Saturday, 19 March 2016 11:14

ነቀምቴ = ታጨች

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

     ‹‹በውጭ መጓዝ በውስጥ መጓዝ ነው›› ይላሉ። በውጭ ሲጓዝ በውስጥ መጓዝ ያልቻለ ሰው፤ ‹‹እዚህ ቦታ ነበርኩ›› ከማለት የዘለለ ትርፍ አይኖረውም፡፡ ጉዞ ከልማድ እስር ቤት ያወጣል፡፡ ጠባብ ቦታ፤ ለጠባብ አዕምሮ ይዳርጋል፡፡ ጉዞ ፎገራን ዱር አድርጎ ከማሰብ ያወጣል፡፡ አባይን ሳያዩ ምንጭን እያመሰገኑ ከመኖር ችግር ይጠብቃል፡፡ መጓዝ ደስ ይላል፡፡ ነገሮችን በአዲስ መንገድ የማየት ዕድልን ይፈጥራል፡፡
ጉዞ ገንዘብ እና ፍላጎትን ይጠይቃል፡፡ ህይወታችን በመኖር ትግል የተገነዘ ሲሆን፤ መጓዝ አንችልም፡፡ የሰው ኢኮኖሚያዊ ጥረት፤ ራስን በሕይወት በማቆየት ትግል የተወሰነ በነበረበት የጥንቱ ዘመን፤መጓዝ ከአደን እና ከፍሬ ለቀማ ጋር እንጂ ከመዝናናት (ከማወቅ ጉጉት) ጋር ሊያያዝ አይችልም፡፡
በባህላዊ የኢቮሉዩሽን ሂደት ‹‹የተዝናኖት መደብ›› (Lesiure society) የተፈጠረው፤ ከንብረት ባለቤትነት መፈጠር ጋር ተያይዞ ነው፡፡ የንብረት ባለቤትነት በሚታወቅበት፣ ሁሉም ሸቀጦች የግለሰብ ይዞታ በሆኑበት ማህበረሰብ የሚኖር አንድ ድሃ ሰው፤ ለመኖር የሚያስችል ሐብት ለማግኘት ሲል፤ ዘወትር ተግ በማይል ለሥራ የሚያነሳሳ ኃያል ግፊት ውስጥ ይኖራል፡፡ በህይወት የመኖር ጥያቄን ለመመለስ እና ቁሳዊ ምቾትን ለማደላደል ተግቶ ይሰራል፡፡ ዘወትር በቋፍ ያለ ኑሮ የሚመሩ እና ጥቂት ጥሪት ያላቸው ሰዎች፤ ፋታ በማይሰጥ የኑሮ ግፊት ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ ስለዚህ፤ መንፈሳዊ፣ ኪነ-ጥበባዊ፣ ምሁራዊ ፍላጎትን ለማሟላት መጓዝ አይችሉም፡፡ በክፉ ህሊና ወይም ጭካኔ ዓለማዊ ስርዓት፤ የሰዎችን ኑሮ መጥፎ መልክ አስይዞታል፡፡
እንደሚባለው፤ ይህ ዘመን የኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የሰለጠነበት ዘመን ነው፡፡ ከዓለም ህዝብ 75 በመቶው ያህሉ ቴሌቭዥን ይመለከታል፡፡ በቴሌቪዥን የቅንጡዎችን የፈንደለላ ህይወት ይመለከታል፡፡ ሆኖም በቴሌቭዥን ማስታወቂያ የሚመለከተውን ነገር ለመግዛት አይችልም፡፡ የሚመለከተውን ነገር ለመግዛት የሚችለው 20 በመቶው የዓለም ህዝብ ብቻ ነው። 55 በመቶው ይመኘዋል እንጂ አያገኘውም፡፡ ዓለም ከምታመርተው ሽቀጥ እና አገልግሎት ውስጥ 86 በመቶ ያህሉን የሚጠቀሙት 20 በመቶዎቹ የዓለም ህዝቦች ናቸው፡፡ ከዓለም ህዝብ ሃያ በመቶ የሚሆኑትን ድሆችን ወስደን፤ ከዚህ ሸቀጥ እና አገልግሎት ድርሻቸው ምን ያህል ነው ብንል፤1 ነጥብ 3 በመቶው  ብቻ ነው፡፡
