Saturday, 26 March 2016 11:28

ተናዳፊ ግጥም

Written by  ፍርሃት፥ በአበራ ለማ ምርጫና ሂስ ፥ ዕዝራ አብደላ
Rate this item
(4 votes)

     የጥበበ ስራ (ስዕል ወይም ቅርፃ ቅርፅ) ለባለቅኔ የግጥም መቀስቀሻ ሊሆን ይችላል። ሎሬት ፀጋዬ የአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ስር አንድ ሰካራም ሲፀዳዳ፥ አቡኑን ሲያበሻቅጥ ግብ ግብ ገጠመው። በዚያኑ ምሽት “ሰቆቃው ጴጥሮስ” ን ተቀኘ። “አየ፥ ምነው እመ ብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት? / ምነው ቀኝሽን ረሳሻት? / እስከመቼ ድረስ እንዲህ፥ መቀነትሽን ታጠብቂባት?” እያለ  ረቀቀ፤ “ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት” ቴአትር መገቻ ሆነው። ዳሩ ግን ሎሬት ፀጋዬ ከሀውልቱ ጋር ለጥቂት ቀናት ተነጋግሮ፥ ምስጢሩን አልተማጠነም፤ የአቡኑ መዘለፍና የሰማዕቱ ታሪክ የለኮሱት ቅኔ ነበር። ዶስትዮቪስኪ The Idiot በሚለው ልቦለዱ አብይ ገፀባህሪ ልዑሉ፥“የእየሰሱ አካል በቀብር ሳጥን ውስጥ” በተባለ ስዕል ተመስጦ ያውጠነጠነበት ትረካ ይጠቀሳል። ወጣቱ ባለቅኔ ኤፍሬም ሥዩም “ኑ... ግድግዳ እናፍርስ” ስብስቡን ሲያስመርቅ፥ መድረክ ላይ አምስት ጠቢባን ሸራቸውን ወጥረው፥ በነደፋቸው ግጥም ተይዘው ምሱን ስዕል ለገሱት።
በፈጠራ ድርሰት (ግጥምና ልቦለድ) እና በስዕል መካከል አንዱ ሌላውን -inspired- ማነሳሳት ከቻለ ዘውጉ ekphrasis ይባላል። ስርወ ቃሉ የግሪክ ሲሆን የልብን መናገር እንደ ማለት ነው። ኤክፍራሲስ ማለት በአንድ ስዕል በመጠበብ ግጥም ለመቀኘት መብቃት ማለት ነው። ይህ ግን ህፃናት ተረት እንዲወዱ ለታሪኩ ማብራሪያ ደጋፊ ስዕል -illustration- መንደፍ አይደለም። ከአንድ የበቃ የወጣ የፈጠራ ውጤት በመነሳሳት፥ አዲስ እይታ በመንጠቅ መቀኘት እንጂ። ሌላውንም ጥበብ ይነካካል። የሆነ የልቦለድ ምስል ለምሳሌ የዓለማየሁ ገላጋይ አባባል -በአጥቢያ- ለስዕል ወይም ለግጥም ያነሳሳል። “እኔን እያዩ በመሽቆጠቆጥ ኮፍያቸውን ከጭንቅላታቸው ላይ እንደ በግ ቆዳ ይገፋሉ። አንገቴን ቀንጠስ አድርጌ አልፋለሁ።”  እንዲሁም ሙሉ ግጥም ወይም ስንኝ ለሌላ ጥበብ እርሾ ይሆናል። ለምሳሌ፥ “አትወደኝም ያልከው የጠላሁህ የታል / አንድ አንጀት ነው ያለኝ ተኝተህበታል።” ለስዕል፥ ለልቦለድ፥ ለሀውልት የሚበቃ የሴት እንግል ትሸሽጓል። አዳም ረታ የ“ፍቅር እስከ መቃብር” ሰብለወንጌልን ከፍዝ መቼቷ አስኮብልሎ “መረቅ” ልቦለድ ውስጥ ሲያንቦጫርቃት፥ አርመናዊ በፍቅሯ ሲነደፍ ጊዜ ተፈረካከሰ። ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ሰብለወንጌልን ሲስላት እንደ ለበሰች፥ ነጠላ ደርባ ብትሆንም፥ አወላልቃ የፈተነችን ያክል ውብ ሆነች፤ ከመንደሩ ስትመላለስ ተማርኮ አልነበረም የተነቃቃው፥ አንብቦ ወረሳት እንጂ።
