” የተሰኙ ፊልሞችን ዳይሬክት በማድረግ ዕውቅናን ያተረፈው አርቲስት ፍቅረየሱስ ድንበሩ፤ ከ15 በላይ ፊልሞች ላይ በተለያየ መልኩ ተሳትፏል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከአርቲስቱ ጋር በሥራዎቹ፣ በሀገራችን ፊልሞችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተከታዩን ቃለምልልስ  አድርጋለች፡፡
       
    የአይቲ ትምህርትን አቋርጠህ እንዴት ወደ ፊልም ሥራ ገባህ?
እኔ የፊልም ስራ ፍላጎት ቀደም ሲልም ነበረኝ፤ ሆኖም እንዲህ ቶሎ እገባበታለሁ ብዬ አላሰብኩም። ከደሴ የመጣሁት ግን የIT ትምህርት ለመማር ነበር፡፡ በአጋጣሚ የአክስቴ ልጅ አርቲስት ዳዊት ነጋሽ በፊልም ስራ ውስጥ ስለነበር ቀልቤ ወደ ፊልሙ ተሰረቀ፡፡ አንዳንዴ በአካባቢሽ ያሉ ሰዎች ተፅዕኖ ያሳርፉብሻል፡፡ በዚህ መልኩ ወደ ማስተር ፊልም ት/ቤት ገብቼ ለአንድ ዓመት ያህል ለስራዬ ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶችን ተከታተልኩ፡፡ ዳዊት ነጋሽ “ኢዮሪካ”፣ “የፍቅር ኤቢሲዲ”፣ “የማያልቀው መንገድ; እና ሌሎች ፊልሞችን ሰርቷል፡፡ ከእርሱ ጋር ፊልም መስራት ጀመርኩኝ ማለት ነው፡፡
አንተ እስካሁን ዳይሬክት ካደረግካቸው ፊልሞች የትኞቹ ይበልጥ ተወደውልሃል?
እስካሁን አራት ጥሩ ጥሩ ፊልሞችን ዳይሬክት አድርጌያለሁ፡፡ ሁለቱን ማለትም “አምራን” እና “እኔና አንቺ” የተሰኙትን ከአርቲስት ሰለሞን ሙሄ ጋር ነው ዳይሬክት ያደረግነው፡፡ “አይራቅ” እና “ሰኔ ሰላሳ” የተሰኙትን ግን ራሴ ነኝ የሰራኋቸው፡፡ አራቱም ፊልሞች ጥሩ አድናቆትን ቢያተርፉልኝም በተለይ የበኃይሉ ዋሴ (ዋጄ) ስራዎች የሆኑት “አይራቅ” እና “ሰኔ ሰላሳ” እጅግ የወደድኳቸውና ተቀባይነትን ያተረፉ ፊልሞች ናቸው፡፡ በካሜራና በኤዲቲንግ በኩል ከ15 በላይ ፊልሞችን ሰርቻለሁ፤ እየሰራሁም ነው፡፡ የቤዛ ኃይሉና የበኃይሉ ዋሴን ድርሰት አሁንም ቀረፃ ላይ ነን፤ ዳይሬክት እያደረግሁ እገኛለሁ፡፡
ወደ ፊልሙ ስትገባ የጠበቅኸውና ያገኘኸው ነገር ምን ይመስላል?
በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ ወደ 12 ዓመታት ቆይቻለሁ፡፡ በፕሮዳክሽንም ከ15 በላይ ፊልሞችን ሰርቻለሁ፡፡ በአገራችን የፊልሙ እንቅስቃሴ ሲጀመር አንስቶ ነበርኩኝ ማለት ይቻላል፡፡ በፊልሙ ዘርፍ ውስጥ እጅግ በርካታ ፈተናዎች አሉ፡፡ አብረሽ የምትዘልቂው ግን ለሙያው እውነተኛ ፍቅር ካለሽና ስራውን ከወደድሽው ብቻ ነው፡፡ ትልቁና ዋናው የዘርፉ ችግር ፊልምን ለትርፍ ብለው የሚገቡበት ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን በዓመት መቶ ፊልም ቢሰራ እድለኛ የሆኑ በጣም ጥቂት ፊልሞች ሊያተርፉ ይችላሉ፡፡ እነዚያን ፊልሞች እንደ ምሳሌ ይወስዱና ለማትረፍ ብለው ይገባሉ፡፡ ነገር ግን የፊልም ሥራ ሂደት በጣም አድካሚ ነው፡፡
 ብዙ ጊዜ ባለሀብቶች ፊልም ልንሰራ ነበር ብለው ያማክሩኛል፡፡ የመጀመሪያው ጥያቄዬ ስራውን ትወዱታላችሁ ወይ? ነው፡፡ አዎ ይላሉ፡፡ ከውጭ ሲያዩት ስራው ደስ ቢልም ሲገባበት ከተጠበቀው ውጭ ነው፡፡ ከውጭ ያሉት ሰዎች ቁጭ ይሉና ከዚህ ሲኒማ ቤት ይህንን ያህል ቢያገኙ፣ ከዚያኛው ሲኒማ ቤት ይህንን ያህል ቢያገኙ ብለው ትርፉን በአራትና በአምስት ሚሊዮን ብር አድርሰውት ቁጭ ይላሉ፡፡ ፊልሙ ሲሰራ ግን ወይ ትርፍ?! … እነዚህን ሰዎች ደግማችሁ ፊልም ስሩ ብትያቸው በዞረበት አይዞሩም፡፡ አንድ ባለሀብት ደጋግሞ ፊልም ፕሮዱዩስ ካደረገ ብዙ አትርፏል ሳይሆን ስራውን ወዶታል ነው የምንለው፡፡  
የፊልም ስራ ብር ያላቸው ግን ሙያውን የማያውቁት ሰዎች እየገቡበት እየተበላሸ ነው ይባላል?
አንድ ሰሞን እንዲህ አይነት ነገር ነበር፡፡ ባለሀብቱ ብር ስለሰጠ ብቻ ፊልሙን እኔ ካልሰራሁት ይላል። ይህ እንግዲህ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ትንሽ አቅም ያለው የፊልም ባለሙያ እንደምንም ብሎ ራሱ ፊልሙን ፕሮዱዩስ እያደረገ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ይሰራል፡፡ ምንም አቅም ካጣ ሙያተኛ ጥሩ ነገር እስከሚመጣ ዘወር ሊል ይችላል፡፡ የፊልም ስራ እንኳን ሙያ የሌለው ጣልቃ ገብቶበት ሙያተኛ ከሆነው ሃያ እና ሰላሳ ሰው ጋር ስትሰሪ እንኳን ምንም አንቺ ጠንቃቃና ጥሩ ሙያተኛ ብትሆኚም ከቀሪዎቹ ጋር መቶ በመቶ ተግባብቶ መስራት አይቻልም፡፡ በፊልም ስራ አክተሮች ስትመለምይ ሁለት አይነት ተዋንያንን ነው የምታገኚው፡፡ ወይ ስራውን ሙያዬ ብለው የያዙትን ታገኛለሽ አሊያም ሌላ ስራ እየሰሩ በዳይሬክተሩ የሚመረጡ ይኖራሉ፡፡ ሁለተኛዎቹ ስለ ስራው ባህሪና ምን እንደሚፈልግ አያውቁም። ያንን የተመረጡበትን ስራ ሰርተው፣ እንደ ትርፍ ስራ ዞር ይላሉ፡፡ ይሄ ለፊልም ሰሪው እጅግ ከባድ ነው፡፡ ሥራን ሁሉ ያደክማል፡፡ እና የፊልም ሙያ ከባድና ፈታኝ ነው፡፡ ያም ሆኖ እኔ እስከማረጅ ድረስ ከነፈተናው በፊልም ስራ እቀጥላለሁ፡፡
የተደራጀ ስቱዲዮ እንዳለህና ፕሮዳክሽኖችን ራስህ እንደምትሰራ ሰምቻለሁ ------
እውነት ነው፡፡ ወደዚህ ሙያ እንድገባ አስተዋፅኦ ካደረገው የአክስቴ ልጅ ዳዊት ነጋሽ በተጨማሪ የአጎቴ ልጅ ሙሉጌታ አባተም ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ በተለይ የራሴ የተሟላ ስቱዲዮ እንዲኖረኝ ሙሉጌታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጎልኛል፡፡ በተለያዩ አገራት ለስራ ሲንቀሳቀስ ለስቱዲዮ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችን አምጥቶ አሟልቶልኛል፡፡ ስቱዲዮዬ “ኩል ፊልም ፕሮዳክሽን” ይባላል፡፡ በዚህ ስቱዲዮ የራሳችንንም ሆነ ሌሎች በርካታ ፊልሞችን ሰርተንበታል፤ እየሰራንበትም ነው፡፡
በፊት በፊት አንድ ፊልም ተሰርቶ ለአንድ አመትና ከዚያ በላይ በሲኒማ ቤት የመታየት እድል ነበረው፡፡ አሁን ግን ከሶስትና ከአራት ሳምንት በላይ አይታይም፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው?