የዓለም የሐብት ስርጭት የተዛባ ነው፡፡ ለምሣሌ፤ ሃያ በመቶው የዓለም ህዝብ፤ የዓለምን 35 በመቶ ሐብት ገቢ ይወስዳል፡፡ የሦስተኛው ከዓለም ህዝቦች፤ ከዓለም ህዝብ 67 በመቶ ይሆናሉ፡፡ እነዚህ 67 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች፤ ከዓለም የሐብት ገቢ የሚወስዱት 18 በመቶውን ነው። በአንደኛው እና በሦስተኛው ዓለም ህዝቦች መካከል እንዲህ ያለ የሐብት ልዩነት አለ፡፡
ከዓለም ህዝብ ውስጥ 4 ነጥብ 4 ቢሊየን የሚሆኑት የታዳጊ ሐገራት ህዝቦች ናቸው፡፡ይህ ቁጥር 67 በመቶውን የዓለም ህዝብ ቁጥር ይይዛል፡፡ ይህን ያህል ህዝብ (4.4 ቢሊየን) ንፁህ የመጠጥ ውሃ አያገኝም፡፡ 25 በመቶው በማይረባ ቤት ይኖራል፡፡ 20 በመቶው ዘመናዊ የጤና አገልግሎት አያገኙም፡፡
በተቃራኒው፤ የአንደኛው ዓለም ዜጎች፤ የቤት እንስሳትን ለመመገብ፤ በዓመት 17 ቢሊየን ዶላር ያወጣሉ፡፡ ሆኖም፤ 13 ቢሊየን ዶላር ቢያወጡ በዓለም ውስጥ በምግብ እጥረት የሚቸገር ሰው እንዳይኖር ሊያደርጉ ይችሉ ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ ስሌቶችን ሰርተን የሀገራችንን ሁኔታ ማየት ያጓጓል፡፡
የሆነ ሆኖ፤ የእኔ ምድብ ከዓለም ግፉአን ነው፡፡ የሥራ ‹‹ምድቤ›› ከብዕር ገፊዎች ነው፡፡ በአሁኒቱ ኢትዮጵያ፤ ብዕር ገፊዎች ምንዱባን ናቸው፡፡ ስለዚህ፤ በአዕምሮ እንጂ በአካል መጓዝ አይችሉም፡፡ ሆኖም፤ ‹‹አባ ሴና›› የአካል ጉዞ ዕድል አመጣልኝ፡፡ ነቀምትን እንዳያት ጋበዘኝ። ‹‹አባሴና›› ፀሐፊ ነው፡፡ እንደ አዋጊ ጀነራል ልዩ የትኩረት ኃይልን የታደለ ነው፡፡ እንደ ህፃን ውበት ያሸንፈዋል፡፡ እንደ ጥሩ ጄነራል በህይወት ግንባር ፍልሚያ ይገጥማል። እንዲያውም፤ እርሱ እንደ ሲንባድ መርከበኛው ነው። እንደ ሲንባድ በህይወት ገበያ ተመላልሶ፤ ጥቂት ጥሪት ከያዘ በኋላ፤ መርከቡን ጭኖ ዓለምን መጎብኘት ይጀምራል፡፡ አንዳንዶ የኑሮ ሥራዎቹ ከፊል ጉብኝት ናቸው፡፡ አዲስ ነገር ይደፍራል፡፡ ህይወት ደግሞ ለጠቢብ እና ለደፋር ትሸነፋለች፡፡ ትሰጠዋለች፡፡ የሰጠችውን መልሶ ይሰጣታል፡፡ ህይወት እንዲህ ይቀጥላል፡፡
