Saturday, 19 March 2016 11:44

ተናዳፊ ግጥም

Written by  ምርጫና ሂስ ፥ ዕዝራ አብደላ
Rate this item
(1 Vote)

ሳ፥ በሰሎሞን ዴሬሳ
    ምርጫና ሂስ ፥ ዕዝራ አብደላ  

ከአርባ አምስት አመት በፊት የተፃፈ ግጥም፥ ርዕሱ እና ያበቃበት ስንኝ፥ ሁለቱም እነጠላ ፊደል -ሳ- ውስጥ መወሸቃቸው እስከ ዛሬ አንባቢን ያደናግራል።  በወቅቱ የቆሎ ተማሪ አቀርቅሮ ለዜማ ቀለም ሲያደባ፥ ስንኝ ሲፈለፍል ወጣቱና ምሁሩ ሰሎሞን ዴሬሳ ሸፈተና ለአዲስ አፃፃፍ ፈር ቀደደ። በልጅነት ገፅ 43 ተንፍሷል፤ “ድንጋይ ሳልቆጥር / ቃላት ሳልቋጥር / ስንኝ ሳላዛውር / ግጥም ነው ቋንቋ ነኝ / ምን ታረጉኝ” በማለት ተላተመ። አቤ ጉበኛ እና መሰሎቹ አኩርፈው አጥላሉት። ሰሎሞን ስብስቡን “አርባ ተኩል ግጥሞች” ብሎ በመሰየሙ እንዴት ተኩል ግጥም ይኖራል አሰኘ። ሁለት ገፅ ለፈጀ የድንቅ ነጠላ ግጥም ርዕስ ነው። ተጨማሪ ማስረጃ በሚል የመጽሐፉ መውጫ ለአርባ ተኩል ያከለው ማብራሪያ ዛሬም ይናደፋል። “አርባ ... ጭራውን እንደሚነክስ እባብ ስለተጠቀለለ መጀመሪያም መጨረሻም የሌለው ጊዜ። ተኩል ... ግማሽም ቢሆን ከሙሉው ጋር እኩል። 40 የማይቆጠር የሃሳብ መቋጠሪያ ቁጥር ነው።”  ደበበ ስይፉ እንዳለው ሰሎሞን የዘመኑን የሥነግጥም ጥራት ክፉኛ አማሰለው። ከዝነኛው ፈረንሳዊ ባለቅኔ -የዲበዕውነታ አቀንቃኝ- ከ Paul Eluard የቀነጨበው፥ የመጽሐፉን ሽፋን እንደገለጥን የምናነበው ይሻክረናል።  “እረፍት በጠጠርና  በእሾህ መደቦች / ላይ መገቻውን አገኘ”  ወይስ ስቃዩ ጀመረ? አሁን አብረን የምንመሰጥበት “ሳ” ግጥም በእሳቦቱና በስንኝ አደራደሩ ምናብን ይኮሰኩሳል። [ሰሎሞን ደሬሳ የተራብነው ያክል ከሀገር ቤት ተመልሶ ብንሻማበት እንዴት በተጠቀምን? ነቢይ መኮንን ምኞቴን ይጋራል። “ደቂቃም ብትሆን የሴኮንድ ስንጥር / በዕድሜ ዘመኑ ላይ አንዳፍታ እንዲጨምር / እውቀት እየዘራ ሀቅ እያዘመረ / እንዲኖር ለአንድ አፍታ / እውነት እየፃፈ / ውበት እየጫረ / ምነው ለኪነት ሰው / ምነው ለጥበብ ሰው / የዕድሜ  ዕቁብ በኖረ !”  ያሰኛል። መች “እሽቅድምድም” መግቢያው ተነበበና?]
     ተናዳፊ ግጥም 2
[ተናዳፊ ሥሩ ነደፈ ነው። ተሰማ ሀብተ ሚካኤል ሲተረጉሙት የቃሉ ጨረር አይመክንም። (ገጽ 667) “ ንብ ነደፈ፥ በመርዙ ጠዘጠዘ ወጋ ጠቀጠቀ ” ወይም “ በፍቅር ተነደፈ ተያዘ ተቃጠለ ” እንዲሁም“ ባዘቶውን አፍታታ በረበረ ” ..... ግጥም ለጭብጡ፥ ለስንኝ አደራደሩ ወይም ለቋንቋው ምትሀት ምናባችንን ከቧጠጠ ተናዳፊ ነው፤ አንብበነው የምንዘነጋው፥ ጥፍሮቹ የተከረከመው ግን ኢ-ግጥም ነው።]
-------------------------------
     ሳ
በቁም ሲርገበገቡ
ቁጭ ብለው ሲለግሙ
ሲወድቁ  ሲደክሙ
እንደ ጥውልግ ቅጠል
ሲወርዱ እያውለበለቡ
ሳይገደቡ፤
ለመበቀል ሳያስቡ
ሳያልሙ
ሳያ