በፊትም ብዙ የመታየት እድል አልነበረውም፤ የአሁኑ ግን በጣም አነሰ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በፊት  የሲኒማ ቤቶች በቁጥር አነስተኛ ነበር፡፡ ከሶስትና ከአራት አይበልጡም ነበር፡፡ እነዚህ ሲኒማ ቤቶች በየጊዜው ለሚመረተው ፊልም ለመዳረስ ፊልሞች ወረፋ ይጠብቁ ነበር፡፡ አሁን ግን ሲኒማ ቤቶች ቁጥራቸው ወደ 30 እየተጠጋ ነው፡፡ ስለዚህ ወረፋ የመጠበቁ ነገር ትንሽ ቀንሷል፡፡ ስለዚህ አንድ ፊልም የመጀመሪያ ሳምንት በሁሉም ሲኒማ ቤት ይታያል። በሁለተኛው ሳምንት የተወሰኑ ሲኒማ ቤቶች ይገኛል። በሶስተኛው ሳምንት ሁለትና ሶስት ሲኒማ ቤቶች ይገኛል፡፡ እነዛ ሲኒማ ቤቶች ካለሽ ጊዜና የቦታ ርቀት ጋር ላይስማሙ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ አንቺ ከአዲሱ ገበያ ሆነሽ ፊልሙ ያለው ሳሪስ ሲሆን ርቀቱን ታስቢና በቃ በቪሲዲ ሲወርድ አየዋለሁ ብለሽ ትተይዋለሽ፡፡ ይሄ ለፊልሙ ከፍተኛ ችግር ይፈጥራል፡፡
በሌላ በኩል ሲኒማ ቤቶች እየተከፈቱ ስለሆነ የፊልም ሽሚያ ላይ ናቸው፡፡ ስለዚህ ፊልሙ አዲስ ብቻ ይሁን እንጂ ይዘቱ ምንም ይሁን ምን ግዴላቸውም፡፡ ይሄ ደግሞ ገንዘቡን ከፍሎ ጊዜውን ሰውቶ የሚመጣውን ተመልካች ያስከፋል፡፡ በፊልም ስራ ላይ እምነት እንዳይኖረውም ያደርጋል፡፡ ይሄ ደግሞ ኢንዱስትሪውን በእጅጉ ይጎዳዋል፡፡ አሁን በሳምንት ውስጥ ከሀሙስ እስከ እሁድ ሲኒማ ቤት ብትሄጂ አዲስ ሲኒማ ነው የሚታየው፡፡ በነዚህ ቀናት አንድ ፊልም ለምሳሌ ሀሙስ በ8፡00፣ 10፡00 እና በ12 ሰዓት አንድ ፊልም ነው የሚታየው። ምሽቱንም ጨምሮ በሁሉም ሲኒማ ቤት አንድ ፊልም ነው የምታይው፡፡
በዛን ሰዓት በጥቆማ ካላየሽው በሁለተኛው ሳምንት ያንን ፊልም በተወሰነ ሲኒማ ቤት የምታገኚው፡፡ ከሰኞ እስከ ረቡዕ ባለው ጊዜ ማለት ነው፡፡ ሀሙስ እንደገና  ሌላ አዲስ ፊልም ይጀምራል፡፡ እኛ አገር ደግሞ ማስታወቂያ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ከማስነገር የአፍ ለአፍ ማስታወቂያ የበለጠ ይሰራል። እንትን ፊልም እኮ አሪፍ ነው፤ እስኪ እይው ብዬሽ፣ በሁለተኛው ሳምንት ስትሄጂ የለም፤ ይሄ በጣም መጥፎ ነው፡፡
ስለዚህ የሲኒማ ቤቶች መብዛት ጥሩ አይደለም እያልከኝ ነው?
