Saturday, 26 March 2016 11:34

“እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” ሂሳዊ ቅርበት

Written by  ዕዝራ አብደላ
Rate this item
(8 votes)

     በዚህ ልቦለድ ብቻ ተወስነን አዳም ረታ የመለመላቸውን ሴቶች ብናጤን፥ ምን ያህል ይመስጡናል? በተለይም ሎሚሽታ? ሶስት ውብ ወጣት ሴቶች -ምስራቅ፥ ሎሚሽታ እና ሁሉአገርሽ- የእንስትን የባህሪይ ሆነ የአኗኗር መልኮች በከፊል ይወክላሉ። ተነጥላ በራሷ መንገድ የተጓዘችው የአለማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ከነሱ ትለያለች። እንደ ጥላ ውልብ የምትል አዳም ረታ ከሌላ አጭር ልቦለድ የጐተታት ቀለመወርቅ አለች። [ለድልህ፥ ገፅ 177] “ከጐረቤታችን ከእትዬ ቀለመወርቅ በተቀር እቤታችን ቡና ለመጠጣት የሚመጣ አልነበረም። ብዙ ጊዜ ሳገኛቸው አፍ ለአፍ ገጥመው ሲያወሩ ነው። እናቴ ሞታ ጨርቆስ ስትቀበር ያለቀስነው ሶስት ሰዎች ብቻ ነበርን። እኔ፥ ነፍስ አባቷና እትዬ ቀለመወርቅ።” ለዚች ሴት ደራሲው በሕፅን ወይም በግርጌ ማስታወሻ ለአንባቢ ሊገልባት ይገባ ነበር። ከሆነ ስፍራ ውልብ አለች እንጂ ታሪኳ ታፈነ። ለምን ከመንደሩ ሰው ሁሉ ተለይታ የምስራቅ ጓደኛ ሆነች? ትዳር መስርታ ልጅ ወልዳ የዩኒቨርስቲ ትምህርቷን ስትቀጥል፥ ከአንድ ከምታደንቀው ተማሪ ትማግጣለች። ቆይቶ ህሊናዋ ሲቆጠቁጣት ስራዋን ትታ የቤት እመቤት በመሆን ለባለቤቷና ለልጆቿ አገልጋይ ሆነች። ስለዚህ ምስራቅ ከትዳር ውጭ ባልጋለች ተብላ መታማቷ ሁለቱም እኩል የሚያቃስቱበት ሰቆቃና ምስጢራቸው አስተሳሰራቸው፤ ይደማመጣሉ። አዳም ረታ እንደ ጠልሰም ተጠቅልላ ከልቦለዱ የወሸቃት እንስት፥ እንደ ሰባራ ቧንቧ ልትፈስ ያደፈጠች ናት፤ ጐረቤት መባል ብቻ አድበሰበሳት። ደራሲው ንቁ ተደራሲ፥ ጥቆማ የሚከተል አንባቢ ስለሚያደፋፍር ይሆናል በምልክት የቀነበባት።
