Saturday, 19 March 2016 11:55

“እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” ሂሳዊ ቅርበት

Written by  ዕዝራ አብደላ
Rate this item
(4 votes)

ይህ ልቦለድ እንደ ተነበበ አያበቃም፤ ከምናባችን ይፍታታል። አልባሌ የመሰለ ክስተት ድንቅ የኅላዌ ምስጢር እንዴት ፈላበት? ከ“እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” ግላዊ ማኅበራዊ አንኳር የመፈልቀቅ ሂስ ለጊዜው ገታ አድርገን፥ በአዳም ረታ የቋንቋ ምትሀት እና የአተራረክ ጥበብ እንደመም። ፐርሺያዊ ገጣሚና ሱፊ፥ Rumi እንዳስተዋለው ለድምፅ ጋጋታ ሳይሆን ለቃላት ከፍታ መብሰከሰክ ይበጃል፤ ለአበባ ማጐነቆል ዝናብ እንጂ ነጐድጓድ መች ጠቀመው? ወጣት ምስራቅ ገና ትዳር ስታጣጥም፥ ለባለቤቷ ትማግጥ እንደ ነበር ተወራለት። እሱም ቀልቡ ተፍቆ፥ ከውስጡ የሰረገውን ሃሜት ለማለዘብ በስካር ተንገዳገደ፤ ከመንገድ ወድቆ ይሞታል። ምስራቅ ለአመታት ከማኅበረሰብተገለለች፤ በትዝታዋ ተሸብባ ልጇ ታደሰ ተመርቆ ራሱን ሲችል አቃስታ ለዘላለም አሸለበች። ታደሰና ሎሚሽታ ለአምስት አመት ያክል በሰማንያ ተቆራኝተው ቢኖሩም፥ የትዳር አጋሩ ሰለቻትና ለአስናቀ ልቧ ተርበትብቶ ኮበለለች። ይህ ተረት የመሰለ፥ በየመንደራችን የሰማነው በእኛና በጐረቤት የደረሰ ገጠመኝ እንዴት መሳጭ ሥነልቦናዊና ውበታዊ ጓዳ ተበረከተለት?

--- ክፍል 2 ---
“እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” ታሪኩ ስስ ነው። በዚህ ቀጭን የትልም ክር -plot-እየተሽለኮለከ እንደ ጉንዳን የሚርመሰመሰው የኑሮ ጣዕም (ሽንፈት፥ ፍቅር፥ ጥላቻ፥ ጉጉት፥ ንዴት፥ ትዝብት ...) ያጣድፈናል። እንዴት? የለመድነው ክስተት ትኩስነት ብኩርነት ደራርቦ ለእለት በዕለት እንቅስቃሴ መሳቀቁ፥ መንዘሩ፥ መፍካት መጠውለጉ እውስጣችን ለመስረግ ምን አበቃው? ልቦለዱን ደጋግመን ብናነብ ይህ ጥበባዊ-ግባቱ ከምን ፈለቀ? ደራሲ የሆነ እሳት ለማያያዝ ነፋስ እየፈተነው ገና ክብሪት ይጭራል። ለአዳም ረታ ግን እያንዳንዱ ቃል ረመጥ ነው፤ ለዝዞበት አያውቅም። በ“እቴሜቴ ሎሚ ሽታ”  ኖቬላ ብንወሰን እንኳን ቢያንስ አራትኅብረ-ቀለማት ማድነቅ እንችላለን።
አንድ፥ብዕር ነው ብሩሽ እሚያሰኝ የቃላት ስዕል፥ የቋንቋ የልብ ንዝረት ረቂቅነት።ጥቃቅን ግን ሌላው ግለሰብ ሊመሰጥበት ቀርቶ ልብ የማይለውን ምስል፥ እንቅስቃሴ ወይም የሆነ ድርጊት የአዳም ረታ ብዕር ሲፍቀው፥ ሲያሻሸው የሚፈልቅለት ውበት-አስቀያሚነት እስከ ፍፁም ንዝረት፥ እስከ አስደንጋጭ ግርምት ይረቃል።
