Saturday, 19 March 2016 11:02

ጠ/ሚ ኃይለ ማርያም ለአለማቀፉ ማህበረሰብ የእርዳታ ጥሪ አቀረቡ

Written by 
Rate this item
(31 votes)

እስካሁን የተደረገው እርዳታ በጣም አነስተኛ ነው ብለዋል

   ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለ ማርያም ደሳለኝ፤ በድርቁ ለተጎዱ ዜጎች ተጨማሪ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንዲያደርጉ ለአለማቀፉ ማህበረሰብና ለለጋሽ ተቋማት ከትናንት በስቲያ ጥሪ ማቅረባቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለ ማርያም ከአሶሼትድ ፕሬስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ እስካሁን ከአለማቀፉ ማህበረሰብ የተደረገው እርዳታ በጣም አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው በአብዛኛው ዘግይቶ ነው ማለታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ዩኒሴፍን የመሳሰሉ አለማቀፍ ተቋማት በአፋጣኝ ተጨማሪ እርዳታ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውንም ገልጿል፡፡ በሌሎች የአለማችን አካባቢዎች የተከሰቱት ቀውሶች እንዳሉ ሆነው አለማቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ችግር ችላ ማለት የለበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም፣ አገሪቱ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው 750 ሺህ ያህል የጎረቤት አገራት ስደተኞችን እንደማስጠለሏ፣ አለማቀፉ ማህበረሰብ ተጨማሪ ድጋፍ ሊያደርግላት ይገባል ብለዋል - ለአሶሼትድ ፕሬስ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትና ለጋሾች ከ10 ሚሊዮን በላይ የአገሪቱ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ማስታወቃቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ድርቁ ያስከተለውን ችግር ለመቋቋም ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ያስፈልጋል መባሉንም አስረድቷል፡፡
ከፍተኛውን የእርዳታ ያደረገቺው አገር አሜሪካ መሆኗን የጠቀሰው ዘገባው፤ አሜሪካ ከጥቅምት ወር 2014 አንስቶ ለኢትዮጵያ ከ532 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሰብአዊ ቀውስ ድጋፍ እርዳታ መለገሷንና የኢትዮጵያ መንግስትም ችግሩን ለመቆጣጠር ከ380 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጉን አክሎ ገልጿል፡፡


Read 5478 times