በፍፁም አማራጭማ አስፈላጊ ነው፡፡ ፊልሞች የሚመዘኑበት መንገድ አዲስ መሆናቸው ብቻ መሆኑ ጥሩ ጥሩ ፊልሞች፣ የተደከመባቸውና አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፊልሞች በግርግር ሳይታዩ እንዲቀሩ ያደርጋል፡፡ ሲኒማ ቤቶች አዲስ ፊልሞችን ብቻ እየተሻሙ የሚያሳዩበት መንገድ ሲኒማውን ይጎዳዋል ነው ያልኩት፡፡ ፊልም መብዛቱ ሳይሆን መመዘኛ መንገዱ ላይ ትኩረት መደረግ አለበት፤ ካልሆነ መጥፎ ነው፡፡ እኔ ደክሜ በታሪኩም በፕሮዳክሽኑም አሪፍ ፊልም ሰርቼ፣ በግርግርና በለብለብ ከተሰሩ ፊልሞች ጋር የእኔም ፋይዳው ሳይጤን የሚያልፍ ከሆነ፣ ነገም እኔ ፋይዳ ላለው ፊልም ላልጨነቅ ነው ማለት ነው፡፡ ትልቁ ጉዳት ይሄ ነው፡፡
ለአገራችን ፊልም ምን ትመኛለህ? የት ደርሶ ማየት ትፈልጋለህ?
እኔ ፊልሙ እንደ ሆሊውድ እንኳን ባይሆን ኢንዱስትሪው ተለውጦ አድጎ ማየት እፈልጋለሁ። ከልብ ከተሰራ፣ ፓሽን ባላቸው ሙያተኞች ከተሰራ፣ ባለድርሻ አካላት ማለትም መንግስት፣ ሲኒማ ቤቶች፣ ባለሙያዎች የድርሻቸውን ከተወጡ ፊልሙ የምንፈልገው ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡ አሁን ግን በሁሉም አካላት በኩል ደከም ያለ ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በርካታ አገራዊ ድራማዎች እየታዩ ነው፡፡ እንደ ባለሙያ ድራማዎቹ ላይ ምን አስተያየት አለህ?
ድራማዎቹን ሁሉንም ባይሆን አብዛኛዎቹን አያቸዋለሁ፡፡ በነገራችን ላይ የኪነ ጥበብ ስራ ጥራቱን እስከጠበቀ ድረስ መብዛቱ ምንም ችግር የለውም፡፡ አማራጭ ይሆናል፡፡ ተመልካቹም አንዱ ድራማ ባይመቸው ቴሌቪዥኑን አጥፍቶ ቁጭ ከሚል ሌላውን በአማራጭነት ያያል፡፡ ጥራት ካለውና ከበዛ ስራው ፉክክርንም ስለሚያመጣ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ሁለት ድራማዎች ከዚህ ቀደም በስፖንሰርም በጥቅምም የተሻሉ ስለነበሩ ሁሉም ግር ብሎ ወደዚያ  የመግባት ነገር ይታያል፡፡ አንድ ሰሞን የሆነ ጥሩ ፊልም ለማየት ረጅም የሲኒማ ቤት ሰልፍ ከታየ ሁሉም ፊልም ለመስራት ይነሳል፡፡ ይሄ አግባብ አይደለም፡፡ ነገር ግን ጥራቱን እስከጠበቀና ለተመልካች እስከመጠነ ድረስ መብዛቱ ችግር የለውም፡፡
 አሁን ከሚታዩት ድራማዎች የማረከህ አለ?
ሆነ ብዬ ተከታትዬ የማየው ድራማ የለም፡፡ ለምሳሌ አንዱን ድራማ በዚህ ሳምንት ካየሁ ቀጣዩን ክፍል የማየው ከሁለትና ሶስት ሳምንታት በኋላ ሊሆን ይችላል፡፡
ለምን?
አንደኛ ከስራ ብዛት ነው፤ ድራማዎቹ በሚታዩበት ሰዓት እኔ ወይ ቀረጻ ላይ ወይ ሌላ ስራ ላይ ልሆን እችላለሁ፡፡ ሌላው ደግሞ የተወሰኑትን ሁለት ሶስት ሳምንት አከታትዬ ካየኋቸው በኋላ ሀሳብ እንኳን አይኖራቸውም፡፡ አንድ ድራማ በዚህ ሳምንት አንድ ሀሳብ አስተላልፎ በቀጣዩ ሳምንት ጓጉተሽ እንድትጠብቂው ማድረግ አለበት፡፡ አንዳንዶቹ ይሄን ነገር አጣባቸውና እሰለቻለሁ፡፡ ይሄ ደግሞ ይሄን ይሄን ድራማ በደንብ አያለሁ ለማለት እንዳልችል ያደርገኛል፡፡
የውጭ ድራማዎችንና ፊልሞችንስ ታያለህ?