አዳም ረታ ይህን ልቦለድ በምን ምክንያት ሊፅፈው ቻለ? ምናልባት “እቴሜቴ የሎሚ ሽታ/ ያ ሰውዬ ምን አለሽ ማታ/ ምንም ምንም ምንም አላለኝ/ ትዳሩን ፈቶ ልውሰድሽ አለኝ” ይህ የህፃናት ዘፈን እሴቱ ከአዕምሮው ለአመታት እየተንጓለለ ፋታ ስለአልሰጠው፥ ለእያንዳንዱ ስንኝ ታሪክና ሁነት በምናቡ እየፈተለ ለልቦለዱ መነሻ ሳይሆነው አልቀረም። ሌላ ሰው ያወጋለት፥ ያነበበው ሳይሆን ከዚህ የሴት ህልም፥ ምኞትና ስጋት በትውፊታዊ ቅብብሎሽ ለዘመናት የተንከባለለውን አድምጦ ተደምሞ የፈለቀቀው ልቦለድ ይሆናል ነው ግምቴ። ይህ ደግሞ ብጣሽን ነገር ለብርቅ የፈጠራ ውጤት የማብቃት ልዩ ክህሎት ይሻል። በጣም ስስ ከሆነ ትልም/ሴራ ጥበባዊ ጥልቀት መጐልጐል የቻለበትን የአፃፃፍ ክህሎታዊ ንባብ ለጊዜው ገታ አድርገን በሎሚሽታ ሴትነት፥ ወሲባዊ ረሃብ፥ ረግረግነት፥ ስጋትና ፍላጐት እንደመም።
--- ክፍል 3 ---
ሎሚሽታ ትዳሯን አፍርሳ ወይም ፈርሶባት ወደ አዲሱ ፍቅረኛዋ ጉያ መኮብለሏ፥ በማኅበረሰቡ ሴቶች መታማቷ እኩይ እንስት ሊያስመስላት ይችላል። ግን አይደለችም።
** ሀ **
“ወሬ እወዳለሁ። ከሚያበላኝ ከሚያጠጣኝ ይበልጥ የሚያዋራኝን አቀርባለሁ።” [ገፅ፥ 77]
ሎሚሽታ ከታደሰ ጋር ትዳር ከመሰረተች አምስት አመት ቢሞላትም፥ በፍቅር የጀመረችው ግንኙነት እየጣማት ስራዋን ትታ ከቤት መዋል መርጣ ነበር። እየቆየ መሰልቸትና መሰላቸት፥ በዝምታ የተወረረ ጐጆ ውስጥ ማዛጋት ያቅበዘበዛት ይመስላል። ሴት ማንነቷ ተኮራምቶ የትዳር እስረኛ ሆና ስለምንም ጉዳይ መመሰጥ ስታቆም፥ ከባዳ ወንድ እግር መሃል ለኅላዌ ትርጉም ካፈላለገች፥ እንዴት ባለጌ ተብላ ትኮነናለች? ለዚህ ባዶነት ተጠያቂ ማን ነው? “ወሬ” ከእህል ከውሃ በላይ ከተነፈገችና እንደ አንድ መሰረታዊ ፍላጐት ከገነነባት የየዕለት ውሎዋ ድግግሞሽ ምን ያህል ቢጐመዝዛት ነው? መኖር እኮ ማንጋትና ማምሸት ብቻ ከተካው ለህይወት መቅበዝበዝ እንደ ካህን ትንቢት ከራቃት፥ አንሶላ የሚጋፈፋት እንደ ግለሰብ የተነፈገችውን የህይወት ንዘረት እያስተዋለ ካልደረሰላት፥ በባዶነት መታፈን እንኳን ጐጆ የሌላውን ነፍስ ለመናድ አቅም ሸሽጓል።
ትያትር፥ ጭፈራ ቤት፥ ዘመድ ጥየቃ ... ውሰደኝ ብትለው ምናልባት በወር አንድ ቀን ቢተርፈው ነውና ምርጫዋ ከሰፈሯ ራቅ ወደ አለ ቤተክርስትያን መመላለስ ሆነ። አጃቢ ሴት እንዲቀጠርላት ጠየቀች። “... አንዲት ቀን እንኳን ማዕድ ላይ `በስመአብ` ብላ የማታውቀው ሎሚ `ቤተክርስትያን እስማለሁና አጃቢ ቅጠርልኝ` አለችኝ። አልተከራከርኳትም። ግን ውስጤ አድፍጦ የተቀመጠው የጥርጣሬ አውሬ የሚበላው እንዳገኘ ሁሉ እያዛጋ ተነሳ።” የትዳር አጋሯ ታደሰ፥ ከባዶነት ለመሸሽ የሆነ ጥግ ማፈላለጓን፥ ለመተንፈስ መቃተቷን አጢኖ የአናኗር ለውጥ ከመዘየድ ይልቅ ተንኮል ያደራ ጀመር። ብዙ ወንድ የቀማመሳትና በአባቷ ተግሳፅ የታቀበችው ጎረቤቷ ሁሉአገርሽ ነበር የተቀጠረችላት።
