Saturday, 19 March 2016 11:53

ኦ! የደራሲ እውነት ከወዴት ነሽ?

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(1 Vote)

ያኔ! ገና “ጥበብ አትሸጥም” የሚለው መፈክር ከተሰቀለበት ሳይወርድ አንድ “ዜና” ጆሮአችን ደረሰ፡፡ አንድ የኪነ ጥበብ ድርጅት “ፍቅር እስከመቃብር”ን ወደ ፊልም ሊለውጥ እንደሆነ፤ ለደራሲው ለሐዲስ ዓለማየሁ የቅጂ መብት ዋጋ ሰባ ይሁን መቶ ሺህ ብር እንደከፈለ… ኪነት በዋጋ እንዳትተመን “ዘብ የቆምን” ደምፍላታም ወጣቶች ግራ ተጋባን፡፡ አይፈረድብንም፡፡ ደራሲ ብር መቀበል ክብሩ የሚፈቅድ አይመስለንም ነበርና …
“ሐዲስ ዓለማየሁ ብሩን በይፋ ቢቀበሉም በድብቅ ለሌሎች ችግረኞች ይሰጣሉ” ስንል ለመፅናናት ከጃጀለን። ግን፤ ያኔ እንዴት እንዲህ አሰብን?
ትዝ ይለኛል በስነ - ፅሁፍ ክበብ ተሰባስበን ልምዱን እንዲያካፍለን የጠራነው ጎምቱ ደራሲ ሁሉ የሚያስጠነቅቀን ጥቅምንና ጥበብን እንዳናነካካ ነበር፡፡ ደበበ ሰይፉ ሲያየን በቁጥር ላቅንበት መሰል ዝም ብሎ ሲያስተውለን ቆየና እንዲህ አለ፡-
“ገንዘብ ይገኛል ብላችሁ ከሆነ ካሁኑ ምርጫችሁን አስተካክሉ፤ ገንዘብ የሚገኝባቸው ብዙ አማራጮች አሉላችሁ፡፡”
ከደበበ ቀጥሎ ስብሐት መጣና በአካሉም በአንደበቱም እንዲህ የሚል መልዕክት አስተላልፎ ሄደ፤ “ደራሲ ችስታ ነው” ይሄን ንግግሩን ከአካሉና ከአንደበቱ አልፌ ቤቱን በመጎብኘት አረጋገጥኩ። ተረት ሰፈር፤ ጉሮኖ መሰል ቤት በሩ የተዛነፈ ሳንቃ ነው። አንድ ክፍል፤ ወለል አፈር ላይ እንደ ብርድ ልብስ የሳሳች ፍራሽ ተነጥፋ ነበር፡፡ እንድቀመጥ ተጋበዝኩ፡፡ የብሎኬት ድርድር ላይ ንፁህ ጨርቅ ተነጥፎበት እዚያ ላይ ተቀመጥኩ፡፡ የስብሐት ባለቤት የትምወርቅ ክብሪት ሆነ ሳሙና ስትፈልግ ከእግሬ ስር ከብሎኬት አፍ ውስጥ ትመዝዛለች፡፡
ይቺ ናት ደራሲ! ግን አልፈራሁም፡፡ በወጣትነት ደምፍላት መንፈስ እንጂ ስጋ/አካል መኖሩን ገና አላረጋገጥኩማ!
… አንድ ሌላ ቀን ፀጋዬ ገ/መድህንን ጋበዝን፤ “እናንተ ኑ” ብሎ ላከብን፡፡ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ክበብ ውስጥ ተንጋግተን ገባን፡፡ የተመካከሩ ይመስል የሁሉም ደራሲዎች መግቢያ ንግግር አንድ አይነት ነው፡፡ “በጥበብ ለመሸቀጥ ያደፈጥክ ካለህ ትበብ የሚመለክበት ቤተ መቅደስ እንጂ የገበያ ዕቃ እንዳልሆነ እነግርሃለሁ” አለ በሚንቀጠቀጥ ግን በሚያስገመግም ድምፅ፤ “አውቀህ ግባበት!!”