ሁለት፥ መስመራዊ ከመነሻ እስከ መገቻ መተረክ ሳይሆን እንደ ድርጊቱ ክብደት የጊዜ ቅደም ተከተል ተፈርፍሮ እጅጉን የሚጐላ፥ በጣምም የሚደበዝዝ ትዕይንት ይበራያል። አዋቂን የሚያስተክዝ የልጆች ዘፈን፥ ስንኞቹ እንደ ሙዚቃ ኖታ ለትረካው ጠቋሚና ቀስቃሽ ሆነዋል። “ያ ሰውዬ ምን አለሽ ማታ” ስንኞች ተራቸውን ይጠብቃሉ። የትረካው አቅጣጫ ሲሰበር፥ ወደ ሩቅ ትናንቶች ሲጐተት በ“ቸብ ቸብ” ይወረሳል፤ ሌላ ስሜትና እሳቦት እንዲመጥን ነው ቅኝቱ የጐረነነው።
ሶስት፥ ውጫዊ እንቅስቃሴ ሳይሆን ውስጣዊ ሥነልቦናዊ ገመናዊ ህይወትና እስትንፋስ አለርህራሄ ይጐረጐራሉ። ፍልስፍናዊ አመለካከት ይጠልባቸዋል። አንባቢ አምላክን በልቡ እያሻሸ የሚዘጋው የፀሎት መጽሐፍ ሳይሆን፥ እንደ የእንጨት ሙጫ ጭስ የሚያንሰራራ ህልም አይሉት ትካዜ፥ ብቻ መጠበብ ይጀምራል።
አራት፥ የአንፃር ምርጫ -focalization- አንባቢ ከአንድ ገፀባህሪ በላይ ስለ ድርጊቱ ሆነ ያባለታሪኮቹ ምኞትና አስተሳሰብ ያውቃል። እያንዳንዱ ገፀባህሪ ያንን ተመሳሳይ ክስተት እንደ ብስለቱና ፍላጐቱ ሲተርከው የሚሰነጣጠቅ የሚፈረካከስ ጨለማ አለ። በገሀዱ ግኑኝነት ቅርፊቱን ገላውን አስተውለን ሰውን ማማትና ማሞገስ እጅጉን ስህተት መሆኑ ይጐመዝዛል። መጋረጃ ሲተረተር፥ በር ሲወላልቅ ጓዳ ጓዳው ይጋለጣል፤ መሸሸግያ ጥጋጥጉን ይቀማል። ከአዳም ብዕር የሚሰወር ገፅታ የለም፤ እሱ ግን መገሽለጥ ብቻ ሳይሆን መለበድም አይሳነውም። ነጥቦቼ ተንሳፋፊ አረፍተ ነገሮች፥ እፉዬ ገላ ብቻ እንዳይሆኑ ከልቦለዱ መጥቀስ ያስፈልጋል።
ሊንድማን Thinking in Future Tenseበሚል መጽሐፉ ከተራነት ብርሃንን የማንጠፍጠፍ ተሰጥኦ ደንቆታል።“One of life’s most fulfilling moments occurs in that split second when the familiar is suddenly transformed into the dazziling aura of the profundly new ... patterns where only shadows appeared just a moment before.” በህይወትከእጅግ አርኪ ቅፅበቶች አንዱ፥በዚያ ሽርፍራፊ ሴኮንድ ድንገት የተለመደው የተሰለቸው በአብረቅራቂ ፍፁም አዲስ መንፈስ መለወጡ ነው፤ ከአፍታ በፊት ልሙጥ ጥላ ብቻ የረበበበት በንድፎች ይወረራል እንደማለት። ገጣሚ-ሰዓሊ አገኘሁ አዳነ ድልነሳው “መልቲ ብርሃን” በተሰኘ ግጥሙ ብኩርነት ብቻ ሳይሆን እስከ መስመጠ ተቀኘበት።
አንድ፥ ሁለት፥ ሶስት፥ ብለን
ፅልመቱን ዘለልን
. . . . .