-------------------------------
       © ሰሎሞን ዴሬሳ

          [ ልጅነት፥ ገፅ 45]
-------------------------------
ገጣሚው ስለእነማን ነው የሚናገረው? ስንኞች ወዛቸው ሲነጥፍ፥ አንድ ቃል ደግሞ ተፈርፍሮ ሲበተን፥ ከንባባችን ጣዕም አልሰምር ስላለ፥ ግጥሙ ሊደርቅብን ይዳዳዋል። እንዲህ ወረቀት ላይ ተዘርግፎ ስናየው የሆነ ምስል ከምናባችን ይፍታታል። በዚህ ብቻ ሳይሆን ሰሎሞን በሌላ ግጥሞቹም ለስርአተ ነጥብ ይሰስታል። ነጠላ ወይም ድርብ ሰረዝ የግድ ካልሆነ አያስፈልገውም። “ሳ” አራት ነጥብ ተነፈገ ቅኔው አበቃ ማለት በራሱ አራት ነጥብ ነውና)። ቅርፁ -የአንድ ቃል መፈረካከስ- እንደ ጥውልግ ቅጠል መርገፉ ከጭብጡ ጋር ምን ያህል ይዋደዳል? ሰሎሞን በመጽሐፉ መውጫ ለርዕሱ “ሳ” ማብራሪያ ይሰጣል። “ሳ ... ሰ ሱ ሲ ሳ (አንድም ክፍታፍ ሰ) ”፤ ባለጌው ሆሄ የመሰለ አንድምታ በበለጠ አጨፍግጐታል። መዝገበ ቃላት “በግስ ላይ በስተመነሻ እየገባ ግስን ከማሰር የሚያስቀር ምዕላድ”  ይለዋል። ግስን ማጉበጥ ይችላል፤ ለምሣሌ - ሳይወድ ሳይጠላ ምኑን ኖረ?- ሳ ያፈርሳል። ስንኝ መኮማተር ይጀምራል፤ ሀረግ፥ ቃል፥ ግማሽ ቃል ብሎም በአንድ ፊደል ይተካል። “ጋን በጠጠር ይደገፋል” የመሰለ ግጥም አፈተለከ። ይህን የአገጣጠም ዘይቤ ደበበ ሰይፉ “ቋጥኙ” በተባለ ግጥሙ ተውሶታል። የዘውድ ሥርዐት ሲገረሰስ፥ ገደ-ጡፋዊ ምስሉ የፊዩዶ-ቡርዧ አወዳደቅን አጐላው። አጨራረሱን ልጥቀስ።
እንድያ  እንዳልተንከተከተ
እንዳልሳቀ፤
ወደ ቁልቁል
      ወረደ
      ቋጥኙ
      እየ
      ተን
      ሰቀ
        ሰ
        ቀ
የመንሰቅሰቅ እንባ ሲንጠባጠብ፣ የስንኝ አደራደር ለእይታም ሞገስ ሆነው።     
በሰሎሞን ግጥም “ሣያልሙ” የሚለው ቃል ተሰነጣጥቆ እንደ ቅጠል እየተቀነጠሰ ወደ ታች የወደቀው (ወደ ላይ ስበት አይፈቅድምና)  ስርወ ቃሉ `አለመ` ነው። ህልምን፥ ይህን ሰብዓዊ ክስተትን አጡዞታል። ሰዎቹ አወዳደቃቸው የመጨረሻ ቢሆንም እንዴት ህልም ሳይኖራቸው፥ አመፅ ቢቀር ግላዊ ጉጉት ተቀሙ? ዳር የሚያወጡት ተግባር፥ በኑሮ ለመዝለቅ ተስፋ የሚሆናቸው የሚከተሉት የርዕይ ፈለግ አለመኖሩ ባለቅኔውን መዝምዞታል። “እንደ ጥውልግ ቅጠል” ዘይቤ የግጥሙን እይታዊ ቅርፅ ዛፍ አስመሰለው፤ የባህል መድሃኒት ለመቀመም ሳይሆን ለግለሰብ መጠውለግ ወካይ ነው። መስፍን ዓለማየሁ የተረጐመው ድንቅ አጭር ልቦለድ “የመጨረሻው ቅጠል” ተስፋ የፈረጠበት በስዕል የፀደቀ ክስተት በ“ሳ” አልተደገመም። “ሳያልሙ” እንደላባ ሆሄው እየከሰመ ወደ ወለሉ ቢንደረደርም፥ ምናልባት በምናባችን ስናጤነው ተንጠልጥለው ተርገብግበው ረብ ያልነበራቸው፥ ምድር ላይ ፊደላቱ ተገጣጥመው ለአዲስ ህልም ይጠራሩ ይሆን? ልክ በዕውቀቱ ስዩም እንደተቀኘው “ጋን ከጀርባ ወድቆ፥ ገል ኾኖ ቀጠለ/ ከመሰበር ወድያ ሌላ ህላዌ አለ።”  