‹‹አባ ሴና›› ማታ ደወለልኝ፡፡ ደውሎም፤ ‹‹ወለጋ ከእኔ ጋር ትሔዳለህ?›› ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ዕለቱ አርብ ነበር፡፡ እኔ ቅዳሜ ሌላ ቀጠሮ ነበረኝ፡፡ ቀጠሮዬን መቀየር እችል እንደሆነ ለመጠየቅ ደወልኩ፡፡ ሆኖም፤ የደወልኩለት ሰው እኔ ቀጠሮ እንዲቀይርልኝ ከመጠየቄ በፊት፤ እርሱ ቀጠሮውን እንድቀይርለት ጠየቀኝ፡፡ እናም ምክንያቱን፤ በማስተዛዘን ሊነግረኝ ሲያቆበቁብ፤ በጨዋታ አገድኩት። በደስታ ተቀበልኩት፡፡ ራሴን ለወለጋ ሸለምኩት፡፡ ማታ እንቅልፍ እምቢ ብሎኝ ጥቂት ተቸገርኩ፡፡ ድንገተኛው የጉዞ ሐሳብ የፈጠረው ችግር መሰለኝ፡፡ ስለዚህ፤ ነቀምትን ለማየት የሚያግዝ ነገር ለማንበብ ተነሳሁ፡፡
ፀሐፊ በዓይኑ ሥር ያለውን ንቁ ህይወት፤ በአትኩሮት እና በአክብሮት ሊመለከተው ይገባል፡፡ እንዲህ አድርጎ ካላዬ፤ ከሚመለከተው ነገር ሊነገር የሚችል ታሪክ ሊወጣ የሚችል አይመስለውም፡፡ ፀሐፊ፤ ህይወትን በአክብሮት እና በአድናቆት ስሜት ካልተመለከተ ‹‹አዲስ ነገር የለም›› ዓይኑን ሊጨፍን ይችላል፡፡ በ‹‹አውቀዋለሁ›› ስሜት ከተጋረደ፤ ወርቅ እንደ ተሸከመች አህያ ይሆናል፡፡ ህይወት እያሸከመችው ያለውን ሐብት አያውቀውም፡፡ የብዙ ፀሐፊዎች ወይም ተመራማሪዎች ችግር እንዲህ ያለ ነው። እናም ከዚህ ችግር ለመጠበቅ የሚያግዝ ስሜት ለመያዝ ሞከርኩ፡፡ ትንሽ ንባብ ጨመርኩበት፡፡ በንባቤም ከእኔ 108 ዓመታት በፊት ወደ ነቀምት የተጓዘ የአንድ ሩሲያዊ ወታደር መጽሐፍ አገኘሁ፡፡ መጽሐፉ የጉዞ ማስታወሻ ሊባል የሚችል ነው፡፡ ፀሐፊው፤ አሌክሳንድር ቡላቶቪች ነው፡፡
አሌክሳንድር ቡላቶቪች (Alexander Bulatovich) ወደ ነቀምት የሄደው በ1896 ዓ.ም ነበር፡፡ በአድዋ ጦርነት ማግስት ነበር የሄደው፡፡ በአካባቢውን ጎብኝቶ ያየውን ዘግቧል፡፡ በጉብኝቱ ያጋጠመውን ነገር፤ ‹‹ከእንጦጦ እስከ ባሮ›› (From Entotto to the River Baro (1897) በሚል ርዕስ አካቶታል፡፡ ቡላቶቪች ጥሩ ኤትኖግራፊክ መዝገብ ጽፏል፡፡ ይህን ዘገባውን በ1897 አሳትሞታል፡፡  