የበዓሉ ግርማ “ኦሮማይ” በደኅንነት ከየጥሻው ሁሉ ሲታደን አበራ ለማ በአብይ ሴት ገፀባህሪ ተደምሞ፥ ለበዓሉም ተቆርቁሮ ግራ ቀኝ እየገላመጠ “ፊያሜታ” የተሰኘ ግጥም ፃፈ። ከሆነ ቦታ ቢወሽቀውም ለአደጋ አጋልጦታል። (መዓዛ በሸገር ሬድዮ  ከአበራ ያደረገችው ውይይት ዝርዝሩን ያስረዳል።) የዛሬ ሰላሳ ሶስት ዓመት ገደማ አበራ ለማ አንድ የተጠቀለለ ስዕል ዘርግቶ ግድግዳ ላይ ሊያንጠለጥለው ሲሞክር፥ የቅርብ ጓደኛው ያቃሰተ ያክል ነዝሮት ተመሰጠ። ለጥቂት ቀናት በዚህ ስዕል እስረኛ -obsessed- ሆነ። እንደ ምንም ከስዕሉ ጋር መነጋገርና መደማመጥ ሰመረለትና “ፍርሃት” የተባለ ግጥም ተቀኘ፤ ተነፈሰ። ግጥሙን በጉልህ ሆህያት ስዕሉ ላይ በማስቀረፅ በሺህ በሚቆጠሩ ኮፒዎች በየቤቱ ዘለቀ። እስከማውቀው ድረስ በአማርኛ ሥነጽሑፍ ኤክስፋርሲሳዊ -ekpharistic- ግጥም በመቀኘት አበራ ለማ ፈር ቀዳጅ ነው። በዚህ ዘውግ መመሰጥ የሚፈልግ አንባቢ ካለ የ Jan Greenberg መጽሐፍ፤ “New Poems Inspired by Twentith-Century American Art” ጠቃሚ ነው። የአበራ ለማ ግጥምን ከስዕሉ ከምሽጉ አባብለን ስናወርደው፥ የቢጋሩን አጥር ሰብሮ ሌጣውን ስናነበው አልቀዘዘም፤ ተናዳፊ ስለሆነ ችላ አይባልም።
ተናዳፊ ግጥም 3
[ተናዳፊ ሥሩ ነደፈ ነው። ተሰማ ሀብተ ሚካኤል ሲተረጉሙት የቃሉ ጨረር አይመክንም። (ገጽ 667) “ ንብ ነደፈ፥ በመርዙ ጠዘጠዘ ወጋ ጠቀጠቀ ” ወይም “ በፍቅር ተነደፈ ተያዘ ተቃጠለ ” እንዲሁም“ ባዘቶውን አፍታታ በረበረ ” ..... ግጥም ለጭብጡ፥ ለስንኝ አደራደሩ ወይም ለቋንቋው ምትሀት ምናባችንን ከቧጠጠ ተናዳፊ ነው፤ አንብበነው የምንዘነጋው፥ ጥፍሮቹ የተከረከመው ግን ኢ-ግጥም ነው።]
-------------------------------
ፍርሃት
ያመረቡ ልቤ ረገበ እምቢ አለ
አንድ ራሱን ማስገር አቃተው ዋለለ፤
ፍርሃቴ ስጋቴ በላዬ ነገሠ
ውስጥ አንዠቴን ምሶ ቤቴን አጣረሰ።
ግና ምነው ፈራሁ ወኔዬ ባዘቀ
በፍርሃት ነቅዤ ፥ ነፍሴ ተጨነቀ፤
እድሜ እንደብል ሆኖ ሕይወት ካነተበ
ፍርሃት ንጉሥ ሆኖ አገር ካስደመመ
እናንተም እንደኔው ፍርሃት ካባጃችሁ
ጠመንዣው-ዣንጥላው-ውሻው ለምናችሁ?
-------------------------------
©አበራ ለማ
-------------------------------
አበራ ስዕሉ ውስጥ የአዛውንቱን እጦት ስለሚጠቁመው መኖሪያ ክፍል፥ እስከ እርጅና በችግር መላላጥ የመሰለ ድባብ ወይም በምስሉ ጥበባዊ እሴት ለመደመም አልሞከረም። (እነዚህ ሁሉ በቀላሉ ይታያሉ) ይልቅ ከአዛውንቱ ልብና አእምሮ በመሰወር፥ ስዕሉ የቀነበበውን እንቅስቃሴ በማጤን ተደመመ። በዚህ ግጥም የአዛውንቱ ሥነልቦና ነዝሮበታል። ከስዕሉ ተላቆ ብቻውን ሲቀር በአረጋዊ ኅላዌ ሳይወሰን የዘመነኛ ሰው ስጋት -anxiety- ይጠየቅበታል። “ያ መረቡ ልቤ ረገበ እምቢ አለ / አንድ ራሱን ማስገር አቃተው ዋለለ፤” ዘገባ አይደለም። መሳጭ ተለዋጭ ዘይቤ ነው። ልብ እንደ ልበ-ደንዳና ሳይሆን ራስን (ፍላጐት ሆነ ርዕይ) መግራት ለተሳነው ግራ ለተጋባ ግለሰብ ወካይ ነው። የ“ከአድማስ ባሻገር” ገፀባህሪ አበራ ወርቁን