መብራት የጠገበ መሬት የመሰለን
የረገጥነው ብርሃን
አዘቅት ሆኖ ዋጠን።
አዳም ረታ ዛሬ አይደለም እጅጉን ረቆ ደቃቅ እንቅስቃሴ፥ ስሜት ሆነ ድርጊት ... እስከ ዕንቁነት የፈለፈለው፤ አያሌ አንባቢያንን የሚደመሙበት ክህሎት የተካነው ከመነሻው ነው። የዛሬ 33 ዓመት (1975) የደረሰው አጭር ልቦለድ “ትዝታ”(አለንጋና ምስር፥ ገፅ 22)እንደ አብነት ሊነበብ ይችላል። ዳዊት ዳጐስ ያለ መጽሐፍ ዘርግቶ ጫት እየቃመ ደንገዝገዝ ካለ የታፈነ ክፍሉ በንባብ ስሜት እንደ ሰጠመ አጐቱ አንዲት ሴት -ፍሬ ሕይወትን- ይዞ በር ገፍቶ ይገባል። “በተከፈተው በር አጐቴና ያመጣት ሴት ያስገቡት ቀዝቃዛ አየር እንደ ማሕፀን ትሞቅ የነበረችው ክፍሌ ውስጥ ተጠቀጠቀባት” ዝም ብሎ ማድመቂያ ምስል አይደለም። የተናጋሪው ስሜት ከንባብ ወደ ሚቆረፍድ ድባብ ሲንሸራተት እኛም ከክፍሉ የተቀመጥን ያክል ይሰማናል። በበለጠ ግን የምንፈዘው የአፍታ እንቅስቃሴ ስዕል ሲያንሰራራበት ነው። “ደብዛዛ ብርሃን ካለበት አቅጣጫ፥ የፍሬ ሕይወት አንድ እጅ ወደ ፊትዋ እየተንሳፈፈ ሲያልፍ --የራሱ ነፃነት እንዳለው ሁሉ-- አንድ ነገር ብልጭ አለ። ደቃቃ ነገር የፈለቀ መሰለኝ። ቀለበት። የወርቅ፥ የብር ወይ የሌላ ዓይነት ብረታብረት። አንድ ጣትዋን ቅባት ነክቶት ወይም ያልደረቀ የምራቅ ነጥብ ሰፍሮበት ይሆናል። ለብቻዬ ፈገግ አልኩ።”  ይህን የአፍታ እንቅስቃሴ የፊልም ካሜራ እንኳን ይስተዋል። የቀለበትና ምራቅ መተካካት እንስቷ ለድሪያ መፍቀዷ በኢ-ንቁ አእምሮው የደባበሰው ሽርፍራፊ ስሜት። ከምንም ብዙ መፈልቀቅ መች አዳም ተሳነው?
ስለሴት እጅ አንድ ብልጭታ ልድገም። ከ12 ዓመት በፊት በ“ኩል” ንዑስ ርዕስ የደረሰው ትረካ ነው። (ይወስዳል መንገድ፥ ያመጣል መንገድ፥ ገፅ 223) የባለቤቷ ትዝታ ያፈናት ዓለምፀሐይ የተመሰጠችው በምንም ነው ማለት ይቻላል። “ትቼው ከአውቶቡስ ከመውረዴ በፊት እጄን ጐትቶ ህዝብ እያየ (ይታያችሁ በዚያ ግፍያ መሃል) ይስመዋል። ብዙ ጊዜ አይበሉባዬ ላይ እርጥበት ይሰማኛል። አንዳንዴ በነገሩ ልቤ ባብቶ መንገድ ላይ ሰው እንዳይታዘበኝ አድርጌ ሳልታይ አይበሉባዬን እስማለሁ። በከንፈሮቼ መሃል ምላሴን ብዙ ሳላሳልፍ አውጥቼ የተወልኝን የአፉን ወዝ እልሳለሁ። እንዴት ደስ እንደሚለኝ። ይህችንም ደስታዬን አብራኝ ለምትሰራ ልጅ ስነግራት ምን አለች መሰላችሁ? ከት ከት ከት። በቃ ከት ከት። ተሳስቼአለሁ? ወይስ ቀንታ ነው? ወይስ ዞሮባት ነው? መልሱን ፍለጋ አልባዘንኩም።”  