ከእኛ በዕድሜ ብዙም የማይልቀው የሺጥላ ኮከብ እንኳን ከግዴለሽ አለባበስና ሁኔታ ጋር በግዴለሽ አንደበት እንዲህ አለን፤ “በድርሰት ያለህን ታጣለህ እንጂ የሌለህን አታገኝም፤ የጥበብ ትርፏ በጥበብ መርካቱ ላይ ብቻ ነው፡፡”
እንደ ሩቅ ምስራቅ ምዕመን እኛም በስምምነት የአካልን መኖር ካድን፤ ሥጋ የነፍስ ቅዠት ነው አልን። የማይኖርበት ህይወትን ከአለማዊነት ቁስ ሳይሆን ከማይጨበጥ መንፈስ ቀለስን፡፡ በችግር ተጠበስን፣ ተደጋግፈንም መቆም ተሳነን … የኛ ዕውነት ከብስቁልና ጋር ተፈጣጥሞ፣ ከችግር ጋር ቆረበ፡፡ ጥሪታችን በማንበብና በመፃፍ ላይ ተወስኖ ረሃብ የሚከላ ጉርስ፣ እርቃን የሚሸፍን ልብስ ማግኘት መከራ ሆነ፡፡ ያኔ! ከመካከላችን አንዳንዶች በጋዜጠኝነት እስኪቀጠሩ ድረስ አካል በተካደበት ጥበባዊ ዓለም ውስጥ በመንፈስ ቆየን። ሳህታቱም፣ ቅዳሴውም፣ ውዳሴውም ቤተ - መፃህፍት ውስጥ ሆነ፡፡
ያኔ! ስህተት ላይ ወድቀን ነበር ለማለት አይደለም፡፡ ግን ግማሽ እውነት አንጠራውዞናል (ግማሽ እውነት ካለ) በጥበብ አምልኮት ውስጥ ነፍስ ወረብ የምትረግጠው አካልን ምርኩዝ አድርጋ እንደነበር ካድን፡፡ ይሄ የእኛ ብቻ አቋም እንዳልነበር ያረጋገጥኩት ሔለን ዱንሞር የተሰኘች ደራሲ ያለችውን ሳነብ ነበር፡-
“People are always surprised when writers receive money, as if they don’t have mortgages to pay” (እንደማንኛውም ሰው ደራሲዎች የሚከፍሉት የቤት ዕዳ እንደሌለባቸው ሁሉ ገንዘብ ሲቀበሉ ከታዩ ተደናቂው ሰው ይበዛል፡፡)
እኛም በሀዲስ ዓለማየሁ ተደነቅን፡፡ በዓሉ ግርማ “ደራሲው” ልቦለዱ ውስጥ ሲራክ የተሰኘው ገፀ ባህርይ የሚናገረውን ደጋግመን እንል ነበር “ሆድ ሲሞላ ጭንቅላት ባዶ ይሆናል”  ተቃራኒውን የጠየቅነው ግን ዘግይተን ነው፡፡ ሆዱ ባዶ ሲሆን ጭንቅላቱ ይሞላል? የሚያስበውስ ከረሃቡ ፈቅ ይላል?...
…ቆይተን ቆይተን የአለቃ ተክለኢየሱስ ዋቅጅራን መጽሐፍ ተተርጉሞ አገኘን፡፡ “የጐጃም ታሪክ” ውስጥ አለቃ ተክለኢየሱስ እኛን ተቃርነው የሚሉት አለ። ለእቴጌ ጣይቱ የሳሉት የቅድስት ማሪያም ምሥል ሥር “እመቤቴ አታስርቢኝ፤ አታስጠሚኝ፡፡ ረሃብና ጥማት የጥበብ ጠሮች ናቸውና” ሲሉ ፃፉ፡፡ መልዕክቱ ለማሪያምም ለጣይቱም፤ እንዲሁም ለእኛም ነበር፡፡ ተከራከርን፡፡ “የደራሲነት እውነት ከወዴት ነሽ?” አልን፡፡
ተክለኢየሱስ እውነት አላቸው፡፡ ባልዛክን ያህል የፈረንሳይ ደራሲ ችግር ሲያራውጠው፣ ረሃብ ሲያድፈጠፍጠው ባሏ የሞተባትን ማዳም ሐንስካን በባልነት አልተጠለለም? እንግሊዛዊው ዶ/ር ሳሙኤል ጆንሰንም ችግር አክለፍልፎ የጋለሞታ “ጭን አሽከር” አላደረገውም?