ይጠራብናል። ዘመነኛ ግለሰብ መደናገሩ፥ ባህልና ለውጥ ግራ ቀኝ ሲያላትሙት፥ የስዕል ተሰጥኦ፥ ፍቅርና ለትዳር ማዝገም በቅናት ሻሽረው አቅጣጫውን ይስታል። ጓደኛው ሀይለማርያም እንዳስተዋለው፤ “ራሱን በመፈለግ ላይ ነው” አንድ ራስን ማስገር ለወጣትም ለአንጋፋም፥ ለምሁርም ለመሀይም እንደ ብስለቱና ረግረግነቱ ዘወትር የሚመዘምዘን እልህ ነዉ፤ ለመለኮት አደራ ራስችንን በመስጠት እንሸሻለን። በዕውቀቱ ሥዩም አባብሶታል። “ያንን ገለባ ልብ ከደጅ የወደቀው/ `አድራሻህ ወዴት ነው?` ብለህ አትጠይቀው/ የነገው ነፋስ ነው፥ መንገዱን የሚያውቀው።”አበራ ለማ ለቀናት ትክ ብሎ ያስተዋለው ስዕል የነጠፈ ደረቅ ዝርግ ወረቀት አልነበረም። በምናብ ሲተሻሽ የሆነ ሰብዓዊና ፍልስፍናዊ ፍስት ተንጠፈጠፈበት።
    አዛውንቱን ሶስት የእንግልት እጆች ደቁሰውታል። አንድ፥ የሆነ ጉዳይ ለመፈፀም ማቅማማት፥ ግራ የመጋባት እንቅስቃሴ። ሁለት፥ አድፍጦ ከሚጠብቀው ጉዳት አልያም ሥነልቦናው የቀፈቀፈው የሌለ ስጋት፥ በፍርሃት እንዲሸማቀቅ አድርጐታል። ሶስት፥ እንደ ብል ህይወትን የሚፈረፍረው ዕድሜ እርጅና ነው። አዛውንቱ ደራርበው ዣንጥላ፥ ውሻና ጠመንጃ ይዘው ከሆነ ሥፍራ ዘብ ለመቆም የተቀጠሩ ይመስላል። እድሜ ልክ ድሃ ሆኖ መጉበጥ አልያም በስተእርጅና ለዕለት ጉርስ ዕድሜን ተሸክመው ለመዳከር የመገደድ ጣጣ ይመዘምዛል። ለምን ይሆን የዋለሉት? ከቤታቸው ውጭ ምን ይሆን የሚያሰጋቸው?
የዛሬ ሰላሳ ሶስት ዓመት በደርግ ዘመን ግለሰብ በፍርሃት ተሸብቦ፥ ለማመፅ ለመተኮስ ትንፋሽ አጥሮት ነበር። የአዳም ረታ “ይወስዳል መንገድ፥ ያመጣል መንገድ” እና “መረቅ” ልቦለዶቹ አንድ ጭብጥ የዚያ የዘመን መንፈስ -zeitgeist- በሰዎች ማንነት የሰገሰገው ፍርሃት ነው። አበራም በስዕሉ አሳቦ የማኅበረሰቡን አለማመፅ፥ ይህን “ፍርሃት እንደ ንጉሥ ሀገር ካስደመመ”  የተቆጨበትን፥ ጠመንጃ አንግቦ ያቅማማውን ትውልድ ኮንኖበታል። ሳንሱር የማያሳልፈው ግጥም ቢሆንም በባዕድ ሀገር ስዕል ተወሽቆ ለሌላ መቼት እንደ ተገጠመ ቅኔ በየቤቱ ገባ።
አንድ ግጥም ስዕል ያነሳሳውም ቢሆን ወይም ለወቅቱ ድባብ ቢጻፍም ሳይቀዝዝ ዘመን ተሻጋሪ ከሆነ የጥበብ ውጤት ነው። የአበራ ለማ “ፍርሃት” ዛሬም ይነዝራል። “ያመረቡ ልቤ ረገበ እምቢ አለ/ አንድ እራሱን ማስገር አቃተው ዋለለ” ብቻውን ሙሉ ግጥም ነው። የህልውናነት -existentialism- እንኳር ጭንቀት ነው። ልብ የረገበ ሆኖ ራሱን ማስገር አቃተው ማለት ከራስ ጋር ግጭት፥ የተምታታ ህይወትና አቅጣጫ መነፈግም ነው። የተናጋሪው በዕድሜ መብሰል በስክነት ይተካል ስንል ስጋቱ ተባባሰ። በፍዝ ቃላት ሳይሆን በተለዋጭ ዘይቤ ስንኞች መወራጨታቸው ከምናባችን ለመወርዛት ያበቃቸዋል። መቸም ሰው እድሜ እየተጫጨነው ሲያረጅ ውበቱ ገርጥቶ የሚነጥፍ ይመስለናል፤ ዳሩ ግን አበራ ለማ እንደ አስተዋለው ላህያቸው ከገፃቸው ወደ ልባቸው ፈሰሰ እንጂ አልተሻሩም። ለኑሮ መርበትበት፥ ለነገ መስጋት፥ እድሜ አቅምን ቢያደክመውም የዘወትር ፍርሃት መላወሱ ለኑሮ ትርጓሜ ጣዕሙም ነው።

Read 2708 times