አዳም ረታ በ “ኩሳንኩስ” የመለመላት ባሏ የሞተባት  ትኩስ ሙሽራ ዓለምፀሀይ፥ በአደጋ ምክንያት ሽቦ አይኗን ቢቧጥጣትም ፥ በተረፈው አይን ወንድን እያማለለች ለመኖር መቅበጥበጥ የመሰለ እልህ ለምን የ“ሳ” ገፀባህሪያት ተነፈጉ? የዘይቤውን ጀርባ ስናነብ ሰሎሞን በቅጠል መርገፍ ቢመስለውም፥ ህልማቸው እንደ እንባ ከተንጠባጠብስ? ሽንፈት ከሆነስ? ዮሐንስ አድማሱ “ገላጋይ አጣና ግልገሉን በላት” በሚል ርዕስ ስለባከነ ሰው ተመስጧል።  
አዱኛ ስትጠፋ በቱማታም ሆነ ወይ በኮሽታ፥
    የሰው ልጅ መፅናኛው፥
    ሰውም አይደል፥
    እግዜር አይደል፥
    አንድ ዘላላ ዕንባ አንድ የንባ ጠብታ።
የሰሎሞን “ሳ” ግለሰቦች መቀዘዛቸው ተዛመተበት፥ ወይስ ገጣሚው የኑሮ ዘበትነት -the absurdity of life- ለማንበብ ብቻ ሳይሆን ስዕሉ እስኪታየን ድረስ ተቀኘ? ለርዕስ የተሾመው ትንፋሽ፥ የግራ የቀኝ ሆሂያት ሸሽተውበት ብቻውን ለመርበተበት “ሳ” ፊደል አክሎ ቀረ፤ የግለሰብን ብቻነትና ብይትውርና ተወከለበት። ቃል ስንኝ አከለና ከሚታመቅ በተራው ተከታተፈና ይህን እሳቦት አባባሰው። የግለሰብ የዕለት እንቅስቃሴ፥ ይህ ዘበትነት፥ የኑሮ ቅጥ ማጣት፥ ከንቱነት የታከከበት ነው። “በቁም ሲርገበገቡ/ ቁጭ ብለው ሲለግሙ / ሲወድቁ  ሲደክሙ” ... እነዚህ ስንኞች ህይወት ትርጉም አልባ ነው የመሰለ እሳቦት ጥዶባቸዋል። “ In a philosophical movement that flaunts the ultimate freedom of the individual , one finds lack of direction.”  የግለሰብን የመጨረሻ ነፃነት ለይስሙላ ያሳወቀ የፍልስፍና እንቅስቃሴ፥ በአቅጣጫ ቢስነት መርገቡ ይረብሸናል እንደ ማለት። የፈለግነውን ለመፈፀም ነፃ ብንሆንም፥ ራስን እስከ መግደል ድረስ አንወርድም ባይ ነው አልበርት ካሙ። የሰሎሞን ግጥም “ሳ” ራስን እስከ ማጥፋት፥ አልያም በሌላው (እንደ ጊዜ፥ ሰው፥ ተስፋ-ቢስነት፥ ስንፍና...) በመሰለ ሃይል እስከ መሰነጣጠቅ ተቀረፀበት።  የስንኝ አደራደርና መፈረካከስ  ከጭብጡ አጣዳፉነት የሰመረ ነው። “ግጥምን የሚያረክሰው ያንዳንድ መስመሮች መበላሸት ሳይሆን፥ የሀሳብ ወይንም የስሜት ሀቅ ማጣት ወይንም ለገጣሚው ባይተዋር መሆን ነው።” ብሏል ሰሎሞን ዴሬሳ በ ዘበት እልፊቱ  መግቢያ። ይህ አባባሉ “ሳ” ን አዟዙረን በአንኳሩ ለመደመም ያነሳሳናል።

Read 2715 times