የደራሲነት እውነት ከሆድና ከጭንቅላት፣ ከብስቁልናና ከድሎት ፈቅ አይል ይሆን? ሌሎች አማራጮች ፈለግን፡፡ አሁንም ዞሮ ፀጋዬ ገብረመድህን አገኘን፡፡ ፀጋዬ “ሕሊና” መፅሔት ላይ የደራሲን እውነት ከባቢያዊ አድርጐት አገኘን፡፡ እንዲህ ይላል፡፡
“ሕዝብ መካከል ሆነህ ነው ስለ ሕዝቡ የምትፅፈው፣ የሕዝቡ ሙቀት ካልሞቀህ፣ በሕዝቡ ሕዝባዊነት ውስጥ ካልታቀፍክ የሱን ሕይወት አትተረጉምም፡፡ ስለዚህ ብዙ የብዕር ሰዎች፣ እንደምሳሌ የአሁኑን ትልቁን የሩሲያ ደራሲ ሶልዘንሂትሲንን እንመልከት፣ የታል የሚፅፈው? መሞት መጀመር ማለት እኮ ነው ከሀገር ሕዝቦች አካል ውጭ ከተለየ በኋላ፣ የሕዝብን ሳቁንና ብሶቱን ለመካፈል ከማትችልበት ርቀት ትዝታህ ሁሉ ይተንብሀል፣ እሰው በር ላይ ተቀምጠህ ምን ትፈጥራለህ? አጥንቴ የህዝቦቼን ሙቀት ተመግቦ ያደገ ስለሆነ አፍሪካዊ ሙቀቴን እንዳጣ አልፈልግም፣ በረዶም አልወድ፣ አለም ካደነቀው ጠንካራው የኢትዮጵያ ባህል መለየትም ለእኔ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ እርሱን ደካማ አድርጐ የማቅረብ ቅጥረኝነት ነው፡፡ ያኔም ብዕሬን ካገር ለማራቅ የተወጠነብኝ፡፡ ደስቶየቭስኪ ካገሩ ሲወጣ ነው የብዕሩ ሞት የተቃረበው፡፡”
ለፀጋዬ ህዝብ ባህር ነው፡፡ ደራሲ ደግሞ የባህር ውስጥ ነዋሪ ፍጡር፤ ያለ ባህር የባህር ነዋሪ ምን መጠጊያ አለው? ይሄን ይዘን ወደ ፀጋዬ ገብረመድህን ህይወትና ሥራ ጐራ ካልን በግብርም ተተርጉሞ እናገኘዋለን፡፡ የፈራው እና የጠላው የበረዶ አገር፣ ኑሮውን አበድኖበት ይማረር ነበር፡፡ አሜሪካ ብሮንክስ ኒውዮርክ ተቀምጦ ልቡና መንፈሱ ግን ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ላይ ይንሳፈፍ ነበር፡፡ ሥራው ግን እዚህ እንደነበረበት ዘመን አልሰላለትም፡፡ ንግግሩ በተሃ፣ ግጥሙ ዘገባ ሆኖ ነበር፡፡
ዛሬ የዶላሩ ብድር ባፋቸው ገብቶ ልጓሙ
ይኸው በአዲስ ግዳጅ ፍቅር፣ ወንድማማቾች ተሳሳሙ
የሚል ዜና አስታራቂዎች፣ በአለም ነጋሪት ቢያሰሙ
እኔም ቴሌግራፍ ደብዳቤ፣ ለወንድሞች ለማቀበል…
አሁን ይሄ ምኑ የፀጋዬን ግጥም ይመስላል? በእርግጥም እንዳለው ከሀገር መውጣቱ ሥራውን ነጥቆታል፡፡ ይሁንና ጉዳዩ የሁሉም ደራሲዎች እውነት አይደለም፡፡ ለምሳሌ አዳም ረታ፣ የፀጋዬ ተቃራኒ ደራሲነቱን እንደሚያሰላው ይናገራል፡፡ ለአዳም ሀገር እንደ ተራራ ነች፡፡ ካልራቋት እራሷ ላይ ሆነው ምኗም የማይታይ “ተራራኮ ቁልጭ ብሎ የሚታይህ ስትርቅ ነው” ይላላ፡፡
ይሄን ጊዜ ነው ኦ! የደራሲ እውነት ከወዴት ነሽ? ማለት፡፡

Read 1652 times