“... መጀመሪያ ጨዋ መስላኝ ነበር አጃቢ ስትፈልግ። ... ሎሚሽታ ቤተክርስትያን የምትሄደውና የማይገባትን የግዕዝ መዝሙረ ዳዊት እየተውተረተረች የምታነበው ፍትወት የሚያቃጥላቸው ዘጠኝ ጐራሽ ዓይኖቿን ከጠርጣሪ ለመከላከል ሳይሆን አልቀረም እላለሁ። እንደ እኔ ነፃነት ቢኖራት ትንሽ ባለአንድ ቤት አልጋ ተከራይታ... `የአገሬ ወንዶች ሆይ! ኑና ሒሳቤን ሰጥታችሁኝ ወደ ምትሄዱበት ሂዱ` ብላ ትለጥፍ ነበር።” ሁሉአገርሽም ብቻነት፥ የትዳር ባዶነት ሎሚሽታን ማቅበዝበዙን ሳታመዛዝን ጋለሞታ ናት ብላ ፈረደች። ደራሲው አንድን እንቅስቃሴ ከሶስት ተራኪዎች አንፃር እያዛዟረ ሲተርክ እንመሰጣለን። ሎሚሽታ ውስጧ የታመሰውን ሳያስተውሉ፥ በአደባባይ ድርጊቷ ብቻ ለቀነበቧት የቅርብ ሰዎች አለመንበርከኳ፥ እንደ ምስራቅ አለመሰበሯ አንድ እሴቷ ነው። ከቤተክህነት መመላለሷ የበጃት ቢኖር ከሚመጥናት ወንዳወንድ አስናቀ ልቦና ውስጥ ለመንዘር እድል ማግኘቷ ነው እንጂ ለተለያዩ ወንዶች ቀሚሷን አልገለበችም፤ የሁሉአገርሽ ሃሜት የቅናት መሰለ። ለመኖር መድፈር ብቻ ነው ሎሚሽታን ከባዶነትና ባዳነት የሚያስጥላት። ገጣሚ ዳዊት ፀጋዬ፥ ሎሚሽታን ተዋውቆ  የተቀኘላት ያክል አገኛት። “ምን    ዐይነት ጨለማ ነው ልባችንን የከበበው?/ ምን ዐይነት ድንዛዜ ነው ሕይወታችንን የወረረው?/ ምን ዐይነት ድንዳኔ ነው መንፈሳችን ላይ የሰለጠነው?/...... / እንዴት አይነት ልብ ነው፥ ማንስ ተብሎ ይጠራ?/ መኖር የማይደፍር! መሞት የሚፈራ!”  [አርነት የወጡ ሐሳቦች፥ ገፅ 59] ሎሚሽታ ተንቀሳቀሰች።
** ለ **
እምሳለምበት ቤተክርስትያን ሴቶች ረድፍ መጣና፥ ... እኔ ሴት መስሎኝ ጆሮዬን ሳውሰው ጠጋ ብሎ፥ በዚያ በሚያምር ጐርናና እንደ ዳምጠው መኪና በሚካበድ ድምፁ :-
`እሰይ! ጠረንሽ እኰ የሎሚ ነው` አለኝ።
በእውነት ነው የምለው ድንግጥግጥ አልኩ።