ጥቃቅን ግን መሳጭ የመግለጥ ተሰጥኦ ቢሆንም፥ አዳም በምናቡ ይህን እንዴት ማየት ቻለ እያሰኘ ነፍስ ይዘራበታል። ይህ ምስል ከልቦለዱ እሴት ጋር ሲፋተግ እኛም -አንባቤ- ራሳችንና አካባቢያችን ትክ ብሎ የመመልከት አቅም ይቀሰቀስብናል። ለሂስ ወደ ተመረጠው “እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” እንመለስ።
“ከተቀመጠችበት ተነስታ ጓዳ ገባች። በመኝታ ቤት መስኰት መጨለም ወደ ጀመረችው የአዲስአባ ሰማይ አያለሁ። ነጭ የደመና ብጣሽ ግራጫ ሰማይ ላይ በምስማር እንደ ተመታ ሁሉ ቀጥ ብሏል። እናቴ ከጓዳ የከሰል ምድጃ ይዛ ወደ ሳሎን አለፈች። እንድመጣ ጠራችኝ። ሰማይ ላይ ሳፈጥ ቆየሁ። ሳሎን ስገባ ከሰል ምድጃው ላይ ጀበና ተቀምጧል። የምድጃው ፍም ተንገልጧል። ሶፋ ላይ ስቀመጥ አስራ ሁለት ሲኒዎች የሸፈኑት የእንጨት ረከቦት መጣና ከእግሬ ትንሽ ራቅ ብሎ ተቀመጠ። ከዛ ጐን ከዕጣን ማንደጃ ላይ እየተከዘ የሚነሳ የመላዕክት ጅራት የመሰለ ጭስ” [ገፅ 104]
ታደሰ ከሎሚ ሽታ የመሰረተው ትዳር ፈርሶ፥ ስለ አለፈ ህይወቱ በምልስት ሲተርክ እንዴት ይህ አዕምሮ ውስጥ ሊቀር የማይችል ትዕይንት ፈካለት? አሁን እየተፈፀመ ያለ ትኩስነት፥ ከአመታት በፊት የተደረገ የተፋቀ ትዝታ ባለመሆኑ አዳም ዛሬና ድሮ ተቀላቀለበት? ጊዜ እንደ ጠጅ  ከብርሌ እየዋለለ እንዳሻን መዳፋችን ላይ አንጠባጥበን የምንልሰውየታሸገ ፈሳሽ ነው ወይ? ተራኪው ሥነልቦናዊ እንግልት እየመዘመዘው ሳለ ይህ ጊዜ ያደበዘዘው እንቅስቃሴ እንደ የመጀመሪያ ፍቅር በጥራት ይታወሰዋል? የተደረገ ነው ወይስ ዛሬ ከምናቡ ፈጥሮ እየዋሸን ነው? ወዘተ. ቢያሰኝም ስናነበው የገለጣው ጥበባዊ ውበት ያፈዘናል። ሰማይ ላይ በሚስማር የተመታ ደመና፥ ከዕጣን ማንደጃ እየተከዘ የሚነሳ ጭስ ዘይቤው ቅኔን ያደናግዛል። “መከርኩ።  አስመከርኩት። በዕንባዬ ለመንኩ። እምቢ አለ። `እምቢ` የምትለው ቃል ከንፈሮቿ ላይ ስትፈነዳ የተፈናጠረ ደቃቅ ምራቅ አፍንጫዬ ላይ ሲያርፍ ተሰማኝ። አልጠረኩትም። ዐይኖቼን ጨፈንኩና ረቂቅ ቅዝቃዜውን በቆዳዬ ጠጣሁ። እናቴን እወዳታለሁ።” [ገፅ፥105]የእናትን ፍቅር ከምራቅ ፍንጣሪ ማጠለል የአዳም ብርቅና ልዩ ችሎታ ነው፤ የጊዜን ፍሰት በዕውነታ ህግጋት መዳኘት፥ ዛሬ ነው ወይስ ያረጀ ትናንት ብሎ ለመብሰክሰክ የማይፈቅድ ረቂቅነት ነው።