በተቻለኝ መጠንና ባለኝ ሰዓት የውጭዎቹን በተለይ ሲትኮም ድራማዎችን አያለሁ፡፡ ለምሳሌ “The Big Bang Theory”ን አያለሁ፤አሁን ድንገት ስለጠየቅሽኝ ነው እንጂ ሌሎችም አሉ፡፡  
አገራችን የሶስት ሺህ ዓመት ታሪክ ቢኖራትም ፊልሞቻችን በአብዛኛው ሃሳብ የላቸውም እየተባሉ ይተቻሉ፡፡ በተለይ ከውጭዎቹ ፊልሞች ጋር ሲነጻጸሩ------
በነገራችን ላይ እኛም አገር ሀሳብ ያላቸው ፊልሞች አሉ፤ በቁጥር ብዙ አይደሉም እንጂ፡፡ እሩቅ ሳልሄድ የኔን “አይራቅ” እና “ሰኔ ሰላሳ”ን ብጠቅስልሽ በጣም ጥሩ ሀሳቦች አሏቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ብዙ ግብረ መልሶችም አግኝቼባቸዋለሁ፡፡ ሆሊውድም ብትሄጂ ሀሳብ ያላቸውንም የሌላቸውንም ፊልሞች ታገኛለሽ፡፡ እኛ አገር ትልቅ ሀሳብ ያላቸውን ፊልሞች ለመስራት በጀትም ያስፈልጋል፤ ትልቅን ሀሳብ በትንሽ በጀት መስራት ይቻላል ይባላል፤ ነገር ግን ሀሳቡን የሚያጅቡ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ አንዱ ችግር በጀት ነው፡፡ ኢንዱስትሪው ምንም ዋስትና የለውም።
እንዴት ማለት?
ሀሳብ ኖሮኝ በትልቅ በጀት ትልቅ ፊልም ልስራ ብል፣ የምሰራው ተበድሬ ወይ ከቤተሰብ ወስጄ አሊያም ከባለሀብት ጋር ተፈራርሜ ይሆናል፡፡ ከዚያ በሲኒማ ቤት አሳይተሽ፣ ያንን ያወጣሽውን ብር እንኳ ብር መመለስ አትችይም፤ትርፍማ አይታሰብም። ዞሮ ዞሮ ቀደም ሲል ወዳነሳነው ችግር ነው የምመልስሽ፡፡ እኔ ስሰራ እርግጠኛ የማልሆንበትን በጀት አልይዝም፤ በአሁን ወቅት በ500 ሺህም በአምስት ሚሊዮንም ብር ፊልም መስራት ይቻላል። በጀትሽን ከፍ ባደረግሽ ቁጥር ስጋት እየጨመርሽ ነው የምትሄጂው፡፡ ካላተረፍሽ ባለሀብቱም እጁን ይሰበስባል፡፡ አሁን የአድዋን ታሪክ፣ የእነቴዎድሮስን ልስራ ብትይ ቦታው፣ የአክተሮች ብዛት --- ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ነው፡፡
አሁን ምን አይነት ስራ እየሰራህ ነው?
አሁን በዳይሬክቲንግ ያጋመስኩት አንድ ፊልም አለ፤ ጊዜያዊ ርዕሱ “ፅዮን” ይባላል፡፡ በሱ ስራ በጣም ውጥረት ውስጥ ነኝ፡፡ ሌሎችም ስራዎች ይቀጥላሉ፡፡ ፊልም የሙሉ ሰዓትና ዋና ስራዬ ነው፡፡  
ከዳይሬክቲንግ ውጭ ድርሰትና ትወና አትሞክርም?
በፍፁም፡፡ በድርሰቱም የለሁበትም፤ የመተወን ፍላጎትም የለኝም፡፡
በመጨረሻ …
በዙሪያዬ ያሉትን ባለቤቴን ሰላም አሰፋን፣ ዳዊት ነጋሽን፣ ሙሉጌታ አባተን፣ ልጆቼንና የ“ኩል ፊልም ፕሮዳክሽን” አባላትን በጣም አመሰግናለሁ፡፡ የእነሱ እገዛና ድጋፍ ባይኖር ለዚህ አልደርስም ነበር። ሌሎች ስማቸው ያልተጠቀሰ ከጎኔ ያሉትን ሁሉ አመሰግናለሁ፡፡   

Read 1643 times