... ከአፍንጫው በስተቀር ፊቱን በምታምር ቀይ ጥለት ያላት ነጠላ ሸፍኗል። መሬት የሚያብስ የአገር ባሕል ቀሚስ ለብሷል።... ደጀ ሰላም የማይባል ለስጋዬ የጣፈጠ ዝርዝር ነገረኝ። ... ረዥም የሚጣፍጥ ልብ የሚያሸፍት ነገር በዚያ ደብዛዛ የዓመቷ ማሪያም ሌሊት እንደሚሞቅ የድምፅ ጣዝማ ነገር በጆሮዬ ቀዳዳ አንቆረቆረ። ... በተለወጠ አስመሳይ ሴተኛ አካሄዱ እየተንኳተተ እኔ ካለሁበት ቦታ ተነስቶ ሲሄድ በዕፍረትና በመገረም አየሁት። ባለቤቴ ታደሰ እዚያው ቤተክርስትያን ግቢ በወድያ በኩል ዛፍ ስር ቆሞ እንደ መልካም መሪ ጌታ በሁለት እጆቹ ዳዊቱን ፊት ለፊት ዘርግቶ ይዞ ያንቸለችል ነበር። አስናቀ ... ታደሰ አጠገብ ሄዶ ሲቆም አየሁት። መጀመሪያ አፈርኩ። ቀጥሎ ግን በአስናቀ ደፋርነትና ጮሌነት ተደስቼና ተገርሜ እተንበረከኩበት ቦታ ጉልበቴን እስኪያመኝ በሳቅ ፍርፍር አልኩ።”  [ገፅ፥ 77-78]
አዳም ረታ ትረካውን የጀመረው መቋጫው አካባቢ ብቻ ሳይሆን ማንንም አንባቢ በሚያጓጓ ልዩ ትዕይንትም ነው። የእመቤታችን ንግሥ ዕለት ሎሚሽታ ተንበርክካ፥ ታደሰ ዳዊቱን ዘርግቶ ለመንፈሱ ሲያደባ፥ ሁሉአገርሽ ምናልባት በድባቡ ተወስዳ ማሪያምን ለሆነ ጉዳይ ትማፀናት ሳለች፥ ከበዓሉ ከንግሡ ከመንፈሱ የላቀ፥ በህልሙ ለሎሚሽታ የሚባንን፥ ፍትወታዊ ፍላጐት የተጠናወተው ወጣት ድንገት ተላወሰ። ልቦለዱን ስናነብ ይህ ትዕይንት ከሶስት አቅጣጫ ተቀርጿል። አስናቀ፥ ሁሉአገርሽ እና ሎሚሽታ እንደ ስሜታቸው አስተውለውታል።  ሁሉአገርሽ በአካል ገሸሽ ብትልም ትዝብቷ ግን ጠባብ ነው። ለፍቅር፥ ለአካል ውበት የመንገብገብ ኃይል ሰውንና እግዜርን ሳይፈሩ እስከ ደጀ ሰላም የመለጠጥ ድፍረት ሰብዓዊ ጥያቄ አልጫረባትም። ሎሚሽታ በባለቤቷ ተበድላ ይሆን? ፍቅር ተነፍጋ ይሆን? ለሌላ ተባዕት ወከክ ተርከክ የምትልበት ምክንያት ምንድነው ብላ ለማመዛዘን አልጣረችም። ሰው ገበናው ውስጥ የተሸሸገ፥ ሥነልቦናው የተሰነጣጠቀ ለመበርገግ አንድ ኮሽታ፥ ለመፈወስ እፍኝ ፍቅር የሚለማመጥ ውስብስብ መሆኑን ለመረዳት ያዳግታታል። ንቃተ-ህሊናዋ መንጋዊ ነው፤ በማኅበረሰቡ የጥሩና የመጥፎ ድንጋጌ ስለተወረሰ እንደማንም ተራ ነው ፍርዷ። “አስናቀ የምትለው ያ ጥቁር ልጅ ደጀ ሰላም ሊያያት ሲመጣ እንደማያውቅ ...ገሸሽ ብዬ የቤተክርስትያን ግድግዳ ተደግፌ ቆሜአለሁ። ... እንዲያ ግርማ የሚያደፈርስ የማይሆን ነገር ደጀሰላም ውስጥ ያደርጋል። ...አስናቀ ሎሚ ሽታን እየተንፏቀቀ ሲቀርባትና ሲያንሾካሽኩላት የተረጋጋ ዓይን ያወጣ ፈቃደኝነቷን አየሁ።” እያለች ሁለቱን ታጠላላለች።