ሎሚ ሽታ ከባለቤቷ ታደሰ እየተላቀቀች ልቧ ለአዲስ ወንድ ሲንሸራተት ትረካዋ ይመስጣል።
“ ... ጐኑ ተጋድሜ ገና ሳገባው አደርገው እንደነበረ ሁሉ ሆዱን እዳብስለታለሁ፥ ችፍ ያለ ቅንድቡን በአመልካች ጣቴ እካክክለታለሁ፥ በጅልጃላ ውስጥ ሱሪው ስር እጄን አስገብቼ ፀጉር የፈሰሰበት ጭኑን እነካከዋለሁ። ከደስታ ይልቅ ውስጤ የሚሰማኝ አነጣጥሬ ያለመውደዴ ቁጭት ነው። ታድያ እሱ እንዳይሰማኝ አድርጌ ወደ ውጭ እተነፍሳለሁ፤ አተነፋፈሴን ከሰማኝም የፍቅር ስራው ያረካኝ ለመምሰል በወዛም ፀጉር የተሸፈነ ፊቱን አፌን ከፍቼ እስምለታለሁ። ... ሳገባው ወድጄው ነበር። ውሸት አይደለም። አሁንም እወደዋለሁ። ግን አንድ ቀን ከቤቴ ልወጣ ስል ደጃፌ ላይ ይኼን `አስናቀ` የተባለውን ወጣት አገኘሁት። ደነገጥኩ። በሁለመናዬ።”  [ገፅ፥ 83]
ሎሚ ሽታ አንሶላ ስር ድርጊትን በስሜቷ አሻሽታ፥ የመምሰልና የመሆን ጭንቀት፥ የልብና የአካል ትርታ፥ አብረው ተኝተው ባዳነት ደባልነት ሲነጣጥላቸው ጥቃቅኑ ይተረካል። በተራው ይህን ህይወት ታደሰ ሲተርከው በአንፃር ለውጥ ምክንያት ሰው እንደ መሰለው መፍረዱ ይኮሰኩሳል። የልቦለዱ ሃምሳው ገፅ በዚህ መልክ ዕዝራ ፓውንድ እንዳለው፤ በአንድምታ የተለበለብ የቋንቋ ትርታና ንዝረት ነው። ጀርመናዊ ፈላስፋ ሾፕንሆር ያስተዋለው ለ“እቴሜቴ ሎሚ ሽታ”  ትረካ ይስማማል። “The business of the novelist is not to chronicle great events but to make small ones interesting. “የልቦለድ ደራሲ ተግባር ግዙፍ ሁነቶችን መዘገብ ሳይሆን፥ ከትንንሽ ጉዳይ ጣዕም እየቀዳ መተረክ እንጂ እንደማለት። “ጊዜን ላንዳፍታ ቆም ማድረግን፥ ለማስተዋል፥ ለመሳቅ፥ ለመተከዝ ፋታ ማግኘትን የማይመኝ ማን አለ?” ብሎ ቢጠይቅም ሰሎሞን ዴሬሳ፥ የአዳም ረታ ብዕር ጊዜን ብቻ ሳይሆን ስሜትን፥ ምስልን፥ ኮሽታን፥ ትንፋሽ ጭምር በቃላት ዘለዓለምነት ይለግሳቸዋል። ሁሉአገርሽ የቤተ ክርስትያን ግድግዳ ስትደገፍ ምን ተሰማት?  “በሚበርድ ጠዋት ግድግዳው ይሞቃል። በሃሳቤ ሺህ መላዕክት ግድግዳው ውስጥ ከሲሚንቶው ጋር ተገንብተው ጀርባዬ ላይ ሲተነፍሱብኝ ይታየኛል። ያስፈራል፤ እና በመደመምም ይሞላል።” የአዳም ረታ ልቦለድ ምናባችን እንዳይፈዝ ለህይወት ግለት ነው።
ክፍል 3 ይቀጥላል

Read 3173 times