ቡላቶቭ መቶ አለቃ ነው፡፡ ወደ ሐገሩ ተመልሶ፤ ጡረታ ከወጣ በኋላ በምንኩስና ኖሮ፤ ምድርን ተሰናብቷል፡፡ እንዲህ ይላል፤ ‹‹በ1896 ዓ.ም የበጋው ወራት፤ ብዙ የታወቀ ወዳልሆነው የምዕራብ ኢትዮጵያ ግዛት የመሄድ ዕድል ገጠመኝ፡፡ ይህ ዕድል እንዲያልፈኝ አልፈለግኩም፡፡ በወቅቱ፤ በዴዴሳ ወንዝ አካባቢ ያለውን ግዛት ማየት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም አካባቢውን ለማየት የቻሉት ሦስት አውሮፓውያን ብቻ ናቸው›› ይላል፤ በመግቢያው፡፡
ቡላቶቪች እንደሚለው፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታ ግዛቶችን ለማየት ያልተቻለው፤ ፍላጎት ሳይኖር ቀርቶ ወይም የማይታለፍ የተፈጥሮ መሰናክሎ ኖሮ አይደለም፡፡ ሆኖም በማዕከላዊ መንግስቱ እና አካባቢውን ያስተዳድሩ በነበሩ ነፃ የኦሮሞ ጎሳዎች መካከል የማያባራ ጦርነት ይደረግ ስለነበረ ወደ አካባቢው መሄድ ችግር እንደነበር ጠቅሷል፡፡
‹‹ለጥናት የሚያግዙ የሳይንስ መሣሪያዎች አልነበረኝም፡፡ ግን የምፈልገውን ዕቃ እንዲያመጡልኝ አዝዤ ለጉዞ መሰናዳት የምችልበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ጨርሶ ከሚቀር እንዲሁ ሄጄ የቻልኩትን ጥናት ማድረግን መርጫለሁ›› የሚለው ቡላቶቪች፤ በችኮላ የተሰራ ጥናት በመሆኑ ሥራው ስህተት እንደማያጣው አመልክቷል፡፡ ከወለጋ ጉዞው ከተመለሰ በኋላ እርሱ ራሱ በርካታ ነገሮችን ለማረም እንደሞከረም ገልጧል። ‹‹በሥራው የተሳሳተ ሰው፤ ምንም ካልሰራ ሰው ይቆጠራል›› የሚለውን ብሂል የሚጠቅሰው ቦላቶቪች፤ በሥራው የተሳሳተ ነገር እንደማይጠፋ እየተረጠረ፤ ‹‹የአቅሜን ያህል እውነቱን ለማስፈር ወስኜ ሰርቸዋለሁ፡፡ እንዲታተምም ቆርጫለሁ›› ይላል፡፡
በጥቅምት ወር 29፣ 1896 ዓ.ም ወደ ወለጋ ለጉዞ ሲነሳ፤ አፄ ምኒልክ በወቅቱ አካባቢውን ያስተዳድሩ ለነበሩት ለዳዝማች ደምሰው እና ደጃዝማች ተሰማ ሁለት ደብዳቤዎችን ጽፈው እንደሰጡት ይናገራል፡፡ ጥቅምት 28 ምኒልክ ዘንድ ቀርቦ ሽኝት እንደተደረገለት፤ በማግስቱም በእንጦጦ ሰፍረው የነበሩ የሩሲያ ቀይ መስቀል አባላት እና ሌሎች በርካታ ሐበሻ ጓደኞቹ አሸኛኘት አድርገውለት ወደ ሌቃ ጉዞ እንደ ጀመረ ይገልጻል፡፡