ሎሚሽታ ከአስናቀ ቀጠሮ አልነበራትም። ተንበርክካ መንፈሷን ለእግዜር አደራ ስትሰጥ ወይም -ጥብቅ አማኝ ስለአልሆነች- ከምናቧ የሚርመሰመስ ስጋት ሆነ ተስፋ አስደምሟት ሳለች፥ እንደ ሴት ለብሶ ድንገት ከመንፈሳዊ ድባብ ያባነናት አስናቀ ነው። የሴትነት ኩራቷን፥ ገና ውብ መሆኗን ያረጋገጠላት እንቅስቃሴ ብቻነት ያፈዘዘውን ልቦናዋን ነፍስ ዘርቶበታል። አስናቀ ይህን ገላ፥ ይህን ውበት ለማጣጣም አላቅማማም። የ “የፍቅር እስከ መቃብር” በዛብህ፥ ሰብለወንጌል ዕቃ ለማውረድ ስትንጠራራ በቅርጿ ተርበተበተ እንጂ መች አፈፍ አድርጐ ገላቸው እኩል ነዘረ? የ “አደፍርስ” አብይ ገፀባህሪ ሮማንን ከህልም ወደ ተግባር ለማሻገር አቅም አንሶታል። አስናቀ ግን የማርያም ንግሥ ዕለት፥ ማኅበረሰቡ ለስለት ለፀሎት ባደገደገበት ምሽት፥ እሱ ለፍቅር አባዜ ማርያምን ምዕምናንን መኖራቸውን ዘንግቶ ሰብሮ ገባ። በአማርኛ ልቦለድ ያልተለመደ መቼት ነው፤ ስንቱ ለነፍሱ የመንፈስ ምስጢር ሲያባብል፥ ሥጋዊ ነገር እየከነከነው ሲፀልይ፥ አፍቃሪ እንደ ሴት ተሸፋፍኖ ሎሚሽታን ተሻሻት፤ ደጀሰላም የፍቅር ደብዳቤ ተለዋጭ ዘይቤ ሆነ።
ታደሰ የተለበለቡ ትናንቶቹን፥ህመሙን ከሎሚሽታ ሸሸጐ፥ ለሥነልቦና ቀውሱ መታከም ሲኖርበት እንደ ጤነኛ ሰው ከቤተክርስትያን ዳዊት የሚደግም እየመሰለ ባለቤቱን በሚስጥር ይቃኛት ነበር።“ አጃቢ ቅጠርልኝ ካለች በኋላ ከስራ እየቀረሁ ባልጠረጠረችኝ ጊዜና ቦታ ሰለልኳት። ከማን ጋር እንደ ዋለች አየሁ። ... እያንዳንዷን ገጠመኝ ማስታወሻዬ ውስጥ በዝርዝር አሠፈርኩ። ... እኔ ቤተክርስትያን አንድ ቀን አብሬአት ሄጄ ራቅ ብዬ ስቆም አስናቀ የተባለው ጐረምሳ ወዳጇ አጠገቧ ሴት መስሎ መጥቶ ሲቆም እኔ ጋም ተጠግቶ ሲያሾፍብኝ ምን የሚያስቅ አለ? ... የመራቅ ድርጊቷን ባልገባት ግን በረቀቀ መንገድ ራሴ እየደገፍኩ እልህ ሁሉ ገብታ ፈጥና እንድትሄድልኝ ገፋፋኋት።”  [ገፅ፥ 123-124] ለአምስት አመታት እንደ ገረድ እያገለገለችው፥ ብቻነት መሰልቸት እስኪበልዛት ድረስ ተኮማተረች። ከአቅሟ በላይ ሲሆን ለአደባባይ የቋመጠችው ሎሚሽታ፥ ትኖር የነበረው ወጥመድ ውስጥ መሆኑ ይሰቅቃል። ይህን አለማወቋም አያዎነቱ፥ ማኅበረሰቡ እሷን እንደ ሴሰኛ፣ ታደሰን እንደ ሰለባ መፈረጁ የከፋ ነው። የሚኖሩት የጋራ ህይወት ዘመም ሲል፥ ለትዳሯ ብላ ብርቅ አምስት አመታት ማባከኗን ሳያመዛዝን፥ አይኖቿ ወንድ ፍለጋ ለምን እንደተቅበዘበዙ ሳያስብበት አድብቶ ጉድጓድ ማሰላት። ለምን ምርር ብሏት እንድትኮበልል መንገድ ጠረገላት? እሷ ህሊናዋ እየወቀሳት፥ ጉረቤት እያማት፥ እሱ ጥፋተኛ ሳይመስል እየታዘነለት በዳይና ተባዳይ ቦታ የመለዋወጣቸውን ማኅበረሰባዊ ድፍረት ደራሲው በድንቅ ትረካ አፍርጦታል። ማኅበራዊ ፍርድና አቋም ግለሰብን አለአግባብ ሲዳጨው ጉዳቱ የከፋ ነው።
  የገላዋ ውበት አልያም ወሲባዊ ጣዕሟ ፍቅር የሚያስይዝ፥ አስተሳሰቧ ግን የሻሸረ ከንቱ ሴት ለታደሰ ወይም ለአስናቀ ሳይሆነ ለሚያውጠነጥን ተባዕት ፍዳ ናት። ደበበ እነሎሚሽታ እየታወሱት በ“ቅዠት ... ቅዠት” ግጥሙ ተቀኝቷል። “ፈገግታውን በመስቷት እያስተካከለ፥ ሌላ ቋንቋ ባይገባት፤/ እንደማንም ናትና እንደማንም ያባብላት?/ ልዩነቱን ይረደዋል/ መደዴነቷን ያውቀዋል።/ ልቧን ገልጦ ያየ ሲመስለው/ ቤህ ነው እሚሣቀቀው።/ ተስፋ እሚቆርጠው።/ ይሁንና አፍቅሯታል፥/ ተራነቷ ሳይጠፋው፥ `ልዩ` ናት ሲል አምልኳታል። /...... / ግን ሀክ ብሎ ላይተፋት/ ነብሱ ውስጥ ተሸንቅራ/ ተቀርቅራ።” [ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ፥ ገፅ 25-26] አዳም ረታ ከጡት መያዣ ሥር የተወሸቀ ብጣሽ ክር የሚያርገብገብ የቋንቋ ምትሀት በጀው እንጂ የተመለመሉት ሴት ገፀባህሪያት አስተሳሰባቸው የእንስት ተራነት ይመሰክራል። የማኅበረሰብ ድንጋጌ፥ እምነትና ጭቆና ውጤት በመሆናቸው ዛሬም ተኳኩለው ሞባይል ቢወለውሉም በአመዛኙ ፍዝ ናቸው። ግን እንደተወርዋሪ ኮከብ በብርሃን ምናባችንን የሚሰነጥቁ ሴቶች የተፍታቱበት፥ በደራሲው ብዕር የገነኑም አሉ።
ሴት ብሎም ወንድ ተራ ወይም ጥልቅ መሆናቸው አይደለም አዳም ረታን እንቅልፍ የሚነሳው። ተረክ ማነፅ፥ በትረካ ፍጥነት፥ በባህል ሆነ በአስተሳሰብ ተጋፊ ሁነቶች ጊዜን መስፈር፥ በቋንቋ ምጥቀት ደቂቅና ግዙፍ ድርጊቶችን ማንጠፍጠፍ እንዴት የኅላዌን ማቃሰት ሆነ መቦረቅ ኮሽታውም ቢሆን አንባቢን ማስበርገጉ ነው ለብዕሩ ንዝረት።  
ክፍል 4 ይቀጥላል

Read 4338 times