Saturday, 19 March 2016 10:55

ኢዴፓ በግጭቶች ላይ አስቸኳይ ሃገራዊ ውይይት እንዲካሄድ ጠየቀ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

    በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የተከሰተው ግጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ያመለከተው የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ከመሆኑ በፊት መንግስት ሃገራዊ የውይይት መድረክ በአስቸኳይ እንዲያዘጋጅ ጠየቀ፡፡
ፓርቲው በሁለት ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ የአቋም መግለጫ ያወጣ ሲሆን፤ በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞና ግጭት መንግስት እያስተናገደበት ያለው አግባብ ትክክል አለመሆኑንና ችግሩ የመልካም አስተዳደር እጦት ውጤት ብቻ ነው በማለት አቅልሎ ከመመልከት ይልቅ የችግሩን ትክለኛ መነሻ እንዲመረምር አሳስቧል፡፡
በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የሚታዩት ወቅታዊ ግጭቶችና ጥያቄዎች በዋናነት ብሄረሰባዊ ማንነትን መሰረት አድርገው የሚፈጠሩ መሆናቸውን የፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት በመግለጫው ጠቅሶ፤ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ካልቻለ የሀገሪቱ ህልውና አደጋ ላይ ይወድቃል፤ ብሏል፡፡
መንግስት ችግሩን ለመፍታት የኃይል እርምጃ ከመጠቀም እንዲቆጠብ ያሳሰበው ፓርቲው፣ የደረሰው ጉዳት በገለልተኛ አካል እንዲጣራ፤ የታሰሩ ሰዎች ሰብአዊ ክብራቸው እንዲጠበቅ፤ በአስቸኳይ በግልፅ ፍ/ቤት እንዲዳኙ እና በጠበቆቻቸውና በቤተሰቦቻቸው እንዲጎበኙ ጠይቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በፓርላማ ቀርበው፣ “ለችግሩ ዋነኛ ተጠያቂዎቹ እኛ ነን” ማለታቸውን ፓርቲው አድንቆ፤ ተጠያቂ ነን ካሉ ተጠያቂዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለፍርድ እንዲያቀርቡ ጠይቋል፡፡
በኦሮሚያ ጉዳይ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ችግሩ የተፈታ በማስመሰል አድበስብሰው መዘገባቸውን የተቃወመው የፓርቲው መግለጫ፤ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎችም ግጭቱን ከሚያባብሱ ተግባራት እንዲቆጠቡ ጠይቋል፡፡
በሌላ በኩል በሀገሪቱ የተከሰተው የድርቅ ችግር፣ የሰው ህይወት መቅጠፍ ከመጀመሩ በፊት ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ህዝቡ ከምንጊዜውም በበለጠ ድጋፍ እንዲያደርጉ መንግስት ጥሪ እንዲያቀርብና ድርቁን ለፖለቲካ ፍጆታ ለመጠቀም የሚሞክሩ ኃይሎችም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ፓርቲው ጠይቋል፡፡


Read 1908 times