ቡላቶቪች 17 አሽከሮችን፣ 7 በቅሎዎችን እና አንድ ፈረስ ይዞ ጉዞ ወደ ሌቃ ጀመረ፡፡ ብዙ ጓዝ ይዟል። ጉዞውም በጅማ መንገድ አድርጐ ነው፡፡ በአጋሰስ የጫነውን ጓዝ አሁንም - አሁንም የማደላደል ሥራ ስለበዛበት፤ በመጀመሪያው ቀን 16 ኪ.ሜ ያህል ተጉዞ፤ ሜታ አካባቢ እንዳደረ ይተርካል፡፡ ቡላቶቭ፤ በሦስት ቀናት ሊጓዝ የቻለው፤ 79 ኪ.ሜ ብቻ ነው፡፡ በሦስተኛው ቀን አዋሽን ተሻግሮ የአፄ ምኒልክ ልጅ የወይዘሮ ዘውዲቱ ባል ከሆኑት ደጃዝማች ውቤ ቤት እንዳደረ ይገልጻል፡፡
‹‹በአራተኛው ቀን ደግሞ የጓደኛዬ የደጃዝማች ኃይለ ማርያም ሹም ከሆኑ አንድ ኦሮሞ ቤት አደርን፡፡ የሹሙ ቤት በጉደር ወንዝ ዳርቻ ባለ ውብ የሆነ ሥፍራ ይገኛል። ደጃዝማች ኃይለማርያም፤ የራስ መኮንን ታላቅ ወንድም ሲሆኑ በጊዜው አዲስ አበባ ስለነበሩ መልዕክተኛ ወደ ሹሙ ልከው፤ አመሻሹ ላይ ብዙ ድርጎ (200 እንጀራ፣ ጠጅ፣ ጠላ፣ ማር፣ ቅቤ ዶሮ እንቁላል እና ለአሽከሮቹ አዋዜ) ገባልን›› የሚለው ቡላቶቪች፤ ለእርሱ መስተንግዶ ብዙ በግ እንደታረደ ይተርካል፡፡
አስገራሚው ነገር ቡላቶቭ ጥሬ ሥጋ ይወዳል፡፡ እንዲያውም፤ ‹‹እንደታረደ ወዲያው ቀርቦ እንደሚቀርብ ጥሬ ሥጋ የሚጣፍጥ ሌላ ምግብ ለማሰብ ይከብዳል። ችግሩ ኮሶ ሊጣባ ይችላል፡፡ በኮሶ የማይቸገር ሐበሻ ማግኘት ይቸግራል፡፡ ከንጉሡ እስከ የኔቢጤው ሁሉም ይቸገራሉ፡፡ ስለዚህ በየሁለት ወሩ ያለማቋረጥ ኮሶ ይጠጣሉ፡፡ ሐበሾች የጠና በሽታ በታመሙ ጊዜ፤ እንዲሁም ሥጋወደሙ ከመቀበላቸው በፊት ኮሶ ይጠጣሉ፡፡ ለአንድ ሐበሻ፤ ኮሶው ሳይሽርለት እንደ ተጣባው መሞት ነውር ነው›› ይላል፡፡
እርሳቸው አዲስ አበባ ቢሆኑም፤ ሰው ልከው በግብዣ ያንበሸበሹት ደጃዝማች ኃይለማርያም፤ቀደም ሲል ግዛታቸው ሰፊ የነበረና ከአራት ዓመታት በፊት ከእቴጌ ጣይቱ ጋር የሆነ ጭቅጭቅ በመፍጠራቸው ግዛት እንደ ተቀነሰባቸው ይተርካል፡፡ ይሁንና እርሱ ጉዞ ባደረገ ጊዜ ከተቀነሰባቸው ግዛት ከፊሉ (ጨቦ፣ ጉራ እና ጥቁር የተባሉ አካባቢዎች) እንደተመለሰላቸው ያጫውተናል፡፡
የእኔ የወለጋ ጉዞ ከቡላቶቭ ይለያል፡፡ እኔ ወደ ወለጋ የሄድኩት በላንድ ክሩዘር፤ በአምቦ በኩል ነው፡፡ በማለዳ ተነስቼ ‹‹አባ ሴና››ን እየጠበቅኩት ነው፡፡ ‹‹አባ ሴና›› አለባበሱ ጥበብ ነው፡፡ የክላሲካል እና ሞደርን ዘዬ ድብልቅ ይመስለኛል፡፡ አለባበሱ ለህይወት ያለውን ቀና አመለካከት ይገልጻል ነው፡፡ ከመኪናው ወርዶ፤ እንደ ማለዳ በጠራ ሰላምታ ተቀበለኝ፡፡ እርሱ ወደ ቤት ሲዘልቅ፤ እኔ ወደ መኪናው ሄድኩ፡፡ ተነሳን፡፡  




Read 2550 times